የካልሲየም እጥረት በሰውነት ውስጥ ሲኖር ምን ይፈጠራል ?
የካልሲየም እጥረት (ሃይፖካልሴሚያ) በደም ውስጥ ያለው የካልሲየም መጠን በጣም ዝቅተኛ ሲሆን የሚፈጠር ሁኔታ ሲሆን ይህም እንደ የጡንቻ ህመም እና ድካም ያሉ ምልክቶችን ያስከትላል። የተለያዩ የጤና እክሎች የካልሲየም እጥረት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ በዋነኝነት ያልተለመደ የፓራታይሮይድ ሆርሞን (PTH) ወይም ቫይታሚን ዲ መጠን በሰውነት መኖር ይጠቀሳሉ። የካልሲየም እጥረት ቀላል ወይም ከባድ እና ጊዜያዊ ወይም ሥር የሰደደ ሊሆን ይችላል።
ካልሲየም በሰውነት ውስጥ ለምን ይጠቅማል ?
ካልሲየም በሰውነት ውስጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ንጥረ ነገሮች አንዱ ሲሆን አብዛኛውም የሰውነት ካልሲየም በአጥንቶቻችን ውስጥ ይገኛል ። ይሁን እንጂ የካልሲየም በደም ውስጥ መኖር እጅግ አስፈላጊም ነው። በደም የሚገኘው ካልሲየም ነርቮች እንዲሰሩ ፣ እየደማን ከሆነ ደም እንዲረጋ ፣ ልብ በትክክል እንዲሰራ እንዲሁም ጡንቻዎች እንዲኮማተሩ በማድረግ እንድንቀሳቀስ ይረዳናል።ካልሲየም ለአጥንት ጥንካሬም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ስለዚህ የካልሲየም እጥረት ሲኖር እነዚህ እስፈላጊ ተግባራት በሰውነት ውስጥ እንዳይፈፀሙ እንቅፋት ይሆናል።
በአመጋገባችን ውስጥ በቂ ካልሲየም ከሌለ ሰውነታችን ካልሲየምን ከአጥንታችን በመውሰድ በደማችን ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል ። ይህም የአጥንት መሳሳትን ያስከትላል።
የካልሲየም እጥረት በምን ምክንያት ይከሰታል ?
በደም ውስጥ ኖርማል የካልሲየም መጠን እንዲኖር የሚረዱ ብዙ ውስብስብ የሰውነት ተግባራት ያሉ ሲሆን በዚህም ምክያት በርካታ የጤና ሁኔታዎች እና እክሎች የካልሲየም እጥረት ሊያስከትሉ ይችላሉ ። ከእነዚህም ውስጥ ሶስቱ ዋነኛ መንስኤዎች የሚከተሉትን ይመስላሉ።
- የፓራታይሮይድ ሆርሞን ማነስ (ሃይፖፓራታይሮይዲዝም) :- ፓራታይሮይድ ሆርሞን በደም ውስጥ ያለውን የካልሲየም መጠን ለመቆጣጠር የሚረዳ ሆርሞን ሲሆን የዚህ ሆርሞን ማነስ ሲኖር የካልሲየም እጥረት ይከሰታል። ሃይፖፓራታይሮይዲዝም በዘር በሚተላለፍ በሽታ ምክንያት ወይም ከዚህ በፊት በቀዶ ጥገና ፓራታይሮይድ ሆርሞን የሚያመነጨው እጢ ከተወገደ ሊከሰት ይችላል።
- የቫይታሚን ዲ እጥረት :- ቫይታሚን ዲ ካልሲየም በሰውነታችን እንዲወሰድ እና ጥቅም ላይ እንዲውል የሚረዳ ንጥረ ነገር ሲሆን የዚህ ንጥረ ነገር እጥረት ሲኖር ለካልሲየም እጥረት ሊዳርግ ይችላል። የቫይታሚን ዲ እጥረት በዘር በሚተላለፍ በሽታ፣ በቂ የፀሀይ ብርሃን ባለማግኘት እና በአመጋገብ በቂ ቫይታሚን ዲ አለመኖር ምክንያት ሊመጣ ይችላል።
- ስር የሰደደ የኩላሊት ጉዳት(chronic renal failure) :- ይህም በደም ውስጥ ያለውን የፎስፈረስ መጠን እንዲጨምር እና በኩላሊት ውስጥ የሚመረተውን የቫይታሚን ዲ መጠን እንዲቀንስ በማድረግ ለካልሲየም እጥረት ይዳርጋል።
ከእነዚህ በተጨማሪ የካልሲየም እጥረት በሚከተሉት ሁኔታዎች ምክንያት ሊከሰት ይችላል።
- የቆሽጥ ብግነት
- ለረጅም ጊዜ የቆየ ደካማ የካልሲየም አመጋገብ
- እንደ ኮርቲኮስቴሮይድ ፣ ሪፋምፒሲን ፣ ክሎሮኩዊን እና ካልሲቶኒን በመሳሰሉት መድኃኒቶች ሳቢያ
- እንደ ዲጆርጅ ሲንድሮም ያሉ አንዳንድ የዘረ የሚተላለፉ በሽታዎች
- በሰውነት ውስጥ የማግኒዥየም እጥረት (ሃይፖማግኒዝሚያ) መኖር ካለ የካልሲየም እጥረት ሊከሰት ይችላል።
የካልሲየም እጥረት ማን ላይ ሊከሰት ይችላል?
የካልሲየም እጥረት ጨቅላ ሕፃናትን ጨምሮ በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል። ብዙውን ጊዜ የካልሲየም እጥርት የሚከሰትበት እድሜ በመንስኤው የሚወሰን ሲሆን ለምሳሌ በጨቅላ ሕፃናት ላይ ከተከሰተ ምክንያቱ በዘር የሚተላለፍ በሽታ ነው።
የካልሲየም እጥረት ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?
መጠነኛ የካልሲየም እጥረት ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ምንም አይነት ምልክት አያሳዩም። እጥረቱ ከባድ ሲሆን ግን ምልክት ማሳየት የሚጀምሩ ሲሆን ከሚያሳዩአቸው ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
የጡንቻ ችግሮች
- የጡንቻ ህመም
- የጡንቻ መገተር
- በእንቅስቃሴ ጊዜ በጭን እና በእጆች ላይ ህመም መኖር
- በእጅ፣በእግር እንዲሁም አፍ አካባቢ የመደንዘዝ ስሜት
ከባድ የካልሲየም ካለ ደግሞ እንደ መናድ ፣ የልብ ምት መዘበራረቅ እና ሞት ሊያስከትል ይችላል።
ከፍተኛ ድካም
ዝቅተኛ የካልሲየም መጠን የድካም ስሜት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የማዞር ስሜት፣ የአንጎል ጭጋግ ፣ግራ መጋባት እና የመርሳት ችግርን ያስከትላል።
የጥፍር እና የቆዳ ችግሮች
- የቆዳ ድርቀት
- ደረቅ እና በቀላሉ የሚሰበሩ ጥፍሮች
- የፀጉር መከርደድ
- ችፌ (ኤክዜማ)
- ሶርያሲስ ያሉ ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ
የአጥንት መሳሳት
የአጥንት መሳሳት እኪፈጠር ድረስ አመታት ሊወስድ ይችላል።
ከባድ የወር አበባ ምልክቶች እንዲኖሩ ያያደርጋል።
የጥርስ ችግሮች
- የጥርስ መበበስ
- በቀላሉ የሚሰበር ጥርስ
- የድድ መቆጣት
- ደካማ የጥርስ ስር እና
- በጨቅላ ህፃናት ላይ የጥርስ እድገትን ይጎዳል።
ድባቴን ሊያስከትልም ይችላል።
የካልሲየም እጥረት ምርመራ
ሐኪሞ በመጀመሪያ የህክምና ታሪክ እና የቤተሰብ ታሪክ ማለትም በቤተሰብ ውስጥ የካልሲየም እጥረት እና የአጥንት መሳሳት መኖሩን ይጠይቃል። የካልሲየም እጥረት እንዳለ ከጠረጠረም በደምዎ ውስጥ ያለውን የካልሲየም መጠን ለመፈተሽ የደም ምርመራ ያደርግሎታል። የደም የካልሲየም መጠኖ ከ 8.8 ሚ.ግ/ ዴ.ሊ በታች ከሆነ ሐኪሞ የ ካልሲየም እጥረት እንዳለቦት ያረጋግጣል። የእጥረቱን መንስኤ ለማወቅ እና በሌሎች የሰውነትዎ ክፍል ላይ ያለውን ተጽዕኖ ለመለየት የሚከተሉትን ምርመራዎችም ያደርጋል።
- ደም ውስጥ ያለውን የማግኒዥየም፣ የፎስፈረስ፣ የፓራታይሮይድ ሆርሞን (PTH) እና የቫይታሚን ዲ መጠን ለማወቅ የደም ምርመራ ያደርግልናል
- ኤሌክትሮካርዲዮግራም (ECG) : የልብ ምትን ለመለካት ያስችላል
- እንደ ቦን ስካን(bone scan) ያሉ የአጥንት ምስል ምርመራዎች
የካልሲየም እጥረት እንዴት ይታከማል?
አብዛኛውን ጊዜ የካልሲየም እጥረትን ለማከም ቀላል ሲሆን በአመጋገብ ላይ ተጨማሪ ካልሲየምን በማከል ማከም ይቻላል። ነገር ግን ሐኪሞ ካዘዘሎት መጠን በላይ የካልሲየም ንጥረ ነገርን መውሰድ እንደ የኩላሊት ጠጠር ላሉ ከባድ የጤና እክሎች ሊዳርግ ስለሚችል አይመከርም። ለካልሲየም እጥረት ከሚታዘዙ የካልሲየም ንጥረ ነገሮች ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
- ካልሲየም ካርቦኔት (Calcium carbonate) - በካልሲየም ንጥረ ነገር እጅግ የበለፀገ ነው
- ካልሲየም ሲትሬት (Calcium citrate) - በጣም በቀላሉ በሰውነት ተወስዶ ጥቅም ላይ ይውላል
- ካልሲየም ፎስፌት (Calcium phosphate) - ይህም በቀላሉ በሰውነት ውስጥ በመወሰድ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን የሆድ ድርቀትንም አያስከትልም
የካልሲየም ንጥረ ነገሮች በፈሳሽ፣ በታብሌት እና በሚታኘኩ እንክብሎች ይገኛሉ። አንዳንድ ጊዜ በአፍ በሚወሰዱ የካልሲየም ንጥረ ነገር ነገሮች እና በአመጋገብ ለውጥ የደም የካልሲየም መጠኖ ካልተስተካከለ ሐኪሞ የካልሲየም ንጥረ ነገሩን በመርፌ እንዲወስዱ ሊያደርግ ይችላል።
ብዙውን ጊዜ ህክምና ከተጀመረ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለውጥ ማሳየት ይጀምራሉ። እጥረቱ ከባድ ከሆነም በየወሩ ወይም በየሶስት ወሩ ከሐኪሞ ጋር ክትትል ያስፈልጎታል።
- እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር የካልሲየም እጥረት መንስኤውን ማከም ትልቁ እና እጅግ አስፈላጊ የህክምናው ክፍል መሆኑን ነው።
የካልሲየም እጥረት የጎንዮሽ ጉዳቶች ምን ምንድን ናቸው?
የካልሲየም እጥረት እንደ አይን ጉዳት፣ ያልተለመደ የልብ ምት እና የአጥንት መሳሳት ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች የሚያስከትል ሲሆን የአጥንት መሳሳት ደግሞ የሚከተሉትን የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል
- የአካል ጉዳተኝነት
- ለመራመድ መቸገር እና
- የአጥንት ስብራትን ሊያስከትል ይችላል።
የካልሲየም እጥረትን እንዴት መከላከል ይቻላል?
አመጋገብዎ ላይ የካልሲየም ንጥረ ነገር የያዙ ምግቦችን በማከል የካልሲየም እጥረትን መከላከል ይቻላል። ካልሲይርምን ከወተት እና ከወተት ተዋጽኦዎች እንዲሁም ከሚከተሉት ምግቦች ማግኘት ይቻላሉ
- ሰርዲን
- ሳልሞን
- ባቄላ
- ብሮኮሊ
- በለስ እና
- የስንዴ ዳቦ የካልሲየም ይዘት ካላቸው ምግቦች ጥቂቶቹ ናቸው።




