አልማዝ ባለጭራ (Herpes zoster)

Melat Geatchew
Jul 12, 2025
undefined

አልማዝ ባለጭራ (Herpes zoster)

 

 

 

አልማዝ ባለጭራ በሽታ በቆዳ ላይ የሚወጣ ሕመም ያለው ሽፍታ ነው፡፡ ቫሪሴላ ዞስተር (Varicella zoster) በሚባል ቫይረስ አማካኝነት ይከሠታል። 

 

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ በዚህ በሽታ ይጠቃል፡፡ ይህ ሕመም የሚከሠተው አስቀድሞ ጉድፍ (Chickenpox) በተያዙ ሰዎች ላይ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ሰዎች በጉድፍ በሽታ ተይዘው እንደነበረ ላያውቁ ወይም ላያስታውሱ ይችላሉ። 

አልማዝ ባለጭራ እንዴት ይከሠታል?

 

ቫሪሴላ ዞስተር ሰዎች በጉድፍ እንዲታመሙ የሚያደርግ ቫይረስ ሲሆን፤ ሕመሙ ከአለፈ በኋላ ይህ ቫይረስ በአከርካሪ እና በአንጎል አቅራቢያ በሚገኙ ነርቮች ውስጥ ይቀመጣል። አመቺ ሁኔታን ሲያገኝ ይህ ቫይረስ በነርቮች ውስጥ በመጓዝ በቆዳችን ላይ አልማዝ ባለጭራ በሽታ እንዲከሠት ያደርጋል።

 

ለበሽታው መከሠት አመቺ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

 

በሽታ የመከላከል ዐቅም የሚቀንሱ ሁኔታዎች።    

  •   ኤች. አይ. ቪ. ኤድስ ሕመም
  •   የካንሰር በሽታ ወይም የኬሞቴራፒ ሕክምና
  •  አንዳንድ መድኃኒቶች (Steroids)
  •   ከፍተኛ ውጥረት ወይም ጭንቀት 
  • ዕድሜ በተለይም ከ 50 ዓመት በላይ

     

    የአልማዝ ባለጭራ ምልክቶች

 

  • አልማዝ ባለጭራ ማንኛውንም የሰውነት ክፍል ሊያጠቃ ይችላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን በአንድ ጎን በኩል በደረት፣ በሆድ ወይም በጀርባ ላይ ሲወጣ ይስተዋላል። 
  • ይህ ሕመም ቆዳ ላይ ሽፍታ ከማሳየቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ የመደንዘዝ፣ የማቃጠል እና የማሳከክ ስሜት ይኖረዋል። ይህ ስሜት ከታየ 1 ወይም 2 ቀናት በኋላ በአንድ የሰውነት ጎን ብቻ የቆዳ መቆጣት እና የቀበቶ ቅርፅ የመሰለ ዉሃ የቋጠረ ሕመም ያለው ሽፍታ መታየት ይጀምራል። ብዙ ጊዜ ሽፍታው ከጥቂት ቀናት በኋላ መድረቅ እና መክሰም ይጀምራል፡፡ ከዚያም በአንድ ወይም ሁለት ሳምንት ውስጥ ይጠፋል። 
  • በተጨማሪ ትኩሳት ፣ ድካም፣ ራስ ምታት እና ህመሙ በተከሰተበት አካባቢ ንፍፊት (Lymphadenopathy) መውጣት ሊኖር ይችላል።

     

    አልማዝ ባለጭራ ተላላፊ ነውን? 

      ታማሚዎች በቀጥታ አልማዝ ባለጭራን ማስተላለፍ አይችሉም። ነገር ግን የጉድፍ ክትባት ያልወሰደ ወይም ጉድፍ ታሞ የማያውቅ ሰው በታማሚው አካባቢ በሚሆንበት ጊዜ በጉድፍ በሽታ ሊጠቃ ይችላል። 

       ቫይረሱ ከታማሚው ሰው ጋር በሚደረግ ቀጥታ የቆዳ ንክኪ ወይም በትንፋሽ አማካኝነት ይተላለፋል። ስለዚህ የጉድፍ ክትባት ያልወሰደ ወይም ጭራሽ ታሞ የማያውቅ ሰው ከታማሚው ጋር የቅርብ ንክኪ ባያደርግ ይመረጣል።

 

አልማዝ ባለጭራ ምን ዓይነት ከባድ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል?

አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ችግሮች የሚከሠቱት ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ወይም በሽታ የመከላከል ዐቅማቸው በቀነሰ (Immunocompromised) ሰዎች ላይ ነው።

 እነዚህም የሚከተሉት ናቸው።

 

ከአልማዝ ባለጭራ በኋላ የሚከሠት የነርቭ ሕመም (Postherpetic neuralgia)

  • ይህ ሽፍታው ከተከሠተበት ጊዜ ጀምሮ በተመሳሳይ የሰውነት ክፍል ላይ ቢያንስ ለ 3 ወራት የሚቆይ ሕመም እና ማቃጠል ሲኖር ነው። ሕመሙ ከቀላል እስከ ኑሮን ሊያውክ የሚችል ከባድ ማቃጠል እና ውጋት ሊደርስ ይችላል። 
  • አብዛኛውን ጊዜ ሕመሙ ከጊዜ በኋላ እየቀነሰ ቢሄድም አንዳንድ ጊዜ ግን እየተመላለሰ ለወራት ወይም ለዓመታት ሊዘልቅ ይችላል። ስለዚህ ሕመሙን ለማስታገስ የጤና ባለሙያዎች የተለያዩ መድኃኒቶችን ሊያዝዙ ይችላሉ።

 

       የዐይን ችግር

  • ይህ የአልማዝ ባለጭራ ሽፍታ ዐይን፣ ግንባር እና አፍንጫ አካባቢ ሲከሠት ሊያጋጥም የሚችል ከባድ የዐይን ችግር ነው። 
  • ይህ ሕመም በአግባቡ ካልታከመ እይታን ሊያሳጣ ስለሚችል፤ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ሽፍታ ሲከሠት በፍጥነት የጤና ርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል። 

    የቆዳ ኢንፌክሽን

  • አንዳንድ ጊዜ ሽፍታው ሊቆስል እና ቆዳችን በሽታ አምጪ በሆኑ ተሕዋስያን ሊበከል ይችላል። ይህም በቆዳችን ላይ ጠባሳ ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህ ከፍተኛ ትኩሳት ወይም መግል በሚኖርበት ጊዜ ወደ ጤና ተቋም መሔድ ያስፈልጋል።

    የጆሮ ብግነት ወይም መቆጣት

  • በተጎዳው ጆሮ በኩል የፊት ጡንቻ መስነፍ (የፊት መጣመም)፣ የጆሮ ሕመም እና በጆሮ ውስጥ ሽፍታ መውጣት ምልክቶቹ ናቸው። ብዙውን ጊዜ በፀረ ቫይረስ መድኃኒት እና ብግነትን በሚቀንሱ መድኃኒቶች (Steroids) ይታከማል።

ያልተለመደ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ አልማዝ ባለጭራ በሳንባ፣ በአንጎል እና በጉበት ላይ ለሞት የሚዳርግ ውስብስብ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል። 

 

 

የአልማዝ ባለጭራ ምርመራዎች ምንድን ናቸው?

 

የጤና ባለሙያዎች ሽፍታውን በማየት እና ስለምልክቶቹ በመጠየቅ ስለበሽታው መረዳት ይችላሉ። እንዲሁም ከሽፍታው ላይ ናሙና በመውሰድ  ምርመራ ሊደረግ ይችላል።

 

የአልማዝ ባለጭራ ሕክምና

 

 በቤት ውስጥ የሚደረግ ሕክምና

  • ሽፍታው የአለበትን አካባቢ ንጽሕና መጠበቅ፣ በተጨማሪም እርጥበት እንዳይኖር በጥንቃቄ ማድረቅ
  • ቆዳን የበለጠ ሊጎዱት ስለሚችሉ እርጥበት ያላቸውን ቅባቶች እና ክሬሞችን ማስወገድ
  • የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ በቂ ዕረፍት ማድረግ
  • ሰፋ ያሉ እና ምቾትን የሚሰጡ ልብሶችን መልበስ
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ፣ ውጥረትን መቀነስ 

በሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚደረጉ ሕክምናዎች

  • የፀረ ቫይረስ መድኃኒቶች፤ እነዚህ መድኃኒቶች የቫይረሱን መራባት ለማገድ፣ የሕመሙን ክብደት እና ቆይታ ለመቀነስ እና ሽፍታው በፍጥነት እንዲድን ለማድረግ ያግዛሉ። በተለይም ሽፍታው በተከሠተ በ72 ሰዓታት ውስጥ መወሰድ ከተጀመሩ ውጤታቸው ጥሩ ይሆናል።
  • የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች፤ አንዳንድ ጊዜ ሕመሙ ከባድ ሊሆን እና የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ።
  • የ ፀረ ተሕዋስያን መድኃኒቶች፤ ቆዳ በበሽታ አምጪ ተሕዋስያን ከተበከለ እና ኢንፌክሽን ከተፈጠረ አንቲባዮቲክስ መድኃኒቶች ይታዘዛሉ።

     

    አልማዝ ባለጭራ መከላከያ መንገዶች

 

  • ሕፃናት የጉድፍ መከላከያ ክትባትን እንዲወስዱ ማድረግ
  • በአደጉት አገራት ዕድሜያቸው ከ 50 በላይ ለሆኑ ሰዎች የአልማዝ ባለጭራ መከላከያ ክትባትን እንዲወስዱ ይደረጋል።
  • የአልማዝ ባለጭራ ታማሚ እስኪያገግም ድረስ ርቀትን መጠበቅ ያስፈልጋል። በተለይም የጉድፍ ክትባትን ከአልወሰዱ ወይም በጉድፍ ተይዘው የማያውቁ ከሆነ ይህን ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል። 

 

 

Comments (0)