‹‹ይሄንን ነገር ከዚህ በፊት አይቼዋለሁ›› የሚል ስሜት ተሰምቶዎታል ?››
በእውኑ ዴዣ ቩ (Déjà vu) ምንድን ነው?
ዴዣ ቩ ማለት ከዚህ በፊት በአንድ ወቅት ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ የሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ያህል የሚሰማዎት ጊዜያዊ ስሜት ነው። ነገር ግን ሁኔታው ፈጽሞ ከዚህ በፊት ያልተከሰተ ሲሆን ይህም ክስተት 97% በሚሆኑ አዋቂ ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ያጋጥማቸዋል ።
ዴዣ ቩ አብዛኛውን ጊዜ ለአፍታ የሚቆይ ፈጣን ስሜት ሲሆን ከስሜቱ በኋላም ነገሮች ወደ መደበኛ ሁኔታቸው ይመለሳሉ።
የዴዣ ቩ መንስኤ ምንድን ነው?
የነርቭ ስፔሻሊስት ሐኪሞች እንደሚናገሩት ዴዣ ቩ የሚከሰተው በማስታወስ ችሎታ(memory recollection) እና አንድን ነገር ከዚህ በፊት የማወቅ ስሜት (familiarity) ላይ ሚና በሚጭወቱ የአእምሮ ክፍሎች መካከል በሚኖር የግንኙነት ችግር ምክንያት የሚከሰት ክስተት ነው። በትውስታ እና በአዲስ ክስተት መካከል ያለውን መስመር የሚያደበዝዝ የተሳሳተ የአእምሮ ምላሽ ነው። በሌላ አነጋገር በአንጎልዎ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ክፍሎች መካከል ያለመግባባት ችግር ሲፈጠር ይከሰታል። እነዚህ የአእምሮ ክፍሎች ለማስታወስ ኃላፊነት ያለው ቴምፖራል ሎብ (temporal lobe) እና አዲስ መረጃ ለመቀበል ኃላፊነት ያለው ሂፖካምፐስ (hippocampus) ናቸው።
ምንም እንኳን ተመራማሪዎች ለምን እንደሆነ እርግጠኛ ባይሆኑም አንዳንድ ሰዎች በሚከተሉት ሁኔታዎች ምክንያት ለዴዣ ቩ የበለጠ ተጋላጭ እንደሆኑ ይገልጻሉ፦
- ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ሲኖራቸው
- ብዙ ጊዜ የሚጓዙ ከሆነ
- ያዩአቸውን ሕልሞች የሚያስታውሱ ከሆነ ለዴዣ ቩ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።
ዴዣ ቩ በጤና እክሎች ምክንያት ሊከሰት ይችላል?
አንዳንድ የጤና ሁኔታዎች ዴዣ ቩን ሊያስከትሉ ይችላሉ። እነዚህም የሚከተሉትን ይመስላሉ
ድካም ወይም የእንቅልፍ እጥረት
በቂ እንቅልፍ ወይም በቂ እረፍት ያለው እንቅልፍ ካላገኙ የአእምሮዎን ነገሮችን የመለየት ችሎታ ይስተጓጎላል። ይህም ይህ ክስተት ለምን ብዙውን ጊዜ ምሽት ላይ እንደሚከሰት ሊያስረዳ ይችላል ።
ውጥረት እና ጭንቀት
ውጥረት ወይም ጭንቀት አእምሮ መረጃ የሚቀበልበትን እና ይህን መረጃ የሚረዳበት መንገድ እንዲቀየር ሊያደርግ ይችላል።
ማይግሬን ራስ ምታት
ለከፍተኛ ራስ ምታት (ማይግሬን) ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በሕመሙ ወቅት ወይም ከዚያ በኋላ ዴዣ ቩ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ማይግሬን ያለበት ሰው ብዙውን ጊዜ ግራ በመጋባት አዲስ ክስተቶችን ነገሮችን ከማስታወስ ጋር መለየት ሊያቅተው ይችላል።
የመርሳት በሽታ (Dementia)
በአንጎል የፊት ለፊት ክፍል እና ቴምፖራል ሎብ በሚባለው ክፍል ላይ ጉዳት የሚያደርስ የመርሳት በሽታ (frontotemporal dementia) ያለባቸው ሰዎች የማያቋርጥ ዴዣ ቩ ሊያጋጥማቸው ይችላል።
የቴምፖራል ሎብ የሚጥል በሽታ (Temporal lobe epilepsy)
ሁሉም የሚጥል በሽታዎች በፊልም ላይ እንደሚታዩት አይደሉም። ቴምፖራል ሎብ በተባለው የአእምሮ ክፍል ላይ ብቻ የሚከሰተው የሚጥል በሽታ ከመናድ(ከመንቀጥቀጥ) ይልቅ የዴዣ ቩ ስሜትን ሊያስከትል ይችላል።
ለዴዣ ቩ ስሜት የጤና ባለሞያዎችን መቼ ማማከር ያስፈልጋል?
አልፎ አልፎ የሚከሰት ዴዣ ቩ የሚያስጨንቅ ነገር አይደለም። ብዙ የነርቭ ሐኪሞች እንደሚገልጹት ዴዣ ቩ ጤናማ በሆኑ ግለሰቦች ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰት ክስተት ሲሆን ብዙውን ጊዜ በዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ሊከሰትም ይችላል። ነገር ግን ይህ ስሜት በተደጋጋሚ የሚያጋጥምዎ ከሆነ ወይም ከጥቂት ሰከንዶች በላይ የሚቆይ ከሆነ እንዲሁም ሌሎች ምልክቶች አብረውት ካሉ የሕክምና ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው።
የዴዣ ቩ ስሜቱ ከሚከተሉት አሳሳቢ ምልክቶች ጋር አብሮ ከመጣ ሐኪም ማማከር ይኖርቦታል ፦
- ግራ መጋባት
- ራስ ምታት
- ንቃተ ህሊና ማጣት (Loss of awareness)
- ሰውነትን ለማንቀሳቀስ መቸገር (Weakness)
- መናድ/መንቀጥቀጥ (Seizures)
በአጠቃላይ
አልፎ አልፎ የሚያጋጥም “ይሄንን ነገር ከዚህ በፊት አይቼዋለሁ ወይም አድርጌዋለሁ” የሚለው ስሜት የሚያሳስብ ነገር ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ተደጋጋሚ ዴዣ ቩ ካለ ችላ አይበሉት። የዴዣ ቩ ስሜትዎ መንስኤ ምን እንደሆነ ከተጠራጠሩ ግን የነርቭ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን ያማክሩ።




