ሙሉ የጤና ምርመራ በየስንት ጊዜ ማድረግ ያስፈልጋል?

Elsabet Azezew
Sep 30, 2025
undefined

                        ሙሉ የጤና ምርመራ በየስንት ጊዜ ማድረግ ያስፈልጋል?

       በሽታን ከመታከም ይልቅ መከላከል የተሻለ በመሆኑ በመደበኛነት የጤና ምርመራ ማድረግ ወሳኝ ነው።  ለተለያዩ የህክምና ሁኔታዎች ያለዎትን ተጋላጭነት በየጊዜው መገምገም፣ ለካንሰርና ለሌሎች በሽታዎች ምርመራ ማድረግ፣ እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤዎን መገምገም ጤናማ ሆነው እንዲቆዩ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ (chronic diseases) ወይም ለሕይወት አስጊ በሆኑ በሽታዎች የመያዝ እድልዎን ይቀንሳል።

               ሙሉ የጤና ምርመራ በየስንት ጊዜ መደረግ አለበት?

       አንድ አዋቂ ሰው በየስንት ጊዜው መደበኛ የሆነ የጤና ምርመራ ማድረግ እንዳለበት የሚወሰነው በእድሜው፣ ለበሽታ ባለው ተጋላጭነት እንዲሁም ባለበት የጤና ሁኔታ ነው።

   ምንም እንኳን በዚህ ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች ቢኖሩም፣  በአጠቃላይ መደበኛ የጤና ምርመራ በሚከተሉት ጊዜያት እንዲያደርጉ ይመከራል፦

  • እድሜዎ ከ45 ዓመት በታች እና ጤናዎ ጥሩ ከሆነ በየአንድ እስከ በየሶስት አመት መደበኛ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል 
  • ከ45 ዓመት በኋላ በዓመት አንድ ጊዜ ምርመራ ማድረግ ይኖርቦታል 
  • እንደ ስኳር በሽታ ወይም ሥር የሰደደ የሳንባ በሽታ(COPD) ያሉ በሽታዎች ካለብዎት በእድሜዎ ሳይወሰን በዶክተርዎ በተደጋጋሚ መታየት አለብዎት። ሐኪምዎ ባሎት ተጋላጭነት፣ በምርመራ ውጤቶ እና አሁን ባሎት የጤና ሁኔታ ላይ በመመስረት በምርመራዎቾ መካከል ያለውን ጊዜ ሊያሳጥር ወይም ሊያራዝም ይችላል።

            መደበኛ የጤና ምርመራ ማድረግ የሚሰጠው ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

  ከጤና ባለሙያዎ ጋር የሚያደርጓቸው መደበኛ የጤና ምርመራዎች ለጤናዎ ብዙ ጥቅሞችን ሊያስገኙ የሚያስችሉ ሲሆን  ከእነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • ለሕይወት አስጊ ሊሆኑ የሚችሉ የጤና ችግሮችን አስቀድሞ ለማግኘት እና እርምጃ ለመውሰድ ያስችላል።
  • የጤና እክሎችን በወቅቱ ለማከም ያግዛል ፤ ይህም ቶሎ የመዳን እድሎን ይጨምራል።
  • ያሉ የጤና ችግሮችን በየጊዜው ለመከታተል ፤ ይህም ምልክቶች እንዳይባባሱ እና ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል ያግዛል።
  • ወቅታዊ ክትባቶችን እና ቅድመ ምርመራዎችን ለማግኘት ያስችላል።
  • በጊዜው ባልተገኙ ውስብስብ እና ከባድ የጤና እክሎች ምክንያት የሚመጣ ተጨማሪ የህክምና ወጪዎችን ይቀንሳል።
  • ከሐኪሞ ጋር ግልጽ እና ሐቀኛ ግንኙነት ለመፍጠር ያስችላል። 
  • ጤናማ እና ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚያስችሉ አዳዲስ መንገዶችን ለማወቅ እንዲሁም ጤናዎን ለማሻሻል ያግዛል ።

           የጤና ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት የትኞቹ ምርመራዎች መካተት አለበት? 

     ዓመታዊ የጤና ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት ሐኪምዎ ያለፈውን የጤና ታሪክዎን እና አሁን ያሉበትን የጤና ሁኔታ ይገመግማል ፤ እንዲሁም ተገቢውን ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ ያዛል።

 

           ለወንዶች እና ለሴቶች የሚደረገው የአዋቂዎች ዓመታዊ ምርመራ የሚከተሉትን ማካተት አለበት 

  • የህክምና ታሪክ
  • አስፈላጊ ከሆነ የቤተሰብ የህክምና ታሪክ
  • የሚወስዷቸው የመድሃኒቶች እና ያለብዎ የአለርጂ ዝርዝር
  • ከዚህ በፊት የወሰዱት የክትባት እና የምርመራ ውጤት ታሪክ ሐኪሞ ይወስዳል። 

ለሚከተሉት ሁኔታዎችም ቅድመ ምርመራም ያደርግሎታል 

  • ለደም ግፊት 
  • ለድባቴ 
  • ለከመጠን በላይ ውፍረት ይህም በሰውነት ክብደት ሚዛን ወይም በ ቢ.ኤም.አይ (B.M.I) ላይ የተመሰረተ ነው  
  • እድሜአቸው ከ15 እስከ 65 ዓመት ለሆኑ አዋቂዎች እና ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭነት ላላቸው ሰዎች  የኤችአይቪ ምርመራ ይደረጋል
  • የሄፓታይተስ ሲ ምርመራ 
  • ለዓይነት 2 የስኳር በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ሰዎች ወይም ለበሽታው የቤተሰብ ታሪክ ላለባቸው ሰዎች ሁሉ የስኳር ምርመራ ይደረግላቸዋል  
  • እድሜአቸው 50 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሰዎች የአንጀት ካንሰር ቅድመ ምርመራ እና
  • ሲጋራ የሚያጨሱ ወይም ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ሲያጨሱ ለነበሩ እድሜአቸው ከ55 እስከ 80 ዓመት ለሆኑ አዋቂዎች የሳንባ ካንሰር ተጋላጭነትን ለመገመም በየዓመቱ የሲቲ ስካን ምርመራ (low dose CT scan) ይደረጋል 

           ለሴቶች የሚደረጉ ተጨማሪ ምርመራዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ 

  • እድሜአቸው ከ50 እስከ 74 ዓመት ለሆኑ ሴቶች ማሞግራም የተባለ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ
  • እድሜአቸው ከ21 እስከ 65 ዓመት ለሆኑ ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ (ፓፕ ስሚር)
  • 45 ዓመት እና ከዚያ በላይ ለሆናቸው ሴቶች የኮሌስትሮል ምርመራ
  • እንዲሁም 65 ዓመት እና ከዚያ በላይ ለሆናቸው ሴቶች የአጥንት መሳሳት (osteoporosis) ምርመራ ከላይ ከጠቀስናቸው ምርመራዎች በተጨማሪ ይደረግላቸዋል ። 

          ለወንዶች የሚደረጉ ተጨማሪ ምርመራዎች ደግሞ የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ 

  • የማጨስ ታሪክ ላላቸው እድሜአቸው ከ65 እስከ 75 ዓመት ለሆኑ ሰዎች ሆድ ውስጥ የሚገኝ አዎርቲክ የተባለ የደም ወሳጅ ቧንቧ ግድግዳ ከመጠን በላይ መለጠጥ ችግር (abdominal aortic aneurysm) ምርመራ ይደረጋል። 
  • የፕሮስቴት ምርመራ በአጠቃላይ ባይመከርም እድሜአቸው 50 ዓመት እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ወንድ አዋቂዎች  ምርመራው ሊደረግ ይችላሉ።
  • እንዲሁም ከ35 ዓመት ጀምሮ የኮሌስትሮል ምርመራ ይደረግሎታል። 

Comments (0)