ኢርፎን ማድረግ የመስማት ችሎታን ይጎዳል ?
ትራንስፖርት ውስጥ ሆነው ወይም ስራ እየሰሩ ኢርፎን በመጠቀም ከፍ ባለ ድምፅ ሙዚቃ ወይም ፖድካስት ማዳመጥ ይወዳሉ ? ነገር ግን ይህ ልማድ የመስማት ችሎታዎን ሊጎዳ እንደሚችል ያውቃሉ ? የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ለከፍተኛ የድምፅ መጠን መጋለጥ ከጊዜ በኋላ የመስማት ችሎታን እንደሚቀንስ ይናገራሉ።
በተለይ ህፃናት፣ ታዳጊዎች እና ወጣቶች በየቀኑ ከ70 ዲሲቤል በላይ በሆነ ድምፅ ለብዙ ሰዓታት ሙዚቃ የሚያዳምጡ ከሆነ ለዚህ ጉዳት ተጋላጭ ናቸው። የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደሚገልጸው 50 በመቶ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ12 እስከ 35 ዓመት የሆኑ ሰዎች ለረጅም ጊዜ ለፍተኛ ድምፅ (ለምሳሌ በጆሮ ማዳመጫ መሣሪያዎች አማካኝነት በሚሰሙት ሙዚቃ) በመጋለጣቸው ምክንያት ለመስማት ችግር ተጋላጭ እንደሆኑ ይናገራል።
አብዛኛውን የመስማት ችግር እድሜ ከመግፋት ወይም ከእርጅና ጋር ተያይዞ ይመጣል የሚል የተሳስተ አመለካከት አለ። ነገር ግን ብዙ ሐኪሞች እንደሚገልጹት አብዛኛው የመስማት ችግር ለከፍተኛ ድምጽ የመጋለጥ ውጤት ነው።ልክ ከፍተኛ የቆዳ መሸብሸብ እና መጎዳት ጤናማ የእርጅና አካል እንዳልሆነው እና ብዙውን ጊዜ በፀሃይ ጨረር (UV ray) ጉዳት ምክንያት እንደሚመጣው ሁሉ ለከፍተኛ ድምፅ ካልተጋለጡ በስተቀር በእርጅና ጊዜ በጥሩ ሁኔታ የመስማት እድሎ ሰፊ ነው።
የመስማት ችሎታ መቀነስ ጤናዎ ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ
ሳይረበሹ ሙዚቃ ለማዳመጥ ወይም የተለያዩ ቪዲዮዎችን ለማየት የሚጠቀሟቸው ኤርፎኖች የመስማት ችሎታዎን በእጅጉ ይጎዳዋል። በተለይ ወጣቶች እነዚህን መሳሪያዎች የሚጠቀሙ ከሆነ በእድሜያቸው አጋማሽ ምናልባት በ40ዎቹ መጀመሪያ ወይም አጋማሽ ላይ ሲደርሱ እድሜው 70 ወይም 80 የሆነ አዛውንት ጋር ተመሳሳይ የመስማት ችሎታ መቀነስ ይኖራቸዋል።
መግባባትን አዳጋች ከማድረግ በተጨማሪ የመስማት ችሎታን ማጣት ከግንዛቤ መቀነስ (cognitive decline) ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገራል።
በ2011 የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው የመስማት ችግር ከሌላቸው ሰዎች ጋር ሲነፃፀር የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች ለመርሳት በሽታ የመጋለጥ እድላቸው የሚከተለውን ይመስላል
- መጠነኛ የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች ለመርሳት በሽታ (dementia) የመጋለጥ ዕድላቸው በእጥፍ ገደማ ይጨምራል።
- መካከለኛ የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች በበሽታው የመያዝ እድላቸው በሶስት እጥፍ ከፍ ይላል
- ከባድ የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች ደግሞ ለመርሳት በሽታ የመጋለጥ እድላቸው በአምስት እጥፍ ከፍ ያለ ነው።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የመስማት ችግርን በወቅቱ ለመስማት በሚረዱ መሳሪያዎች (hearing aids) ማከም ለግንዛቤ መቀነስ ችግር እና ለመርሳት በሽታ የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል ።
ኢርፎን ሲጠቀሙ ጤናማ የድምፅ ገደቦችን እንዴት ያስቀምጡ?
በድምፅ መጋለጥ ምክንያት የሚመጣ የመስማት ችግር ለአንድ ጊዜ ለከፍተኛ ድምፅ ከተጋለጡ በኋላ ወይም ለጀሮ መጥፎ የሆኑ የመስማት ልማዶችን አዘውትረው የሚጠቀሙ ከሆነ በጊዜ ሂደት ሊመጣ ይችላል።
ስለዚህ የጀሮዎን ደህንነት ለመጠበቅ የሚከተሉትን መንገዶች ይከተሉ ፡-
1. የሚያዳምጡትን ነገር ድምፅ ከ70 ዲሲቤል(dBA) በታች ያድርጉ
ብሔራዊ የጤና ተቋማት (The National Institutes of Health (NIH)) ድምፅ የሚለካው በዲሲቤል መሆኑን ገልጾ ከ70 ዲሲቤል (dBA) በታች ያሉ ድምፆችን ለረጅም ጊዜ ቢሰሙም የመስማት ችግር የማምጣት ዕድላቸው አነስተኛ ነው ። ሆኖም ከ85 dBA በላይ ለሆኑ ድምፆች ለረጅም ጊዜ መጋለጥ የመስማት ችግርን ሊያስከትል ይችላል።
- የመሳሪያዎች የዲሲቤል መጠናቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ ስለሆነ የሚጠቀሙትን የስልክ ወይም የተለያዩ መሳሪያዎች ድምጽ ከ50% በላይ እንዳያልፍ እና የሚያዳምጡበትን ጊዜ እንዲቀንሱ ይመከራል።
- እንደ አይፎን ባሉ ስልኮች ላይ የመስማት (Hearing) አፕሊኬሽንን በመጠቀም አማካይ የድምፅ ደረጃዎን መከታተል እና ከ70 dBA በታች መቆየቱን ማረጋገጥ ይችላሉ።
2. የድምፅ ደረጃ መለኪያ መተግበሪያ (Sound Level Meter App) ይጠቀሙ
አካባቢዎ ምን ያህል ጫጫታ እንዳለው ለመለየት የሚረዱ ብዙ ነፃ ወይም ርካሽ የድምፅ መለኪያ አፕሊኬሽኖች አሉ። እነዚህም መተግበሪያዎች አንድ ድምፅ ከፍተኛ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመለየት ይረዳሉ።
3. የመስማት ችሎታን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚያስችሉ የድምፅ መከላከያዎችን (Hearing Protection) ይጠቀሙ
በዙሪያዎ ካለው ጫጫታ እርስዎን ለመጠበቅ የታቀዱ ብዙ የድምፅ መከላከያ መሳሪያዎች አሉ።
4. የመስማት ችሎታዎ እየቀነሰ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶችን በደንብ ይወቋቸው
በጣም ከተለመዱት የመስማት ችሎታ መቀነስ የመጀመሪያ ምልክቶች አንዱ ጫጫታ በበዛበት አካባቢ ለመስማት መቸገር እና ሰዎች የሚናገሩትን ነገር እየሰሙ ነገር ግን የሚናገሩትን ነገር ለመረዳት አለመቻል ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በጀሮ ውስጥ የሚሰማ ህውታም (Tinnitus) የመስማት ችሎታ መቀነስን ከሚያሳዩ የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች አንዱ ነው።
5. በየጊዜው የመስማት ችሎታዎን ይመርመሩ
ከ50 ዓመት በላይ ከሆኑ ወይም ደህንነቱ ላልተጠበቀ የድምፅ መጠን ከተጋለጡ በየዓመቱ የመስማት ችሎታዎን እንዲመረመሩ ይመከራል። የመስማት ችሎታዎ ላይ ለውጥ ካስተዋሉ ወይም በጆሮዎ ውስጥ አዲስ ወይም እየተባባሰ የሚሄድ ህውታ ካጋጠምዎ ግን ወዲያውኑ የመስማስ ችሎታዎን መመርመር ይኖርቦታል።


