ምች

Melat Geatchew
Jul 12, 2025

ምች ምንድን ነው ?

                

ቅባት ያለው ምግብ በልተው ፀሐይ ላይ ወጥተው ምች መቶዎት ያውቃል?

     ይህም በተለምዶ ምች እየተባለ የሚጠራው በከንፈርዎ ላይ የሚወጣ ሕመም ያለው እብጠት ሲሆን፤  የሚመጣውም ኤች ኤስ ቪ (HSV) በሚባል ቫይረስ አማካኝነት ነው።

ብዙውን ጊዜ ይህ እብጠት ውስጡ ውሃ የቋጠረ እና ተሰብስቦ በአንድ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ከ 2 እስከ 3  ሳምንታት ባሉት ውስጥ ይድናል። ሕመሙ ከዳነ በኋላ በአብዛኛው ጠባሳ ትቶ የማለፍ ባሕርይ የለውም።

 

በሽታው እንዴት ይተላለፋል?

ይህ ቫይረስ በመነካካት ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ይተላለፋል፡፡ በዋነኝነት በሰው ላይ በሽታ የሚያስከትሉ ሁለት ዝርያዎች አሉት። እነዚህም፤ 

  1.   ኤች ኤስ ቪ 1 (HSV 1) እና
  2.   ኤች ኤስ ቪ 2 (HSV 2) ናቸው።

ኤች ኤስ ቪ 1 ቫይረስ በብዛት በአፍ እና ከንፈር አካባቢ ያለ ቆዳን ሲያጠቃ፤ ኤች ኤስ ቪ 2 (HSV 2) ደግሞ የመራቢያ አካላትን ያጠቃል። ነገር ግን አሁን ላይ የፆታዊ ግንኙነት ባህል እየተቀየረ ስለመጣ የ ኤች ኤስ ቪ 1 (HSV 1) ቫይረስ የመራቢያ አካላትን በተመሳሳይ ኤች ኤስ ቪ 2 (HSV 2) ቫይረስ ደግሞ አፍ አካባቢ ያለን ቆዳ ሲያጠቃ ይታያል።

ሁለቱም የቫይረስ ዓይነቶች በመሳሳም፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት እንዲሁም ፎጣ እና የፂም መላጫ በመለዋወጥ ወይም በጋራ በመጠቀም በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፉ ይችላሉ። ይህም እንደሚያመለከተው ማንኛውም ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ የቆዳ ግንኙነት በሽታውን ሊያስተላልፍ እንደሚችል ነው።

 

  የበሽታ ምልክቶቹ  ምንድን ናቸው?

በሽታው የሚያሳየው ምልክት ሊለያይ ይችላል። አንድ ሰው በቫይረሱ የተጠቃው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ ምልክቶቹ ከበድ የማለት እና የመቆየት ባሕርይ አላቸው።

ለምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ በበሽታው የተጠቃ ሰው

  •  ትኩሳት
  •  ከፍተኛ ሕመም
  • የጉሮሮ ሕመም
  • ራስ ምታት
  •  የጡንቻ ሕመም እና 
  • አንገት አካባቢ ያሉ ንፍፊቶች ማበጥ ሊኖረው ይችላል።

ሰዎች በዚህ በሽታ፤

1. ለመጀመሪያ ጊዜ ሊጠቁ ወይም

2. ተደጋግሞ የሚመጣ በሽታ ሊኖራቸው ይችላል።

ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታውን ከአስከተለ በኋላ እዚያው አካባቢ ያለ ነርቭ ውስጥ ተሽሽጎ ይቆያል። ከዚያ የሚቀሰቅሰው ነገር ሲኖር ራሱን በመግለጥ ሌላ በሽታ (ምች ) ይስከትላል።

 

 እነዚህ ቀስቃሽ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡                                                                 

  • የፀሐይ ብርሃን                                                               
  • ንፋስ
  • በሽታ የመከላከል ዐቅም ከቀነሰ፤ ለምሳሌ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ     
  • ሌላ የቫይረስ በሽታ ወይም ትኩሳት ከአለ
  • ጭንቀት
  • ድካም
  • የሆርሞን ለውጥ ከአለ (ለምሳሌ በወር አበባ ጊዜ)
  • በቆዳ ላይ የተፈጠረ አደጋ ከአለ

በአጠቃላይ ግን በዋነኛነት የሚታዩ ምልክቶች፤

  • የላይኛውን ወይም የታችኛውን የከንፈር ጠርዝ በቀኝ ወይም  በግራ በኩል ሕመም የአላቸው ትናንሽ ውሃ የቋጠሩ እባጮች፤
  • ቁስሉ ከመውጣቱ አስቀድሞ አካባቢው ሊያሳክክ እና ሊያቃጥል ይችላል።
  •  እየቆየ ሲሄድ እነዚህ እባጮች ሊፈነዱ ከዚያም ጥቃቅን ክፍት ቁስሎችን እና ቅርፊቶችን ሊተው ይችላሉ።

   

ወደ ሐኪም ቤት መሄድ የሚያስፈልገው መቼ ነው?

 

  •  ምልክቶቹ ከባድ ከሆኑ
  •  በሽታ የመከላከል ዐቅምን የሚቀንሱ ሌሎች በሽታዎች ከአለብዎ
  • በሽታው በሁለት ሳምንታት ውስጥ ለውጥ ከሌለው
  •  ተደጋግሞ የሚከሠት በሽታ ከሆነ
  •  ዐይንዎን ማቃጠል እና መቅላት ከጀመረ 

 

ከበሽታው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ምንድን ናቸው?

በሽታው ወደ ተለያዩ የሰውነታችን ክፍል ሊሰራጭ ይችላል።

 ለምሳሌ፤

  •  ወደ የጣት ጥፍር 
  •  አንጎል 
  • መተንፈሻ ቧንቧ 
  • ዐይን (የማየት ችሎታን ይቀንሳል) እና የመሳሰሉት የሰውነት ክፍሎች።

 

በሽታውን እንዴት ማከም እና መከላከል ይችላል?

በሽታው በዓመት ከ 9 ጊዜ በላይ ከተከሠተብዎ ወይም ተከትለው ለሚመጡ ችግሮች የተጋለጡ ከሆኑ ሐኪምዎ የሚዋጥ መድኃኒቶችን ሊያዝዝልዎ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን በሽታው ቀለል ያለ ስለሆነ መድኃኒት መውሰድ ላያስፈልግ ይችላል። 

በሽታውን ለመከላከል የተሻለ የሆነው መንገድ፤ በመጀመሪያ ደረጃ በሽታው እንዳይዘን የራሳችንን ጥንቃቄ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ አንዴ ከተያዝን ደግሞ በሽታውን የሚቀሰቅሱብንን ነገሮች ለይቶ በማወቅ መጠንቀቅ ነው።

 

 

በሽታው እንዳይዘን ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች ምንድን ናቸው?

 

  • ቆዳው ላይ ትናናሽ ውሃ የቋጠሩ ነገሮች ከአለበት ሰው ጋር መሳሳምም ሆነ ማንኛውንም ዓይነት የቆዳ ንክኪ አለማድረግ
  • እንደ ፎጣ፣ የከንፈር ቀለም እና የፂም መቁረጫ/መላጫ የመሳሰሉ ነገሮችን ከመጋራት መቆጠብ
  •  በሽታው ከአለብዎ ደግሞ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ እጅዎን መታጠብዎን አይረሱ።

ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች በመተግበር ራስዎን ከበሽታው መከላከል ይችላሉ።   

 

በምች ለሚመጡ ቁስለቶች በቤታችን ምን ማድረግ እንችላለን?

  · የ ሕመም ማስታገሻ

    በምች በሽታ ከሚመጡ ቁስለቶች ጋር በተያያዘ የሚሰማዎትን ሕመም ለመቀነስ፤ በፋርማሲ የምናገኛችውን አይቡፐሮፈን  ወይንም ፓራሲታሞል በፋርማሲ ባለሙያው ትዛዝ መሠረት መጠቀም፡፡

 · ቅዝቃዜ

ከምች በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን በቁስሎቹ ዙርያ የሚከሠት የቆዳ መቆጣትን እና ማቃጠልን ለመቀነስ በቀዝቃዛ ውሃ በተነከረ ጨረቅ ወይም በበረዶ በቀን ውስጥ ለተወሰኑ ጊዘያት ከ5 - 10 ደቂቃ በቦታዉ ላይ መያዝ፡፡

 

 · ራስን ከጭንቀት ነጻ ማድረግ 

የአእምሮ ውጥረትን መቀነስ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ዐቅም ይጨምራል፡፡ ስለዚህም የሚያዝናኑ ነገሮችን በማድረግ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ራስዎን ማዝናናት ይችላሉ፡፡

 

 

ለምች በሽታ የባህል ሕክምናን መጠቀም ተገቢ ነዉ? 

የአገራችን የባህል ሕክምና ዳማ ከሴ (Ocimum Lamiifolium) የተባለውን ሃገር በቀል ተክል ቅጠሎች ጭማቂ በመጠጣት ወይም ቅጠሎቹን አንድ ላይ ጨፍልቆ ቁስሎቹ ላይ በማድረግ እንድንጠቀም ይመክራል። 

በዳማ ከሴ (Ocimum Lamiifolium) ጠቅላላ አጠቃቀም እንዲሁም ስለ ምች አምጪ ትሕዋስያን (anti viral) ባሕርያት ላይ  የተደረጉ ጥናቶች የሉም፡፡ ሆኖም ግን ስለ አጠቃላይ ፀረ ሕዋስ እና የሰውነት መቆጣትን መቀነስ (Anti-inflammatory) ባሕሪያት አስመልክቶ የተደረጉ አንዳንድ የሃገር በቀል ጥናቶች አሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

Comments (1)

kelelaw moges
Aug 9, 2025

አመሰግናለሁ