በኦርጋኖፎስፌት መመረዝ(Organophosphate poisoning)
በኦርጋኖፎስፌት መመረዝ (Organophosphate poisoning) ሰውነታችን በተወሰኑ የግብርና ምርቶች ውስጥ ለሚገኙ ኬሚካሎች ስንጋለጥ የሚከሰት መመረዝ ሲሆን እነዚህም ከሚካሎች የነርቭ ስርዓትን በመጉዳት ለሕይወት አስጊ የሆኑ ምልክቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ኦርጋኖፎስፌት በሚከተሉት ምርቶች ይገኛል
- ፀረ ተባይ መድኃኒቶች
- ፀረ-ነፍሳት (ነፍሳትን ይገድላል)
- አረም ማጥፊ መድኃኒቶች (አረሞችንና እፅዋትን ያጠፋል)
- የኬሚካል የጦር መሳሪያ ፤ እነዚህ የነርቭ ስርዓትዎን የሚነኩ ኬሚካሎች ሲሆኑ እንደ ጦር መሳሪያ ወይም በግብርና ላይ ጥቅም ላይ ይውላሉ
ኦርጋኖፎስፌት የነርቭ ስርዓትን እና የሰውነት አካላት ተግባርን በማስተጓጎል ሰውነትን ይጎዳል። ለከመጠን በላይ ኦርጋኖፎስፌት ለአጭር ጊዜም ሆነ ለረጅም ጊዜ መጋለጥ የመተንፈስ ችግርን እንዲሁም ህይወትን አደጋ ለይ ለሚጥሎ የጤና ችግሮች ይዳርጋል።
መመረዝ የሚያስከትሉ የኦርጋኖፎስፌት ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?
መመረዝን የሚያስከትሉ በጣም የተለመዱ ኦርጋኖፎስፌቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- ክሎርፓይሪፎስ (Chlorpyrifos) (ዱርስባን በመባልም ይታወቃል)
- ዲያዚኖን (Diazinon)
- ፈንቲዮን (Fenthion)
- ማላቲዮን (Malathion)
- ፓራቲዮን (Parathion)
የኬሚካል የጦር መሳሪያ ውስጥ ሳሪን (Sarin) የተባለው ኦርጋኖፎስፌት በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል።
የኦርጋኖፎስፌት መመረዝ ምን ያህል የተለመደ ነው?
ኦርጋኖፎስፌቶች በመደበኛ የአየር ሁኔታ ጊዜ ቀለም አልባ ወይም ቡናማ ቀለም ያለው ፈሳሽ ሲሆን አንዳንዶቹ ሽታ የሌላቸው ፤ ሌሎች ደግሞ የፍራፍሬ ሽታ አላቸው።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ እስከ 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ገበሬዎች በየዓመቱ ቢያንስ አንድ ጊዜ በኦርጋኖፎስፌት ይመረዛሉ። በፀረ-ተባይ መድኃኒት እንዳይጎዱ የሚረዱ እንደ መከላከያ አልባሳት እና ኬሚካሉን ወደ ውስጥ እንዳይተነፍሱ የሚያግዙ የመተንፈሻ መሳሪያዎች በማይጠቀሙ አርሶ አደሮች ላይ ደግሞ በተደጋጋሚ ይከሰታል።
ሳሪን የተባለው ኦርጋኖፎስፌት እንደ ኬሚካል የጦር መሳሪያ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውልም ይስተዋላል። በጃፓን ውስጥ በሁለት የአሸባሪዎች ጥቃቶች ላይ ሆን ተብሎ ጥቅም ላይ ውሏል።
ለኦርጋኖፎስፌት መመረዝ ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው?
በኦርጋኖፎስፌት መመረዝ ሰውነት ለኦርጋኖፎስፌት ሲጋለጥ የሚከሰተው ሲሆን ይህም ኬሚካል በአፍና በአፍንጫ ወይም በቆዳ ወደ ሰውነት ይገባል።
የሚከተሉት ሁኔታዎች በኦርጋኖፎስፌት የመመረዝ እድልን ይጨምራሉ ፦
- በመደበኛነት የፀረ-ተባይ ፣ የፀረ-ነፍሳት ወይም የአረም ማጥፊያ ምርቶችን የሚጠቀሙ ከሆነ
- ጦርነት ወይም ሽብር በተስፋፋባቸው ቀጠናዎች የሚኖሩ ከሆን
- በእርሻ ቦታ አካባቢ የሚኖር ወይም የሚሰራ ሰው በኦርጋኖፎስፌት የመመረዝ እድሉ ከፍተኛ ነው።
የኦርጋኖፎስፌት መመረዝ ምልክቶች ምንድ ናቸው?
የኦርጋኖፎስፌት መመረዝ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን የሚከተሉትን ምልክቶችንም ያስከትላል
- በልብና የደም ዝውውር ስርዓት - የልብ ምት መጨመር ወይም መቀነስ፣ የደም ግፊት ከፍ ማለት ወይም ዝቅ ማለት፣ መደበኛ ያልሆነ የልብ ምት
- በማዕከላዊ የነርቭ ስርዓት - ራስ ምታት፣ እረፍት ማጣት፣ የሚጥል በሽታ (seizures)፣ እራስን መሳት እና ኮማ
- በዓይን - የዓይን ማንባት፣ መቅላት፣ የአይን ብሌን መጥበብ።
- ምግብ መፈጨት ስርዓት - የሆድ ህመም፣ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ፣ ተቅማጥ ፣ የሰገራ ማምለጥ
- በሽንት ፍኛ እና ቱቦ ስርዓት - የሽንት መብዛት ወይም ማነስ ፣ የሽንት ማምለጥ
- በጡንቻና በአጥንት ስርዓት - የጡንቻ መድከም ፣ የጡንቻ መኮማተር፣ ያለፍቃድ የሚከሰት የጡንቻ መንቀሳቀስ(መንቀጥቀጥ)
- በመተንፈሻ አካላት - የትንፋሽ ማጠር ፣ በምንተነፍስበት ጊዜ የፉጨት ድምፅ መኖር (wheezing)፣ ደረት ላይ ጨብጦ የመያዝ ስሜት፣ቶሎ ቶሎ መተንፈስ (hyperpnea) ወይም ከተለመደው በታች ዝቅተኛ አተነፋፈስ (bradypnea)፣ ከሳንባ የሚወጣ ውሃማ ፈሳሽ (bronchorrhea) እና አክታ ፣ ከመጠን በላይ የሆነ ንፍጥ እና ምራቅ
- ቆዳ - ከመጠን በላይ ማላብ
የኦርጋኖፎስፌት መመረዝ አደገኛ (አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው) ምልክቶች
- በጣም የጠበቡ የዓይን ብሌኖች (very narrowed pupils)
- ግራ መጋባት (confusion)
- መነጫነጭ (agitation)
- መናድ (የሚጥል በሽታ)
- ላብ፣ ምራቅ፣ አክታ እና እንባን ጨምሮ ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ፈሳሾች መውጣት
- መደበኛ ያልሆነ የልብ ምት (irregular heartbeat)
- እራስን መሳት (collapse)
- የመተንፈስ ችግር ወይም ሙሉ በሙሉ መተንፈስ ማቆም (respiratory depression or arrest)
- ኮማ (coma)
የኦርጋኖፎስፌት መመረዝ ምርመራ
ለጎጂ ኬሚካል እንደተጋለጡ ከጠረጠሩ ሐኪሞዎ የህክምና ታሪክ በመውሰድ እና የአካል ምርመራ በማድረግ በምን እንደተመረዙ ይለያል። የኦርጋኖፎስፌት መመረዝ ሰውነት ላይ የሚያስከትለው ምልክቶች በጣም በፍጥነት መታየታቸው ከሌሎች የኬሚካል መመረዞች ይለየዋል።
ሐኪሞዎ የተመረዙበት ኬሚካል ኦርጋኖፎስፌት እንደሆነ ካረጋገጠ በኋላ የመመረዝዎ ክብደት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የተለያዩ የደም እና የሽንት ምርመራዎችን ያደርግሎታል።
እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር የኦርጋኖፎስፌት መመረዝ ለሕይወት አስጊ ስለሆነ ሐኪምዎ ሁሉም የላካቸው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤቶች ከመምጣታቸው በፊት ህክምና ሊሰጥዎ ይችላል።
የኦርጋኖፎስፌት መመረዝ እንዴት ይታከማል?
የኦርጋኖፎስፌት መመረዝ ህክምና የመጀመሪያው ዓላማ ታካሚውን ከበለጠ አደጋ ማዳን ነው። ሐኪሞ የሚከተሉትን በማድረግ ያሉበትን የጤና ሁኔታ ያረጋጋል
- ሰውነትዎ የበለጠ እንዳይመረዝ ሁሉንም ልብስዎ በማስወገድ ቢያንስ 3 ጊዜ ገላዎን በውሃ እና በሳሙና እንዲታጠቡ ያደርጋል
- ኦርጋኖፎስፌት የአተነፋፈስ ተግባርን ስለሚጎዳ የመተንፈስ ችግር እንዳይከሰትቦ ይቆጣጠራል
- መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ከሰውነትዎ ለማስወገድ በደም ስር ፈሳሽ (intravenous fluids) ይሰጦታል።
ከዚህ በተጨማሪም ሐኪሞ አተነፋፈስዎን ለማረጋጋት አትሮፒን (atropine) የሚባል መድሃኒትም ሊሰጦ ይችላል። እንዲሁም የነርቭ እና የጡንቻ ችግሮችን ለማስታገስ ፕራሊዶክሲም (pralidoxime) የተባለ መድሃኒት ይሰጦታል። የኦርጋኖፎስፌት መመረዙ ከባድ ከሆነም ሐኪሞች ብዙውን ጊዜ የሚጥል በሽታን (seizures) ለመከላከል ወይም ለማስቆም ቤንዞዲያዜፒንስ (benzodiazepines) የተባሉ መድኃኒቶችን ያዝሎታል።




