ከሻይ ጋር ፈጽሞ መመገብ የሌለባችሁ 6 የምግብ አይነቶች
ሻይ በዓለም ዙሪያ በጣም ከሚወደዱ መጠጦች መካከል አንዱ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ከተለያዩ ምግቦች እና መክሰሶች ጋር አብሮ ይቀርባል።ሆኖም አንዳንድ ምግቦች የሻይን ጣዕም ሊያጎሉ ቢችሉም ሌሎች ግን የሻይውን መዓዛ እና ጣዕም በመለወጥ አዎንታዊ ተፅዕኗቸው ይጎላል። ከዚህም አልፈው አንዳንድ ምግቦች በሻይ ውስጥ የሚገኙትን ጠቃሚ ንጥረነገሮች በሰውነት እንዳይወሰዱ እና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ያደርጋሉ።
ከሻይ ጋር መወሰድ የሌለባቸውን ምግቦች ማወቅዎ ይህን ጥንታዊ መጠጥ ለማጣጣም እና ሙሉ ጥቅሞቹን ለማግኘት ያግዞታል። የሻይ አፍቃሪ ከሆኑ እነዚህን የሻይ እና ምግብ ጥምረቶች በማስታወስ ደስ ከማይል የጣዕም ግጭት እንዲሁም ከከእነዚህ ጥምሮች ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ ከሚችሉ የጤና እክሎች እራስዎን መታደግ ይችላሉ።
ከሻይ ጋር መወሰድ የሌለባቸው 6 ምግባች እንደሚከተሉት ቀርበዋል
1) እንደ ሎሚ ያሉ ኮምጣጣ ፍራፍሬዎች
ሻይ ላይ ሎሚ መጨመር ለጤና ጠቀሜታ ቢኖረውም ከፍተኛ መጠን ያለውን ሎሚ ወይም ሌሎች ኮምጣጣ ፍራፍሬዎችን ከሻይ ጋር መውሰድ የምግብ መፈጨት ችግርን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ኮምጣጣ ፍራፍሬዎች ውስጥ ያለው ከፍተኛ የአሲድ መጠን ሻይ ውስጥ ካለው ታኒን (tannins) የተባለ ንጥረ ነገር ጋር ሲቀላቀል ቃርን ፣ የምግብ አለመፈጨትን እና የጨጓራ መቆጣትን ያስከትላል።
2) በብረት ንጥረ ነገር የበለፀጉ ምግቦች
እንደ ስፒናች፣ ቀይ ሥጋ እና ጥራጥሬ ያሉ ምግቦች ለሰውነት አስፈላጊ በሆነው በብረት ንጥረ ነገር የበለፀጉ ናቸው። ሻይ ታኒን (tannins) እና ኦክሳሌት(oxalates) የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ስለሚይዝ በእፅዋት እና በስጋ ውስጥ የሚገኘውን ነን ሂም (nonheme iron) የተባለውን የብረት ዓይነት በሰውነት እንዳይወሰድ እና ጥቅም ላይ እንዳይውል ያደርጋል። ስለዚህ ብረትን ከያዙ ምግቦች ሙሉ ጥቅማቸውን ለማግኘት ከሻይ ጋር ባይወሰዱ ይመከራል።
3) በርበሬ እና ቅመም የበዛባቸው ምግቦች
በርበሬ እና ቅመም የበዛባቸውን ምግቦች ከሻይ ጋር መውሰድ የጨጓራ ህመምን ሊያባብስ ይችላል። በሻይ ውስጥ የሚገኘው ታኒን የተባለው ንጥረ ነገር የጨጓራ ግድግዳን ሊያስቆጣ የሚችል ሲሆን በርበሬ እና ቅመም ውስጥ ከሚገኘው ካፕሳይዲን (capsaicin) ከተባለ ንጥረ ነገር ጋር ሲቀላቀል ደግሞ የሆድ አሲድ መጨመርን ፣ የምግብ አለመፈጨትን እና ቃርን ሊያስከትል ይችላል።
4) ከፍተኛ የካልሲየም መጠን ያላቸው ምግቦች
እንደ ጎመን ያሉ አረንጓዴ ቅጠላቅጠሎች ፣ የወተት ተዋፅዖዎች እና በፋብሪካ በካልሲየም የተጠናከሩ ምግቦች ሻይ ውስጥ የሚገኘውን ካቴኪን (catechins) የተባለውን አንቲኦክሲዳንት (antioxidant) ንጥረ ነገር በሰውነት ውስጥ እንዳይወሰድ እና ጥቅም ላይ እንዳይውል ያደርጋሉ። ካልሲየም ከእዚህ ንጥረ ነገር ጋር በመጣመር ውጤታማነቱን እና ሻይ ለሰውነት የሚሰጠውን አጠቃላይ የጤና ጥቅም ይቀንሳል።
5) ስኳር የበዛባቸው የታሸጉ ምግቦች
ስኳርና አርቴፊሻል ማጣፈጫ ቅመም የያዙ ምግቦች ሻይ የሚሰጠውን የጤና ጥቅም ይቀንሳሉ። እነዚህ ምግቦች ከፍተኛ የግላይሴሚክ መጠን ስላላቸው ሻይ የሚሰጠውን የደም የስኳር መጠን የማስተካከል ጥቅም ያጣፋታል።
6) ቀዝቃዛ ምግቦች
ቀዝቃዛ ምግቦችን ከትኩስ ሻይ ጋር አብሮ መውሰድ የማይመከር ሲሆን ይህም የሙቀት መጠናቸው የተለያየ በመሆኑ የምግብ መፈጨት ስርዐትን ሊያስተጓጉሉ ስለሚችሉ ነው። የተለያየ የሙቀት መጠን ያላቸውን ምግቦች በአንድ ጊዜ መመገብ የምግብ መፈጨት ሥርዓትዎን ሊያውክና ማቅለሽለሽን ሊያስከትል ይችላል። ይህንን ለመከላከል ትኩስ ሻይ ከጠጡ በኋላ ማንኛውንም ቀዝቃዛ ነገር ከመውሰድዎ በፊት ቢያንስ ለ30 ደቂቃዎች መጠበቅ ይኖርቦታል።


