የሴቶች ንፅህና ምክሮች (Feminine hygiene tips)

Elsabet Azezew
Jul 12, 2025

                                         

      የሴቶች ንፅህና ምክሮች (Feminine hygiene tips)

 

የወር አበባ ምንድን ነው?

 

የወር አበባ (Menstruation) የሚለው ቃል ወርሃዊ የማህጸን ግድግዳ መሸርሸር እና መፍሰስን ይገልጻል። የወር አበባ  ከፊል ደም እና ከፊል የሰውነት ህዋሳት ሲሆን  በማህጸን በር አድርጎ በሴት ልጅ ብልት በኩል ይፈሳል። ይህ ክስተት በሆርሞን አማካኝነት ይከሰታል።

እነዚህ ሆርሞኖች የማህጽን ግድግዳ እንዲወፍር ያደርጋሉ።  ይህም እርግዝና በሚፈጠርበት ወቅት ጽንስ በማህጽን ግድግዳ ላይ እንዲተከል እና እንዲያድግ የሚረዳ ክስተት ነው። ሆኖም ጽንስ እየጠነቀ የነበረው ማህጸን ውስጥ ጽንድ ሳይፈጠር ሲቀር ግን ይህ የማህጸን ግድግዳ ይሸረሸራል፤ ይህንንም የወር አበባ ብለን የምንጠራውን የደም መፍሰስ ያስከትላል።

 

የወር አበባ ዑደት የምንለው የትኛውን ነው?

 

የወር አበባ ዑደት የሴት ልጅ አካል በየወሩ እራሱን ለእርግዝና የሚያዘጋጅበትን ሁኔታ ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል ነው። የወር አበባ ዑደቶ የወር አበባችን  ከጀመረበት የመጀመሪያ ቀን እስከ የሚቀጥለው የወር አበባችን የመጀመሪያ ቀን ያለውን ጊዜ የሚገልጽ ነው። የእያንዳንዷ ሴት ዑደት ትንሽ ቢለያይም ሂደቱ ግን ተመሳሳይ ነው።

 

ኖርማል የወር አበባ ዑደት የምንለው ለምን ያህል ጊዜ  ነው?

 

አማካኝ የወር አበባ ዑደት 28 ቀናት ሲሆን  ከ 21 እስከ 35 ቀናት ውስጥ ሊሆን ይችላል ።   

 

የወር አበባ  ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

 

የወር አበባ የሚቆይበት ግዜ በአማካኝ  ከ 3 እስከ 7 ቀናት ሊቆይ ይችላል።

 

የወር አበባ ከየትኛው የእድሜ ክልል ይጀምራል?

 

ብዙ ሴቶች ከ 12 አመታቸው ጀምረው የወር አበባ ያያሉ። ይሁን እንጂ ከ 8 እስከ 16 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የወር አበባችን ቢጀምር ኖርማል ነው። በአጠቃላይ ግን ብዙ ሴቶች ከጉርምስና እድሜአቸው መጀመሪያ ማለትም ጡት እና የብልት ፀጉር ማውጣት ከጀመሩ ከጥቂት አመታት በኃላ የወር አበባ ማየት ይጀምራሉ።

የሴት ልጅ ያለምንም አካላዊ  እና የበሽታ ችግር ለ 12 ተከታታይ ወራት የወር አበባ ማየት ስታቆም ማረጥ እንለዋለን። ይህም በአማካኝ 51ኛ ዕድሜ ላይ ይከሰታል።

 

የወር አበባ ዑደታችን በጊዜ ሂደት ሊለወጥ ይችላል?

 

በ 40ዎቹ ወይም 50ዎቹ እድሜአችን ላይ ያለው የወር አበባ ዑደት ከ በጉርምስና እድሜአችን ካለው ዑደት ሊለይ ይችላል።  የወር አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ስናይ በአብዛኛውን ጊዜ ረዘም ያለ ዑደት እና ከባድ የወር አበባ መፍሰስ ሊኖረን ይችላል። 20ዎቹ የእድሜአችን ክልል ውስጥ ስንደርስ ዑደታችን የበለጠ የተስተካከለ ፣ ወጥ  እና መደበኛ ይሆናል። አንዴ ሰውነታችን ወደ ማረጥ መሸጋገር ሲጀምር የወር አበባ ዑደታችን እንደገና ይዛባል።

በተጨማሪ የወር አበባ ዑደታችን  በተለያዩ የሰውነታችን ሆርሞኖች ላይ ተፅዕኖ በሚያደርጉ የህይወት ክስተቶች ምክንያት ሊቀየር ይችላል፣ ለምሳሌ እንደ ከወሊድ በኋላ  እና የምናጠባባቸው ወቅቶች ላይ ሊቀየር ይችላል። 

 

በወር አበባ ወቅት ንፅህናን መጠበቅ ለሴት ልጅ ጤንነት እና ምቾት ወሳኝ ነው። የንፅህና አጠባበቅ ሂደቶች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ 

 

  • ኢንፌክሽኖችን እና መጥፎ ጠረንን ለመከላከል የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን በመደበኛነት መቀየር አለብን:: የትኞችን የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች በስንት ሰአት እንቀይር የሚለውን ከታች እንመለከታለን
  • ፓድ(ሞዴስ) እና የፓንት ላይነሮችን የምንጠቀም ከሆነ በየ 4-8 ሰዓታት መቀየር አለብን።
  • ቴምፖን (Tampon) የምንጠቀም ከሆነ በየ4-8 ሰዓቱ መቀየር አለብን። ቴምፖንን ሁል ጊዜ ቢያንስ በስምንት ሰአታት ውስጥ ማስወገድ ተገቢ ነው።
  • የወር አበባ ካፕ ወይም ዲስክ እንደ የንፅህና መጠበቂያ አማራጭ ከመረጥን  በየ4-12 ሰዓታት ውስጥ ልንለውጥ ይገባል።እነዚህን የወር አበባ ካፖች ደግመን የምንጠቀማቸው ከሆን ከመጠቀማችን በፊት በደንብ ማጠባችንን እና ንፁህ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን።
  • ሌላኛው ነገር ጠረን አልባ የሆኑ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ብንጠቀም ብግነት የመፈጠር ዕድልን ይቀንስልናል።
  • ከዚህ በተጨማሪ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ከመቀየራችን በፊት እና ከቀየርን በኃላ እጃችንን በደንብ መታጠብ አለብን ይህም የባክቴሪያን የመስፋፋት ዕድል ይቀንሳል።
  • በወር አበባ ወቅትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት አየር በቀላሉ ሊዘዋወርባቸው የሚችሉ የጥጥ ፓንቶችን ማድረግ እና ሚጠቡንን ወይም ሚያጠብቁንን ልብሶችን አለመልበስ እርጥበት እንዳይፈጠር በማድረግ  በፈንገስ ምክንያት የሚከሰት ኢንፌክሽንን መከላከል እንችላለን።
  • በየቀኑ ሻወር ማድረግ እና የብልት አካባቢን ሽታ በለሌላቸው ሳሙናዎች በጥንቃቄ መታጠብ በወር አበባ ጊዜ ንፅህናችንን ለመጠበቅ ይረዳናል:: እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር  ቢኖር ስንታጠብ የብልት የውጭ ክፍል ብቻ ነው መታጠብ ያለብን ::የሴት ልጅ  ብልት ውስጣዊ ክፍል እራሱን በተፈጥሮ ስለሚያፀዳ ጣታችንን አስገብተን መታጠብ ከማንፃት ይልቅ የበለጠ ለኢንፌክሽን ይዳርገናል::
  • በቂ ውሃ መጠጣት እና የተመጣጠነ ምግብን መመገብ። በአንቲኦክሲዳንት ፣ በቪታሚን ሲ እና ኢ፣ በኦሜጋ -3 እና ኦሜጋ -6 ፣ በፋቲ አሲድ እና በፕሮቲን የበለፀጉ የተለያዩ ምግቦችን መመገብ የብልት እና ማህጸን  ጤና ለመጠበቅ ያስችለናል።
  • በመጨረሻም የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን በአግባቡ ማስወገድ ለግል እና ለአካባቢ ንፅህና ወሳኝ ስለሆነ ይህን ማድረግ ተገቢ ነው::

 

Comments (0)