የድድ መሸሽ ከድድ በሽታዎች አንዱ ሲሆን ጥርስን የከበበው ድድ ወደኋላ እየሸሸ ይሀዳል፣ በዚህም ምክንያት የጥርስ ውስጠኛው ክፍል ወይም የጥርስ ሥር ወደ ውጪ እንዲጋለጥ ያደርጋል። ይህም ጥርሶችዎ ለመቦርቦር የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም ጥርሶችዎን ሲቦርሹ ወይም ሲመገቡ የሚረብሽ ስሜት ሊያጋጥሞት ይችላል ።
የድድ መሸሽ ቀላል፣ መካከለኛ ወይም ከባድ ሊሆን ይችላል። በአንድ ጥርስ ላይ ወይም በብዙ ጥርሶች ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
የድድ መሸሽ በሚከሰትበት ጊዜ፣ በጥርሶች እና በድድ መስመር መካከል ቀዳዳዎች ወይም ክፍተቶች ይፈጠራሉ። ይህ ደግሞ በሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች በቀላሉ እንዲከማቹ ያደርጋል። ሳይታከሙ ከቀሩ፣ ለጥርሶች ደጋፊ የሆኑት ህብረ ህዋሳት እና የአጥንት መዋቅሮች ከባድ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል፣ ይህም በመጨረሻ ጥርስ መውለቅን ሊያስከትል ይችላል።
የድድ መሸሽ ቀስ በቀስ የሚከሰት ስለሆነ ብዙ ሰው እንዳለበት ላያቅ ይችላል። ምንም እንኳን በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ሊያጠቃ ቢችልም፣ ከ65 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ግን በይበልጥ የተለመደ ነው።
የድድ መሸሽ መንስኤዎች እና አጋላጭ ሁኔታዎችኔታዎች
የተጠየቁት የድድ መሸሽ መንስኤዎችና አጋላጭ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው።
- በጣም ጠንከር አድርጎ ወይም በኃይል መቦረሽ
- የጥርስ መቦርቦር
- የድድ ኢንፌክሽኖች መኖር- ይህ የድድ መሸሽ ዋነኛ መንስኤ ነው
- በቂ ያልሆነ የጥርስ እንክብካቤ- በቂ ያልሆነ መቦረሽ፣ በክሮች ማጽዳት (flossing) እና ፀረ-ባክቴሪያ የአፍ ማጠቢያ (antibacterial mouthwash) አለመጠቀም ጥርስ ላይ ቆሻሾች እንዲጣበቁ ያደርጋል፣ ይሄም ኢንፌክሽን ይፈጥርና ለድድ መሸሽ ያጋልጣል
- በድድ ላይ አደጋ ወይም ጉዳት መድረስ
- የብሬስ ወይም ሌሎች የጥርስ ማስተካከያ ሕክምናዎች ታሪክ መኖር
- ያልተስተካከለ የጥርስ አቀማመጥ መኖር- ጥርሶች እርስ በእርስ እኩል በማይገናኙበት ጊዜ፣ በድድ እና በአጥንት ላይ ከመጠን በላይ ኃይል ሊጫኑ ይችላሉ፣ ይህም ድድ እንዲሸሽ ያደርጋል።
- ማጨስ ወይም የሚታኘክ ትምባሆ መጠቀም- ይህ ለማስለቀቅ የሚያስቸግር ቆሻሾች ጥርስ ላይ እንዲጣበቁ ያደርጋል፣ ይሄም ኢንፌክሽን ይፈጥርና ለድድ መሸሽ ያጋልጣል
- ጥርስን መፋጨት (Grinding Your Teeth)- ጥርሶችዎን ማፋጨት በጥርሶች ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር ስለሚችል፣ ድድ እንዲሸሽ ሊያደርግ ይችላል።
- ከንፈር እና ምላስ መበሳት- ጌጣጌጦች ከድድ ጋር በሚተሻሹበት ጊዜ የድድ ህብረ ህዋሳት እስኪጠፉ ድረስ ሊያዳክሙት ይችላሉ።
- የሆርሞን ለውጦች- በሴት ሕይወት ዘመን ውስጥ የሚከሰቱ የሴት ሆርሞን መጠን መለዋወጦች፣ ለምሳሌ በጉርምስና፣ በእርግዝና እና በወር አበባ መቋረጥ ወቅት፣ ለድድ መሸሽ ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆን ሊያደርጉ ይችላሉ
- በቤተሰብ ውስጥ የድድ መሸሽ ታሪክ መኖር
- ዘረመል- አንዳንድ ሰዎች ለድድ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲያውም፣ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከጠቅላላው ሕዝብ 30% ያህሉ ጥርሶቻቸውን በሚገባ ቢጠብቁም እንኳ ለድድ መሸሽ ተጋላጭነት ሊኖራቸው ይችላል
የድድ መሸሽ ምልክቶች
የድድ መሸሽ በጣም ግልጽ የሆነው ምልክት የጥርስ ሥር መታየት ነው። ሌሎች የድድ መሸሽ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ:
- በድድ አካባቢ ህመም ወይም ምቾት ማጣት።
- ለሙቀት፣ ለቅዝቃዜና ለጣፋጭ ነገሮች በጣም ስሜታዊ መሆን።
- ጥርሶችን በሚቦርሹበትና በክሮች (floss) በሚያጸዱበት ጊዜ መረበሽ።
- በሃኪም የጥርስ ጽዳት በሚደረግበት ጊዜ መረበሽ።
- ከመቦረሽ በኋላ ደም መፍሰስ
- ቀይ የሆኑ፣ ያበጡ ድዶች መኖር
- መጥፎ የአፍ ሽታ መኖር
- በግልጽ የሚታይ ወደኋላ ያፈገፈገ ድድ መኖር
- የሚንቀሳቀሱ (የላሉ) ጥርሶች መኖር
የድድ መሸሽ እንዴት ይመረመራል/ይታወቃል?
በተለመደው የጥርስ ምርመራ ወቅት የድድ መሸሽ ሊታወቅ ይችላል። የጥርስ ሐኪሞች በእያንዳንዱ ጥርስ ዙሪያ የሚገኙትን የድድ ኪሶች (periodontal pockets) ጥልቀት ለመለካት ፔሪዮዶንታል ፕሮብ (periodontal probe) የተባለ ልዩ መሣሪያ ይጠቀማሉ።
- ጤናማ ድድ ያላቸው ሰዎች እነዚህ ኪሶች ከ1 እስከ 3 ሚሊሜትር ይለካሉ።
- የድድ መቆጣት ወይም እብጠት (gingivitis) ያለባቸው ሰዎች ኪሶቹ ወደ 4 ሚሊሜትር አካባቢ ሊለኩ ይችላሉ።
- የድድ በሽታ/ኢንፌክሽን ያለባቸው ሰዎች ኪሶቻቸው ከ5 ሚሊሜትር በላይ ጥልቀት ሊኖራቸው ይችላል።
ብዙውን ጊዜ የድድ ማሽቆልቆል ያለባቸው ሰዎች አብሮ የመጣ የአጥንት መሳሳት(bone loss) ይኖራቸዋል።
የድድ መሸሽ ሕክምና
የቀዶ ጥገና ያልሆኑ ሕክምናዎች
ቀላል የድድ መሸሽ ከሆነ በተለያዩ መንገዶች ሊታከም ይችላል። ከነዚህም መካከል
- የጥርስ ጥልቅ ጽዳት- እንደ ስኬሊንግ እና ሩት ፕላኒንግ ያሉት የጥርስ ህክምናዎች ከድድ አካባቢ የሚገኘውን ጎጂ ባክቴሪያ ለማስወገድ ይረዳሉ
- የኢንፌክሽን መከላከያ መድሃኒት- ጎጂ ባክቴሪያዎችን ለማስወገድ የኢንፌክሽን መከላከያ መድሃኒት ሊሰጥ ይችላል።
- የጥርስ ቦንዲንግ (Dental bonding)- የተጋለጠውን የጥርስ ሥር የጥርስ ቀለም ባለው ሙጫ በመጠቀም መደበቅ።
- ብሬስ ማድረግ - ጠማማ፣ ያዘነበሉ ወይም የዞሩ ጥርሶች ለድድ ማሽቆልቆል አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ብሬስ ጥርሱን ወደ ትክክለኛው ቦታ ሊመልሰው ይችላል፣ ይህም የድድ ዳርቻ በራሱ ጊዜ እንዲስተካከል ያስችለዋል
- የድድ ስሜታዊነትን መቀነስ (Reducing Gum Sensitivity)- የድድ መሸሽ የጥርስዎ ሥር እንዲጋለጥ ያደርጋል፤ ይህም የጥርስን ስሜታዊነት በጣም ይጨምራል። የጥርስ ሐኪምዎ ስሜታዊነትን ለመቀነስ ፍሎራይድ ቫርኒሽ ወይም ሌሎች የስሜት ማጥፊያ መድሃኒቶችን (desensitizing agents) ሊጠቀም ይችላል። በተጨማሪም፣ በቤትዎ ስሜት ማጥፊያ የጥርስ ሳሙና መጠቀም ይችላሉ። ነገር ግን፣ እፎይታን ለመስጠት በርካታ ሳምንታት ሊወስድ ይችላል።
የድድ መሸሽ ቀዶ ጥገና ህክማና (Gum Recession Surgery)
በሽታው ከፍተኛ የአጥንት መሳሳት የሚያመጣ ከሆነ እና በጣም የከፋ ከሆነ በጥልቅ ጽዳት መታከም ላይችል ይችላል። በድድ መሸሽ የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን የድድ ቀዶ ጥገና ሊያስፈልግ ይችላል። በአጠቃላይ ሁለት አማራጮች አሉ፦ ፍላፕ ቀዶ ጥገና (flap surgery) እና ግራፍቲንግ (grafting)።
- ፍላፕ ቀዶ ጥገና (Flap Surgery)- የጥርስ ሃኪሙ ድዱን ያነሳና ያጸዳዋል። ጽዳቱ ሲያልቅ የተነሳው ድድ ወደ ቦታው ይመልሰዋል። ድዱ ከጥርስ ጋር ይበልጥ ስለሚጣበቅ ከፍላፕ ቀዶ ጥገና በኋላ ጥርሶች ይበልጥ ረጅም መስለው ሊታዩ ይችላሉ።
- ግራፍቲንግ (grafting)- የዚህ ሕክምና ግብ የድድ ህብረ ህዋሳት ወይም አጥንቶችን መልሶ ማደስ ነው። ይህ ሂደት ከአፍ ጣሪያ ላይ የተገኘ የድድ ህብረ ህዋስ ግራፍት (graft) በመጠቀም፣ የድድ ሥሮቹን ለመሸፈን በስፌት ማሰርን ያካትታል።ይህ ሂደት ትክክለኛ የአፍ ጤና እንክብካቤ ከሌለ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል ልብ ማለት ያስፈልጋል።
መከላከያ መንገዶች
መደበኛ የአፍ እንክብካቤ በተለይም በዘር ውርስ ምክንያት ቀጭን የድድ ህብረ ህዋስ ላለባቸው ሰዎች የድድ መሸሽ አደጋ ሊቀንስ ይችላል። ነገር ግን ድድ እንደገና ሊያድግ አይችልም። የድድ መሸሹ እንዳይባባስ ለመከላከል እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ። ከመከላከያ መንገዶቹም መካከል፤
- ጥርስዎን በቀን ሁለት ጊዜ በደንብ ይቦርሹ።
- በየቀኑ በጥርስ ክር (floss) ያጽዱ።
- ለስላሳ የጥርስ ብሩሽ ይጠቀሙ።
- ከማጨስ ወይም የሚታኘክ ትምባሆ ከመጠቀም ይቆጠቡ።
- በቀን ሁለት ጊዜ ፀረ-ተህዋሲያን የአፍ ማጠቢያ (antimicrobial mouthwash) ይጠቀሙ።


