ጥርስዎን ከቦረሹ በኋላ አፍዎን በውሃ መጉመጥመጥ ይመከራል?
አብዛኞቻችን ጥርሳችንን መቦረሽ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ተመሳሳይ ልማድ አለን ፤ ይህም መቦረሽ፣የጥርስ ሳሙናውን መትፋት እና መጉመጥመጥ ነው።ይሁን እንጂ ጥርስዎን ከቦረሹ በኋላ አፍዎን በውሃ መጉመጥመጥ ሁልጊዜ አይመከርም።
ፍሎራይድ እና የጥርስዎን ሽፋን (tooth enamel) የሚያጠነክሩ ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ከያዙ የጥርስ ሳሙናዎች ሙሉ ጥቅማቸውን እንዲሰጥዎት በጥርሶችዎ ላይ ትንሽ ተጨማሪ ጊዜ ሊቆዩ ይገባል።በዚህ ፅሁፍ ጥርስ ከቦረሹ በኋላ አፍን መጉመጥመጥ ስለሚሰጣቸው ጥቅሞች እና ስለሚያስከትለው ጉዳት እንመልከት።
ከቦረሹ በኋላ ጥርሶን መጉመጥመጥ የሚያስከትለው ጉዳት
አፍዎን ከቦረሹ በኋላ መጉመጥመጥ የተለመደ ልማድ ቢሆንም የጥርስ ጤና ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ከቦረሹ በኋላ ወዲያውኑ አፍዎን መጉመጥመጥ አይመከርም።
ፍሎራይድ ጥርስን ከመበስበስ ለመከላከል ከሚረዱ ንጥረ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ትንሽ መጠን ያለው ፍሎራይድ በተፈጥሮ በአንዳንድ ምግቦች ውስጥ ይገኛል። እንዲሁም አንዳንዴ የጥርስ ጤናዎን ለማሻሻል ወደ ሚጠጡት ውሃ እና የአፍ ጤናን ለመጠበቅ በሚያስችሉ ምርቶችም ላይ ይጨመራል።ፍሎራይድ ለጥርስዎ በጣም የሚጠቅመው በቀጥታ በጥርሶ ላይ ሲቀባ ነው። በተለይ በጥርስዎ ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ሲቆይ ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል ።
ከቦረሹ በኋላ አፍዎን መጉመጥመጥ ዝም ብሎ የመጣ ልማድ አይደለም። በአጠቃላይ ከፍተኛ መጠን ያለውን ፍሎራይድ እንዲውጡ አይመከርም። አንዳንድ የጥርስ ማፅጃ ምርቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ፍሎራይድ ስለሚይዙ፣ ብዙ ፍሎራይድ ወደ ሆድ እንዳይገባ ለመከላከል መጉመጥመጥ ይመከር ነበር። እንዲሁም በአፍ ውስጥ የሚቀረውን ጠንካራ የሳሙና ጣዕም በውሃ ለመተካት በሚል ብዙ ሰው ይጉመጠመጣል።
ይሁን እንጂ ጥርስዎን ከቦረሹ በኋላ ወዲያውኑ መጉመጥመጥ ጥርስዎ ከፍሎራይድ ማግኘት ያለበትን አብዛኛውን ጥቅም እንዲያስወግዱ ያደርጋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የአፍ ጤና ፋውንዴሽንን ጨምሮ አንዳንድ ባልሙያዎች በአሁኑ ጊዜ የሚመክሩት ከቦረሹ በኋላ አፍን ከመጉመጥመጥ ይልቅ አፍ ውስጥ የቀረውን የጥርስ ሳሙና እንዲተፉ ነው። እንዲሁም ከቦረሹ በኋላ ለ 10 ደቂቃዎች ወይም ከዚያ በላይ ምን አይነት ምግብ እና መጠት ባይወስዱ ይመከራል።
ጥርስዎን ከቦረሹ በኋላ አለመጉመጥመጥ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት
አብዛኛውን ጊዜ ለብዙ ሰዎች ጥርሳቸውን ከቦረሹ በኋላ አፋቸውን አለመጉመጥመጥ ምንም አይነት ጉዳት የለውም። ሆኖም ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው አንዳንድ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉ።
ከፍተኛ የፍሎራይድ መጠን ያላቸውን የጥርስ ምርቶችን መዋጥ ፈጽሞ አይመከርም ። ከመጠን በላይ የሆነ ፍሎራይድ ወደ ሆድ ከገባ የሚከተሉትን ሊያስከትል ይችላል፦
- ማቅለሽለሽ
- ተቅማጥ እና
- የሆድ ህመም ያስከትላል ።
ሆኖም እነዚህ የጎንዮሽ ጉዳቶች የአተር ፍሬ መጠን የሚያክል ፍሎራይድ የያዘ የጥርስ ሳሙና ከመጠከም የመከሰት እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው ። ብዙውን ጊዜ እነዚህ የጎንዮሽ ጉዳቶች የሚከሰቱት ልጆች ለአዋቂዎች ታስበው የተሰሩ ከፍተኛ የፍሎራይድ መጠን ያላቸውን ምርቶች ሲጠቀሙ ወይም በጥርስ ሐኪም ቢሮ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ከፍተኛ የፍሎራይድ መጠን ያላቸውን ምርቶች ተገቢ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውሉ ብቻ ነው።
ስለዚህ ጤናማ የሆነ አዋቂ ሰው ትንሽ መጠን ያለው የጥርስ ሳሙና በመዋጥ ብቻ ለከፋ የፍሎራይድ መመረዝ የመጋለጥ እድሉ እጅግ በጣም አናሳ ነው።


