እንቅርት በታችኛው አንገት ውስጥ በፊት ለፊት የሚገኝ እጢ ነው፡፡ የልብን፣ የጡንቻን እና የምግብ መፈጨት ሥራን እንዲሁም የአንጎል እና የአጥንት ዕድገትን የሚቆጣጠር ሆርሞኖችን ያመነጫል።
የእንቅርት በሽታ በሀገራችን
በሀገራችን የእንቅርት ችግር 1.2 % ቢሆንም ከግማሽ በላይ የሚሆነው ታማሚ ግን ይህ ችግር እንዳለበት አያውቅም።
በሴቶች ላይ ለምን ይበዛል?
ይህም የሆነው በሴት ሆርሞን ኤስትሮጅን (estrogen) አማካኝነት ነው። ይህም ኤስትሮጅን የእንቅርት ዕጢ እንዲተልቅ ያደርገዋል።
የእንቅርት ዕጢን የሚያተልቀው ምንድንነው?
● የአዮዲን ንጥረ ነገር እጥረት
● የእንቅርት ሆርሞን መብዛት
● የእንቅርት ካንሰር (neoplastic)
● የእንቅርት መቆጣት
● እርግዝና፣ የጉርምስና ዕድሜ
● አንዳንድ መድኃኒቶች ( amiodarone,lithium) ናቸው።
የእንቅርት ዕጢ (Thyroid nodules) የተለመደ ከመሆኑም በላይ አብዛኛውን ጊዜ ለጤና ጎጂ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያመጣ ይችላል።
● በአንገት ላይ የግፊት ስሜት
● የትንፋሽ እጥረት
● ምግብ ለመዋጥ መቸገር
● የድምፅ መቀየር፣ ብዙ ጊዜ መጎርነን
● ይህ ችግር የአለባቸው ሕመም ሊኖራቸው ስለሚችል ቅርብ የሕክምና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህም በሕክምና ተቋማት የእንቅርትን ምንነት ለመለየት ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ።
የእንቅርት ሆርሞን መብዛት (Hyperthyroidism)
አንዳንድ ጊዜ የእንቅርት ዕጢ በጣም ብዙ የእንቅርት ሆርሞን እንዲመረት ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ለሚከተሉት ምልክቶች ይዳርጋል፡፡
● የስሜት መረበሽ ወይም በቀላሉ መናደድ
● እንቅልፍ የማጣት ችግር
● የድካም ስሜት
● ያልታሰበ ክብደት መቀነስ ከምግብ ፍላጎት መጨመር ጋር
● ፈጣን የልብ ምት
● መንቀጥቀጥ
● ሙቀት መሰማት፣ ማላብ
● የወር አበባ መዛባት፣ ልጅ ለመፀነስ መቸገር
● የዐይን ኳስ ወደፊት መውጣት እና
● ቶሎ ቶሎ መፀዳዳት ናቸው።
ሕክምናውስ?
ሕክምናው መድኃኒቶችን፣ ቀዶ ጥገናን እና ሬዲዮአክቲቭ አዮዲንን ሊያጠቃልል ይችላል። በአጠቃላይ ሁለት ዓይነት መድኃኒቶች ይሰጣሉ ።
● ዕጢው የሚያመርተውን ሆርሞን የሚቀንሱ ( anti-thyroid)
● ምልክቶችን ለመቀነስ የሚረዱ (Beta blockers)
እነዚህም የእንቅርት ሆርሞን ሚዛን እስኪስተካከል ድረስ ምልክቶችን በመቀነስ የበለጠ ምቾት እንዲኖር ያደርጋሉ።
● ሬዲዮአክቲቭ አዮዲን
መድኃኒቱ የሚወሰደው በሚዋጥ ክኒን ወይም ፈሳሽ መልክ ሲሆን ዕጢው እንዲጠፋ ያደርጋል። ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ ሴቶች ይህንን ሕክምና መጠቀም የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም የሕፃኑን የእንቅርት ዕጢ ሊጎዳ ይችላል። ሕክምናውን የወሰዱ ሴቶችም ለማርገዝ ከመሞከራቸው በፊት ቢያንስ 6 ወር መጠበቅ አለባቸው።
● ቀዶ ጥገና
ሌሎች የሕክምና ምርጫዎች ካልተሳኩ በቀዶ ጥገና ዕጢው እንዲወጣ ይደረጋል። ነገር ግን በአብዛኛውን ጊዜ ቀዶ ጥገናው ከመደረጉ በፊት የሆርሞኑን መጠን ለማስተካከል እና ምልክቶቹን ለመቆጣጠር የሚያግዙ በአፍ የሚወሰዱ እንክብሎች ይታዘዛሉ።
የመድኃኒቶቹ መጠን የሚስተካከለው ተከታታይ የደም ምርመራዎችን በማድረግ ስለሆነ ታማሚዎች በመደበኛነት በጤና ተቋም ክትትል ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ በሬዲዮአክቲቭ አዮዲን ወይም በቀዶ ጥገና ሕክምና የተደረገላቸው ሰዎች ከሕክምና በኋላ በጣም ትንሽ የእንቅርት ሆርሞን ሊቀራቸው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት በቀሪው ሕይወታቸው የእንቅርት ሆርሞን ክኒኖች መውሰድ ሊኖርባቸው ይችላል።




