ከንፈርሽን ማስተለቅ ትፈልጊያለሽ ?
ከንፈሮችሽ ውብ፣ በመጠን ተለቅ ያሉ እና እብጥ ያሉ እንዲሆኑ ከፈለግሽ ምናልባት ከንፈር ለመጨመር እና ለማሳመር የሚረዱ ነገሮችን አስበሻል። ይህ ሂደት ቀላል ነው በቀዶ ጥገና ወይም በመርፌ በሚሰጡ የህክምና ሂደቶች ሊከናወን ይችላል። ፊለሮች ወይንም መሙያዎች የፊት መጨማደድን ለመመለስ ለማለስለስ እና የፊት ወይም የሰውነት ገፅታን ለማሻሻል ከቆዳ ስር የሚወጉ ንጥረ ነገሮች ሲሆኑ በብዛት በጄል መልክ ያሉ እና በመርፌ በባለሙያ የሚሰራ የቆዳ ማስዋቢያዎች ናቸው። ለመዋቢያነት እንዲሁም ጠባሳን ለማከም ወይም የአጥንት እና የድድ የህክምና ለመስጠት ልንጠቀምባቸው እንችላለን።
የከንፈርን መጠን ለመጨመር በጣም ታዋቂው እና የተለመደው መንገድ የከንፈር መሙያዎች ወይንም ፊለርስ (Fillers) ናቸው። በጣም ቀላል እና ከቀዶ ጥገና ይልቅ ፈጣን የማገገሚያ ጊዜ አላቸው። የአሰራር ሂደቱም ከበርካታ የከንፈር መሙያ ዓይነቶች ውስጥ አንዱን ወደ ከንፈር ውስጥ ማስገባትን ያካትታል።
ብዙ ጊዜ እድሜያችን ሲጨምር በተፈጥሮ ኮላጅን የተባለውን ፕሮቲን እና ስብን ቀስ በቀስ እናጣለን፣ ይህም ከንፈርን ጨምሮ የፊት ቆዳን እንዲሳሳ እና ውጥር የሚል ገጽታው እየጠፋ ይመጣል። የከንፈር መሙያዎች ወይንም ፊለርስ የሚሠሩት በተለያየ ምክንያት የሌለውን ወይንም የጠፋውን ኮላጅን እና ስብን በመተካት ነው።
የምትፈልጊውን የከንፈር መልክ ለመወሰን
የከንፈር ፊለር መሙላትን ለማድረግ በምታስቢበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊታሰብበት የሚገባው ነገር ምን አይነት የፊለር አይነት ነው አንቺ የፈለግሽው የሚለውን መመለስ ይኖርብሻል። የከንፈሮችሽን ጠርዞች ጎላ ያለ ቅርጽ እንዲኖራቸው ትፈልጊያለሽ ወይንስ ትልቅ ሆነው እንዲታዩ የሚረዱ ፊለሮች መሙላት ትፈልጊያለሽ? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማወቅ ምን አይነት ፊለር ለአንቺ ተስማሚ እንደሆነ ለመወሰን ይረዳሻል።
የምትፈልጊውን የፊለር አይነት መምረጥ
የፊለር አይነት በምትመርጭበት ጊዜ ምርጫሽን ለመወሰን የፊለር ባህሪ እና አይነቶቹን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። ከታሪክ አኳያ ኮላጅን - በእንስሳት አካላት ውስጥ የሚገኝ ፕሮቲን ንጥረነገር - ይህ አይነቱ የፊለር አይነት በጣም የተለመደው የከንፈር መሙያ አይነት ነው። ይሁን እንጂ በአሁን ሰዓት እምብዛም ጥቅም ላይ አይውልም። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በጣም ረጅም ጊዜ ስለማይቆይ ነው። በተጨማሪም ለብዙ ሰዎች የሰውነት አለርጂ መነሻ ሊሆን ይችላል።
ሁለተኛው አይነት የፊለር አይነት ደግሞ የሃያዩሮኒክ አሲድ ሙሌት ወይንም ፊለር አሁን ሰዓት በብዛት ጥቅም ላይ ከሚውሉት የከንፈር ማስዋቢያ እና ማሳደጊያ ፊለር ነው። ሃያዩሮኒክ አሲድ ከባክቴሪያ የተሠራ ጄል-መሰል ንጥረ ነገር ነው። በቆዳ ውስጥ ከሚገኙ የውሃ ሞለኪውሎች ጋር በማያያዝ ወፍራም የከንፈር ገጽታን ይፈጥራል። እነዚህ ሙሌቶች በዝግታ ወደ ሰውነታችን ሊሳቡ እና የሚፈልጉትን አይነት መልክ ለማግኘት ባለሙያዎች ሊወፍሩት ወይም ሊያቀጥኑት ይችላሉ።
ስንት ግዜ ይቆያሉ ?
የኮላጅን ፊለሮች ለ 3ወር ብቻ የሚቆዩ ሲሆኑ የሃያዩሮሊክ አሲድ ፊለሮች ደግሞ እንደ አይነታቸው እና አገልግሎታቸው ከ 6 እስከ 18 ወር ሊቆዩ ይችላሉ ። የሃያዩሮሊክ ፊለሮች በየስድስት ወሩ ተደጋጋሚ ሕክምናዎችን በምድረግ ለውጡ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል። ብዙ ተመራማሪዎች የሃያዩሮኒክ አሲድ መርፌዎች ቆዳችን ብዙ ኮላጅን የተባለውን ለውበት የሚረዳንን ፕሮቲን እንዲያመነጭ ስለሚያደርግ ሴቶች በከንፈሮቻቸው ውስጥ የበለጠ ተፈጥሯዊ ውፍረት እንዲፈጠር ያደርጋል።
የከንፈር ፊለሮች የሚያስከትሉት አደጋዎች
ለሃያዩሮኒክ አሲድ የአለርጂ ምላሾች - አንዳንድ ሰዎች ለሲህ አይነቱ የ ፊለር አይነት የአላርጂክ ምላሽ (Allergic reaction) ለውጦችን ሊያሳዩ ይችላሉ ። የመከሰት እድሉ በጣም ዝቅተኛ ቢሆንም ግራኑሎማ የተባሉ የቆዳ እብጠት ሊኖር ይችላል።
ሌላኛው ብዙም ያልተለመደ የጎንዮሽ ጉዳቱ ደግሞ የታገደ የደም ቧንቧ ነው። ይህ ወደ ከንፈር የሚሄደውን የደም ፍሰት ይቀንሳል። በመጨረሻም የከንፈር አካላትን ሊጎዳ ይችላል፣ነገር ግን ለዶክተሮች መለየት ቀላል ነው ።
ፊለር ካስደረግን በኋላ ….
ከሂደቱ በኋላ በከንፈሮቻችሽ ላይ አነስተኛ እብጠት ሊኖር ይችላል። እንዲሁም መርፌዎቹ በከንፈሮቻችሽ ውስጥ የተወጉበት ትንሽ ቀይ ቦታዎች ሊታዩ ይችላሉ።
በከንፈር አካባቢ መበለዝ እና የቆዳ ቀለም መቀየር ሌላው የተለመደ የጎንዮሽ ጉዳት ሲሆን ይህም ለአንድ ሳምንት ያህል ሊቆይ ይችላል። ከሂደቱ በኋላ ከንፈርሽ ፊለሩ ወይንም መሙያው በመኖሩ ምክንያት የተለየ ስሜት ሊሰማሽ ይችላል።
አንዳንድ ሴቶች ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ፈገግ ለማለት ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ።ይህም የሆነበት ምክንያት ከንፈራቸውን ሲያንቀሳቅሱ ትንሽ ህመም ስለሚሰማቸው ይህ ደግሞ የተለመደ እና እየተጠፋ ተሚመጣ ህመም ነው።
የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሐኪምሽ ለሁለት ቀናት ያህል ከንፈርሽን ወደፊት እንደመሳም አይነት እንቅስቃሴ እንዳታደርጊም መመሪያ ሊሰጥሽ ይችላል።




