በአንድ ወቅት በመጽሃፎች፣ በጋዜጦች፣ በሰዎች እና በእኛ አእምሮ ይፈቱ የነበሩ ብዙ ተግባራት አሁን በኤ.አይ (AI) ተተክተዋል። እነዚህ መሳሪያዎች የማሰብ ጥረታችንን በመቀነስ እና የዕለት ተዕለት ኑሮን ጊዜ የሚወስድ እና የሚያስጨንቅ እንዳይሆን በማድረግ ቅልጥፍናንና ምርታማነትን ከፍ አድርገዋል።
የሰው አንጎል አዳዲስ የነርቭ መስመሮችን ይፈጥራል እና ነባር የሆኑትን ያስተካክላል። ይህ ሂደት ኒውሮፕላስቲክቲ (neuroplasticity) የሚባል ሲሆን ለመማር፣ ክህሎት ለማዳበር እና ለአጠቃላይ የአእምሮ ተግባራችን ወሳኝ ነው። ነገር ግን ቴክኖሎጂ ሕይወታችንን ቀላል ማድረግ ሲቀጥል፣ በኤ.አይ (AI) ላይ ከልክ ያለፈ ጥገኝነት ይኖረናል። በዚህም ምክንያት በጥልቅ የማሰብ ፍላጎታችንን እና ተነሳሽነታችንን ይቀንሳል ፣ ይህም አእምሮአችን አዳዲስ የነርቭ መስመሮችን ለመፍጠር እንዲቸገር ያደርገዋል፣ ከዚያም የአእምሮ መዳከም (Cognitive Atrophy) ያጋጥመናል።
በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (MIT) ተመራማሪዎች የወጣ አዲስ ጥናት፣ እንደ ጽሁፎችን መጻፍ ባሉ ከፍተኛ የእውቀት እና ማሰብ በሚጠይቁ ተግባራት ላይ በኤ.አይ (AI) ላይ መመርኮዝ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ አቅርቧል።
በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (MIT) የተደረገው ጥናት አስገራሚ ውጤቶችን አሳይቷል።
- 54 አሜሪካውያን አዋቂዎች (ከ18-39 ዓመት) ለአራት ወራት አራት ድርሰቶችን እንዲጽፉ ተጠይቀው ነበር፤ ከተሳታፊዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ቻት ጂፒቲን (ChatGPT)፣ ሌሎቹ ደሞ እንደ ጉግል (google) አይነት የኢንተርኔት መተግበሪያዎችን እና የተቀሩት ደግሞ ያለ ምንም መሳሪያ አንጎላቸውን ተጠቅመው እንዲጽፉ ተደርገዋል።
- በመጀመሪያዎቹ ሦስት ድርሰቶች፣ ቻት ጂፒቲን የተጠቀመው ቡድን የአንጎል የኤሌክትሪክ ትስስራቸው (electrical connectivity) ከሌሎቹ ሁለቱ ቡድኖች ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል።
- የመጨረሻው ድርሰት ላይ ቡድኖች እንዲቀያየሩ ታዘዙ። አንጎላቸውን ብቻ የሚጠቀሙት ቡድን ቻት ጂፒቲን እንዲጠቀሙ እና ቻት ጂፒቲን ይጠቀሙ የነበሩት ቡድኖች ደግሞ አንጎላቸውን ብቻ እንዲጠቀሙ ተደረገ።
ተመራማሪዎቹ የአንጎልን ምርመራ (EEGs)፣ የቋንቋ ግምገማ እና ከስራው በኋላ የተደረጉ ቃለ-መጠይቆችን በመጠቀም፣ ቻት ጂፒቲን መጠቀም የሚከተሉትን ችግሮች አሳይቷል፦
- አንጎላቸውን ብቻ ከተጠቀሙት ቡድን ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም ዝቅተኛ የአእምሮ የኤሌክትሪክ ትስስር መኖር- በኤ.አይ (AI) እገዛ በበዛ ቁጥር፣ በተለይም በማስታወስ፣ በትኩረት እና በሥራ አመራር ውስጥ የተሳተፉ ቁልፍ የአንጎል አካሎች ያነሰ ተሳትፎ አሳይተዋል።
- በፅሁፋቸው ላይ የባለቤትነት ስሜት መቀነስ፤ ኤ.አይ (AI) ተጠቃሚዎች የፅሁፉ ባለቤትነት ላይ የተደበላለቀ ስሜት ነበራቸው።
- ከፃፉት ድርሰት ውስጥ ጥቅሶችን በደንብ ማስታወስ አለመቻል።
በተጨማሪም በኤ.አይ(AI) ቡድን ውስጥ ያሉት ድርሰቶች በይዘት የበለጠ ተመሳሳይነት ነበራቸው፣ በአንጎል ብቻ የጻፉት ቡድን ግን ይበልጥ የተለያዩ ሃሳቦች ነበራቸው።
AI ተግባራትን ቀላል ቢያደርግም፣ የሚጠይቀው የጥረት ማነስ ከጊዜ ወደ ጊዜ የእውቀት ብቃትን፣ ሂሳዊ አስተሳሰብን እና የፈጠራ ችሎታን ሊያዳክም ይችላል።
በ2024 በተሰራ ጥናት መሠረት፣ ጥልቅ አስተሳሰብ በሚጠይቁ ተግባራት ላይ በAI መሳሪያዎች ላይ መመርኮዝ የሚከተሉትን አደጋዎች ሊያስከትል ይችላል፦
- የአእምሮ ተሳትፎ መቀነስ
- እንደ ስሌት ያሉ የአእምሮ ችሎታዎችን ችላ ማለት
- የማስታወስ አቅም መዳከም
- ትኩረት ቶሎ ማጣት እና ትኩረት የማድረግ ችግሮች
- እውቀትን በአዲስ ሁኔታዎች ላይ መተግበር አለመቻል
- የሥነ ምግባር እና ማኅበራዊ ስጋቶች (ከዘው ጋር ያላቸው ግንኙነት መቀነስ)
- የአእምሮ ጤና ችግሮች (እንደ በራስ መተማመን መቀነስ)
የኤ.አይን አሉታዊ ተጽዕኖ እንዴት መቀነስ ይቻላል?
መልሱ በቀላሉ "ኤ.አይን መጠቀም ይቀንሱ" አይደለም። እንዴት እንደሚጠቀሙበት ማጤን ያስፈልጋል። ኤ.አይ በአንዳንድ መንገዶች ጥቅም ላይ ሲውል፣ ጥልቅ አስተሳሰብን ሊያበረታታ፣ የፈጠራ ችሎታን ሊያነሳሳ እና ውጤታማነትን ሊያሻሽል ይችላል። በዕለት ተዕለት ሕይወትዎ ውስጥ ጥቂት ቀላል እንቅስቃሴዎችን ማካተት አንጎልዎን ሊያነቃቃና ጤናማ የነርቭ እድገትን ሊያበረታታ ይችላል።
የAIን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ
1 . ኤ.አይን መረጃን ለማረጋገጥ ብቻ ይጠቀሙ
ኤ.አይ ለእርስዎ እንዲጽፍ ወይም እንዲያስብ መፍቀድ ውጤታማ ቢመስልም የረጅም ጊዜ ሂሳዊ አስተሳሰብን ሊያዳክም ይችላል። ስለዚህ እንዲያስብልን ከማረግ ይልቅ መረጀን ለማረጋገጥ ብቻ ይጠቀሙ። ኤ.አይን ለጽሑፍ ከተጠቀሙ፣ በራስዎ ቃላት ያስተካክሉ።
2. ዲጂታል ዲቶክስ (Digital Detoxing)
ከዲጂታል መሳሪያዎች ለተወሰነ ጊዜ መራቅ የአእምሮ ጭንቀትን እና ውጥረትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ታይቷል። ዲጂታል ዲቶክስ ማለት በቤት ውስጥ ወይም በቀን ለተወሰኑ ሰዓታት ከቴክኖሎጂ ነጻ ጊዜ ማሳለፍ ነው። ይህንን ጊዜ ያለ ስልክ ወይም ኮምፑተር ስራዎትን ለመስራት ይሞክሩ፡ የወረቀት መጽሐፍ ወይም ጋዜጣ ያንብቡ፣ ውጭ ይራመዱ ወይም ከእራት ጠረጴዛ ላይ ስልኮችን ይከልክሉ።
3. ስልክ ወይም ኮምፑተር ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜን መከታተል
በስልክ ወይም ኮምፑተር ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመከታተል ይሞክሩ። ይህ አጠቃቀምዎን ሚዛናዊ ለማድረግ ያበረታታል። ምንም አይነት ትኩረትን የሚከፋፍል ነገር ሳይኖር ተግባራትን ማጠናቀቅ እና ለራስዎ ጊዜ መወሰን የበለጠ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲያተኩሩ፣ አስጻሰብን እንዲያሻሽሉ እና ጭንቀትን እንዲቀንሱ ሊረዳዎ ይችላል።
4. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎ ውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማካተት ከመጠን በላይ ኤ.አይ አጠቃቀም በአእምሮ ችሎታ እና በአጠቃላይ የአንጎል ጤና ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ይረዳል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አጠቃላይ የአእምሮ ብቃትን፣ የማስታወስ ችሎታን እና ትኩረትን ያሻሽላል።
5. አንጎልዎን መጠቀም
አንጎልን ንቁ ለማድረግ ከሚጠቅሙ መንገዶች አንዱ አእምሮ በሚያነቃቁ ተግባራት ላይ በየጊዜው መሳተፍ ነው። እንቆቅልሾችን መስራት፣ ሱዶኩ ወይም ቼዝ መጫወት፣ ማንበብ እና አዲስ ቋንቋ ወይም የሙዚቃ መሳሪያ መማር የአእምሮ ብቃትን ይጨምራሉ።
6. ኤ.አይን እንደ መርጃ መሳሪያ ብቻ መጠቀም
ኤ.አይን ከማማከርዎ በፊት መልሱን በራስዎ ማሰብ ልምድ ያድርጉ። ኤ.አይ ምላሽ ሲሰጥ፣ ምላሹን ይፈትሹ፣ ኤ.አይ ሁልጊዜ ትክክል አይደለም።
7. አመጋገቦን ያስተካክሉ
አመጋገብ ለአንጎል ጤና በጣም ወሳኝ ነገር ነው። እንደ ኦሜጋ-3 (Omega-3 fatty acids) ያሉ ንጥረ ነገሮችን መውሰድ መማርን፣ የማስታወስ ችሎታን እና የአንጎልን የደም ፍሰት ይጨምራል።


