ኖርማል ወይንም ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን የምንለው መቼ ነው ?
የደም ግፊትን (Blood pressure) በትክክል መለካት እና መተርጎም የደም ግፊትን ለመመርመር እና ለመቆጣጠር አስፈላጊ ነው። የደም ግፊት ስንለካ የምንጠቀማቸው መሳሪያዎች በትክክል የሚሰሩ መሆናቸውን ፣ ተገቢ የሆኑ የስፋት መጠኖች መጠቀማችንን እንዲሁም በህክምና ተቋም ውስጥ የምንለካ ከሆነ የጤና ባለሙያዎች በተገቢው መልኩ የሰለጠኑ እና ታካሚው ወይንም የደም ግፊት መጠኑ የሚለካለት ሰው በአግባቡ መቀመጡን ማረጋገጥ ተገቢ ነው።
የደም ግፊት መጠንን መለኪያ ስልቶች ?
የደም ግፊት (Blood pressure) ከሚከተሉት ሶስት ተቀባይነት ካላቸው ስልቶች አንዱን በመጠቀም ሊለካ ይችላል።
- የእንቅስቃሴ የደም ግፊት ክትትል (ABPM)
- በቤት ውስጥ የሚደረግ የደም ግፊት ክትትል
- በሐኪም ቢሮ ላይ የተመረኮዙ የደም ግፊት ልኬታዎች ናቸው።
የእንቅስቃሴ የደም ግፊት ክትትል (ABPM) ፦
ይህ ለ24-48 ሰአታት ውስጥ ያለን የደም ግፊት መጠን በሚለካ መሳሪያ የሚደረግ ሲሆን መሳሪያው በታካሚው እጅ ላይ ለ 24 ወይንም 48 ሰዓታት ውስጥ የሚለካ ነው። ይህም ማለት ቀን ላይ በየ15 እስከ 20 ደቂቃ፣ በእንቅልፍ ጊዜ( በምሽት ግዜ ) በየ60 ደቂቃው ልኬታን ይወስዳል። እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን ነገር በዚህ ልኬት የሙሉ 24-ሰዓት ንባቦችን ማግኘት ካልተቻለን የ6 እስከ 8 ሰአት ABPM ንባብ በቂ ሊሆን እንደሚችል ነው።
የቤት የደም ግፊት ክትትል ፦
በቤት ውስጥ የሚደረግ የደም ግፊት ልኬት በታካሚዎች ወይንም በቤተሰቦቻቸው በቤት ውስጥ የሚደረግ ሲሆን ብዙ ግዜ ይህ የልኬት ዘዴ ታካሚዊች አሁን ያላቸውን የደም ግፊት መጠን እንድናውቅ እና ታካሚዎችም በቤታቸው በምቶት እንዲለኩ ያደርጋል። ነገር ግን ይህ የክትትል አይነት በብዛት እና በተለያዩ ምክንያቶች አስተማማኝ የልኬት መረጃ ሊሰጠን ስለማይችል የህክምና ውሳኔ ከመወሰናችን በፊት በህክማን ተቋም ለክተን ማረጋገጥ ይኖርብናል። እንዲሁም የደም ግፊት ላለባቸው ታካሚዎች ለሕክምና ክትትላቸው ጠቃሚ ነው።
በህክምና ተቋም ውስጥ የሚደረግ የደም ግፊት ክትትል ፦
ይህ በህክምና ተቋም ውስጥየሚደረግ የደም ግፊት ልኬት ሲሆን ለደም ግፊት ምርመራ እና ሕክምና ዋነኛው ስልት ወይም መንገድ ነው።
የደም ግፊት ምርመራ ከማድረጋችን በፊት ማድረግ ያለብን ቅድመ ሁኔታዎች
የደም ግፊት ልኬት ከመለካታችን በፊት ማስተካከል ያሉብን የተለያዩ ነገሮች አሉ። የደም ግፊት ምርመራ ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ነገሮችን ምርመራው ከመደረጉ ከ 30 ደቂቃ በፊት ማስወገድ ተገቢ ነው። እነዚህም ምግብ መመገብ፣ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ (የደም ግፊትን ይቀንሳል) ፣ ሲጋራ ማጨስ እና ካፌይን መውሰድን እና የመሳሰሉት ናቸው።
እነዚህም የተጠቀሱበት ምክንያት ከታች የምናያቸው ይሆናሉ፦
- ሲጋር ማጨስ በጊዜያዊነት የደም ግፊትን ከፍ ያደርገዋል።
- ካፌይን ያያዙ መጠጦች ለምሳሌ ቡና ፣ ሻይ ፣ ኮካ ኮላ እና የመሳሰሉትን መውሰድ የደም ግፊትን መጠን በእጅጉ ከፍ ሊያደርግ ይችላል ፤ በዋነኛነት ሁል ጊዜ ቡና የማይጠጡ ሰዎች ቡና ሲጠጡ ይህ የመጠን መጨመር ይታያል።
- የደም ግፊትን በቀዝቃዛ ክፍል (12ºC ወይም 54ºF) ውስጥ መውሰድ ወይም በሽተኛው እያወራ መለካት ልኬታውን ከ8 እስከ 15 mmHG ከፍ ያደርገዋል።
የደም ግፊት ምርመራ በምናደርግበት ጊዜ አቀማመጣችን ምን መምሰል አለበት?
- የደም ግፊታችንን በምንለካበት ወቅት በመቀመጫ ወንበር ወይንም ምርመራው በሚደረግልን አልጋ ላይ ጀርባችንን ተደግፈን እና እግሮቻችንን ሳናጣምር መቀመጥ አለብን። ጀርባችንን ሳንደገፍ መቀመጥ የዲያስቶሊክ (የታችኛው) ግፊትን በ 6 mmHG ከፍ ያደርግብናል። እንዲሁም እግራችንን አጣምረን መቀመጥ የሲስቶሊክ (የላይኛው) ግፊትን ከ 2 እስከ 8 mmHG ከፍ ሊያደርግብን ይችላል።
- የደም ግፊት ምርመራ ስናደርግ እጆቻችንን በልባችን ትይዩ ጠረጼዛ ላይ አስደግፈን ማስቀመጥ ተገቢ ነው።እጃችንን ሳናስደግፍ አንጠልጥለን ምርመራውን ማድረግ የደም ግፊት ልኬታችንን ከ10 እስከ 12 mmHG ከፍ ያደርግብናል። ይህም የሚሆንበት ምክንያት የመሬት ስበት ኃይል አማካኝነት የደም ግፊታችን ላይ ሃይድሮስታቲክ የሚባል ሌላ አይነት ግፊት ስለሚጨምር ነው።
- የደም ግፊታችንን ከመለካታችን በፊት ሌላኛው ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ቢያንስ ለአምስት ደቂቃዎች በፀጥታ መቀመጥ ነው። ምርመራ በምናደርግበት ወቅት ሽንታችንን ቋጥሮ መያዝ ፣ ማውራት እና የምንመረመርበት ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ጫጫታ ካለ የደም ግፊት ልኬታችን ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል።
ከላይ የጠቀስናችውን ነገሮች አድርገንም እንኳን አንዳንዴ ሐኪም ስናይ ልንፈራ እንቺላለን ይህም የደም ግፊት መጠናችንን ከሌላው ጊዜ በተለየ ከፍ ሊያደርግብን ይችላል። ከ20 እስከ 30 በመቶ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ይህ ነገር ያጋጥማል።እነዚህ ታካሚዎች ወይም ምርመራውን የሚያደርጉ ሰዎች በሕክምና ተቋም ላይ የደም ግፊት ምርመራ ሲያደርጉ ግፊታቸው ከፍ ቢልም ከሕክምና ተቋም ውጪ ምርመራው ሲደርግ ግን ኖርማል የሆን ልኬታ ይኖራቸዋል።
ከፍተኛ የደም ግፊት አለ የምንለው መቼ ነው?
ከፍተኛ የደም ግፊት መጠንን ከማየታችን በፊት ኖርማል የምንለው የደም ግፊት መጠን ስንት እንደሆን ማወቅ አለብን።
- ኖርማል የደም ግፊት መጠን የምንለው ሲስቶሊክ (የላይኛው) ግፊታችን ከ 90 እስከ 120 ሲሆን እና ዲያስቶሊክ (የታችኛው) ግፊታችን ከ 60 እስከ 80 ሲሆን ነው።
- ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን የምንለው ደግሞ ሲስቶሊክ (የላይኛው) ግፊታችን ከ 120 እስከ 129 ሲሆን እና ዲያስቶሊክ (የታችኛው) ግፊታችን ከ 80 በታች ሲሆን ነው።
ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን ያላቸው ሰዎች ለደም ግፊት በሽታ እና ለልብና የደም ሥር (cardiovascular) ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የደም ግፊት መድኃኒቶችን ቢወስዱም ምንም አይነት የጤና ጥቅም አያገኙም።
የደም ግፊት ሕመም
ሁለት አይነት የደም ግፊት ሕመም ደረጃዎች አሉ።
- ደረጃ 1 የደም ግፊት ሕመም የምንለው ሲስቶሊክ (የላይኛው) ግፊት ከ130 እስከ 139 ሲሆን እና ዲያስቶሊክ (የታችኛው) ግፊት ከ80 እስከ 89 ሲሆን ነው።
- ደረጃ 2 የደም ግፊት ሕመም የምንለው ደግማ ሲስቶሊክ (የላይኛው) ግፊት ቢያንስ 140 እና ከዚያ በላይ ሲሆን እና ዲያስቶሊክ (የታችኛው) ግፊት 90 እና ከዚያ በላይ ሲሆን ነው ።
አብዛኛዎቹ የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች የደም ግፊታቸው ፕራይመሪ የደም ግፊት (ቀደም ሲል ኢሴንሻል(essential) የደም ግፊት የሚባለው) ሲሆን ይህ ማለት የደም ግፊት ሕመማቸው መንስኤው አይታወቅም ማለት ነው። ጥቂት ሰዎች ደግሞ ሰከንዳሪ (Secondary ) የደም ግፊት ሕመም የሚባለው ያለባቸው ሲሆን ይህም የደም ግፊት ሕመሙ ሊስተካከል የሚችል መንስኤ አለው ማለት ነው። አብዛኛውን ጊዜ መንስኤዎቹ የኩላሊት ወይም የሆርሞን መዛባት ችግሮች ናቸው።


