የሰውነት ስብ (ኮሌስትሮል) መጠንን ለማሻሻል የሚረዱ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች

Al Amin Worku
Nov 18, 2025
undefined

የሰውነት ስብ (ኮሌስትሮል) መጠንን ለማሻሻል የሚረዱ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች

 

ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር መድኃኒት መውሰድ ብቻ በቂ ባለመሆኑ፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤዎችን መከተል ኮሌስትሮልን እና ከእርሱ ጋር የተያያዙ የልብና የደም ሥር በሽታዎችን ለማከም ዋናውና የማይተካው መንገድ ሲሆን፣ መልካም ዜናው ደግሞ አብዛኛዎቹ የሚመከሩት የአኗኗር ለውጥ መፍትሄዎች በቀላሉ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ መሆናቸው ነው።

የኮሌስትሮል መጠንን ለማሻሻል የሚረዱ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች በጣም ወሳኝ ናቸው። እነዚህ ለውጦች ጥሩውን ኮሌስትሮል (HDL) ከፍ ለማድረግ እና መጥፎውን ኮሌስትሮል (LDL) እንዲሁም አጠቃላይ ስብን (Triglycerides) ለመቀነስ ይረዳሉ።

ዋና ዋና የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች የሚከተሉት ናቸው

 

1.የአመጋገብ ለውጦች (Dietary Changes)

ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር አመጋገብ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር ከሚረዱን ወሳኝ የሕክምና አማራጮች ውስጥ አንዱ አመጋገብዎን ጤናማ ማድረግ ነው። አንዳንድ ምግቦች የኮሌስትሮል መጠንን ለመቀነስ ሲረዱ ሌሎች ደግሞ ከፍ ሊያደርጉ ይችላሉ። 

ኮሌስትሮልን ለማስተካከል የሚረዱ ምግቦች መካከል የሚከተሉት ይካተታሉ፡- 

1.አትክልትና ፍራፍሬ (በፋይበር፣ በቪታሚኖች እና በፀረ-ኦክሲዳንት የበለጸጉ በመሆናቸው መጥፎ ኮሌስትሮልን ለመቀነስ ይረዳሉ፤ ሁሌም ግማሹን የምግብ ሳህንዎን እንደ ኢትዮጵያ ባንዲራ በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ ቅጠላ ቅጠሎችና ፍራፍሬዎች ለመሙላት ይሞክሩና ሲመገቡም እነዚህን በመጀመሪያ መብላት ጥሩ ነው)፣ 

2.አሰርነት ያላቸው የእህል ዘሮች (አሰርነታቸው ያልጠፋ ያልተፈተጉ ጥራጥሬና እህል ምግቦች የተሻሉ ናቸው)፣ ጤናማ ቅባት ያላቸው የቅባት እህሎች (ለምሳሌ ለውዝ፣ አልሞንድ እና መሰል ዘሮች የጎጂ ኮሌስትሮልን መጠን ለማሻሻል ሊረዱ ይችላሉ፤ 

3.ከተጠባበሱ ማቆያ ስናክ ምግቦች ይልቅ አንድ እፍኝ ለውዝ መመገብ በኮሌስትሮል ጤና ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል)፣ አሳ (በጠቃሚ ኦሜጋ-3 የቅባት አይነቶች የበለጸጉ በመሆናቸው ኮሌስትሮልን ለመቀነስና የደም ሥር ሕመምን ተጋላጭነት ይቀንሳሉ) እንዲሁም ጤናማ የዘይት አይነቶችን መጠቀም (ቅቤን ወይም ማርጋሪን ከመጠቀም ይልቅ በወይራ ዘይት መተካት ጎጂ ኮሌስትሮልን በመቀነስ ጥሩ ኮሌስትሮልን ከፍ እንዲል ሊረዳ ይችላል)።

4.ጤናማ ያልሆኑ ቅባቶችን መቀነስ: በዋናነት ሳቹሬትድ (Saturated) እና ትራንስ (Trans) የሚባሉትን ቅባቶችን መቀነስ። እነዚህም በቀይ ሥጋ፣ ሙሉ ወተት ተዋጽኦዎች፣ በቅቤ እና በከፊል የጠነከሩ (partially hydrogenated) ዘይቶች ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህን መቀነስ መጥፎ ኮሌስትሮል (LDL) እንዲቀንስ ይረዳል።

5.ጤናማ ቅባቶችን መመገብ: እንደ አቮካዶ፣ ለውዝ (Nuts)፣ ወይራ ዘይት እና እንደ ሳልሞን ባሉ የሰቡ ዓሳዎች ውስጥ የሚገኙትን ጤናማ ቅባቶች (Monounsaturated and Polyunsaturated Fats) ይምረጡ።

6.የሚሟሟ ፋይበር ያብዙ (Soluble Fiber): ይህ ፋይበር ኮሌስትሮልን ከአንጀት በመምጠጥ ከሰውነት ውስጥ ለማስወጣት ይረዳል። በአጃ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ምስር፣ ፖም እና ሲትረስ ፍራፍሬዎች ውስጥ በብዛት ይገኛል።  

7.ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ ይውሰዱ: ይህ ቅባት መጥፎ ኮሌስትሮልን (LDL) በቀጥታ ባይቀንስም፣ የልብ ጤናን ያሻሽላል እና በደም ውስጥ ያለውን ስብ (Triglycerides) በእጅጉ ይቀንሳል። ተልባ እና መሰል ጥራጥሬ (flaxseed) ውስጥ የሚገኘው ኦሜጋ-3 በደም ውስጥ ያለውን ስብ (Triglycerides) በእጅጉ ለመቀነስ እና የልብ ጤናን ለማሻሻል ይረዳል።

8.ስኳር የበዛባቸው ምግቦች እና መጠጦች፡- ከፍተኛ የስኳር መጠን የበዛባቸው ምግቦች የደም ቅባት መጠን ከፍ እንዲል ከማድረግ በተጨማሪ ለውፍረትና ቦርጭ መጨመር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

 

በርካታ የስነ ምግብ ባለሙያዎች የተለያዩና አንዳዴም እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ የአመጋገብ አይነቶችን ሲመክሩ እንሰማለን። ለመሆኑ የትኞቹ ናቸው የሚሰሩት እና በሳይንስ የተደገፉት?

 

  • የሜዲትራኒያን አመጋገብ (Mediterranean Diet)፡ ይህ የአመጋገብ ስርአት ስላለው የጤና ጥቅሞች ከሌሎች የአመጋገብ አይነቶች ሻል ያለ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች አሉት። ለአጠቃላይ ጤና በሚሰጠው ላቅ ጥቅም በሰፊው ይወደሳል። ይህ የአመጋገብ አይነት አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣ አሰርነት ያላቸው እህል ምግቦች፣ አሳ እና የወይራ ዘይትን መጠቀም ይመክራል። በአንጻሩ  በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችና ስጋን መገደብ ያዝዛል። በርካታ ጥናቶች ከሌሎችን የአመጋገብ አይነቶች የተሻለ ኮሌስትሮልን ለማስተካከል፣ የደም ግፊትን ለማስተካከልና የልብ ህመም ተጋላጭነትን ይቀንሳል ሲሉ ያስረዳሉ።
  • የደም ግፊት ለመቀነ የሚረዱ የአመጋገብ ዘዴዎች ( Dietary Approaches to Stop Hypertension, DASH Diet): በመጀመሪያ የደም ግፊትን ለመቀነስ የተነደፈ የአመጋገብ ስልት ቢሆንም ኮሌስትሮልንም ለመቀነስ ውጤታማ ነው። ይህ የአመጋገብ ስልት አትክልቶችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ ያልተፈተጉ ሙሉ እህሎችን፣ አሳ እና ዶሮ ምግብን ማዘውተር የሚመክር ሲሆን ጨው፣ ቀይ ሥጋ እና ጣፋጮች መገደብ ይደግፋል። ይህ አመጋገብ የኮሌስትሮል መጠን እና አጠቃላይ የልብ ጤናን እንደሚያሻሽል በበርካታ ጥናቶች ተረጋግጧል።
  • ቬጂቴሪያን አመጋገብ (vegetarian diet): ይህ አመጋገብ የእጽዋት ተዋጽኦ ምግቦችን ብቻ መመገብ የሚመክር ሲሆን ምንም አይነት ስጋ እና የባህር ምግቦችን የማያካትት ነው። አንዳንድ ለዘብተኛ የቬጀቴሪያን አመጋገብን የሚከተሉ ሰዎች እንቁላል እና የወተት ምግቦችን ሊበሉ ይችላሉ። ከእንሣት ተዋጽኦ ብቻ የሚገኘውን የሳቹሬትድ ቅባት መጠን በእጅጉ ይቀንሳል። ስለሆነም የኮሌስትሮል መጠን ለማስተካከል ይረዳል።
  • ከፍተኛ ቅባት ያላቸውን የስጋ ምግቦች መገደብ ተገቢ ነው። በተለይም በሃይል የሰባ ስጋ እና ጉበት ይገድቡ። በተጨማሪም የተጠበሱ ስጋ ምግቦች ያስወግዱ። ስጋን ጠብሶ ከመመገብ ይልቅ ስጋን ቀቅለው መብላት የተሻለ ነው። ከአንሣት ስጋ ይልቅ የዶሮ ስጋ የተሻለ ነው – ዶሮን ሲያዘጋጁ የሚታዬውን ስጋ መልቀምና ቆዳውን ማውጣት ይመከራል።
  • በፋብሪካ የተቀነባበሩና ያለቀላቸው ምግቦችን ይገድቡ። እንደ ቺፕስ፣ ኩኪስ፣ የታሸጉ ጣፋጭ ለስላሳ መጠጦችና ጁሶች፣ ለረጅም ሰአት ፍሪጅ የቀዘቀዙ ተጠባሽ ምግቦች መመገብ ይገድቡ። በሳቹሬትድ ፋት እና ትራንስ ፋት የበለፀጉ ከመደብር የሚገዙ ያለቀላቸው ምርቶችን ይገድቡ።

    እነዚህና ሌሎችም የመጋገብ ስልቶች በስፋት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሲሟገቱ ይሰማሉ። እውነታው ግን አንዱ ከሌላው ይበልጣል የሚል ጥርት ያለ ሳይንሳዊ ጥናት የለም። ለሁሉም ሰው የሚሰራ የአመጋገብ ቀመር ማስቀመጥ ያስቸግራል። ዋናው በዘላቂነት መተግበር የሚችል ስልት መንደፍና በየጊዜው እያሻሻሉ መሄድ መልካም እንደሆነ አብዛኛውን የስነ ምግብ ባለሙያዎች የሚያስማማ ጉዳይ ነው።

 

2. የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (Physical Activity)

መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ኮሌስትሮልን ለማሻሻል በጣም ውጤታማ ነው።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚጠቅመው ሸንቀጥ ለማለት ብቻ አይደለም። ይልቁንም የኮሌስትሮል መጠንን ለማሻሻል እና የልብ ጤናን ለመጠበቅ ከሚረዱት ምርጥ መንገዶች አንዱ ነው። መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጥሩ ኮሌስትሮልን ይጨምራል፣ ጎጂ ኮሌስትሮልን ይቀንሳል፣ ትራይግሊሰርይድን ይቀንሳል። በተለይም ከጤናማ አመጋገብ ጋር ሲጣመር እጅግ ከፍተኛ የጤና ጥቅሞች አሉት።

ምን ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ያስፈልጋል?

የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የጤና ጥቅሞች ለማጣጣም የግድ ማራቶን ሯጭ መሆን አያስፈልግዎትም። ማንኛውም አይነትና መጠን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጠቃሚ ነው። የቻሉትና ያክል መንቀሳቀስ እና አብዝቶ መቀመጥን መቀነስ ነው። በተለይም በሳምንት ቢያንስ ከ150 ደቂቃ ያላነሰ ኤሮቢክ እንቅስቃሴዎችን አዘውትሮ መስራት መልካም ነው። በሳምንት ሁለት ወይም ሶስቴ የጥንካሬ ስፖርቶች መስራት ተጨማሪ የጤና ቱሩፋቶች ያጎናጽፋል።

ባጭሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ 

  • ጥሩውን ኮሌስትሮል ይጨምራል (HDL): የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የሰውነትዎ ጥሩ ኮሌስትሮል (HDL) መጠን እንዲጨምር ይረዳል።
  • የእንቅስቃሴ ዓይነት: በቀን ቢያንስ 30 ደቂቃ፣ በሳምንት አምስት ቀን መጠነኛ እንቅስቃሴዎችን (እንደ ፈጣን የእግር ጉዞ) ለማድረግ ይሞክሩ።
  • ክብደት ማንሳት: ክብደት ማንሳት የሰውነት ስብን በማቅለጥ ጡንቻ እንዲጎለብት በማድረግ አጠቃላይ ጤናን ያሻሽላል።

    የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን መጨመር

  • በምሳ ሰዓትዎ ፈጣን የእግር ጉዞ ማድረግ።
  • ወደ ሥራ ቦታዎ በብስክሌት መሄድ።
  • የሚወዱትን የስፖርት አይነት መጫወት።

3.ሌሎች የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች

 

  • ማጨስን ያቁሙ (Quit Smoking): ማጨስ ጥሩውን ኮሌስትሮል (HDL) ዝቅ ያደርጋል እና የልብ በሽታ ተጋላጭነትን በእጅጉ ይጨምራል። ማጨስን ማቆም የ HDL ደረጃን በፍጥነት ያሻሽላል።  
  • ማጨስ ካቆሙ ከ 20 ደቂቃዎች በኋላ: የደም ግፊትዎ እና የልብ ምትዎ በሲጋራ ምክንያት ከጨመረበት መጠን ይመለሳሉ።
  • ማጨስ ካቆሙ ከ 3 ወራት በኋላ: የደም ዝውውርዎ እና የሳንባዎ ተግባር መሻሻል ይጀምራሉ።
  • ማጨስ ካቆሙ ከአንድ ዓመት በኋላ: ለልብ በሽታ የመጋለጥ እድልዎ አጫሽ ከሆነ ሰው ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ይቀንሳል።
  • ክብደትን ይቆጣጠሩ: በተለይም በሆድ አካባቢ ያለው ስብ መጥፎ ኮሌስትሮልን ይጨምራል እና ጥሩ ኮሌስትሮልን ይቀንሳል። ትንሽ ክብደት መቀነስ እንኳን የኮሌስትሮል መጠንን በእጅጉ ያሻሽላል።
  • ጭንቀትን ይቀንሱ (Manage Stress): ሥር የሰደደ ጭንቀት ኮሌስትሮልን እና የደም ግፊትን ጨምሮ ሌሎች የአደጋ መንስኤዎችን ሊያባብስ ይችላል። ለማረጋጋት እንደ ዮጋ፣ ሜዲቴሽን ወይም ጥልቅ ትንፋሽ መውሰድ ያሉ ዘዴዎችን ይሞክሩ።
  • በቂ እንቅልፍ ማግኘት: ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ በቂና የሚያረካ እንቅልፍ መተኛት ለጤና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። የእንቅልፍ ችግር ከከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን፣ የደም ግፊት መብዛትና ስኳር ህመም ጋር የተያያዘ ነው። ስለሆነም የኮሌስትሮል መጠን ለመቆጣጠር እና አጠቃላይ ጤንነትና ለማበልጸግ በእየለቱ ከ6-8 ሰአታት ጥራት ያለው እንቅልፍ ይኑርዎት።
  • አልኮልን ይገድቡ: ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት የደም ስብን (Triglycerides) ከፍ ሊያደርግ እና ለደም ግፊት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። መጠኑን ይቀንሱ ወይም ሙሉ ለሙሉ ያቁሙ።

     

    ከላይ እንደዘረዘርነው ሁሉን አቀፍ የአኗኗር ለውጥ ማድረግ ከፍ ያለ ትርፍ እንደሚያስገኝ አውርተናል። ለሁሉም ሰው የሚሆን አንድ የአኗኗር ዘይቤ መቀመር ባይቻልም ዋናው ነጥብ ትንንሽ ለውጦች ትላልቅ ውጤቶችን እንደሚያመጡ እሙን ነው። በተጨማሪም የኮሌስትሮል መጠንን መቆጣጠር በአንድ ጀምበር ከባድ ለውጦችን በማድረግም አይደለም። ይልቁንም በጊዜ ሂደት ሊወጥሏቸው የሚችሏቸው ጤናማ ልማዶችን ስለመጀመርና በጽናት ስለመቀጠል ነው። ወደ ትክክለኛው የጤና መንገድና አስተሳሰብ ይመለሱ። የትኞቹን ለውጦች ማድረግ እንዳለቦት፣ እንዴት እንደሚቀጥል እና አንደሚያጸኑት ያቅዱ፣ ይወስኑ፣ እርምጃ ይጀምሩ። በእራስዎ ፍጥነት ይሂዱ፤  ቀስ በቀስ ተጨማሪ ለውጦችን ያካትቱ። ጤናማ የአኗኗር ለውጥ ለማድረግ መቼም አይረፍድም። ትንሽ ለውጦች ዛሬ በመጀም በረጅም ጊዜ ጤናዎ ላይ ከፍተኛ መሻሻሎችን ሊያመጡ ይችላሉ።

Comments (0)