ፀጉርዎ ጠንካራ ቢሆንም፣ ከዕለት ተዕለት አጠቃቀምና እንክብካቤ ጉድለት ሊጎዳ ይችላል። የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅ የተጎዳ ፀጉር አንዱ ምልክት ነው። የሚከሰተው የፀጉር ውጫዊ መከላከያ ሽፋን (cuticle) በመሳሳቱ ሲሆን፣ ይህም የፀጉሩን ውስጠኛ ክፍል ለጉዳት በማጋለጥ ፀጉራችን ደካማ እና ደረቅ ያደርገዋል። የፀጉር ዘርፎችም በቀላሉ እንዲሰባበሩ ያደርጋል።
ለረጅም ጊዜ ፀጉርዎትን ካልተቆረጡ ጥቂት መሰንጠቆች መኖር የተለመደ ነው። ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል በአንድ ወቅት የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅ ያጋጥመዋል። ነገር ግን ከመጠን በላይ ከሆኑ እና ከቆረጡ በኋላም በፍጥነት ከተመለሱ፣ ተጨማሪ እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው እንደደረሰ ያመለክታል።
የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅ ብዙ አይነት ቅርጾች ያሉት ሲሆን ብዙውን ጊዜ ግን "V" ወይም "Y" ቅርጽ ይይዛሉ።
የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅ መንስኤዎች
የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅ የሚከሰተው የፀጉር ውጫዊ መከላከያ ሽፋን ሲጎዳ ወይም ሲሰበር ነው። የተለመዱ መንስኤዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- ከመጠን በላይ ጥብቅ የፀጉር አሠራሮች፦ ፀጉርን በመለጠጥ እና ከመጠን በላይ አጥብቆ ማሰር ፀጉር በመሃል እንዲሰነጠቅ ያደርጋል።
- የተሳሳተ ፀጉር አቦራረሽ መንገድ፦ ከመጠን በላይ መቦረሽ ወይም ትክክለኛ ያልሆነ የፀጉር ብሩሽ መጠቀም ፀጉር እንዲሰነጠቅ ሊያረግ ይችላል። በተጨማሪም ፀጉርን በፎጣ በኃይል ማድረቅ የውጭውን ሽፋን ስለሚያዳክመው ለመሰነጣጠቅ ይዳርጋል።
- የአየር ሁኔታ መፈራረቅ፦ ለፀሐይ፣ ለንፋስ እና ለአየር ብክለት መጋለጥ የፀጉርን መከላከያ ሽፋን በማበላሸት ጫፎቹ እንዲሰነጠቁ ያደርጋል።
- የሙቀት ጉዳት (Heat Damage)፦ የሙቀት መከላከያ ሳይጠቀሙ እንደ ፀጉር ማድረቂያ እና መተኮሻ የመሳሰሉ በሙቀት የሚሰሩ የፀጉር ማስተካከያዎችን መጠቀም የፀጉር ድርቀትንና መሰባበርን ያስከትላል።
- ደረቅ ፀጉር መኖር፦ በቂ እርጥበት አለማግኘት የፀጉር ዘለላዎች ለስላሳ ሳይሆኑ እንዳይቆዩ ያደርጋል። ይህም ፀጉር እንዲደርቅ እና ለመሰንጠቅ እንዲጋለጥ ያደርጋል።
- ኬሚካል ያላቸው የፀጉር ምርቶች መጠቀም፦ እንደ ፐርም (perms)፣ የፀጉር ቀለም እና ፀጉርን የሚያለሰልሱ ኬሚካሎች (relaxers) ያሉ የኬሚካል ምርቶች የፀጉርን አወቃቀር ስለሚቀይሩ ለመሰንጠቅ የበለጠ ተጋላጭ ያደርጉታል።
- ማእድን የበዛበት ውሃ (Hard water)፡ ማእድን የበዛበት ውሃ (ጠንካራ ውሃ) በፀጉር ላይ ጎጂ ማዕድናትን በማስቀመጥ፣ ተፈጥሯዊ ዘይቶችን በማስወገድ እና ፀጉርን ከጊዜ በኋላ ደረቅና በቀላሉ የሚሰባበር በማድረግ የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅን ያስከትላል።
- ትክክለኛ ያልሆነ የፀጉር ምርት መጠቀም ፦ ጠንካራ ኬሚካሎችን የያዙ ሻምፖዎችን እና ኮንዲሽነሮችን ወይም ለፀጉርዎ አይነት የማይስማሙ ምርቶችን መጠቀም እርጥበትን በማስወገድ እና ፀጉርን በማዳከም ለፀጉር ጫፍ መሰንጠቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
- ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፦ በአመጋገብ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ማጣት ፀጉርን ከውስጥ በማዳከም ለጉዳትና ለመሰንጠቅ የበለጠ ተጋላጭ ያደርገዋል።
የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅን ለመከላከል የሚረዱ ምክሮች
የተሰነጠቀ ፀጉርን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ብቸኛው መንገድ በመደበኛነት መቆረጥ (regular trims) ነው። ሆኖም፣ አዲስ መሰንጠቅ እንዳይፈጠር ለመከላከል፣ በቀላሉ የሚጎዱ የፀጉር ጫፎችን ለመጠበቅ እና እንዲሁም እንዳይታዩ ለመደበቅ የሚረዱ መንገዶች አሉ።
1. የፀጉር እንክብካቤ ዘዴዎች
የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅን ለማስወገድ ፀጉርዎን በትጋት መንከባከብ ያስፈልጋል። ሰፋፊ ጥርስ ያለው ማበጠሪያ በመጠቀም፣ ፀጉርን በቀስታ ማፍታታት፣ ጤናማ ምርቶችን ወደ ጭንቅላት ቆዳ በማሸት ማስገባት፣ እና በተጨማሪም ለፀጉርዎ አይነት የሚሆን የእንክብካቤ መርሃ ግብር በመምረጥ ይጠቀሙ።
- ደረቅ ፀጉር ከሆነ: እርጥበት የሚሰጥ (moisturizing) ሻምፑ እና ኮንዲሽነር ይጠቀሙ።
- ቀጭን እና ለስላሳ ፀጉር ከሆነ: ብዛት የሚሰጥ (volumizing) ሻምፑ እና ኮንዲሽነር ይጠቀሙ።
- የተጎዳ ፀጉር ከሆነ: የመጠገን ባህሪ ያለው (repairing) ሻምፑ እና ኮንዲሽነር ይሞክሩ።
2. ፀጉርዎን ከታጠቡ በኋላ ጥንቃቄ ያድርጉ
እርጥብ ፀጉር ለጉዳት የተጋለጠ ነው፣ ስለዚህ ሻምፑ እና ኮንዲሽነር ከተጠቀሙ በኋላ ፀጉርዎን በጥንቃቄ መንከባከብ አስፈላጊ ነው።
አንዳንድ ሰዎች ፀጉራቸውን በፎጣ አሽተው የማድረቅ ልማድ አላቸው፣ ነገር ግን ይህ ፀጉርን ሊጎዳ ይችላል። ተደጋጋሚ ማሸት የፀጉር መሰባበርን ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም የፀጉርን ውጫዊ ሽፋን በመጉዳት የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅን ወይም መጎሳቆልን ያመጣል።
በምትኩ፣ መሰባበርንና ጉዳትን ለማስወገድ ፀጉርዎን በማይክሮፋይበር ፎጣ በመዳሰስ ወይም በመጠፍጠፍ ማድረቅ ይመከራል። ማይክሮፋይበር ፎጣ ከሌለዎት፣ እርጥበትን የሚመጥ ሆኖ ለስላሳ የሆነ የጥጥ ቲሸርት ይጠቀሙ።
3 . የፀጉር አሠራር መቀየር
ፀጉርዎን የማይጎትቱ እና በቀላሉ የማይተሳሰሩ ፀጉር ማሲያዛዎችን ይጠቀሙ። ላላ ያሉ የፀጉር አሠራሮች ፀጉርዎ ጠንካራና ጤናማ እንዲሆን ይረዳሉ።
- በክረምት ወቅት፦ ላላ ተደርጎ የሚሰራ አሰራር የፀጉርዎን ጫፎች ከቀዝቃዛ አየር መድረቅ ለመጠበቅ ይረዳል።
- በበጋ ወቅት፦ የፀሐይ ጨረሮችን በሚቀበሉበት ጊዜ ፀጉርዎን ከመጠን በላይ ሙቀት እንዳይጎዳ ለመከላከል ኮፍያ ወይም ራስ መሸፈኛ ይጠቀሙ።
4. ደረቅ ፀጉርን ይከላከሉ
ፀጉርዎ እርጥበት ሲያገኝ ይጠነክራል እና ለጉዳት የመቋቋም አቅሙ ይጨምራል። ይህ ደግሞ የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅን ይከላከላል። ደረቅ ፀጉርን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ማወቅ መሰንጠቅን ለማስወገድ እና ፀጉርዎን ለስላሳ ለማድረግ ይረዳል። ፀጉርዎን በሚታጠቡበት ጊዜ እርጥበት የሚሰጥ ኮንዲሽነር ይጠቀሙ፤ እንዲሁም በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ የፀጉር ማስኮችን (hair mask) ይጠቀሙ። የፀጉር ማስክ ፀጉርዎን በእርጥበት እና በንጥረ ነገሮች የሚመግብ እና መጎሳቆልንና መድረቅን የሚቀንስ የመንከባከቢያ ዘዴ ነው። በተጨማሪም የፀጉር ጉዳት የመከሰት ስጋትን በመቀነስ ለስላሳና አንፀባራቂ ፀጉር እንዲኖር ያደርጋል። በፀጉር ማስክ ውስጥ ያሉት ምርቶች በመደበኛው ኮንዲሽነር ውስጥ ከሚገኙት የበለጠ የጠነከሩ ናቸው። ማስኩ በፀጉርዎ ላይ ከ20 ደቂቃ እስከ በርካታ ሰዓታት ወይም አንድ ሌሊት ሙሉ ድረስ ማቆየት ይችላሉ።
ዝግጁ የሆነ የፀጉር ማስክ መግዛት ወይም የራስዎን የሚከተሉትን ንጥረ ነገሮች በመጠቀም ማዘጋጀት ይችላሉ፦
- የኮኮናት ዘይት
- ሬት
- ማር
- የወይራ ዘይት
- ሙዝ
በተጨማሪም በሳምንት አንድ ጊዜ የፀጉር ሕክምና ያድርጉ። የፀጉር ሕክምና (Hair treatment) ለፀጉርዎ ተጨማሪ እርጥበት ይጨምራል። የፀጉር ሴረም (Hair serums) እና የፀጉር ቅባቶች (hair oils) አዘውትሮ መጠቀም ለደረቀ ፀጉር እርጥበትን ለመመለስ ይረዳሉ።
5. የሙቀት መጠኑን ይቀንሱ
ከተቻለ ፀጉርዎን ከታጠቡ በኋላ በአየር እንዲደርቅ ይፍቀዱለት፣ ከዚያም ሙቀት ያላቸውን መሳሪያዎች ሳይጠቀሙ ያስተካክሉት።
ፀጉርዎ በአየር እንዲደርቅ ጊዜ ከሌለዎት፣ የፀጉር ማድረቂያዎን በዝቅተኛ የሙቀት መጠን ለመጠቀም ይሞክሩ። ሙቀት ያላቸው የፀጉር መስሪያ መሳሪያዎች ላይ ያለውን የሙቀት መጠን ይቀንሱ። በተጨማሪም እነዚህን መሳሪያዎች መጠቀም ከመጀመርዎ በፊት ሙቀት መከላከያ ስፕሬይ (Heat Protection Spray) ይጠቀሙ። ይህ በፀጉርዎ እና በሙቀቱ መካከል ተጨማሪ የመከላከያ ሽፋን ይፈጥራል።
6. ከሚካል ያላቸውን ምርቶች ሲጠቀሙ በመካከል ያለውን ጊዜ ያራዝሙ
እንደ ፀጉር ቀለም መቀባት፣ ፐርም (perm) ወይም ፀጉር ማለስለሻ (relaxing) ያሉ የኬሚካል ምርቶችን፤ በተለይም በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ምርቶችን ከተጠቀሙ፣ በፀጉርዎ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።
የፀጉር ጉዳት፣ መሰባበር እና የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅ የመከሰት እድልን ለመቀነስ የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ይችላሉ፦
- ከሚካል ያላቸውን ምርቶች ሲጠቀሙ በመካከል ያለውን ጊዜ ያራዝሙ፦ ከተቻለ በመካከል ከ8 እስከ 10 ሳምንታት ፀጉሮትን ለማሳረፍ ይሞክሩ።
- አንድ አይነት ኬሚካል ምርት ብቻ ይጠቀሙ: በአንድ ጊዜ አንድ አይነት ኬሚካል ምርት ብቻ ይጠቀሙ።
- የፀጉር ማስክ ይጠቀሙ፦ በሳምንት አንድ ጊዜ የፀጉር ማስክ ይጠቀሙ
7. በሐር የተሰራ የትራስ ጨርቅ ላይ ይተኙ
በሌሊት ፀጉርዎን መጠበቅ የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅን ለመከላከል ይረዳል። ከጥጥ ትራስ ልብስ ይልቅ፣ በሐር (silk) ወይም በሳቲን (satin) ትራስ ልብስ ላይ ይተኙ።
በሐር ወይም በሳቲን ትራስ ልብስ ላይ መተኛት ፀጉርዎ በትራሱ ላይ በቀላሉ እንዲንሸራተት ያስችላል። በፀጉር እና በትራስ ልብስ መካከል አነስተኛ ሰበቃ መኖሩ የፀጉር ጉዳት እና መሰባበርን ለመከላከል ይረዳል።
ሌላው አማራጭ ፀጉርዎን ለመጠበቅ በሌሊት የሐር ሻሽ ማድረግ ነው።
8. መሰንጠቅን የሚከላከሉ ምርቶች ይጠቀሙ
የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅን ለመከላከል የሚያግዙ የፀጉር ምርቶችን መጠቀም ይጀምሩ። ጤናማ ፀጉር የሚጀምረው በሚመርጡት ሻምፑ ነው። የፀጉርን ተፈጥሯዊ መከላከያ ዘይት ሳያስወግድ፣ የራስ ቆዳን፣ ፀጉሩን ሙሉ እና ጫፎቹን ማጽዳት አለበት።
9. ፀጉርዎን ከጫፍ እስከ ሥር በቀስታ ይቦርሹ
ፀጉርን በትክክል ለመቦረሽ፣ ከጫፎቹ መጀመር እና የተቋጠሩ ፀጉሮችን በቀስታ መፍታት ያስፈልጋል። ቀስ በቀስ፣ እያንዳንዱን የፀጉር ዘርፍ እስከ ሥሩ ድረስ መፍታት እስኪችሉ ድረስ ብሩሹን ከፍ እያደረጉ መቦረሽ ይችላሉ።
ፀጉርዎ እርጥብ በሚሆንበት ጊዜ ከመቦረሽ ይልቅ፣ ከመታጠብዎ በፊት በቀስታ ለመቦረሽ ይሞክሩ። ኮንዲሽነር ሲጠቀሙ ደግሞ ፀጉርዎን ለመፍታት ጣቶችዎን ይጠቀሙ። ፀጉርዎ እርጥብ በሚሆንበት ጊዜ ይበልጥ ተሰባሪ ይሆናል። እርጥብ ሆኖ መቦረሽዎ በፀጉርዎ ላይ ጉዳት በማድረስ የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅን ያፋጥነዋል።
10. የፀጉር ጫፍ መሰንጠቅን ለመከላከል በመደበኛነት ይቁረጡ
በመደበኛነት ወደ ፀጉር ቤት በመሄድ ፀጉርዎን ጤናማ ያደርገዋል የፀጉሮትን ጫፍ ይቆረጡ ። ፀጉርዎ ለረጅም ጊዜ ጤናማ እና ጠንካራ ያደርገዋል።በአማካይ በየ 6-8 ሳምንቱ ይቆረጡ።
11. በተደጋጋሚ ፀጉርዎን ከመታጠብ ይቆጠቡ
በየቀኑ ፀጉርዎን ላለመታጠብ ይሞክሩ። ፀጉርን ብዙ ጊዜ መታጠብ የፀጉርን ተፈጥሯዊ ዘይት በማስወገድ ፀጉር እንዲደርቅ እና መሰንጠቅ እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል። በሳምንት 1-2 ቀን ብቻ ለመታጠብ ይሞክሩ።
12. በሚዋኙበት ጊዜ ፀጉርዎን ይጠብቁ
በመዋኛ ገንዳ ውስጥ ያለው ክሎሪን እና በባህር ውሃ ውስጥ ያለው ጨው ለፀጉርዎ ጎጂ ናቸው። እጅግ በጣም ጠንካራ እና አድራቂዎች ስለሆኑ፣ ከዕረፍት ሲመለሱ ፀጉርዎ ደረቅ እና በቀላሉ የሚሰባበር ቢመስል አያስደንቅም። መፍትሄው ከመዋኘትዎ በፊት ፀጉርዎን በንጹህ ውሃ ማጠብ/መንከር ነው። ምክንያቱም ፀጉር ልክ እንደ ስፖንጅ የመምጠጥ አቅሙ እስከሚሟላ ድረስ ብቻ ነው እርጥበት መያዝ የሚችለው። በንጹህ ውሃ ሲያጠጡት፣ ክሎሪን እና ጨው ወደ ውስጥ እንዳይገቡ የሚከላከል የማይታይ መከላከያ ይፈጥራሉ።
የተሰነጠቀ ፀጉርን መደበቅ ይቻላል?
የተሰነጠቀ ፀጉርን መጠገን ካልተቻለ፣ ጉዳቱ ብዙም እንዳይታይ ማድረግ ይችላሉ። ከነዚህም መንገዶች መካከል
1. ቅባት እና እርጥበት መጠቀም
እንደ የኮኮናት ዘይት፣ የአልሞንድ ዘይት ወይም ሌላ ዓይነት ለፀጉር ወዝ የሚሰጡ ምርቶችን በፀጉርዎ ጫፍ ላይ ይቀቡ። እነዚህ ምርቶች ፀጉርን አንፀባራቂ ከማድረግ ባሻገር ፀጉርዎን በማለስለስ የተሰነጠቀውን ፀጉር ለመደበቅ ይረዳሉ።
2. የፀጉር አሠራር ማስትካከል
ሌላው አማራጭ የፀጉርዎን ጫፎች የሚደብቁ የፀጉር አሠራሮችን መምረጥ ነው።
- ፀጉርዎን ጠምጥመው ወይም ቋጥረው ማስያዝ
- የፀጉር ቅጥያ መጠቀም መሞከር ይችላሉ።
3. በየጊዜው መቆረጥ
የተሰነጠቀው ፀጉር ወደ ላይ እየጨመረ በመሄድ የፀጉር ገመዱን ሊሰነጥቅ እንደሚችል ያስታውሱ። ስለዚህ፣ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል የተጎዳውን ፀጉር መቁረጥ ያስፈልግዎታል።
4. የፀጉር ማስኮችን መጠቀም
የፀጉር ማስኮች ፀጉርን በጥልቀት እርጥበት የሚሰጡ እና የፀጉር ገመዶችን የሚያጠናክሩ ሕክምናዎች ናቸው። የተሰነጠቀ ፀጉርን ለመደበቅ እና የፀጉርዎን አጠቃላይ ገጽታ ለማሻሻል በጣም ጠቃሚ ናቸው።


