የደም ግፊት በሽታ በጥቁር ሰዎች ላይ ለምን ይበዛል?

Eyasu Yebeltal
Nov 26, 2025
undefined

                   የደም ግፊት በሽታ በጥቁር ሰዎች ላይ ለምን ይበዛል?

የደም ግፊት በሽታ ሰዎችን በአለም አቀፍ ደረጃ የሚያጠቃ ህመም ነው። ነገር ግን ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ይህ ህመም ጥቁር የቆዳ ቀላም ባላቸው ማህበረሰቦች መካከል ከሌሎች በተለየ በብዛት የሚከሰት፣ ቀደም ባለ እድሜ የሚመጣ እና የከፋ ጉዳት ያለው ሊሆን ይችላል። ይህ ልዩነት ለምን እንደሚፈጠር መረዳት ለመከላከል፣ ቅድመ ህክምና እና ጤናማ ህይወት በጣም ጠቃሚ ነው። በዚህ ጽሁፍ ምክንያቶቹን እና ግለሰቦች ጤናቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ ያብራራል።

የዘር ግንድ ሚና

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የአፍሪካውያን የዘር ግንድ ያላቸው ሰዎች፡-

  • ከሌሎች በበለጠ በሰውነታቸው ውስጥ ጨውን ይዘው መቆየት ይችላሉ
  • የደም ግፊትን ለሚጨምሩ አንዳንድ ሆርሞኖች ከፍተኛ ምላሽ ይኖራቸዋል

በዚህም ምክንያት በምግብ ውስጥ አነስተኛ መጠን ያለው ጨው እንኳን ሲመገቡ የደም ግፊታቸው ከሌሎች የበለጠ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ይሁን እንጂ የዘር ግንድ ብቻውን ሙሉውን ተጽእኖ መፍጠር ስለማይችል ለደም ግፊት ሌሎች በርካታ ምክንያቶች አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

ጭንቀት እና ማህበራዊ ጫና

ሥር የሰደደ ጭንቀት በሰውነታችን ውስጥ የጭንቀት ሆርሞኖችን የሚጨምር ሲሆን እነዚህ ሆርሞኖች የደም ስሮች እንዲጠቡ እና ልብ ጠንክሮ እንዲሰራ በማድረግ የደም ግፊትን በጊዜ ሂደት ይጨምራሉ። ከጭንቀት ጋር የተያያዙ የተለመዱ አስተዋጽዖ አበርካቾች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-

  • የኢኮኖሚ ጫና
  • የጤና እንክብካቤ አገልግሎት እጦት
  • ምቹ ባልሆነ አካባቢ መኖር ወይም መሥራት

የረዥም ጊዜ ጭንቀት ለደም ግፊት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው።

የአኗኗር ዘይቤ 

የደም ግፊት መጨመር በዕለት ተዕለት ልማዶች እና በአኗኗር ሁኔታዎች ሊባባስ ይችላል። እነዚህ ምክንያቶች ሁሉንም የሰው ዘር ሊጎዱ የሚችሉ ቢሆንም በቂ ሀብት በሌላቸው ማህበረሰቦች ውስጥ ተጽኗቸው የበለጠ ነው።

የጤና እንክብካቤ ተደራሽነት እንቅፋቶች

በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ ሁኔታ ጥቁር ቆዳ ያላቸው ማህበረሰቦች ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ያሉ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። አስተዋጽዖ አበርካቾች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡- 

  • መደበኛ የጤና ክትትል አለመኖር
  • በቂ የጤና ተቋማት በአካባቢያቸው አለመኖር
  • ለምርመራ ወይም ለመድኃኒት የሚሆን የገንዘብ ችግር
  • ዘግይቶ መመርመር እና ዘግይቶ ሕክምና ማድረግ

የደም ግፊት በብዛት ምንም ምልክት ስለሌለው መደበኛ ምርመራን አለማድረግ ሳይታወቅ ለረጅም ጊዜ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የደም ግፊትን ያስከትላል።

በዘር ምክንያት ብቻ ሳይሆን የምክንያቶች ጥምረት እንደሆነ መረዳት

በጥቁር ሰዎች ላይ ያለው የደም ግፊት መጨመር የሚመጣው ከዘረመል፣ ከአካባቢ፣ ከጭንቀት፣ ከማህበራዊ ተግዳሮቶች እና ከጤና አጠባበቅ ተደራሽነት ጥምረት ሲሆን እነዚህን ምክንያቶች መረዳት ግለሰቦች ጤንነታቸውን እንዲቆጣጠሩ ይረዳቸዋል። 

እንዴት አደጋን መቀነስ ይቻላል

ብዙ የአደጋ መንስኤዎች ቢኖሩም የደም ግፊትን መከላከል እና መቆጣጠር ይቻላል። 

  • የሚመገቡትን የጨው መጠን ይቀንሱ። በተጨማሪም የታሸጉ እና የተጠበሱ ምግቦችን ይገድቡ።
  • ብዙ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ይመገቡ። እንደ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ አቮካዶ፣ አረንጓዴ ቅጠላቅጠሎችን እና ሌሎች በፖታስየም የበለጸጉ ምግቦችን ያግኙ።
  • በአካል ንቁ ይሁኑ። ቢያንስ የ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ወይም ቀላል የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በሳምንት ለተወሰኑ ቀናት ያድርጉ።
  • ጤናማ ክብደትን ይጠብቁ። ትንሽ ክብደት መቀነስ እንኳን የደም ግፊትን ለመቀነስ ይረዳዎታል።
  • ማጨስን ያስወግዱ እና አልኮልን ይገድቡ።
  • በአተነፋፈስ ልምምዶች፣ በማሰላሰል ወይም ከሚወዱት ሰው ጋር ጊዜ ባማሳለፍ ጭንቀትን ለመቆጣጠር ይሞክሩ። 
  • ቀደም ብሎ ማወቁ ህይወትን ስለሚያድን የደም ግፊትዎን በየጊዜው ይለኩ።
  • የታዘዙልዎትን መድሃኒቶችን ያለማቋረጥ ይውሰዱ።

Comments (0)