ቀዶ ጥገና በቅርብ አሰርተዋል ?
ከቀደ ጥገና ቁስልዎ የሚወጣ ውሃማ ወይም ቢጫ ቀለም ያለው ፈሳሽ አይተውስ ተጨንቀዋል?
ይህ ፈሳሽ ሴረስ ፈሳሽ ወይም ሴረስ ድሬኔጅ (Serous drainage) የምንለው ሲሆን በአብዛኛው ከቁስል ወይም ከተቆረጠ ቦታ የሚወጣ ውሃማ ወይም ቢጫ ቀለም ያለው ከውሃ ትንሽ የሚወፍር ፈሳሽ ነው። ይህ አይነቱ ከቁስል የሚወጣ ፈሳሽ ቁስሎ ለመዳን የሚያደርገው ሂደት በመሆኑ ስጋት ሊፈጥርቦት አይገባም ።
ሆኖም ግን ከቁስልዎ ብዙ ሴረስ ፈሳሽ ሲፈስ ካስተዋሉ ወይም የሚፈሰው ፈሳሽ እንደ መግል ወፍራም ከሆነ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን መኖሩን ሊያመለክት ስለሚችል የጤና ባለሙያ ማማከር ይኖርቦታል።
ሴረስ ፈሳሽ ምንድን ነው ?
ሴረስ ፈሳሽ (Serous drainage) ፕሮቲኖች የሌሉት ፕላዝማ ነው። ፕላዝማ የደም ፈሳሹ ክፍል ሲሆን ከ 90 በመቶ በላይ ውሃ እና ከ10 በመቶ ያነሰው ደግሞ ጠጣር ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ይዟል ። እነዚህም ንጥረ ነገሮች እንደ ፋይብሪኖጅን ያሉ ፕሮቲኖችን ያካትታሉ ። ይህም ደም እንዲረጋ የሚያግዝ በጉበትዎ የሚመረት ፕሮቲን ነው።
አንድ ሰው ሲጎዳና ከጉዳቱ ደም መፍሰስ ሲጀምር ደም ውስጥ ያሉት ፕሮቲኖች ወደ ቆዳዎ ስር በመሄድ ከቁስሎ ብዙ ደም እንዳይፈስ ለመከላከል ደም እንዲረጋ ያደርጋሉ። ፈሳሽ ፕላዝማ (ፕሮቲን የሌለው) ወደ ቁስሉ ወለል ሲወጣ ፕሮቲኖቹ ደግሞ ከቁስሉ ስር ይቀራሉ። ደም በሚረጋበት ጊዜም እነዚህ ፕሮቲኖች ፈሳሽ ደምዎን ወደ ከፊል-ጠጣር (semisolid) በመለወጥ የደም መፍሰስ እንዲቆም ያደርጋሉ።
ሴረስ ፈሳሽ ለምን ከቁስልዎ ይፈሳል?
ሴረስ ፈሳሽ የበሽታ የመከላከል ስርዓትዎ ቁስልዎን ለመፈወስ በትክክል እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው። ስለዚህ ትንሽ መጠን ያለው ሴረስ ፈሳሽ መደበኛ ነው።
ከቁስልዎ ሊወጡ የሚችሉ ፈሳሾች ምን ምንድን ናቸው ?
ከደም በተጨማሪ ከቁስል ሊወጡ የሚችሉ ሦስት የተለያዩ የፈሳሽ ዓይነቶች አሉ፤ እነሱም፡
- ሴረስ ፈሳሽ (Serous drainage)
- ሴሮሳንጂነስ ፈሳሽ (Serosanguinous fluid)
ሴሮሳንጂነስ ፈሳሽ የሴረስ ፈሳሽ እና የደም ቅልቅል ሲሆን ብዙውን ጊዜ ፈዛዛ ሮዝ ወይም ቀይ ቀለም ይኖረዋል። ይህ ፈሳሽ ልክ እንደ ሴረስ ፈሳሽ ቁስልዎ እየዳነ እንደሆነ የሚያሳይ ምልክት ነው። መጠኑ ብዙ ካልሆነ የሚያሰጋ አይደለም።
- ፑሩለንት ፈሳሽ (Purulent drainage)
ከሦስቱ ዓይነቶች በጣም ወፍራም የሆነው ሲሆን ነጭ፣ ቢጫ ወይም ቡናማ ቀለምም አለው። ይህ ባክቴሪያ ወደ ቁስልዎ ገብቶ ኢንፌክሽን መፍጠሩን ያመለክታል። መጥፎ ሽታም ሊኖረው ይችላል።
ሕክምና እና እንክብካቤ
ቁስልዎ ሲድን ሴረስ ፈሳሽ በራሱ ይቆማል። ቁስልዎን መንከባከብ ሴረስ ፈሳሽ ቶሎ እንዲቆም እንዲሁም ኢንፌክሽንን ለመከላከል ይረዳዎታል። ቁስልዎን ለመንከባከብ የሚከተሉትን ማድረግ ይችላሉ
- ቁስሉን በሳሙና እና በውሃ ቀስ ብለው ይጠቡ። ካጠቡ በኋላም ቁስሉን በንፅሁ ጨርቅ ያድርቁ
- ቁስሉን በፋሻ ወይም በቁስል መሸፈኛ ይሸፍኑ
- ፋሻውን በየቀኑ ወይም በሐኪምዎ ትእዛዝ መሰረት ይቀይሩ
- ሐኪምም ቁስልዎን ለመንከባከብ የተለየ መመሪያ ከሰጥዎት እሱን ይከተሉ።
እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብዎት ነገር እንደ አልኮል ወይም ሃይድሮጂን ፔሮክሳይድ ያሉ ቁስልን ለማፅዳት የሚረሱ መድኃኒቶችን በተደጋጋሚ መጠቀም የቁስልዎን የመዳን ሂደት ሊያዘገዩ ወይም በትክክል እንዳይድን ሊያደርጉ ስለሚችሉ ቁስልዎ ላይ ምን መጠቀም እንዳለብዎ የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
መቼ ሐኪምዎን ማማከር ይኖርቦታል?
የሚከተሉት ሁኔታዎች ካጋጠሙዎት የጤና ባለሙያ ያማክሩ:
- ቁስልዎ አልድን ካለ
- ከቁስልዎ የሚወጣው ፈሳሽ ብዙ ከሆነ ወይም የቁስልዎን ጨርቅ (ፋሻ) ሲቀይሩ በፈሳሽ የተነከረ ከመሰለ
- ቢጫ ወይም ነጭ መግል (pus) ከቁስሉ የሚፈስ ከሆነ
- ከባድ ህመም ከተሰማዎት
- ቁስልዎ አካባቢ እብጠት ከተከሰተ
- ትኩሳት ወይም ብርድ ብርድ የሚል ስሜት ከተሰማዎት
- በቁስልዎ ዙሪያ ያለው መቅላት እየሰፋ ከሄደ ሐኪምዎን በአፋጣኝ ማማከር ይኖርቦታል።




