ማግኒዥየም ምንድን ነው እና ለምን ይታዘዛል?

Tsion Girma
Dec 5, 2025
undefined

 ማግኒዥየም ምንድን ነው?

 

ማግኒዥየም (Magnesium) በሰውነታችን ውስጥ ከ300 በላይ ለሚሆኑ የኬሚካል ሂደቶች (biochemical reactions) ወሳኝ ሚና የሚጫወት ጠቃሚ ማዕድን ነው። እያንዳንዱ የሰውነት ሴል ማግኒዥየምን ይፈልጋል፤ ከ60% በላይ የሚሆነው ማግኒዥየም  ደግሞ በአጥንቶቻችን ውስጥ ይገኛል።

ይህ ማዕድን ከምግብ በሚገኝበት ጊዜ ተፈጥሯዊ ነው፣ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ የአመጋገብ ችግር፣ የጤና እክሎች ወይም መድሃኒቶች በሰውነታችን ውስጥ የማግኒዥየም መጠን እንዲቀንስ ያደርጋሉ። የጤና ባለሙያዎችም በነዚህ ምክንያቶች ወይም ሌሎች የጤና ጥቅሞችን ለማግኘት ሲሉ የማግኒዥየም ተጨማሪ መድሃኒቶችን (supplements) ሊያዝዙ ይችላሉ።

 

 ማግኒዥየም ለምን ይታዘዛል? 

ማግኒዥየም የሚታዘዝበት ዋናው ምክንያት በደም ውስጥ ያለው መጠኑ ሲቀንስ ነው። ይህ ሁኔታ "ሃይፖማግኔዜሚያ" (Hypomagnesemia) ተብሎ ይጠራል። ዝቅተኛ የማግኒዥየም መጠን ምልክቶች የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ማቅለሽለሽ፣ ድካም  ሊሆኑ ይችላሉ። በጣም ሲቀንስ ደግሞ የመደንዘዝ፣ የጡንቻ መኮማተር (cramps)፣ ያልተለመደ የሰውነት እንቅስቃሴ (seizures) እና ያልተለመደ የልብ ምት (abnormal heart rhythm) ሊያስከትል ይችላል።

 

ማግኒዥየም እንዲቀንስ የሚያደርጉ የተለመዱ ምክንያቶች፦

  • አንዳንድ የአንጀት በሽታዎች፡ እንደ ክሮን በሽታ (Crohn's disease) ወይም ሴሊያክ በሽታ (celiac disease) ያሉ በሽታዎች
  • የስኳር በሽታ (አይነት 2)፡ በደም ውስጥ ያለው ከፍተኛ የስኳር መጠን የኩላሊት ሥራን በማወክ ማግኒዥየም በሽንት እንዲወገድ ያደርጋል።
  • የአልኮል ሱሰኝነት (Alcohol Dependence)፡ ደካማ አመጋገብ እና የአልኮል ተፅዕኖ የንጥረ ነገርን መቀነስ ያስከትላል።
  • እድሜ መግፋት፡ ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ሰውነት ማግኒዥየምን የሚቀበልበት ብቃት ይቀንሳል።
  • አንዳንድ መድሃኒቶች፡ ለምሳሌ የአሲድ መጠንን የሚቀንሱ መድኃኒቶች (Proton Pump Inhibitors)፣ አንዳንድ የልብ መድኃኒቶች (Diuretics) እና አንቲባዮቲኮች።

 

የማግኒዥየም ዋና ዋና የጤና ጥቅሞች

ማግኒዥየም እንደ ተጨማሪ መድሃኒት ሆኖ በሚታዘዝበት ጊዜ ወይም በአመጋገብ ውስጥ በበቂ መጠን ሲወሰድ በሰውነት ላይ የሚሰጣቸው ጥቅሞች ብዙ ናቸው።

 

1. ለጡንቻና ለነርቭ ሥራ

ማግኒዥየም የጡንቻዎችን መኮማተር እና መፍታትን ይቆጣጠራል። እንዲሁም የነርቭ ግፊቶች በትክክል እንዲተላለፉ ወሳኝ ነው። ለዚህም ነው አንዳንድ የጡንቻ መኮማተር (Leg cramps) እና የነርቭ ስርአት መዛባት ላለባቸው ሰዎች የሚታዘዘው።

 

2. የደም ግፊትና የልብ ጤና

ማግኒዥየም የደም ሥሮችን በማዝናናት (relax) የደም ግፊትን ለመቆጣጠር ይረዳል። ዝቅተኛ የማግኒዥየም መጠን ለልብ ሕመም ተጋላጭነትን እንደሚጨምር ጥናቶች ያመለክታሉ። በተለይ በድንገተኛ የልብ ምት መዛባት (arrhythmias) ውስጥ በሀኪም ክትትል ስር በደም ሥር (IV) የሚሰጥ ማግኒዥየም ሕክምና ወሳኝ ነው።

 

3. የአጥንት ጤና

ከ50-60% የሚሆነው የማግኒዥየም ክምችት በአጥንት ውስጥ ይገኛል። ማግኒዥየም የአጥንት መዋቅር እንዲገነባ ብቻ ሳይሆን፣ ቫይታሚን ዲ (Vitamin D) ወደ ንቁ (active) ቅርፅ እንዲቀየር በማገዝ ካልሲየም በአግባቡ እንዲመረት ያግዛል። ይህም ለኦስቲዮፖሮሲስ (Osteoporosis - የአጥንት መሳሳት) ለመከላከል ይረዳል።

 

4. የደም ስኳር ቁጥጥር

ማግኒዥየም ኢንሱሊን በሰውነት ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን የመቆጣጠር ችሎታን (Insulin Sensitivity) ያሻሽላል። የአይነት 2 የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ማግኒዥየም ስለሚጎድላቸው፣ ተጨማሪ ማግኒዥየም መውሰድ የደም ስኳር መጠናቸውን ለማስተካከል ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

 

ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሞችና አስተውሎቶች

ከላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ጥቅሞች በተጨማሪ ማግኒዥየም ለሌሎች የጤና ሁኔታዎችም ጥቅም ላይ ይውላል።

 

5. ለማይግሬን ራስ ምታት (Migraine Headaches)

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ማግኒዥየም የነርቭ ግፊቶችን እና የደም ሥር መጥበብን በመቆጣጠር የማይግሬን ራስ ምታትን ድግግሞሽ  ይችላል። ማግኒዥየም እጥረት ያለባቸው ሰዎች ለማይግሬን የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑም ተጠቁሟል።

 

6. ለሆድ ድርቀት (Constipation) እና አሲድነት

በተለይ ማግኒዥየም ሃይድሮክሳይድ (Magnesium Hydroxide) በአንጀት ውስጥ ውሃ እንዲጨምር በማድረግ  ይህም ለጊዜያዊ ሆድ ድርቀት እንደ ማለስለሻ (laxative) ያገለግላል። እንዲሁም ለልብ ማቃጠል (Heartburn) እንደ አሲድ ማጥፊያ (Antacid) ሆኖ ያገለግላል።

 

7. በእርግዝና ወቅት ለሚከሰት የደም ግፊት (Pre-eclampsia/Eclampsia)

በእርግዝና ወቅት ለሚከሰት አደገኛ የደም ግፊት ማግኒዥየም ሰልፌት (Magnesium Sulfate) በሆስፒታል ውስጥ በደም ሥር የሚሰጥ ዋነኛው የመከላከያ እና ህክምና መንገድ ነው።

Comments (0)