ፆታዊ ትንኮሳ (Gender Based violence)
ፆታዊ ትንኮሳ፣ ከነፃ ፈቃድ ወይም ከስምምነት ውጭ የሚደረግ ወሲባዊ ጥቃት ነው፤ ይህ አካልን መነካካት፣ ጥቃት ለማድረስ ሙከራ ማድረግ ወይም ወሲባዊ ሃሳቦችን እና ንግግሮች መሰንዘርን ጭምር ያካትታል። ፆታዊ ትንኮሳ በሁለቱም ፆታዎች፣ በየትኛውም ዕድሜ ወይም በማንኛውንም የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ሊከሰት ይችላል። ስለዚህ ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል፣ የፆታ ጥቃት ሊደርስበት ወይም ሊያደርስ ይችላል። ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ፣ ጤና፣ የሥራ ዕድል እና የሕይወት ደህንነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ የአለው የህብረተሰባችን ችግር ነው።
ስለ ፆታዊ ትንኮሳ ማወቅ የአሉብን ነገሮች
- አብዛኛውን ጊዜ ጥቃቱ ተሚፈፀመው በቅርብ ሰው ነው፤ ለምሳሌ ጓደኛ፣ ዘመድ፣ የሥራ ባልደረባ፣ ጎረቤት ወይም የቤተሰብ አካል
- ብዙውን ጊዜ ፆታዊ ትንኮሳ በአካል የሚፈፀም ጥቃት ቢሆንም፣ በቴክኖሎጂ ( በስልክ፣ በበይነ መረብ፣ በምስል)፣ በሃሳብ ልውውጥ (በንግግር) እና በፁሁፍ ጨምሮ ሊፈፀም ይችላል።
- በአገራችን ፆታዊ ትንኮሳ የተለመደ ችግር ሲሆን በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጥቃቱ ሰለባ ይሆናሉ።
- አብዛኛውን ጊዜ ግን ተጎጂዎች ስለጥቃቱ ለህግ ባለሙያዎች፣ ለጓደኞቻቸው ወይም ለቤተሰብ አባል ለመናገር ያፍራሉ፤ ወይም ማስፈራሪያን እና ዛቻን በመፍራት ከመናገር ይቆጠባሉ።
- አብዛኛውን ጊዜ ፆታዊ ትንኮሳ (ከ11 እስከ 20 ዓመት) ወጣቶች ላይ ይከሰታል።
የፆታዊ ትንኮሳ መዘዞች ምንድናቸው?
አካላዊ መዘዞች
- የኃይል ድብደባ፣ የአካል ቁስለት፣ መድማት፣ ህመም
- የብልት መቁሰል፣ መበለዝ፣ ፊስቱላ እና
- ለአባላዘር እና ለኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ መጋለጥ ናቸው።
የስነ-ልቦና መዘዞች
- ድብርት፣ ጭንቀት
- የስነ ልቦና ህመም (PTSD, somatic disorder, sexual problems)
- ራስን የማጥፋት ሀሳብ ወይም ራስን ለማጥፋት መሞከር
- ለደንዛዥ እፅ፣ ሲጋራ፣ አልኮሆል መጠጥ ሱስ መጋለጥ
- ለአደጋ አጋላጭ ለሆነ የወሲብ ህይወት መጋለጥ
- ሥራ፣ ማኅበራዊ ህይወት በአግባቡ አለመምራት
- የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች፣ በወደፊት ህይወታቸው ላይ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የመግባት ዕድላቸው ሰፊ ነው።
ለመሆኑ አስገድዶ የመደፈር ጥቃት ሲደርስ በአፋጣኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል
- ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ ልታገኝበት ወደምትችልበት፣ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የህክምና ተቋም መውሰድ፣
- ስለ ጥቃቱ ዝርዝር መረጃ መውሰድ (ጥቃቱ የደረሰበትን ሰዓት፣ ሁኔታ ጥቃቱን ያደረሰው ሰው ማንነት፣ እድሜ ወዘተ) ይህ መረጃ በቀጣይነት ለሚደረግ የሕክምና እርዳታ ወሳኝ ከመሆኑም በላይ ጥቃት አድራሹንም ሕግ ፊት ለማቅረብ ይረዳል፣
- ጎን ለጎን ጉዳዮን ለሕግ አካላት ማሳወቅ፣
- የስነ ልቦና ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት።
- ከጥቃቱ በሁላ ልብስ መቀየር፣ ገላን መታጠብ ወይም መጠራረግ አያስፈልግም፤ ከጥቃቱ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በዚሁ ምክንያት ይጠፋሉ። በጥቃቱ ምክንያት ለኤች አይ ቪ፣ የአባላዘር ኢንፌክሽኖች እዲሁም ለእርግዝና(ለአካለ መጠን ከደረሰች) ልትጋለጥ ትችላለች።
ሰዎች ፆታዊ ጥቃት እንዲያደርሱ የሚገፉፏቸው ሁኔታዎች ምንድናቸው?ግላዊ ጠባዮች
- አልኮሆል እና አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም፣ ወይም ሱሰኛ መሆን
- ግልፍተኝነት፣ ለሌሎች አለማሰብ፣ ጠበኛ እና አመፀኛ ባህሪ
- ሩካቤን ከልጅነት ዕድሜ መጀመር፣ አስገዳጅ ወሲባዊ ትዕይንቶችን መውደድ
- ልቅ እና አደገኛ ወሲባዊ ህይወት መምራት
- የፆታን አድልዎ መሰረት የአደረጉ ማኅበረሰባዊ ትውፊቶችን መቀበል
- ሴቶችን መጥላት፣ የወንድነት ባህሪን አጉልቶ ማሳየት
- ራስን የመጉዳት ወይም የማጥፋት ዝንባሌ
- ቀድሞውኑ ተመሳሳይ ችግር አድርሰው ከነበረ
የቤተሰብ ችግር
- በቤተሰብ ውስጥ ችግር እና አመፅ መኖር
- በልጅነት ጊዜ ለአካላዊ፣ ለወሲባዊ ወይም ለስሜታዊ ጥቃቶች ተጋልጠው ከነበረ
- በቤተሰብ ውስጥ የስነ ልቦና መደጋገፍ አለመኖር፤
- በወላጅ እና በልጆች መካከል ጤናማ ግንኙነት አለመኖር
- የአቻ ግፊት፣ ጠብ አጫሪ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ተሳታፊ መሆን
ማኅበረሰባዊ ኩነቶች
- ድህነት፣ የሥራ ዕድል አለመኖር
- ፆታዊ ጥቃትን የሚከላከል እና አግባብነት የአለው የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር
- በማኅበረሰቡ ውስጥ ፆታዊ ጥቃትን የሚያወግዝ ስራዓት አለመኖር፤ የፆታ እኩልነትን አለማመን
- ማኅበረሰቡ በጥቃት አድራሾች ላይ በአግባቡ እርምጃ አለመውሰድ
በአንፃሩ ፆታዊ ጥቃት ከማድረስ የሚጠብቁ ባህሪያት ምንድናቸው?
- በቤተሰብ መካከል የአለውን ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መወያየት እና መደጋገፍ ማጠናከር
- ስነ ልቦናዊ እና ስሜታዊ ጤንነት
- ትምህርት መማር ወይም የእውቀት ልህቀት
- ሌሎችን መውደድ፣ ስለሌሎች ስሜት ማሰብ
እንዴት መከላከል ይቻላል?
- ፆታዊ ትንኮሳን የሚቃወሙ ማኅበራዊ እሴቶችን ማጎልበት
- ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል የሚጠቅሙ ክሂሎቶችን ማስተማር
- ማኅበራዊ እና ስሜታዊ ልቀትን ማጎልበት
- ለወጣቶች ጤናማ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የፍቅር ጊዜ እዲመሩ የሚያስችሏቸውን ክሂሎቶች ማስተማር
- ጤናማ የወሲብ ሕይወት እዲኖር ማበረታታት
- የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት መጨመር፤ ይህም የሴቶች እና የህፃናት ድህነት እዲቀንስ ያደርጋል።
- ፍትሃዊ የሆነ የትምህርት ዕድል እዲያገኙ ማድረግ
- ስለፆታ እኩልነት ግንዛቤ መፍጠር፤
- የሴት ልጆች እና የወጣት ሴቶች የመሪነት ክሂሎቶችን ማዳበር
- የፆታዊ ትንኮሳን የሚከላከል አካባቢን መፍጠር
- የትምህርት ቤቶችን ደኅንነት መቆጣጠር እና ማሻሻል
- በሥራ ቦታ የአሉ ፖሊሲዎችን መገምገም
- ማኅበረሰቡን ማስተማር
- የጥቃት ሰለባዎችን ወይም ተጎጂዎችን መንከባከብ
- ለፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች፣ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ሕክምና ማቅረብ
- ተጎጂዎችን ማዕከል የአደረጉ አገልግሎቶች ማቅረብ




