የራስ መሳት ምክንያቶች እና የመጀመሪያ እርዳታ

Biruh Tesfaye
Dec 27, 2025
undefined

ራስን መሳት በሕክምናው ዘርፍ ሲንኮፓል ኤፒሶድ (syncopal episode) ወይም ሲንኮፒ (syncope) ተብሎ የሚጠራአ ሲሆን ይህም የሚከሰተው ወደ አንጎልዎ የሚሄደው የደም ፍሰት መጠን ሲቀንስ ነው። በዚህም ምክንያት አንጎልዎ በቂ ኦክስጅን ስለማያገኝ ለጥቂት ጊዜ ንቃተ ህሊናዎን ያጣሉ። ራስን በመሳት ወቅት ግለሰቡ ይወድቃል ወይም ይዘረራል፤ ይህም ደም ወደ አንጎል ተመልሶ እንዲፈስ ያስችላል። የደም ፍሰቱ መመለሱ ደግሞ ግለሰቡ ንቃተ ህሊናውን መልሶ እንዲያገኝ ያደርገዋል።

ራስን መሳት የተለመደ ክስተት ነው። ምንም እንኳን ሰዎች እድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ራስን መሳት በብዛት የሚያጋጥም ቢሆንም፣ በልጅነት ጊዜን ጨምሮ በማንኛውም የእድሜ ክልል ላይ ሊከሰት ይችላል። የራስን መሳት ክስተቶች አብዛኛውን ጊዜ ለሰከንዶች ወይም ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ የሚቆዩ ናቸው። ንቃተ ህሊናዎን መልሰው ሲያገኙ ጊዜያዊ የግራ መጋባት ስሜት ሊከተል ይችላል።

ለራስን መሳት መንስኤ የሚሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሲንኮፒ በውስጣዊ የጤና እክል ወይም በአካባቢያዊ ቀስቃሽ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። እንዲሁም ራስን መሳት በጣም አስቸጋሪ ለሆነ ሁኔታ ከሚሰጥ ስሜታዊ ምላሽ ሊመነጭ ይችላል። ከፍተኛ ሕመም፣ የደም ስኳር መጠን መቀነስ ወይም የደም መጠን መለዋወጥ ለሲንኮፒ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። የደም ግፊትዎ ወይም የልብ ምትዎ በድንገት ከቀነሰ፣ ድንገት ራስዎን ሊስቱ ይችላሉ።

ራስን መሳት ጉዳት የሌለው ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ የሌላ ስር የሰደደ የጤና እክል እንደ ምልክት ሊታይ ይችላል። ራስን መሳት ከጉዳት አልባ እስከ ለሕይወት አስጊ የሆኑ የተለያዩ መንስኤዎች ሊኖሩት የሚችል ምልክት ነው። እንደ ከፍተኛ ሕመም፣ ንዴት፣ ከፍተኛ ላብ፣ ድካም፣ ወይም የሰውነት አቀማመጥን በድንገት በመቀየር ምክንያት ደም በእግር ውስጥ መከማቸት ያሉ ለሕይወት አስጊ ያልሆኑ በርካታ ነገሮች ራስን መሳትን ሊቀሰቅሱ ይችላሉ።

የተለመዱ የሲንኮፒ መንስኤዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • ዝቅተኛ የደም ግፊት መኖር
  • የደም ሥሮች መስፋፋት
  • መደበኛ ያልሆነ የልብ ምት መኖር
  • የአካል አቀማመጥን በድንገት መቀየር፤ ለምሳሌ በጣም በፍጥነት መቆም፣ ይህም ደም በእግር ወይም በታችኛው የሰውነት ክፍል ውስጥ እንዲከማች ሊያደርግ ይችላል
  • ለረጅም ጊዜ መቆም
  • ከፍተኛ ሕመም ወይም ፍርሃት
  • ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ውጥረት (Stress)  
  • እርግዝና
  • በሰውነትዎ ውስጥ የጨው እና የፈሳሽ መጠን በጣም መቀነስ (Dehydration)  
  • ከፍተኛ ድካም
  • የአፍንጫ መታፈን ማስታገሻዎች ወይም የተወሰኑ የደም ግፊት መድኃኒቶችን መውሰድ
  • በጣም ሞቃት በሆነ አካባቢ መቆየት
  • ከመጠን በላይ ምግብ ወይም ቡና መውሰድ 
  • አልኮል ያለባቸውን መጠጦች በብዛት መጠጣት

አንዳንድ ሰዎች ደም ሲያዩ ራስን ሊስቱ ይችላሉ። በተጨማሪም ሲንኮፒ በበርካታ ምክንያቶች ጥምረት ሊቀሰቅስ ይችላል፤ ለምሳሌ የፈሳሽ እጥረት እያለብዎ የደም ስኳር መጠንዎ ቢቀንስ፣ ሁለቱ ተዳምረው ራስዎን እንዲስቱ ሊያደርጉ ይችላሉ።

የምልክቶች እና የቅድመ ማስጠንቀቂያዎች

ራስዎን ከመሳትዎ በፊት ራስዎን ሊስቱ እንደሆነ ሊሰማዎት ይችላል። ራስን ለመሳት የተቃረበ ሰው ማዞር፣ ማቅለሽለሽ፣ የመረበሽ (እርጋታ የማጣት) ስሜት፣የራስ ምታት፣ የማየት ችሎታው መደብዝዝ፣ የመስማት ችግር፣ በጆሮ ውስጥ የሚጮህ ድምፅ፣ የልብ ምት መጨመር፣ የልብ ትርታ መሰማት፣ ማዛጋት፣ የድካም ስሜት፣ መንቀጥቀጥ ወይም መርበትበት፣ የሰውነት መቀዝቀዝ ወይም ድንገተኛ ላብ ሊያገጥመው ይችላል።

የሲንኮፒ (ራስን መሳት) አይነቶች

በርካታ የራስን መሳት አይነቶች አሉ፦

  • ሪፍሌክስ ሲንኮፒ (Reflex syncope)፦ በጣም የተለመደው የራስ መሳት ዓይነት ነው። ይህም የሚከሰተው አንዳንድ የሰውነት ግብረ-መልሶች (reflexes) በአግባቡ ቁጥጥር በማይደረግባቸው ጊዜ ነው። ይህም የልብ ምትዎ እንዲቀንስ እና የደም ግፊት እንዲወርድ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ደግሞ በተራው ወደ አንጎልዎ የሚሄደውን የደም ፍሰት እንዲቀንስ ያደርገዋል። ሦስት ዓይነት የሪፍሌክስ ሲንኮፒ አይነቶች አሉ፦
  • ቫሶቫጋል (Vasovagal)፦ ይህ የሚከሰተው ሰውነትዎ ለአንድ ቀስቃሽ ሁኔታ ከልክ ያለፈ ምላሽ ሲሰጥ ነው። እንደ ከፍተኛ ሕመም፣ ጭንቀት ወይም ለረጅም ጊዜ መቆም ያሉ ብዙ ዓይነት ቀስቃሽ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። 
  • ሲቹዌሽናል (Situational)፦ ይህ ዓይነቱ ራስን መሳት እንደ መሳቅ፣ መሳል ወይም ምግብ መዋጥ ያሉ አንዳንድ ድርጊቶችን በሚፈጽሙበት ጊዜ የሚከሰት ነው።
  • ካሮቲድ ሳይነስ (Carotid sinus)፦ ይህ ዓይነቱ ራስን መሳት የሚከሰተው በአንገትዎ ውስጥ በሚገኘው የካሮቲድ የደም ቧንቧ (carotid artery) ላይ ጫና ሲያርፍ ነው። በአንገት እንቅስቃሴዎች፣ አንገታቸው ጠባብ የሆኑ ሸሚዞችን በመልበስ ወይም ጺም በመላጨት ወቅት ሊከሰት ይችላል።
  • ፖስቸራል ወይም ኦርቶስታቲክ ሲንኮፒ (Postural or orthostatic syncope)፦ የአካል አቀማመጥ በመቀየሩ ምክንያት በድንገት የሚከሰት የደም ግፊት መቀነስ ነው። ይህም ከመቀመጥ ወይም ከመተኛት ድንገት ሲቆሙ በሚመጣ የደም ግፊት መቀነስ ምክንያት ሊከሰት ይችላል። የደም ግፊቱ የሚቀንሰው በምድር ስበት (gravity) ተጽዕኖ ሳቢያ ነው። በተለመዶው ፣ አንጎልዎ ይህንን ሁኔታ ለማስተካከልና ለማረጋጋት ይሠራል። ነገር ግን በኦርቶስታቲክ ሲንኮፒ ጊዜ ይህ አይከሰትም ስለዚህም ወደ ራስ መሳት ሊያመራ ይችላል። ለዚህ ዓይነቱ ራስን መሳት በቂ ፈሳሽ አለለመጠጣት፣ የደም መፍሰስ፣ አንዳንድ የደም ግፊት መድኃኒቶች፣ የጭንቀት እና የስኳር በሽታ መድኃኒቶች፣ አልኮል አብዝቶ መጠጣት እና ስር የሰደዱ የጤና እክሎች መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
  • ካርዲያክ ሲንኮፒ (Cardiac syncope)፦ በልብ ወይም በደም ሥሮች ችግር ምክንያት ወደ አንጎል የሚሄድ የደም ፍሰት ሲታጎል የሚከሰት ነው። እነዚህ ሁኔታዎች መደበኛ ያልሆነ የልብ ምት (arrhythmia)፣ የደም መርጋት፣ የልብ ቫልቭ በሽታ ወይም የልብ ድካምን ሊያካትቱ ይችላሉ። በልብ ችግር ምክንያት ለሚመጣ ራስን መሳት ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች፣ ወንድ መሆን፣ የልብ በሽታ መኖር እና በቤተሰብ ውስጥ የልብ ሕመም ወይም ራስን የመሳት ታሪክ መኖር።
  • ኒውሮሎጂክ ሲንኮፒ (Neurologic syncope)፦ ወደ አንጎል የሚሄደውን የደም ፍሰት የሚገድብ በአንጎል ውስጥ ያለ ችግር ነው። እንደ የመጣል በሽታ (seizure)፣ ስትሮክ (stroke) ወይም ጊዜያዊ የደም ፍሰት መቋረጥ (TIA) ያሉ የነርቭ ችግሮች ሲኖሩ ሊከሰት ይችላል።
  • ምክንያቱ ያልታወቀ ሲንኮፒ፦ ለአንዳንድ መድኃኒቶች የሚሰጥ የጎንዮሽ ጉዳት ለሲንኮፒ የመጋለጥ እድልን ሊጨምር ይችላል። ራስዎን ያስሳተዎት ምክንያት ምን እንደሆነ ካላወቁ የሕክምና ባለሙያ ማማከርዎን ያረጋግጡ።

ለራስን መሳት የሚደረግ የመጀመሪያ እርዳታ

በተለምዶው ራስን መሳት ያጋጠማቸው ሰዎች ያለምንም ዘላቂ ጉዳት በሰከንዶች ውስጥ በፍጥነት ያገግማሉ። ሆኖም ራስን መሳት በውስጣዊ የጤና እክል ምክንያት ከሆነ ወይም በተደጋጋሚ የሚከሰት ከሆነ፣ ተጎዳው ሰው ሐኪም ማማከር ይኖርበታል።

አንድ ሰው ራስን ሲስት የሚከተሉት እርምጃዎች ለማገገም ሊረዱ ይችላሉ፦

  • ደህንነትን ማረጋገጥ፦ አንድ ሰው ድንገት ሲዝለፈለፍ ጉዳት እንዳይደርስበት ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ላይ መሆኑን ያረጋግጡ። ቆሞ ከሆነ በቀስታ ወደ መሬት እንዲያርፍ ያግዙት።
  • ራሱን የሳተውን ሰው ያስተኙት፦ በጀርባቸው እንዲተኙ ያድርጉ፤ እግራቸውን ደግሞ ከፍ ያድርጉላቸው (ይህ ደም ወደ አንጎል እንዲመለስ ይረዳል)።
  • ምላሽ መስጠታቸውን ማረጋገጥ፦ ግለሰቡን በቀስታ በመነቅነቅ ደህና መሆኑን ይጠይቁት። ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ አተነፋፈሱን እና የልብ ትርታውን ይፈትሹ።
  • መተንፈሳቸውን ያረጋግጡ፦ ግለሰቡ በአግባቡ እየተነፈሰ መሆኑን ያረጋግጡ። የማይተነፍስ ከሆነ፣ ወዲያውኑ ሲ.ፒ.አር (CPR) ያስፈልጋቸዋል።
  • ጥብቅ ያሉ ልብሶችን ያላሉ፦ በአንገት እና በወገብ ዙሪያ ያሉ ማናቸውንም ጥብቅ ልብሶች (እንደ ክራባት ወይም ቀበቶ) ያላሉ።
  • ይከታተሉ እና ያረጋጉ፦ ግለሰቡ ንቃተ ህሊናውን ካገኘ በኋላ ቢያንስ ለ10 ደቂቃ ያህል ተኝቶ እንዲቆይ ያድርጉ እና እንዲረጋጋ ይርዱት።  ሙሉ በሙሉ ንቃተ ህሊናው ሲመለስም ውኃ ይስጡት።
  • የሕክምና እርዳታ መፈለግ፦ ግለሰቡ በፍጥነት ንቃተ ህሊናውን ካላገኘ፣ ወይም ራስን መሳቱ ከደረት ሕመም፣ ከግራ መጋባት ወይም ከሌሎች አሳሳቢ ምልክቶች ጋር የተያያዘ ከሆነ ወዲያውኑ የአስቸኳይ ጊዜ የሕክምና እርዳታ ያግኙ።

ራሱን የሳተ ሰው ሲያጋጥምዎት እነዚህን ፈጽሞ አያድርጉ፦

  • የተጎዳው ሰው ጭንቅላቱን በሁለት እግሮቹ መካከል አድርጎ እንዲቀመጥ ማድረግ
  • ፊታቸውን በውኃ መርጨት
  • ክብሪት ወይም ለላ ጠረን ያለው ነገር ማሸተት

ከእነዚህ ስልቶች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ራስን መሳትን ለመከላከል ወይም ራስን የሳተን ሰው ለመርዳት ውጤታማ አይደሉም።

ራስን መሳትን መከላከል

ሁሉንም የራስ መሳት ክስተቶች መከላከል ባይቻልም፣ የተወሰኑ እርምጃዎችን በመውሰድ ተጋላጭነትን መቀነስ ይቻላል። ራስዎን ሊስቱ እንደሆነ ከተሰማዎት፣ ስሜቱ እስኪያልፍ ድረስ መሬት ላይ ይተኙ። ይህ በድንገት በመውደቅ እንዳይጎዱ ያደርግዎታል። ራስዎን የመሳት ስሜት ሲሰማዎት ሊረዱዎት የሚችሉ ሌሎች መንገዶች፦

  • በቂ ፈሳሽ መውሰድ፦ የደም መጠንን ለመጠበቅ እና የፈሳሽ እጥረት እንዳይከሰት ለመከላከል በቂ ፈሳሽ ይጠጡ።
  • በመደበኛነት መመገብ፦ መደበኛ ምግቦችን እና መክሰስን በመመገብ የደም ስኳር መጠንዎ የተረጋጋ እንዲሆን ያድርጉ።
  • ድንገተኛ የአካል አቀማመጥ ለውጥን ማስወገድ፦ ከመቀመጥ ሲነሱ የሚከሰት የደም ግፊት መቀነስንን ለመከላከል ከመቀመጥ ወይም ከመተኛት ሲነሱ በቀስታ ይንቀሳቀሱ።
  • ውጥረትን (Stress) መቆጣጠር፦ የማረጋጊያ ዘዴዎችን ይለማመዱ እና ውጥረትን ያስወግዱ።
  • ቀስቃሽ ሁኔታዎችን መለየት፦ እንደ ለረጅም ጊዜ መቆም ወይም በጣም መሞቅ ያሉ ራስን መሳትን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን በመለየት ያስወግዱ።
  • የጤና ባለሙያ ማማከር፦ ራስን መሳት በተደጋጋሚ የሚከሰት ከሆነ ወይም ከሌሎች ምልክቶች ጋር ተያይዞ ከመጣ፣ መንስኤው የሆነውን የጤና እክል ለመለየት የሕክምና ባለሙያ ያማክሩ።

Comments (0)