የሳንባ ምች በሽታ (Pneumonia)

Melat Geatchew
Jul 14, 2025
undefined

የሳንባ ምች በሽታ (Pneumonia)

የሳምባ ምች በአንዱ ወይም በሁለቱም ሳንባዎች የሚገኙትን የአየር ከረጢቶች የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ በሽታው በሳንባ ውስጥ በአሉት የአየር ከረጢቶች ውስጥ ቁስለትን ያስከትላል፡፡ በዚህም ምክንያት በሽተኛው መተንፈስ ሊያስቸግረው ይችላል ። 

ባክቴሪያዎችን፣ ቫይረሶችን እና ፈንገሶችን ጨምሮ የተለያዩ ተሕዋስያን የሳንባ ምች ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

 

የሳንባ ምች አጋላጭ ሁኔታዎች ምን ምንድን ናቸው?

የሳንባ ምች በሽታ ማንኛውንም ሰው  ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚከተሉት የማኅበረሰቡ ክፍሎች ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው።

  • ዕድሜያቸው 2 ዓመት ወይም ከዚያ በታች የሆኑ ሕፃናት፤
  • ዕድሜያቸው ከ 65 በላይ የሆኑ ሰዎች፤
  • በሆስፒታል ውስጥ እና በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ተኝቶ ይታከም የነበረ ታማሚ በተለይም ደግሞ በመተንፈሻ ማሽን የሚታገዝ ከሆነ፡፡
  • ሌላ ተጓዳኝ በሽታ ካለ  አስም፣ ስኳር፣ ደም ግፊት ወይም የልብ በሽታ ከአለ በሳንባ ምች የመጠቃት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
  • በቅርቡ እንደ ጉንፋን ያሉ የመተንፈሻ አካላት በሽታ የያዛቸው ሰዎች፤
  • ከሥራ እና ከመኖሪያ አካባቢ ጋር በተያያዘ ለሳንባ ፀር የሆኑ ኬሚካሎች ካሉ፤
  • ሱጋራ የሚያጨሱ፣ የተወሰኑ የአደንዛዥ ዕፅ ዓይነቶችን የሚወስዱ ወይም ከመጠን በላይ አልኮል መጠጥ የሚጠጡ ሰዎች፤
  • የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓታቸው የተዳከመ ሰዎች፤ - የኤች.አይ.ቪ / ኤድስ ታማሚዎች፣ ኬሞቴራፒ (chemotherapy) ወይም ለረጅም ጊዜ ስቴሮይድ (steroid) ይወስዱ የነበሩ ሰዎች ለበሽታው የተጋለጡ ናቸው፡፡

 

ምልክቶቹ ምን ምንድን ናቸው?

የሳንባ ምች ከ ቀላል እስከ ከባድ የተለያዩ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል። ይህም የሚወሰነው እንደ ተሕዋሱ በሽታ የማስከተል ዐቅም እና እንደ በሽተኛው በሽታን የመከላከል ጥንካሬ ይወሰናል። ለምሳሌ ፦ ሕፃናት፣ ዕድሜያቸው ከ 65 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋውያን እንዲሁም ተጓዳኝ የጤና ችግር የአለባቸው ሰዎች ከበሽታው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ከባድ ችግሮች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። 

ብዙውን ጊዜ የሳንባ ምች መለስተኛ ምልክቶች ከጉንፋን ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ረዘም ላለ ጊዜ ይቆያሉ። እነዚህ ምልክቶች የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያካትቱ ይችላሉ።

  • ትኩሳት፣ ላብ ወይም ብርድ ብርድ ማለት፡፡
  • ሳል  - አክታ የቀላቀለ ሊሆን ይችላል።
  • የድካም ስሜት
  • የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና ተቅማጥ ሊኖር ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪም ከበድ ያሉ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል። ለምሳሌ፦

  • ሲተነፍሱ ወይም ሲስሉ የሚከሠት የደረት ሕመም፤
  • የትንፋሽ እጥረት (ቶሎ ቶሎ መተንፈስ)፤
  • የከንፈር እና ምላስ መጥቆር፤

ከዕድሜ ጋር የተያያዙ ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ፦

  • ዕድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ዐዋቂዎች፤
  • የአእምሮ ግንዛቤ ግራ መጋባት ወይም ለውጦች፤
  • ዝቅተኛ የሰውነት ሙቀት፤
  • ጨቅላ ሕፃናት ላይ ማስታወክ፣ ኃይል ማጣት ወይም ጡት ሲጠቡ የማቆራርጥ ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ ፡፡

የሳንባ ምች እንዴት ነው የሚታከመው?

አብዛኛውን ጊዜ ተገቢው የሕክምና ክትትል ከተደረገ የሳንባ ምች ሙሉ በሙሉ ይድናል፡፡ ሕክምናው የሚወሰነው እንደ በሽታው ዓይነት፣ እንደሚታየው ምልክት እና ሌሎች የጤና እክል ሁኔታዎች ካሉ ነው፡፡

የሕክምናው ግብ ኢንፌክሽኑን መቆጣጠር፣ ማከምና ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን መከላከል ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ እስኪያገግሙ ድረስ ሕክምናውን በጥንቃቄ መከተል አስፈላጊ ነው፡፡

  • የሳንባ ምች በባክቴሪያ አማካኝነት የመጣ ከሆነ አንቲባዮቲክ (ፀረ ባክቴሪያ) ይታዘዛል፡፡ ይህም የሳንባ ምች ዋና የሕክምና መንገድ ሆኖ እናገኘዋለን።
  • ከዚህ በተጨማሪም ምልክቶችን ለማስታገስ የሚወሰዱ መድኃኒቶች አሉ። ለምሳሌ ትኩሳትን በፓራስታሞል፣ በአስፕሪን እና በመሳሰሉት መድኃኒቶች ማስታገስ ይቻላል። ነገር ግን ከሐኪም ጋር ሳይነጋገሩ ሳልን የሚቀንሱ መድኃኒቶችን መውሰድ አይገባም፡፡ ኢንፌክሽኑን ለማስወገድ ሰውነት የሚሠራበት አንዱ መንገድ ሳል ነው፡፡ 
  • ሞቃት መጠጦችን መጠቀምና በእንፋሎት መታጠን የአየር መተላለፊያን ለመክፈት ይረዳል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ከመተንፈስ ይልቅ መተንፈስ እየከበደና እያስቸገረ ከሄደ ወዲያውኑ ሐኪም ማነጋገር፡፡
  • ሳንባ እንዲድን እና ጤነኛ እንዲሆን ሲጋራ ከማጨስ ፈጽሞ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ 
  • በቂ ዕረፍት ማድረግ፡፡
  • የሳንባ ምች ምልክት በጣም ከባድ ከሆነ ግን ሆስፒታል መተኛትና በደም ሥር የሚሰጡ መድኃኒቶችን መውሰድ እንዲሁም ኦክስጂን መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል። 

ከሳንባ ምች ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ምን ምንድን ናቸው?

  • የባክቴሪያ በደም ውስጥ መሰራጨት (bacteremia)፤  ይህም በሽታው ወደ ሌላ አካል እንዲሰራጭ ያደርገዋል።
  • የመተንፈስ ችግር  
  • የሳንባ ውሃ መቋጠር (pleural effusion) 
  • የሳንባ መግል መያዝ 

የሳንባ ምችን እንዴት መከላከል ይቻላል?

  • ክትባት መውሰድ ፦ አንዳንድ የሳንባ ምች የሚያመጡ ተሕዋስያንን በክትባት መከላከል ይቻላል፡፡ 
  • ሲያስሉ እና ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫን መሸፈን፡፡
  • ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ማቆም፡፡ ሲጋራ ማጨስ ለሳንባ ምች ተጋላጭነትን ይጨምራል።
  • አዘውትሮ እጅን በሳሙና እና በውሃ መታጠብ፡፡
  • በሽታ የመከላከል ሥርዓትን ለማጠናከር ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መጠበቅ፡፡ በቂ ዕረፍት መውሰድ፤ ጤናማ ምግብ መመገብ እንዲሁም መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡

 

Comments (0)