ለሆድ መነፋት፣ ህመም እና ለጋዝ ስሜት መቼ ሐኪም ማማከር ይኖርቦታል?

Elsabet Azezew
Jan 4, 2026
undefined

                         ለሆድ መነፋት፣ ህመም እና ለጋዝ ስሜት መቼ ሐኪም ማማከር ይኖርቦታል?

አብዛኛው ሰው የሆድ መነፋት ስሜት ምን እንደሚመስል ያውቃል። የሆድ መነፋት ሲያጋጥምዎ ሆድዎ እንደተወጠረና እንደተለጠጠ የሚሰማዎት ሲሆን ልብስዎም በሆዶ አካባቢ ሊጠቦት ይችላል ። ምናልባትም ይህንን ስሜት በበዓላት ወቅት ከባድ ምግብ ከተመገቡ በኋላ ወይም ብዙ የተቀነባበሩ ምግቦችን (junk food) ሲመገቡ ይበልጥ አስተውለውት ይሆናል።

አልፎ አልፎ ለሚከሰት መጠነኛ የሆድ መነፋት ያልተለመደ ነገር አይደለም። ከምግብ በኋላ ማግሳት እንዲሁም ጋዝ ማስወጣትም (መፍሳትም) ጤናማ ተግባር ነው። አንድ ሰው በቀን ውስጥ ከ15 እስከ 21 ጊዜ ሊፈሳ ይችላል ፤ ወደ ሆዱ ውስጥ  የገባው አየር መውጣት ስላለበት። የገባው አየር ወይም ጋዝ በአንጀትዎ ውስጥ በተገቢው መንገድ ካልተንቀሳቀሰ ግን ከባድ የሆድ ህመም ሊያስከትልብዎ ይችላል። 

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የመጀመሪያው እርምጃ መንስኤያቸውን ማወቅ ነው። 

በዚህ ፅሁፍ ለሆድ መነፋት ፣ ለህመም እና ለጋዝ ስሜት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ምክንያቶችን እንዲሁም እነዚህን ምልክቶች መቼ ችላ ሳይሉ ሐኪም ማማከር እንዳለብዎት በዝርዝር እናያለን።

                 መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው ? 

ለምግብ የሚሰጥ ምላሽ

ምግብ በሚመገቡበት ጊዜ የተወሰነ መጠን ያለው አየር ወደ ውስጥ ያስገባሉ። ከመጠን በላይ አየር ወደ ሆድዎ እንዲገባ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦

  • ምግብ እየተመገቡ ማውራት
  • በጣም በፍጥነት መብላት ወይም መጠጣት 
  • የታሸጉ ጋዝ ያላቸው መጠጦችን (carbonated beverages) መጠጣት
  • ስትሮ (straw) በመጠቀም መጠጣት
  • ማስቲካ ማኘክ ወይም ከረሜላዎችን መምጠጥ
  • በትክክል ያልተገጠመ ሰው ሰራሽ ጥርስ (dentures) 

አንዳንድ ምግቦች ከሌሎቹ ይልቅ የበለጠ ጋዝ ያመነጫሉ። ከፍተኛ ጋዝ ከሚያመነጩ ምግቦች መካከል ፦ 

  • ባቄላ
  • ብሮኮሊ (Broccoli)
  • ጥቅል ጎመን
  • አበባ ጎመን
  • ምስር
  • ሽንኩርት እና
  • በቆልት (Sprouts) ይጠቀሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ለአንዳንድ ምግቦች አለመስማማት (intolerance) ሊኖር ይችላል ፤ ለምሳሌ፦

  • እንደ ማኒቶል፣ ሶርቢቶል እና ዚሊቶል ያሉ ሰው ሰራሽ ማጣፈጫዎች
  • የፋይበር ተጨማሪ ምግቦች (Fiber supplements) 
  • ግሉተን (Gluten) ያላቸው ምግቦች
  • ፍሩክቶስ (Fructose) ያላቸው ምግቦች
  • በወተት ተዋጽኦ ውስጥ የሚገኘው ላክቶስ (Lactose ) 

ምልክቶችዎ አልፎ አልፎ ብቻ የሚከሰቱ ከሆነ፣ የተመገቧቸውን ምግብ በማስታወሻ ደብተር መዝግቦ መያዝ ለችግሩ መንስኤ የሆኑትን ምግቦች ለመለየት እና ለማስታወስ ይረዳዎታል። የምግብ አለመስማማት ችግር ወይም የምግብ አለርጂ አለብኝ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ደግሞ ሐኪምዎን ያማክሩ። 

የሆድ ድርቀት (Constipation)

የሆድ መነፋት ስሜት እስኪጀምርዎ ድረስ የሆድ ድርቀት እንዳለብዎ ላያውቁ ይችላሉ። ሰገራ ሳይወጡ ረዘም ያለ ጊዜ በቆየ ቁጥር፣ የጋዝ መከማቸት እና የሆድ መነፋት ስሜት የመከሰት እድሉ ይጨምራል።

የሆድ ድርቀት በሁሉም ሰው ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰት ሲሆን ብዙውን ጊዜ በራሱ ይጠፋል። የሆድ ድርቀት ሲያጋጥምዎ አመጋገቦ ላይ  በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን በማከል ፣ ብዙ ውሃ በመጠጣት ወይም ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ (over-the-counter) መድኃኒቶችን በመጠቀም መፍትሔ ማግኘት ይችላሉ። የሆድ ድርቀትዎ በተደጋጋሚ የሚከሰት ከሆነ ግን ሐኪም ማማከሩ የተሻለ ነው።

ኤክሶክራይን ፓንክሪያቲክ ኢንሰፊሸንሲ (Exocrine pancreatic insufficiency (EPI))

ይህ እክል የሚከሰተው ቆሽት ምግብን በአግባቡ ለመፍጨት የሚያስፈልጉ ኢንዛይሞችን በበቂ ሁኔታ ሳያመነጭ ሲቀር ሲሆን ይህም ሰውነትዎ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ለመውሰድ እንዲቸገር ያደርገዋል።

የዚህ እክል የተለመዱ ምልክቶቹ ጋዝ፣ የሆድ መነፋት እና የሆድ ሕመም ሲሆኑ  የሚከተሉትንም ሊያስከትል ይችላል ፦

  • የሰገራ ቀለም መንጣት 
  • ቅባትነት እና መጥፎ ሽታ ያለው ሰገራ
  • የሚንሳፈፍ፣ ከሽንት ቤት ጋር የሚጣበቅ ወይም ውኃ ደፍቶ ለማስወገድ የሚያስቸግር ሰገራ
  • የምግብ ፍላጎት መቀነስ
  • ክብደት መቀነስ
  • የተመጣጠነ ምግብ እጥረት

ሕክምናው አመጋገብን እና የዕለት ተዕለት ልምዶችን መለወጥ እንዲሁም የፓንክሪያቲክ ኢንዛይም ምትክ መድኃኒቶች (pancreatic enzyme replacement therapy (PERT)) መውሰድ ሊያካትት ይችላል።

የአንጀት መቆጣት ሲንድሮም (Irritable bowel syndrome(IBS))

የአንጀት መቆጣት ሲንድሮም በትልቁ አንጀት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ስር የሰደደ የጤና እክል ነው። ይህ ችግር የምግብ መፈጨት ሥርዓት በትንሽ ነገር ቶሎ እንዲረበሽ ያደርገዋል ፤ በተለይ ደግሞ ለጋዝ ።

ከሚያስከትላቸው ምልክቶች ጥቂቶች እንደሚከተሉት ቀርበዋል ፦ 

  • የሆድ ሕመም ወይም ቁርጠት
  • የሆድ መነፋት
  • በሰገራ ልምድዎ ላይ የሚታዩ ለውጦች፤ ለምሳሌ ተቅማጥ፣ የሆድ ድርቀት ወይም ሁለቱም በተለዋዋጭ የሚከሰቱ ከሆነ

የአንጀት መቆጣት ሲንድሮም ምንም እንኳን መድኃኒት ባይኖረውም ምልክቶቹን የህይወት ዘይቤ ለውጥ በማድረግ፣ ፕሮባዮቲክስ (probiotics) እና የተለያዩ በመድኃኒቶች በመጠቀም መቆጣጠር ይቻላል። 

የአንጀት መቁሰል በሽታ (Inflammatory bowel disease (IBD))

የአንጀት መቁሰል በሽታ አልሰሬቲቭ ኮላይቲስ (ulcerative colitis) እና ክሮንስ ዲዚዝ (Crohn’s disease) የተባሉ የጤና እክሎችን ያጠቃልላል። እነዚህ እክሎዎች በአንጀት ውስጥ ቀጣይነት ያለው መቆጣት እና ቁስለትን ያስከትላል።

ህመሙ የሆድ መነፋት፣ ጋዝ እና የሆድ ህመምን የሚያስከትል ሲሆን ከእነዚህ ምልክቶች በተጨማሪም የሚከተሉትን ሊያስከትል ይችላል ፦

  • ደም የቀላቀለ ሰገራ
  • ተቅማጥ
  • ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት 
  • ክብደት መቀነስ 

ሕክምናው የፀረ ብግነት እና የፀረ ተቅማጥ መድኃኒቶችን፣ ቀዶ ጥገናን እንዲሁም የአመጋገብ ድጋፍን (nutrition support) ሊያካትት ይችላል።

ዳይቨርቲኩላይትስ (Diverticulitis)

ዳይቨርቲኩሎሲስ (Diverticulosis) በትልቁ አንጀት ደካማ ክፍሎች ላይ ትናንሽ ከረጢቶች ሲፈጠሩ የሚከሰት ሲሆን ዳይቨርቲኩላይትስ ደግሞ እነዚህ ከረጢቶች በባክቴሪያ ሲበከሉ እና ኢንፌክሽን ሲፈጠር ወይም ብግነት ሲኖር ይከሰታል።

የሕመሙ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታል፦

  • የሆድ ህመም ወይም ሆድዎን ሲነኩት የሚኖር የህመም ስሜት
  • የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ
  • ትኩሳት
  • ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ 

ሕክምናው እንደ ሕመሙ ክብደት የሚወሰን ሲሆን መድኃኒትዎችን መውሰድ፣ አመጋገብን መለወጥ ወይም ቀዶ ጥገና ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል።

ጋስትሮፓሬሲስ (Gastroparesis)

ጋስትሮፓሬሲስ ጨጓራ ምግብ የሚፈጭበትን እና የሚያስወግድበትን ሂደት በጣም እንዲዘገይ የሚያደርግ የጤና እክል ነው። ይህም ለሆድ መነፋት፣ ለማቅለሽለሽ እና ለአንጀት መታሰር (መዘጋት) መንስኤ ሊሆን ይችላል።

ሕክምናው መድኃኒቶችን፣ የአመጋገብ ለውጥን እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ቀዶ ጥገናን ሊያካትት ይችላል።

                          መቼ ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል?

አልፎ አልፎ የሚከሰት የሆድ መነፋት ወይም ጋዝ አብዛኛውን ጊዜ አሳሳቢ አይደለም። ነገር ግን ምልክቶቹ የማይሻሻሉ ወይም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ከሆነ ፤ በተለይም የሚከተሉትን ምልክቶች ካስተዋሉ ሐኪምዎን ያማክሩ፦

  • ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ መድኃኒቶችን በመውሰድ ወይም አመጋገብዎን በመቀየር ለውጥ ካላመጡ
  • ያለምንም ምክንያት ክብደት መቀነስ ወይም የምግብ ፍላጎት ማጣት
  • የማያቋርጥ የሆድ ድርቀት፣ ተቅማጥ ወይም ማስታወክ
  • የማይቆም የሆድ መንፋት፣ ጋዝ ወይም ቃር
  • በሰገራ ላይ ደም ወይም ንፍጥ የመሰል ነገር (mucus) መኖር
  • በመደበኛ የሰገራ ልምድዎ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መኖር
  • ምልክቶቹ በዕለት ተዕለት ሕይወትዎ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ከሆነ ሐኪምዎን ማማከር ይኖርቦታል።  

የሚከተሉት ምልክቶች ካጋጠሙዎት ግን አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ያስፈልጎታል፦

  • ከባድ የሆድ ሕመም (ቁርጠት)
  • ከፍተኛ ተቅማጥ
  • የደረት ሕመም ወይም
  • ከፍተኛ ትኩሳት ካጋጠምዎ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ያግኙ። 

ሐኪምዎ የህመም ምልክቶችዎን እና የጤና ታሪክዎን በመመርመር እና መንስኤውን በመለየት ችግሩን ለመቆጣጠር ይረዳዎታል።

Comments (0)