በወጣቶች ላይ የካንሰር በሽታ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ እንደሆነ ያውቃሉ ?

Elsabet Azezew
Jan 5, 2026
undefined

                       በወጣቶች ላይ የካንሰር በሽታ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ እንደሆነ ያውቃሉ ? 

                       ስለ ጉዳዩ ማወቅ ያለብዎት መረጃዎች እነሆ

      እድሜ ለካንሰር ከሚያጋልጡ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው ሲሆን በአብዛኛው ከ65 እስከ 74 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ይከሰታል። ሆኖም ግን ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 49 ዓመት በሆኑ ወጣቶች እና  አዋቂዎች ላይ የካንሰር በሽታ በአስደንጋጭ ፍጥነት እየጨመረ ይገኛል። 

      የአሜሪካ የካንሰር ማኅበር (American Cancer Society) ከ34 የካንሰር ዓይነቶች መካከል 17ቱ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች በሆኑ አዋቂዎች ላይ በመጨመር ላይ እንደሆኑ ገልጿል። በአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶች ምክንያት የሚከሰተው የሞት መጠንም እየጨመረ እንደሆነ ዘግቧል።

      የካንሰር በሽታ በወጣቶች ላይ ለምን ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ እንደመጣ ለመረዳት የጤና ባለሙያዎች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

                 በወጣቶች ላይ የካንሰር በሽታ እየጨመረ የመጣበት ምክንያት 

      የጤና ባለሙያዎች በወጣቶች እና በአዋቂዎች ላይ ለሚታየው የካንሰር መጨመር የተለያዩ ምክንያቶች ጥምረት እንደሆነ ያምናሉ።

      በተለያዩ ብሔረሰቦች ወይም ዘሮች መካከል የሚታየው ልዩነት ከዘረ መል (genetics)፣ ከገቢ መጠን፣ ከአካባቢ ሁኔታ እና የሕክምና አገልግሎት ከማግኘት ዕድል ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ለተለያዩ ለካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች መጋለጥ እና በምግብ መፈጨት ሥርዓት ጤና (gut health) ላይ የሚታዩ ልዩነቶችም የራሳቸው ድርሻ ሊኖራቸውም ይችላል።

      ከመጠን ያለፈ ውፍረት መጨመር በተለይም በምግብ መፈጨት ሥርዓት ውስጥ ለሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ ይታመናል። ከመጠን በላይ ውፍረት የሰውነት ብግነትን እና የሆርሞን ለውጦችን በማስከተል ለካንሰር የመጋለጥ እድልን ይጨምራል። በተቀነባበሩ ስኳሮች (refined sugars)  የበለፀጉ መጥፎ የአመጋገብ ልምዶችም በአንጀት ውስጥ ስር የሰደደ ብግነትን በማስከተል የካንሰር የመፈጠር እድልን ይጨምራሉ።

      ሌሎች ለካንሰር መጨመር ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚታሰቡ አጋላጭ ሁኔታዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦

  • እንደ ጭስ ወይም ቤንዚን ላሉ የአካባቢ ብክለቶች መጋለጥ
  • ካንሰር አምጪ ከሆኑ ኬሚካሎች ጋር ንክኪ መኖር
  • መጥፎ የእንቅልፍ ልምዶች
  • አነስተኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ
  • እንዲሁም ብዙ ጊዜ ተቀምጦ ማሳለፍ በትልቁ አንጀት ካንሰር (colorectal cancer) የመያዝ እድልን ከፍ ያደርጋል።

      የዘር ውርስም (genetics) የራሱ ሚና ያለው ሲሆን ቀደም ብሎ በትልቁ አንጀት ካንሰር ከሚያዙ ሰዎች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት በቤተሰባቸው ውስጥ የዚሁ በሽታ ታሪክ አለባቸው። ሆኖም ግን፣ አብዛኛዎቹ በሽታዎች የሚከሰቱት የታወቀ የቤተሰብ የካንሰር ታሪክ በሌላቸው ወጣቶች ላይ በመሆኑ ትክክለኛውን መንስኤ ለይቶ ለማወቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

                  በወጣቶች ላይ በብዛት የሚታዩ የካንሰር ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?

     ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች በሆኑ አዋቂዎች ላይ በጣም የተለመደው የካንሰር ዓይነት የጡት ካንሰር ነው። በወጣቶች ላይ በብዛት የሚታዩ ሌሎች የካንሰር ዓይነቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • የማኅፀን በር ካንሰር (Cervical cancer)
  • የትልቁ አንጀት እና የፊንጢጣ ካንሰር (Colorectal cancer)
  • የጨጓራ እና የአንጀት ካንሰሮች (Gastrointestinal (GI) cancers)  
  • ሊምፎማ (Lymphoma - የፍርንትት ስርዓት ካንሰር)
  • ሜላኖማ (Melanoma - የቆዳ ካንሰር)

     ምንም እንኳን የጡት ካንሰር በብዛት በምርመራ የሚገኘው የካንሰር ዓይነት ቢሆንም የትልቁ አንጀት ካንሰር ግን ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች በሆኑ አዋቂዎች ላይ ከካንሰር ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ሞቶች ዋነኛው መንስኤ ነው። 

     ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ በብዛት የማይከሰቱ እንደ የትርፍ አንጀት ካንሰር እና የፕሮስቴት ካንሰር ያሉ የካንሰር ዓይነቶች በወጣቶች ላይ በብዛት እየተከሰቱ ይገኛሉ። 

                  በወጣቶች ላይ የሚደረገው የካንሰር ምርመራ የተለየ ነው?

     መደበኛ የካንሰር ቅድመ ምርመራዎች (screenings) አብዛኛውን ጊዜ መደረግ የሚጀምሩት በተወሰነ የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ሲሆን ብዙ ወጣቶች ለነዚህ ምርመራዎች ከተቀመጠው የዕድሜ ገደብ በታች ናቸው። በዚህ ምክንያት በወጣትነት ዕድሜ የሚከሰት ካንሰር ብዙ ጊዜ በመደበኛ ቅድመ ምርመራዎች አይታወቅም። 

     ይልቁንም በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚከሰት ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ የሚታወቀው ምልክቶች መታየት ከጀመሩ በኋላ ነው።

     በወጣትዎች እና በአዋቂዎች ላይ የሚታዩ የተለመዱ የካንሰር ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • ከፍተኛ የድካም ስሜት
  • ያለምንም ምክንያት ክብደት መቀነስ ወይም የምግብ ፍላጎት ማጣት
  • የሰውነት መዛል
  • ህመም

    እነዚህ ምልክቶች እንደ ካንሰሩ ዓይነት ሊለያዩ ይችላሉ። ሆኖም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወጣቶች እነዚህን ምልክቶች ሲያዩ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ለማግኘት ይዘገያሉ። ይህም የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ወጣቶች ወደ ሕክምና የመሄድ ልምዳቸው አነስተኛ መሆኑ ነው።

    እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች በወጣት ታካሚዎች ላይ ካንሰር ይኖራል ብለው የመገመት እድላቸው ዝቅተኛ በመሆኑ መጀመሪያ ላይ የካንሰር ምርመራ ላያዝዙ ይችላሉ።

    በዕድሜ ከገፉ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር፣ በወጣትነት የሚከሰቱ ካንሰሮች የሚከተሉት የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው፦

  • በፍጥነት የሚባባሱ (Aggressive) ወይም ዘግይተው የሚታወቁ ናቸው 
  • በዘር የሚተላለፋ (Hereditary) ናቸው ። ይህም ማለት ከቤተሰብ የሚወረስ የዘረ መል ሁኔታ ጋር ተያይዘው የመከሰት እድላቸው በዕድሜ ከገፉ ሰዎች ይልቅ በወጣቶች ላይ ከፍ ያለ ነው ፤ ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚከሰቱ ካንሰሮች በዘር የሚተላለፉ ባይሆኑም። 

                 ወጣቶች ለካንሰር  የመጋለጥ እድላቸውን እንዴት መቀነስ ይችላሉ?

     ካንሰርን ለመከላከል የሚያስችል አስተማማኝ መንገድ ባይኖርም ፣ ወጣቶች የሚከተሉትን ምክሮች በመከተል ለካንሰር ያላቸውን ተጋላጭነት መቀነስ ይችላሉ ። 

 

  • ካንሰርን ለመከላከል ጥረት ያድርጉ 

           ካንሰርን ለመከላከል የሚረዱ እንደ የኤች.ፒ.ቪ (HPV) ክትባት ያሉ ክትባቶችን መውሰድ ፤ ይህም የማኅፀን በር ካንሰርን ለመከላከል ይረዳዎታል። በሚከተሉት መመሪያዎች መሠረት የካንሰር ቅድመ ምርመራዎችን (screenings) በጊዜው ይጀምሩ 

                                    - የጡት ካንሰር ፦ በ40 ዓመት ዕድሜ

                                    -የማኅፀን በር ካንሰር፦ በ25 ዓመት ዕድሜ

                                    -የትልቁ አንጀት ካንሰር፦ በ45 ዓመት ዕድሜ

 

  • የቤተሰብዎን የጤና ታሪክ ይወቁ

          የካንሰር በሽታ ያለባቸው የቅርብ ዘመዶች መኖራቸው ፣ የቅድመ ካንሰር ምርመራውን መቼ ማድረግ እና የትኞቹን የመከላከያ አማራጮች መከተል እንዳለብዎ ይወስናል።

     

  • ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ይከተሉ

          አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ፤ እንዲሁም የተመጣጠነ እና ተፈጥሯዊ ምግቦችን ይመገቡ። ቀይ ሥጋ እና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ሥጋዎችን (processed meats) ከአመጋገብዎ ይቀንሱ ፤ ይህም የትልቁ አንጀት ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ያግዛል። ለካንሰር በሽታ የመጋለጥ እድልን ስለሚጨምሩ ሲጋራ ማጨስን እና አልኮል መጠጥን መቀነስም ይኖርብዎታል።

     

  • ለሕመም ምልክቶችዎ ትኩረት ይስጡ

          ማንኛውም አዲስ ወይም ያልተለመደ የሕመም ምልክት ሲያጋጥምዎ ምርመራ የሚያስፈልግ መሆኑን ለመወሰን በተቻለ ፍጥነት ሐኪሞችን ያሳውቁ።

በወጣቶች ላይ የካንሰር በሽታ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ በመምጣቱ ወጣቶች የህመም ምልክቶችን ችላ ባለማለት እና በፍጥነት የህክምና እርዳታ በማግኘት ህይወታቸውን መታደግ ይችላሉ። 

Comments (0)