ሚኖክሲዲል በቅባት መልክ ለረጅም አመታት የጸጉር መሳሳትን ለማከም ጥቅም ላይ ውሏል። በተለይም ከታካሚዎች ደህንነት አንጻር ለጸጉር መሳሳት ህክምና በመድኃኒት ተቆጣጣሪ አካላት ያለ መድኃኒት ማዘዣ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ጥቅም ላይ እንዲውል ከተፈቀደላቸው ጥቂት መድኃኒቶች አንዱ ነው። በተለይም በቀላሉ መገኘት ስለሚችል እና ስለሚታወቅ ብዙ ሰዎች የጸጉር መሳሳትን ለመመለስ እና ጺም ለማሳደግ የመጀመርያ ምርጫቸው ያደርጉታል።
ሚኖክሲዲል እንዴት ይሰራል?
ሚኖክሲዲል የጸጉር ስሮችን በማነቃቃት እና ወደ ራስ ቅል የተሻለ የደም ዝውውር እንዲኖር በማድረግ የሚሰራ ሲሆን፣ በተለይም የጸጉርን እድገት ደረጃ በማስረዘም እና የእረፍት ደረጃቸውን በማሳጠር የጸጉር ዘለላዎች በጊዜ ውስጥ እንዲፋፉ እና እና እንዲረዝሙ ያደርጋል።
በራሰ በራነት የሚጠቁ ሰዎች የጸጉር ስር ቀስ በቀስ ይቀጭጫል። ሚኖክሲዲል ይህንን መቀጨጭ በቀጥታ በመቃወም የተዳከሙ የጸጉር ስሮችን ያነቃቃል። ይሁንና በዘላቂነት ስራ ያቆሙ የጸጉር ስሮችን ማስነሳት አይችልም።
ከሚኖክሲድል ብዙ ጥቅም ሊያገኝ የሚችለው ማነው?
- የራሰ በራነት ደረጃቸው ገና የሆነ ወይም መካከለኛ ላይ ያለ ሰዎች
- የጸጉር መሳሳት ያለው መሃል አናት ወይም ከጀርባ ከሆነ
- መድሃኒቱን በቶሎ የጀመሩ ሰዎች
በአንጻሩ ለረጅም አመታት ራሰ በራ የነበሩ ሰዎች ላይ እና እራሳቸው ላይ ብዙ ጠባሳ ያለባቸው ሰዎች ላይ የመስራት ዕድሉ አነስተኛ ነው።
ምን አይነት ውጤት መጠበቅ እንችላለን?
ከሚኖክሲዲል የምናገኘው ውጤት አፋጣኝ አይደለም። አብዛኛው ተጠቃሚዎች የሚታይ ውጤት ለማግኘት ቢያንስ ከ 3 እስከ 6 ወር ያለማቋረጥ መጠቀም ይኖርባቸዋል። የመጀመሪያ ጊዜ ተጠቃሚዎች የጽጉር መነቃቀል የሚያዩ ሲሆን፣ ይሄ ብዙ ጊዜ ሊያስደነግጥ ይችላል ነገር ግን ያረጁት ጽጉሮች አዲስ ለሚበቅለው ጸጉር ቦታ መልቀቅ ስላለባቸው የሚፈጠር ነው።
ቀጣይነት ባለው አጠቃቀም፣ በዙ ተጠቃሚዎች 3 ለውጦችን ያስተናግዳሉ።
- የጸጉር መውደቅ መቀነስ
- የጸጉር መፋፋት
- የጸጉር መውደቅ ፍጥነት መቀነስ
ነገር ግን ይህ ውጤት ከሰው ሰው የሚለያይ ሲሆን ተመሳሳይ ውጤት ላይገኝ ይችላ።
ትክክለኛ የሚኖክሲዲል አጠቃቀም እንዴት ነው?
ሚኖክሲዲል በአብዛኛው በቀን አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጎ ሊሰራ ይችላል። በፈሳሽ ወይም ፎም መልክ ሊዘጋጅ ይችላል። እናም በተለመደው ሰዓት ተከታትሎ መጠቀም ግድ ይላል። እንዲሁም የመድሃኒቱን ሰዓት መዝለል ወይም ማቋረጥ የተገኘው ውጤት እንዲመለስ ሊያደርግ ይችላል።
ሚኖክሲዲል የሚሰራው እስከተጠቀሙበት ጊዜ ድረስ ብቻ ስለሆነ የረጅም ጊዜ እቅድ እና ጽናት ይፈልጋል።
የጎንዮሽ ጉዳቶች እና ደህንነት
ሚኖክሲዲል በአጠቃላይ በታዘዘው መልኩ ከተጠቀሙት አስጊ/አሳሳቢ የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው ቢሆንም፡ አንዳንድ ተጠቃሚዎች ላይ የቆዳ መድረቅ ፤ ማሳከክ እና ያልተፈለገ የፊት ላይ ጸጉር መብቀል ሊያመጣ ይችላል (መድሃኒቱ ፊት ላይ ከወረደ)
ሚኖክሲዲል ለራሰ በራነት ፈዋሽ መድኃኒት ነው?
በአጭሩ አይደለም። ነገር ግን የጸጉር መነቃቀል ፍጥነትን ለመቀነስ እና በመዳከም ላይ ያሉ የጸጉር ስሮችን እንዲያንሰራሩ ያደርጋል። በተለይም ከሌሎች ህክምናዎች ጋር ሲዳበል የተሻለ ውጤት ያመጣል።




