የምግብ መመረዝ

Eyasu Yebeltal
Jan 8, 2026
undefined

                    የምግብ መመረዝ 

        የምግብ መመረዝ ምንድነው?

  • የምግብ መመረዝ አብዛኛውን ጊዜ ማቅለሽለሽ ፣ ማስታወክ እና ተቅማጥን የሚያስከትል  ህመም ሲሆን የተመገብነው ምግብ ወይም ዉሃ በባክቴሪያ ፣ በቫይረስ እና በጥገኛ ተውሳክ (Parasites) ወይም በነዚህ ተዋህስያን በተሰሩ መርዛማ ንጥረነገሮች የተበከለ ሲሆን ይከሰታል።
  • እንደ አለም ጤና ድርጅት ጥናት መሰረት በአለማችን ላይ በየዓመቱ ወደ 600 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በዚህ በሽታ ይጠቃሉ።
  •  ከነዚህም ውስጥ 420,000 የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን ከነዚህም መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ናቸው።

        ለምግብ መመረዝ የሚያጋልጡ ምግቦች ምንድናቸው?

  • የዶሮን ሥጋ ጨምሮ የተበከለ ጥሬ ወይም በአግባቡ ያልበሰለ ሥጋ 
  • የተበከለ ጥሬ እንቁላል 
  • የተበከለ ያልተፈላ ወተት
  • የተበከሉ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች
  • ጊዜአቸው ያለፈባቸው እና ደህንነታቸው ያልተጠበቀ የታሸጉ ምግቦች

ነገር ግን ማንኛውንም አይነት ምግብም ሆነ መጠጥ በበሽታ አምጪ ተዋህስያን ሊበከል እና የምግብ መመረዝን ሊያመጣ ይችላል።

        ምግብ እንዴት በበሽታ አምጪ ተዋህስያን ሊበከል ይችላል?

  • እጅን ሳይታጠቡ ምግብን ማዘጋጀት 
  • በአግባቡ ያልታጠበ ወይም ያልበሰለ ምግብ
  • ንፅህናው ባልተጠበቀ አካባቢ ምግብ እና የመጠጥ ዉሃን ማዘጋጀት
  • ለበሽታ አምጪ ተዋህስያን እድገት ተስማሚ በሆነ አካባቢ ምግብን ማስቀመጥ (ለምሳሌ ፍሪጅ አለመጠቀም)
  • አንዳንድ ጊዜ የታሸጉ ምግቦች እጅግ አደገኛ ለሆኑ ተዋህስያን እድገት ምቹ ይሆናሉ (ለምሳሌ ከመደበኛ መጠናቸው አብጠው የሚታዩ የቆርቆሮ ምግቦች)

       ለምግብ መመረዝ ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች እነማን ናቸው?

ሁሉም ሰው ለምግብ መመረዝ ተጋላጭ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች ግን ለምግብ መመረዝ እና ለተያያዥ ችግሮች ይበልጥኑ ተጋላጭ ናቸው። እነዚህም

  • ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት
  • ዕድሜአቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች
  • የተዳከመ የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓት ያላቸው ሰዎች እና
  • ነፍሰ ጡር እናቶች ናቸው።

       የምግብ መመረዝ ምልክቶች ምንድ ናቸው?

ምልክቶቹ ወዲያውኑ ወይም ከጥቂት ቀናት በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ሲሆን ከቀላል እስከ ከባድ ለሕይወት አስጊ ድረስ ሊደርሱ ይችላሉ። ይህም በበሽታ አምጪ ተዋህስያኑ ኃይለኝነት ላይ ይወሰናል።

የተለመዱ የምግብ መመረዝ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ:

  • ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ
  • የሆድ ህመም ወይም ቁርጠት
  • ተቅማጥ፣  እንደ ውሃ የቀጠነ ወይም ደም የቀላቀለ እና
  • ትኩሳት ናቸው።

አንዳንድ ጊዜ የምግብ መመረዝ ከባድ እና ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ  የጤና ችግሮችን ሊያስከትል እና እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።

ለምሳሌ

  • የአንጎል እና የነርቭ ጉዳት፣ ዕይታ ብዥ ማለት
  • የኩላሊት መጎዳት(Renal failure) እና
  • የመገጣጠሚያ ህመም ናቸው።

        ምርመራ

አስፈላጊ ከሆነ የጤና ባለሙያው

  • የሠገራ 
  • የደም እና 
  • የሽንትምርመራዎችን ሊያዝ ይችላል።

        የምግብ መመረዝ እንዴት ይታከማል?

ብዙ ሰዎች ያለ ምንም ዓይነት ሕክምና በራሳቸው ያገግማሉ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ከባድ ህመሞችን እና የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮችን ለመከላከል እና ለማከም የጤና እርዳታ መሻት ያስፈልጋል።

        የጤና እርዳታ መቼ እንፈልግ?

አብዛኞቹ ምልክቶች በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚያልፉ ሲሆን ነገር ግን የሚከተሉት ምልክቶች ሲኖሩ ወደ ጤና ተቋም መሔድ ያስፈልጋል።

  • ደም የቀላቀላ ተቅማጥ ወይም ትውከት
  • ከፍተኛ ትኩሳት (38ሴ በላይ ሙቀት)
  • ተደጋጋሚ ማስታወክ (ወደ ድርቀት(Dehydration) ሊያመራ ይችላል)
  • ከ 3 ቀናት በላይ የሚቆይ ተቅማጥ
  • የሰውነት ፈሳሽ መቀነስ(Dehydration) ምልክቶች ካሉ ሐኪም ቤት መሔድ ያስፈልጋል።

እነዚህም

  • የሽንት መጠን ማነስ ወይም ጭራሽ አለመሽናት
  • አፍ እና ጉሮሮ መድረቅ
  • ድካም ወይም ስንቆም የማዞር ስሜት ናቸው።

ነገር ግን ከላይ እንደተጠቀሰው ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ሰዎች (ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡር፣ አዛውንቶች) ማንኛውም አይነት የምግብ መመረዝ ምልክት ካላቸው ወደ ጤና ተቋም መሔድ አለባቸው።

         በቤታችን ውስጥ ምን ማድረግ አለብን?

ተቅማጥ እና ማስታወክ የሰውነትን ፈሳሽ እና የንጥረነገሮች (Electrolyte) መዛባትን ስለሚያስከትል በቤታችን ውስጥ የሚከተሉትን ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል።

  • በአፍ ብዙ ፈሳሽ መውሰድ ፤የሰውነትን ንጥረነገር ለመተካት ኦ.አር.ኤስ(ORS) መጠቀም
  • ዕረፍት ማድረግ
  • ማስመለሱ እስኪረጋጋ ለጥቂት ሰዓታት ምግብ አለመመገብ
  • ምግብ መመገብ ባሰኝዎት ሰአት የተቀቀለ የሩዝ ዉሃ ወይም ሾርባ መመገብ። ቅባታማ እና ጣፋጭነት ያላቸውን ምግቦች ማስወገድ
  • ለጊዜውም ቢሆን ከወተት፣ ከአልኮሆል ፣ ከታሸጉ መጠጦች ፣ ቅመም እና ቅባት ካላቸው ምግቦች መራቅ ያስፈልጋል።

        የምግብ መመረዝን እንዴት መከላከል ይቻላል?

  • የራስ እና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ
  • ከመፀዳጃ ቤት መልስ እጅን በአግባቡ መታጠብ
  • ንፁህ የመጠጥ ዉሃ መጠቀም ይህ ካልሆነ አፍልቶ እና አቀዝቅዞ መጠጣት ወይም የዉሃ አጋር መጠቀም።
  • አትክልትና ፍራፍሬዎችን ከመመገብ በፊት በደንብ ማጠብ
  • ምግብን ለማቆየት ፍሪጅን መጠቀም ከተቻለ ማቀዝቀዣውን ከ4.4 ሴ በታች ማድረግ።
  • ጥሬ ስጋ እና እንቁላል አብስሎ መመገብ
  • ወተት አፍልቶ መጠጣት
  • የታሸጉ ምግቦችን ከመመገብ በፊት ጊዜአቸውን መመልከት እና ደህንነታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

Comments (0)