የአልዛይመር በሽታ (Alzheimer's disease)

Al Amin Worku
Jan 9, 2026
undefined

የአልዛይመር በሽታ (Alzheimer's disease) 

የአልዛይመር በሽታ የጭንቅላት ህብረህዋሶች እንዲሞቱ እና የአንጎል መጠን እንዲቀንስ የሚያደርግ ደረጃ በደረጃ እየተባባሰ የሚሄድ የነርቭ በሽታ ነው፡፡ ይህ የተለመደ ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የመርሳት በሽታ ሲሆን በተጨማሪም አንድ ሰው ራሱን ችሎ የመንቀሳቀስ ችሎታውን፣ የአስተሳሰብ ፣ የባህሪ እና ማህበራዊ ክህሎቶች እንዲያሽቆለቁሉ ያደርጋል፡፡

በዓለም ዙሪያ የአእምሮ እክል ካለባቸው 50 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ከ 60% እስከ 70% የሚሆኑት የአልዛይመር በሽታ ተጠቂ ናቸው ተብሎ ይገመታል ፡፡

መድሃኒቶች የሕመም ምልክቶች እንዲሻሽሉ ወይም እንዲዘገዩ ሲያስችሉ፤ የአልዛይመር በሽታን የሚፈውስ ወይም በአንጎል ውስጥ ያለውን የሕመም ሂደት የሚቀለብስ ሕክምና እስካሁን ድረስ የለም፡፡ 

የአልዛይመር በሽታ ምልክቶች

የመርሳት ችግር የአልዛይመር በሽታ ዋና ምልክት ነው ፡፡ የመጀመሪያ ምልክቶች የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን ወይም ውይይቶችን ለማስታወስ መቸገር ሲሆን በሽታው እየገፋ ሲሄድ የማስታወስ እክል እየተባባሰ እና ሌሎች ምልክቶች እየታዩ ይመጣሉ

  •  ማህደረ ትውስታ

እያንዳንዱ ሰው አልፎ አልፎ የማስታወስ ክፍተቶች ያጋጥሙታል ፣ ነገር ግን ከአልዛይመር በሽታ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የማስታወስ እክል እየቀጠለ እና እየተባባሰ በመሄድ በመስሪያ ቤት ወይም በቤት ውስጥ የመሥራት ችሎታን ያዳክማል ፡፡

የአልዛይመር በሽታ ያለባቸው ሰዎች-

  • መግለጫዎችን እና ጥያቄዎችን ደጋግመው ይጠይቃሉ
  • ውይይቶችን ፣ ቀጠሮዎችን ወይም ዝግጅቶችን ይረሳሉ ፣ እናም በኋላ ላይ አያስታውሷቸውም
  • በተደጋጋሚ ንብረቶቻቸውን በተሳሳተ ቦታ ያስቀምጣሉ
  • ከዚህ በፊት በሚያውቋቸው ስፍራዎች ይጠፉሉ
  • እየከፋ ሲሄድ  የቤተሰብ አባላትን እና የዕለት ተዕለት እቃዎችን ስሞች ይረሳሉ
  • ዕቃዎችን ለመለየት ፣ ሀሳቦችን ለመግለጽ ወይም በንግግሮች ውስጥ ለመሳተፍ ትክክለኛዎቹን ቃላት ለማግኘት ይቸገራሉ

     

  • ማሰብ እና ማመዛዘን

የአልዛይመር በሽታ የትኩረት እና የማሰብ ችግርን ያስከትላል ፣ በተለይም ስለ ቁጥሮች እና ስለ ረቂቅ ፅንሰ-ሀሳቦች ፡፡

በአንድ ጊዜ የተለያዩ ሃሳቦችን የሚጠይቅ ሥራ መሥራት እየከበደ ይመጣል እንደ ገንዘብ ማስተዳደር ፣ የባንክ ደብተሮችን ማመዛዘን  እና ሂሳቦችን በወቅቱ መክፈል ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ የአልዛይመር በሽታ ያለበት ሰው በአጠቃላይ ቁጥሮችን መረዳት እና ማገናዘብ ላይችሉ ይችላል ፡፡

 

 

  •  ውሳኔዎችን የማድረግ ችሎታ

አልዛይመር በዕለት ተዕለት ሁኔታዎች ውስጥ ምክንያታዊ ውሳኔዎችን የማድረግ ችሎታ ላይ ውድቀት ያስከትላል ፡፡ ለምሳሌ ፣ አንድ ሰው በማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ መጥፎ ወይም ያልተለመዱ ባህርያትን መተግበር ፣ ከአየር ሁኔታው ጋር የማይስማሙ ልብሶችን ለብሶ መውጣት ወይም ለዕለት ተዕለት ችግሮች ውጤታማ ምላሽ አለለመስጠትን ያካትታሉ ፡፡

  • የተለመዱ ተግባራትን ማቀድ እና ማከናወን

እንደ  ምግብ ማብሰል ወይም የሚወዱትን ጨዋታ መጫወት ያሉ ተከታታይ እርምጃዎችን የሚጠይቁ ከዚህ በፊት ያለ ሃሳብ የሚያከናውኗቸው እንቅስቃሴዎች በሽታው እየከፋ ሲሄድ ትግል ይሆናሉ ፡፡ ከጊዜ በኋላም የከፋ የአልዛይመር በሽታ ያለባቸው ሰዎች እንደ መልበስ  እና መታጠብ ያሉ መሠረታዊ ሥራዎችን እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ ይረሳሉ ፡፡

  • የባህሪ  ለውጦች

በአልዛይመር በሽታ ምክንያት የሚከሰቱ የአንጎል ውስጥ ለውጦች በስሜት እና በባህሪ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ፡፡ እነዚህም ለውጦች የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ

  • ድብርት
  • ግድየለሽነት
  • ራስን ከማህበረሰብ ማግለል
  • የስሜት መለዋወጥ
  •  በሌሎች ላይ እምነት ማጣት
  • ብስጭት እና ግልፍተኝነት
  • የእንቅልፍ  ለውጦች
  • ያለ መድረሻ እግር ወደ መራ መጓዝ
  • ምክንያታዊ ያልሆኑ እሳቤዎች

 

  • የበሽታው ምልክቶች እየተባባሱ ቢሆኑም እንኳ አንድአንድ አስፈላጊ ክህሎቶችን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል በበሽታው በጊዜ ስለማይጠቃ የተወሰኑ ክህሎቶች ረዘም ላለ ጊዜ ይቆያሉ ፡፡ ከእነዚህም መካከል መጽሃፍትን ማንበብ ወይም መስማት ፣ ታሪኮችን መናገር ፣ መዝፈን ፣ ሙዚቃ ማዳመጥ ፣ መጨፈር ፣ ስዕል መሳል ወይም የእጅ ሥራዎችን መስራት  ሊያካትቱ ይችላሉ ፡፡

ምን አይነት ምልክት ሳይ ወደ ሃኪም ቤት መሄድ አለብኝ?

በርካታ መታከም የሚችሉ ሁኔታዎች የማስታወስ ችሎታ መቀነስን ወይም ሌሎች የመርሳት በሽታ ምልክቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። የማስታወስ ችሎታዎ ወይም ሌላ የአእምሮ ክንዋኔዎችዎ የሚያሳስብዎ ከሆነ ጥልቅ ግምገማ እና ምርመራ ለማድረግ ከሐኪም ጋር ይወያዩ ፡፡

በቤተሰብ አባልዎ ወይም በጓደኛ ላይ የሚመለከቷቸው የባህሪ ለውጦች የሚያሳስብዎት ከሆነ እርስ በርስ ተነጋግረው ወደ ሃኪም ቤት አብረው ይሂዱ ፡፡

 

የአልዛይመር በሽታ መንሰኤዎች?

የአልዛይመር በሽታ ትክክለኛ መንሰኤው ሙሉ በሙሉ አየታወቅም ፡፡ ነገር ግን በመሰረታዊ ደረጃ አንጎል ውስጥ የሚገኙ ፕሮቲኖች በመደበኛነት ሥራቸውን ሳያከናውኑ ሲቀሩ የአንጎል ህብረህዋስ እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል እና ተከታታይ የመርዛማ ክስተቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ይህም  ነርቮች ላይ ጉዳት ያደርሳል፣ እርስበእርስ ያላቸውን መስተጋብር እንዲያጡ ያደርጋቸዋል በመጨረሻም የነርቭ ህብረህዋስ ሞትን ያስከትላል ፡፡

የሳይንስ ሊቃውንት አብዛኞቹ ሰዎች ላይ የአልዛይመር በሽታ በዘር ፣ በአኗኗር ዘይቤ እና በጊዜ ሂደት በአንጎል ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ አካባቢያዊ ሁኔታዎች የተቃጣ ጉዳት ምክንያት ይመጣል ብላው ያምናሉ ፡፡

ጉዳቱ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው የማስታወስ ችሎታውን በሚቆጣጠረው የአንጎል ክልል ውስጥ ሲሆን ሂደቱ የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ከመታየታቸው ከዓመታት በፊት ይጀምራል። የከፋ ምልክቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ  የአንጎል መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ፡፡

የአልዛይመር በሽታ አጋላጭ ምክንያቶች

  • ዕድሜ

የዕድሜ መጨመር ዋነኛው የታወቀ ለአልዛይመር በሽታ አጋላጭ ሁኔታ ነው ፡፡ አልዛይመር የመደበኛ እርጅና አካል አይደለም ፣ ግን ዕድሜዎ እየጨመረ ሲሄድ የአልዛይመር በሽታ የመያዝ እድሉ አብሮ ይጨምራል ፡፡

  • በቤተሰብ አልዛይመር ያለበት ሰው ካለ

በተለይም ወላጅዎ፣ ወንድምዎ ወይም እህትዎ በበሽታው ከተያዙ በአልዛይመር የመያዝ ተጋላጭነትዎ በተወሰነ ደረጃ ከፍ ያለ ነው ፡፡

  • ዳውን ሲንድሮም(Down Syndrome)

ዳውን ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በአልዛይመር በሽታ ይያዛሉ። የአልዛይመር ምልክቶች ከጠቅላላው ህዝብ አንፃር  ከ10 እስከ 20 ዓመታት ቀደም ብለው ዳውን ሲንድሮም በተያዙ ሰዎች ላይ ይታያሉ፡፡

  • ፆታ

በወንዶችና በሴቶች መካከል ለዚህ በሽታ ተጋላጭነት እምብዛም ልዩነት የለም ፣ነገር ግን በአጠቃላይ ከወንዶች በላይ ሴቶች ረዘም ያለ ዕድሜ ስለሚኖራቸው የአልዛይመርስ በሽታ በመጠኑ ከፍ ብሎ ይታይባቸዋል።

  • ጭንቅላት ላይ የደረሰ አደጋ

ከባድ የጭንቅላት አደጋ ያጋጠማቸው ሰዎች ለአልዛይመር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው ፡፡ በርካታ ትልልቅ ጥናቶች  የጭንቅላት አደጋ የደረሰባቸው ዕድሜያቸው ከ 50 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በአልዛይመር በሽታ የመያዝ ዕድላቸው እንደሚጨምር ያሳያሉ፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከጭንቅላት አደጋው በኋላ ባሉት ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመታት ባሉት ጊዜዐት ውስጥ የአልዛይመር በሽታ የመከሰት እድሉ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ፡፡

  • የአየር ብክለት

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለአየር ብክለት ተጋላጭነት - በተለይም በመኪና ጭስ እና በሚነድ እንጨት- ከአእምሮ እክል አደጋ ጋር የተቆራኘ ነው ፡፡

 

  • ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት

ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮል መጠጣት የአንጎል ህብረህዋሶች ለውጥ እንደሚያመጣ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ይታወቃል፡፡ በርካታ ትልልቅ ጥናቶች እና ግምገማዎች እንደሚያመለክቱት የአልኮል አጠቃቀም ችግሮች በአልዛይመር በሽታ ከመጠቃት አደጋ ጋር ተያይዘዋል

  • የተዛባ የእንቅልፍ ዘይቤ

እንቅልፍ አብዘቶ መተኛት ወይም በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ያሉ መጥፎ የእንቅልፍ ዘይቤዎች ለአልዛይመር በሽታ ተጋላጭ ያደርጋሉ ፡፡

  •  የአኗኗር ዘይቤ እና የልብ ጤና

ከልብ ህመም ጋር ተያይዘው የሚገኙ ተመሳሳይ አጋላጭ ምክንያቶች በአልዛይመር በሽታ የመያዝ እድልን ከፍ እንደሚያደርጉ ጥናቶች አመላክተዋል ፡፡ እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ:

  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ
  • ከመጠን በላይ ውፍረት
  • ሲጋራ ማጨስ ወይም ለሲጋራ ጭስ  መጋለጥ
  • ከፍተኛ የደም ግፊት
  • ከፍተኛ ኮሌስትሮል
  • ቁጥጥር ያልተደረገለት ዓይነት 2 የስኳር በሽታ

የአልዛይመር በሽታ መዘዞች

የማስታወስ እና የቋንቋ ችሎታ ማጣት ፣ ምክንያታዊ ያልሆኑ ውሳኔዎች እና በአልዛይመር የተከሰቱ ሌሎች የባህሪ ለውጦች ለሌሎች የጤና እክሎች ሕክምና ማግኘትን ያወሳስበዋል ፡፡  ለምሳሌ የአልዛይመር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሚከተሉትን በአግባቡ መፈፀም  አይችሉም:

  • ህመም እየተሰማቸው መሆኑን  መናገር
  • የህመም ምልክቶችን ማብራራት
  • የታዘዘላቸውን የሕክምና ዕቅድ መከተል
  • ያጋጠማቸውን የመድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቶች ማስረዳት

የአልዛይመር በሽታ ወደ መጨረሻው ደረጃው እየተሸጋገረ ሲሄድ እንደ መዋጥ ፣ ሚዛንን መጠበቅ ፣ ሰገራ እና ሽንትን መቆጣጠር በመሳሰሉ አካላዊ ተግባራት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይጀምራሉ ፡፡ እነዚህም ለተጨማሪ የጤና ችግሮች ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋሉ፟

  • ምግብ ወይም ፈሳሽ ወደ የመተንፈሻ ቧንቧ ውስጥ አምልጦበመግባት የሳንባ ምች ያስከትላል
  • በተደጋጋሚ መውደቅ
  • ስብራት
  • የአልጋቁራኛ የሆኑ ሰዎች ላይ ባለመገላበጥ ምክንያት የሚመጣ የቆዳ ቁስል
  • የተመጣጠነ ምግብ እጥረት
  • የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ
  • እንደ አፍ ቁስለት ወይም የጥርስ መበስበስ ያሉ የጥርስ ችግሮች

 

የአልዛይመር በሽታን መከላከል ይቻላል?

ይህን ማድረግ የአልዛይመር በሽታን ሙሉበሙሉ ይከላከላል የሚያስብል ሁኔታ የለም ፤ ሆኖም ለአልዛይመር በሽታ የሚያጋለጡ የአኗኗር ዘይቤዎችን በማስተካከል በበሽታው የመያዝ እድልዎን መቀነስ ይችላሉ፡፡

  • በመደበኛነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
  • ጤናማ ዘይቶች (unsaturated fatty acids) ያሉት ምግቦችን መመገብ
  • የደም ግፊትን ፣ የስኳር በሽታንና ከፍተኛ ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር የህክምና መመሪያዎችን በመከተል
  • ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ማጨስን ለማቆም ህኪም እንዲረዳዎ መጠየቅ
  • በማህበራዊ ዝግጅቶች ላይ መሳተፍ ፣ ማንበብ ፣ አእምሮ የሚያነቃቁ ጨዋታዎችን መጫወት ፣ ስነ፟-ጥበብ መፍጠር ፣ የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት እና ሌሎች የአእምሮ እና ማህበራዊ ተሳትፎን ሚጠይቁ ተግባራትን ማከናወን በእርጅና ወቅት ጤናማ አእምሮ እንዲኖረን ይረዳሉ

ለአልዛይመር በሽታ የሚደረግ ምርመራ

  • እርሶ ወይም አብሮት የሚኖረው ሰው ያስተዋለው ለአእምሮ ለውጦችን በጥልቀት መወያየት
  • ሙሉ አካላዊ ምርመራ
  • የደም ምርመራዎች  ሌሎች መታከም የሚችሉ የበሽታ አይነቶች መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ
  • የጭንቅላት ኤም.አር.አይ (MRI) ወይም ሲቲ ስካን (CT Scan)

     

ለአይዛይመር በሽታ የሕክምና አማራጮች

የአልዛይመር መድሃኒቶች የማስታወስ እክልን እና ሌሎች የግንዛቤ ለውጦችን ለማሻሻል ይረዳሉ ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁለት ዓይነቶች መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ውለዋል

ኮሊንስተሬዝ አጋቾች (Cholinesterase inhibitors)  ዶኒፔዚል donepezil ፣ ጋላንታሚን galantamine  እና ሪቫስቲጂሚን rivastigmine የመሳሰሉ መድሃኒቶች በአልዛይመር በሽታ ምክንያት በአንጎል ውስጥ የተፈጠረውን የኬሚካል መዛባት በማስተካከል የነርቭን  እርስበእርስ ግንኙነት ያሻሽላሉ ​።

እነዚህ  መድሃኒቶች በአብዛኛው ምልክቶች ላይ መጠነኛ መሻሻሎችን ያመጣሉ። በተጨማሪም እንደ መነጫነጭ እና ድብርት ያሉ ምልክቶችን ያሻሽላሉ፡፡

ከእነዚህ መድሃኒቶች ዋነኞቹ የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል ተቅማጥ ፣ ማቅለሽለሽ ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት እና የእንቅልፍ መዛባት ይገኙበታል ፡፡ የተወሰኑ የልብ ችግሮች ባሉባቸው ሰዎች ላይ ከባድ የልብ ምት መዛባት (arrhythmia) ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡

ሜማንቲን (Memantine)  ይህ መድሃኒት በሌላ የአንጎል ህብረህዋስ የግንኙነት አውታረመረብ ውስጥ የሚሠራ ሲሆን ከመካከለኛ እስከ ከባድ የአልዛይመር በሽታ የሚያስከትላቸውን ምልክቶች ያሻሽላል ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከ ኮሊንስተሬዝ አጋቾች ጋር በማጣመር ጥቅም ላይ ይውላል። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት የጎንዮሽ ጉዳቶች ሲኖሩት ማዞር እና ግራ መጋባትን ያካትታሉ፡፡

 

 

 

ለአልዛይመር በሽተኞች የሚያስፈልግ እንክብካቤ

የአልዛይመር በሽታ ያለበትን ሰው ስንንከባከብ የኑሮ ሁኔታን ማመቻቸት ለማንኛውም የሕክምና ዕቅድ አስፈላጊ አካል ነው ፡፡ በአልዛይመር በሽታ ለተጠቁ ሰዎች ቋሚ ልምዶችን ማጠናከር እና የማስታወስ ችሎታን የሚጠይቁ ተግባራት መቀነስ ህይወታቸውን ያቀላል ፡፡

የጤንነት ስሜት እንዲሰማቸው እና በራስ የመሥራት ችሎታን ለመደገፍ እነዚህን እርምጃዎች መውሰድ ይችላሉ-

  • ቁልፎችን ፣ የኪስ ቦርሳዎችን ፣ ሞባይል ስልኮችን እና ሌሎች ውድ ዕቃዎችን እንዳይጠፉ በቤት ውስጥ በአንድ ቦታ ያኑሩ ፡፡
  • መድሃኒቶችን ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ያስቀምጡ ፡፡ መጠኖችን ለመከታተል በየቀኑ የማረጋገጫ ዝርዝርን ይጠቀሙ ፡፡
  • አስፈላጊ የስልክ ቁጥሮችን ወደ ታማሚው የሞባይል ስልክ ይመዝግቡ ፡፡
  • በሮች እና መስኮቶች ላይ የማስጠንቀቂያ ደውሎችን ይግጠሙ፡፡
  • መደበኛ ቀጠሮዎች በተቻለ መጠን በተመሳሳይ ቀን በተመሳሳይ ሰዓት መሆናቸውን ያረጋግጡ ፡፡
  • ዕለታዊ መርሃግብሮችን ለመከታተል በቤት ውስጥ የቀን መቁጠሪያ ወይም ነጭ ሰሌዳ ይጠቀሙ ፡፡ የተጠናቀቁ ነገሮችን የማጣራት ልማድ ይገንቡ ፡፡
  • ከመጠን በላይ የቤት እቃዎችን ፣ የተዝረከረኩ ነገሮችን ያስወግዱ፣ ኤሌክትሪክ እቃዎችን አርቀው ያስቀምጡ እና ቤቱ ወለል ላይ ምንጣፍ ያንጥፉ ፡፡
  • በደረጃዎች እና በመታጠቢያ ቤቶች ውስጥ ጠንካራ የእጅ አምዶች ይግጠሙ ፡፡
  • ጫማዎች ምቹ መሆናቸውን እና የማያንሸራትቱ መሆናቸውን ያረጋግጡ።
  • የመስታወቶችን ብዛት ይቀንሱ ፡፡ የአልዛይመር በሽታ ያለባቸው ሰዎች በመስታወቶች  ውስጥ ግራ የሚያጋቡ ወይም የሚያስፈሩ ምስሎች ሊታያቸው ይችላሉ ፡፡
  • የአልዛይመር በሽታ ካለበት ሰው ጋር በሚወጣበት ሰዐት ድንገት ብትጠፋፉ መልሶ ለማግኘት እንዲረዳ ታማሚው ስልክ እና መታወቂያ መያዙን ያረጋግጡ ፡፡
  • በቤቱ ዙሪያ ፎቶግራፎችን እና ሌሎች ለታመሚው ህይወት ትርጉም ያላቸው ነገሮችን ያኑሩ፡፡
  • በተደጋጋሚ ጥያቄዎች በሚያቀርቡበት ጊዜ ላለመሰላቸት ሞክሩ
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እና ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ ያበረታቷቸው

Comments (0)