በእባብ መነደፍ

Eyasu Yebeltal
Jan 9, 2026
undefined

                                    በእባብ መነደፍ

በዓለማችን ላይ በየዓመቱ በግምት 2.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በመርዛማ እባቦች ይነደፋሉ። ከነዚህም ውስጥ ከ 100,000 በላይ የሚሆኑት ለሞት ሲዳረጉ ወደ 400,000 የሚሆኑት ደግሞ ለአካል ጉዳት እና ለዘላቂ የጤና ችግሮች ይጋለጣሉ። በመርዛማ እባብ የተነደፉ ከሆነ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳትን የሚያስከትል እና ለሞት ሊዳርግ ይሚችል ሲሆን መርዝ የሌለው የእባብ ንክሻ እንኳን ቢሆን ለኢንፌክሽን እና ለአለርጂ ችግር ሊያጋልጥ ስለሚችል በተቻለ ፍጥነት ወደ ሆስፒታል በመሔድ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል።

በታዳጊ አገሮች ላይ አብዛኛውን የእባብ ንክሻ የሚከሰተው ከቤት ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወቅት ሲሆን ገበሬዎች ፣ አዳኞች፣ አሳ አጥማጆች እና ዘላኖች ብዙውን ጊዜ  ተጋላጭ ናቸው። ይህ ጉዳት በብዛት የሚከሰተው እባብ ታዳኙን ለማጥመድ ወይም እራሱን ለመከላከል ሲል (ሲረግጡት ወይም በጣም ሲቀርቡት) የመናደፍ ወይም የመናከስ አደጋን ሲያደርስ ነው።

        መርዛማ የሆኑ የእባብ አይነቶች የትኞቹ ናቸው?

በአለማችን ላይ የተለያዩ መርዛማ የእባብ ዝርያ አይነቶች ሲኖሩ በአፍሪካ በጣም አደገኛ የሚባሉት የእባብ ዝርያዎች እደሚከተለው ተጠቅሰዋል።

  • የምስራቁ አረንጓዴው ማምባ እባብ (Eastern green mamba)
  • ጥቁር ማምባ (Black mamba)
  • የግብፅ ኮብራ (Egyptian Cobra) 
  • የምዕራብ አፍሪካው እፉኝትን (Western African viper) እና
  • የኢትዮጲያ መርዛማ እባቦች አብሪስ (ሶማሊኛ) ፣ አምባራዋ ፣ ሻውሳ እና ማራታን (ኦሮምኛ) እንደ ምሳሌነት መግለፅ ይቻላል።

        የመርዛማ እባብ አካላዊ አወቃቀር ምን ይመስላል?

ማስጠንቀቂያ:- ሁሉም መርዛማ እባቦች ከታች የተቀመጠውን “የመርዛማ እባብ አካላዊ አወቃቀር” መስፈርትን ላያሟሉ ስለሚችሉ በአጠቃላይ እባብ በሚያጋጥምበት ወቅት መርዛማነቱን ለማረጋገጥ ወደ እርሱ መቅረብ አያስፈልግም።  

የመርዛማ እባቦች አካላዊ አወቃቀር

  • ወፍራም እና ተለቅ ያሉ ናቸው
  • ከክብ ዐይኖች ይልቅ የድመት ዐይን የሚመስሉ ሞላላ (Elliptical) ቅርፅ ያላቸው ዐይኖች ይኖሩታል ፡፡
  • አንዳንድ ጊዜ ጅራቱን በማወዛወዝ (Rattling) ድምፅን ይፈጥራል። በዚህን ጊዜ ከአካባቢው መራቅ ያስፈልጋል።
  • ሰፋ ያለ ባለ ሦስት ማዕዘን ራስ አለው ፡፡ 
  • የመርዙ ከረጢት ከመንጋጋው ስር ስለሚሆን አንገት እና  ጭንቅላት አካባቢ በቆዳ የተሸፈነ እባጭ(Bulbous shape) ይኖረዋል ፡፡
  • ሙቀትን ለመለካት የሚጠቀሙበት በዐይን እና በአፍንጫ መካከል ሰርጎድ ያለ ነገር ይኖራቸዋል።  
  • አብዛኛውን ጊዜ ቆዳቸው በብዙ ቀለማት የተዥጎረጎሩ ናቸው። ነገር ግን እንደ ጥቁር ማምባ ያሉ በደቡብ እና በምስራቅ አፍሪካ የሚኖሩ እባቦችን አያጠቃልልም።
  • በውኃ ውስጥ ሙሉ አካሉን ከወለል በላይ በማድረግ ይዋኛል። መርዝ አልባ የሆኑት ግን ጭንቅላታቸውን ብቻ ከውኃው ወለል በላይ በማድረግ ይዋኛሉ።

በድጋሚ ልብ ይበሉ:- ሁሉም መርዛማ እባቦች ከላይ ያሉትን መስፈርቶች አያሟሉም። ስለዚህ ከርቀት መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

        በመርዛማ እባብ መነደፍ ምልክቶች ምንድ ናቸው?

የተለያዩ እባቦች የተለያዩ የመርዛማ ንጥረ-ነገሮች ስላሏቸው ምልክቶቹ ሊለያዩ ሲችሉ በጣም የተለመዱ በመርዛማ እባብ የመነደፍ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።

  • ብዙውን ጊዜ የተነደፉበት ቦታ ላይ ጥንድ የቆዳ መበሳት ቁስል ይታያሉ
  • የተነደፉበት ቦታ አከባቢ መቅላት፣ ማበጥ እና ከባድ ህመም ሊኖር ይችላል
  • ከቁስሉ ደም የቀላቀለ ፈሳሽ መውጣት
  • ከመጠን በላይ የደም መፍሰስ ችግር እና ደም መፍሰስን ለማቆም መቸገር
  • በንክሻው አካባቢ ንፍፊት መውጣት

በተጨማሪም የእባቡ መርዝ ሰውነት ውስጥ ከተሰራጨ የሚከተሉት ምልክቶች ይታያሉ።

  • የሰውነት ማቃጠል
  • ከመጠን በላይ ማላብ እና ዉሃ መጠማት 
  • ትኩሳት
  • ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና ተቅማጥ
  • የመደንዘዝ ስሜት (በተለይም በአፍ አካባቢ)
  • የልብ  ምት መጨመር
  • ለመተንፈስ መቸገር
  • የድካም ስሜት፣ መፍዘዝ እና ዕይታ መደብዘዝ
  • ግር ማለት (Confusion)
  • ራስን መሳት፣ መንቀጥቀጥ (እንደ ሚጥል በሽታ አይነት)
  • የሰውነት አለመታዘዝ ወይም ሽባ መሆን

        ሕክምና

ማንኛውም የእባብ ንክሻ በሚያጋጥምበት ወቅት በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሔድ ሲያስፈልግ በጤና ተቋም ውስጥ ድንገተኛ የጤና እርዳታ እስኪደረግ ድረስ የሚከተሉትን ማድረግ ይገባል።

የመጀመሪያ እርዳታ

  • ለሕክምና ይረዳ ዘንድ ንክሻው በተፈፀመበት ጊዜ እባቡ ምን እንደሚመስል ለማስተዋል መሞከር
  • መርዙ እንዳይሰራጭ በማሰብ ንክሻው የተፈፀመበትን ቦታ በጨርቅ ወይም በፕላስቲክ ለማሰር አለመሞከር (ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል)
  • የንክሻውን ቦታ በሳሙና እና በውሃ ማጠብ
  • የተነከሰውን ቦታ ከልብ ወለል በታች ዝቅ አድርጎ መያዝ እና እዛው ማቆየት
  • አካባቢውን በንፁህ እና ረጠብ ባለ ጨርቅ መሸፈን (እብጠትን እና ህመምን ለመቀነስ ይረዳል)
  • እንደ ቀለበት፣ ሰዓት እና ጥብቅ ያለ ልብስ ያሉ እብጠቱን የሚያግዱ ነገሮችን ማስወገድ
  • መርዙን በመምጠጥ ለማውጣት አይሞክሩ

 

በጤና ተቋም ውስጥ የሚደረጉ ሕክምናዎች 

  • የፀረ-መርዝ መድኃኒት(Anti-venom):-ይህ ዋናው መርዙን የሚያጠፋ መድኃኒት ሲሆን በተናደፈው የእባብ መርዝ ዓይነት እና በምልክቶቹ ክብደት ላይ በመመርኮዝ የሚሰጥ ነው። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ይህ  የፀረ-መርዝ መድኃኒት በታዳጊ አገሮች ላይ በቀላሉ አይገኝም።
  • የቁስል መበከል ወይም ኢንፌክሽን እዳይፈጠር ለመከላከል እና ለማከም ጸረ-ባክቴሪያ ይሰጣል።
  • የህመም  ማስታገሻ መድኃኒቶች ይታዘዛሉ።

        በእባብ መነደፍ ወይም ንክሻን መከላከል

በእባብ የመነደፍ ዕድልን ለመቀነስ የሚከተሉትን ማድረግ ተገቢ ነው።

  • እባብ ሲያጋጥም ለመተናኮል፣ ለመግደል ወይም ወደ እባቡ ለመቅረብ አለመሞከር
  • ጫካ እና ረዣዥም ሣር ባለባቸው አካባቢዎች ሲጓዙ ረዘም ያለ እና ጠንካራ የሆነ የቆዳ ጫማ ማድረግ
  • ለዕይታ አስቸጋሪ በሆኑ ጉድጓዶች እና ቦታዎች ላይ እጅ እና እግርን አለመስደድ
  • እባብ በሚገኙባቸው አካባቢዎች የማገዶ እንጨት እና አለቶችን ሲሰበስቡ መጠንቀቅ
  • ድንጋያማ በሆኑ አካባቢዎች ሲጓዙ ጠንቃቃ እና ንቁ መሆን
  • እባብ እንደ አይጥ ያሉ ታዳኝ የሆኑ እንስሳት በሚገኙባቸው መኖሪያ ቦታዎች አካባቢ የመኖር ዕድሉ ሰፊ ስለሆነ፣ እደነዚህ አይነት እንስሳቶችን ከመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ማራቅ 
  • ወደ ሌላ አካባቢዎች ጉዞ ሲያደርጉ በአካባቢው ስለተለመዱ የእባብ ዓይነቶች አስቀድሞ መረጃ መሰብሰብ 
  • አንዳንድ የእባብ ዝርያዎች ምላሳቸውን በማውጣት እና በጀርባቸው በመንጋለል የሞቱ በማስመሰል ለማሞኘት ይሞክራሉ። ስለዚህ እደዚህ አይነት ሁኔታ ሲገጥም መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
  • የሞተ እባብ የሚረጨውን መርዝ መቆጣጠር ስለማይችል ብዙ መርዝን ወደ ሰውነታችን ሊያስገባ ይችላል። ስለዚህ የሞተ የመሰለ እባብ ሲያጋጥም መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
  • አንዳንድ ጊዜ የተቆረጠ የእባብ ጭንቅላት በቅፅበት በመንቀሳቀስ ንክሻ ሊፈጥር እና መርዙን ሊረጭ ይችላል።

Comments (0)