የምግብ አለርጂ

Eyasu Yebeltal
Jan 9, 2026
undefined

                             የምግብ አለርጂ

የምግብ አለርጂ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚጎዳ እና ከቀላል ምቾት ማጣት እስከ ህይወት አስጊ ምላሾች ሊያደርስ የሚችል ሁኔታ ነው። የምግብ አለርጂ ምን እንደሆነ፣ ምልክቶቹን እንዴት እንደሚያውቁ እና እንዴት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስተዳደር እንደሚቻል መረዳት ለታካሚ እና ለቤተሰብ በጣም አስፈላጊ ነው።

        የምግብ አለርጂ ምንድን ነው?

የምግብ አለርጂ አንድ የተወሰነ ምግብ ከተበላ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሚከሰት የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ስርዓት ምላሽ ነው፡፡ ይህን አለርጂ የሚያስከትል የምግብ ንጥረ-ነገር በአነስተኛ መጠን ብንወስድ እንኳን የምግብ መፍጨት ስርዐታችን፣ የአየር መተላለፊያዎቻችን ወይም ቆዳችን ላይ ምልክቶችን ልናይ እንችላለን። በአንዳንድ ሰዎች ላይ የምግብ አለርጂ ከባድ ምልክቶችን አልፎ “anaphylaxis” በመባል የሚታወቀው ለሕይወት አስጊ የሆነ ምላሽን ሊያስከትል ይችላል፡፡

የምግብ አለርጂ ከ 6 - 8 % የሚሆኑ ከ3 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን እና 3 % የሚሆኑ አዋቂዎች ያጠቃል፡፡ የምግብ አለርጂ ሙሉ በሙሉ ፈውስ ባይኖረውም አብዛኞቹ ህጻናት ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ሰውነታቸው ለምግብ አለርጂ የሚሰጠው ምላሽ እየተሻሻለ ይመጣል፡፡

አንዳንድ የምግብ አለርጂ ምልክቶች በስፋት ከተለመደው የምግብ አለመስማማት (food intolerance) ምልክቶች ጋር ሊምታቱ ቢችሉም የምግብ አለመስማማት የሰውነታችንን የበሽታ መከላከል ስርዐት የማያካትት ቀለል ያለ በሽታ ነው።

        የምግብ አለርጂ ምልክቶች

ለአንዳንድ ሰዎች የምግብ አለርጂ ቀለል ያለ ምቾት መንሳት ሲሆን ለሌሎች ግን ከባድና አልፎ ተርፎም ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል፡፡ የምግብ አለርጂ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ ምግብ ከተመገቡ በኋላ ባሉት ጥቂት ደቂቃዎች እስከ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ሲታዩ የተለመዱት የምግብ አለርጂ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ:-

  • አፍ አካባቢ መደንዘዝ ወይም ማሳከክ
  • የቆዳ ማበጥ፣ ማሳከክ ወይም ችፍ ማለት
  • የከንፈር፣ የፊት፣ የምላስ እና የጉሮሮ ወይም የሌሎች የሰውነት ክፍሎች እብጠት
  • የአፍንጫ መታፈን፣ ሲርሲር የሚል የፉጨት ድምጽ ማውጣት 
  • የመተንፈስ ችግር እና
  • የሆድ ህመም፣ ተቅማጥ፣ ማቅለሽለሽ ወይም ማስመለስ የተለመዱት ምልክቶች ሲሆኑ 

የከባድ አለርጂ ምልክቶች

  • የአየር መተላለፊያዎች ትቦዋች ማበጥ እና መጥበብ
  • የደም ግፊት መቀነስ
  • በጣም ፈጣን የልብ ምት እና
  • ማዞር ፣ ራስ ምታት ወይም ራስን መሳት ናቸው። 

        መች ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለብን?

ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች (በተለይም የከባድ አለርጂ ምልክቶችን) ካስተዋሉ ወደ አቅራቢያዎ የሚገኝ የጤና ተቋም መሄድ ያስፈልግዎታል። ለዚህ በሽታ በአስቸኳይ ሕክምና ካልተደረገ እስከ ሞት ደረጃ የሚያደርስ የጤና እክል ነው።

        የምግብ አለርጂ ለምን ይከሰታል?

የምግብ አለርጂ የሚከሰተው የሰውነትዎ በሽታ የመከላከል ስርዓት አንድ የተወሰነ ምግብ ውስጥ ያለን ንጥረ ነገርን በስህተት እንደ ጎጂ በመለየት ይህን ለመከላከል የሚያጠቃ ፀረ-እንግዳ አካል (IgE) በሚያመርትበት ጊዜ ነው። በቀጣይም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ምግብን በሚመገቡበት ወቅት ይህ ፀረ-እንግዳ አካል እንደ ሂስታሚን ያሉ ንጥረነገሮች ወደ ደምስርዎ እንዲለቀቁ በማድረግ ከላይ የተጠቀሱትን የአለርጂ ምልክቶች ያስከትላሉ።   

አብዛኛዎቹ የምግብ አለርጂዎች የሚከሰቱት በተወሰኑ ምግቦች ውስጥ ባሉ ንጥረነገሮች ሲሆን ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።

  • ለውዝ
  • ዓሳ
  • እንቁላል
  • የላም ወተት
  • ስንዴ
  • አኩሪ አተር

        ለምግብ አለርጂ አጋላጭ ምክንያቶች

ለምግብ አለርጂ የመጋለጥ እድልዎን ሊጨምሩ የሚችሉ ምክንያቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ።

  • ዘር:- በቤተሰብ ተመሳሳይ በሽታ ወይም የአስም በሽታ ያለበት ሰው ካለ
  • ሌሎች አለርጂዎች:- ለአንድ ምግብ  አለርጂ ካለብዎ ለሌላውም አለርጂ የመኖር ዕድሉ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡
  • ዕድሜ:- የምግብ አለርጂ ብዙውን ጊዜ በልጆች ላይ በተለይም አራሶች እና ታዳጊዎች ላይ በብዛት ይታያል፡፡
  • አስም:- አስም እና የምግብ አለርጂ በተለምዶ አብረው ይከሰታሉ፡፡ ይህም በሚሆንበት ሰአት ሁለቱም የምግብ አለርጂ እና የአስም ምልክቶች  የከፋ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡

ለከባድ የምግብ አለርጂ(anaphylaxis) የመጋለጥ እድልዎን ሊጨምሩ የሚችሉ ምክንያቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ።

  • የአስም በሽታ መኖሩ
  • በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ወይም ከዚያ በታች መሆን
  • የምግብ አለርጂ ምልክቶችዎን ለመታከም መዘግየት
  • የቆዳ ማበጥ፣ ማሳከክ ወይም ችፍታ አለመኖር

        የምግብ አለርጂ የሚያስከትለው መዘዞች

  • አናፊላክሲስ ወይም ከባድ ለሕይወት አስጊ የሆነ የአለርጂ ችግር
  • የቆዳ አስም(atopic dermatitis)

        ምርመራ

  • ሙሉ አካላዊ ምርመራ
  • የቆዳ ምርመራ:- በዚህ ምርመራ አለርጂ ያመጣል ተብሎ የታሰበውን የምግብ ንጥረነገር በቆዳዎ ስንጥቅ እንዲገባ በማድረግ ሰውነትዎ የሚሰጠው ምላሽ ይታያል።  
  • የደም ምርመራ:- የበሽታ መከላከያ ስርዓትዎ ለተለያዩ ምግቦች የሚሰጠውን ምላሽ እና ከአለርጂ ጋር የተዛመደ ፀረ እንግዳ አካልን ለመለካት ያስችላል፡፡
  • የማስወድ አመጋገብ (elimination diet):- ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንት አለርጂ ያስከትላሉ ተብሎ  የተጠረጠሩ ምግቦችን እንዲያስወግዱ ይጠየቃሉ ከዚያም እነዚህን ምግቦች አንድ በአንድ ወደ አመጋገብ ሰርዐትዎ ይመልሳሉ፡፡ ይህም ሂደት ምልክቶችን ከአለርጂ አምጪው ምግብ ጋር ለማዛመድ ይረዳል፡፡ ነገርግን ይህ ምርመራ የምግብ አለርጂን ከምግብ አለመስማማት መለየት አይችልም፤ በተጨማሪም ከባድ አለርጂ ካለብዎ ለአደገኛ ሁኔታ ሊያጋልጥ ይችላል።
  • አለርጂ ቀስቃሽ ምግቦችን በመጠን ቀስበቀስ እየጨመሩ መመገብ (oral food challenge):- ይህ ምርመራ በጤና ተቋም የሚደረግ ሲሆን አለርጂ ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ምግቦችን እንዲወስዱ በማድረግ የሰውነትዎ ምላሽ ይታያል።

        ሕክምና

የአለርጂ ምላሽን ለማስወገድ ፍቱን መንገድ አለርጂ ከሚያስከትሉ ምግቦች መራቅ ሲሆን ምንም እንኳን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉ አለርጂ የሚቀሰቅሱ ምግቦችን ባለማወቅ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡

  • ለመለስተኛ የአለርጂ ምላሽ:- የፀረ-ሂስታሚን መድሃኒቶች ምልክቶችን ለመቀነስ ሲረዱ እነዚህ መድኃኒቶች ማሳከክን ወይም የቆዳ እብጠትን ለማስታገስ ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ፀረ-ሂስታሚኖች ከባድ የአለርጂ ምላሽን ማከም አይችሉም፡፡
  • ለከባድ የአለርጂ ምላሽ:- የኢፒነፍሪን መርፌ መውሰድ እና ወደ ድንገተኛ ክፍል መሄድ ሲያስፈልግዎ፣ ይህ መርፌ ለድንገተኛ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል ተመጥኖ የተዘጋጀ ስለሆነ ምልክቶችን በሚያስተውሉበት ወቅት ራስዎን ወይም በአቅራቢያ ያለ ሰው እንዲወጋዎት ተደርጎ በቀላሉ የሚሰራና ታፋዎት ላይ የሚወጉት የመድሃኒት አይነት ነው። ከባድ የአለርጂ በሽታ ካልብዎ ይህ መድሃኒት ፈጽሞ ሊለይዎ አይገባም፤ አጠቃቀሙንም እርስዎም ሆነ አብሮት የሚኖር ሰው ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። 

ይህን መድሁኒት ወሰዱ ማለት ሙሉ ህክምና አገኙ ማለት ስላልሆነ መድሃኒቱን ከወሰዱ በኋላ ወደ ድንገተኛ ክፍል ሄደው ተገቢውን ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል።

        መከላከያ መንገዶች

የምግብ አለርጂን መከላከያ መንገዶች ከምንላቸው ውስጥ:-

  • የለውዝ ምርቶችን ቀደም ብሎ ማስጀመር:- ለልጆች ይህን ይዘት ያላቸውን ምርቶችን ቀደም ብሎ ማስጀመር ወደፊት የአለርጂ ተጋላጭነት ለመቀነስ እንደሚረዳ ይነገራል፡፡ ነገርግን የአለርጂ አምጪ ምግቦችን ለልጅዎ ከማስጀመርዎ በፊት ሐኪም ያማክሩ፡፡ ሆኖም የምግብ አለርጂ ቀድሞውኑ ከተከሰተ የአለርጂ ምላሽን ለመከላከል ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምልክቶችን የሚያስከትሉ ምግቦችን ማወቅ እና ማስወገድ ነው ፡፡

የምግብ አለርጂ እንዳለብዎ ካወቁ የሚከተሉትን እርምጃዎች ይከተሉ

  • የምግብ ይዘቶችን በጥንቃቄ በማንበብ ምን እንደሚበሉ እና እንደሚጠጡ ይወቁ፡፡
  • ከባድ አለርጂ ካለብዎ እና በድንገት ምልክቶቹ ካጋጠምዎት ከሌሎች ሰዎች ጋር መግባባት ሊያስቸግርዎ ስለሚችል የምግብ አለርጂ እንዳለብዎ ሌሎች ቀድመው ያሳውቁ። 
  • ለከባድ የአለርጂ ምላሽ ተጋላጭ ከሆኑ የኢፒነፍሪን (epinephrine) መድሃኒት ሁሌም አብሮት መሆን አለበት፡፡
  • በተቻለ መጠን በቤትዎ ውስጥ የተዘጋጀ ምግብ ይመገቡ
  • ከቤትዎ ውጪ ምግብ ቤቶች ውስጥ ምግብ በሚያዙበት ሰዐት የምግቡን ይዘት ሙሉ በሙሉ በተጣራ ሁኔታ ይወቁ። አለርጂ ለመቀስቀስ አነስተኛ መጠን በቂ ስለሆነ የእርስዎ ምግብ የሚሰራበት እቃ ከአለርጂ ቀስቃሽ ምግቦች ጋር ንክኪ እንደሌለው ያረጋግጡ።
  • ጥርጣሬ በሚኖርዎት ጊዜ አለመመገብን ይምረጡ፡፡ በምግብ ቤቶች እና በድግሶች ላይ አለርጂ ቀስቃሽ ምግቦችን የመመገብ እድል ሰፊ ስለሆነ የምግቡን ይዘት በጥንቃቄ አጣርተው እርግጠኛ መሆን ካልቻሉ አነስተኛ መጠን ራሱ የአለርጂ ምልክቶችን ሊያስከትል ስለሚችል አለመመገብን እንዲመርጡ ይመከራል።
  • ልጅዎ የምግብ አለርጂ ካለበት አብረውት ለሚወሉ አዋቂዎች በሙሉ ስለልጅዎ ሁኔታ እንዲያውቁ እና መውሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች እንዲገነዘቡ ማድረግ ተገቢ ነው። ለልጅዎም የበሽታውን ምልክቶች በአግባቡ እንዲለይ እና እርዳታ እንዲያገኝ ያስገንዝቡ።

Comments (2)

dava dawit
Feb 28, 2026

አፍንጫ ላይ የሚያመጣዉ ነገር አለ እኔ አፍንጫ የ አንድግዜ ይጨምራል ሁልግዜ ይቀንሳል ለዉዝ ወይም water mlon ሀብሀብ ወይም የገብስ ስጋ ስበላ ይነፋል//// እንቁላል ወይም ወተት ስጠቀም ይቀንሳል

dava dawit
Feb 28, 2026

አፍንጫ ላይ የሚያመጣዉ ነገር አለ እኔ አፍንጫ የ አንድግዜ ይጨምራል ሁልግዜ ይቀንሳል ለዉዝ ወይም water mlon ሀብሀብ ወይም የገብስ ስጋ ስበላ ይነፋል//// እንቁላል ወይም ወተት ስጠቀም ይቀንሳል