ክትባት ምንድን ነው?

Elsabet Azezew
Jan 10, 2026
undefined

                                            ክትባት ምንድን ነው?

ክትባት በሽታ አምጪ የሚባሉ ተሕዋስያንን በማዳከም ወይም በመግደል አለያም መርዙን በመውሰድና ፕሮቲኑን በማዳቀል የሚሠራ ነው። 

የክትባት ዋና ሥራው በሽታ ከመከሠቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል ሲሆን ሰውነትዎ ለተወሰኑ ኢንፌክሽኖች እንዳይጋለጥ የሰውነትዎን ተፈጥሯዊ የበሽታ የመከላከል አቅምን (Immune system) ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን ያደርጋል።

 

     የክትባት ዓይነቶች

  1. ንቁ ክትባት (Active immunization)

          ይህ ክትባት ሰውነታችን የራሱን የሆነ የበሽታ መከላከል ዐቅም ሥርዓት እንዲገነባ የሚያደርግ ነው። 

  2. ንቁ ያልሆነ ክትባት (Passive immunization)

          ይህ ደግሞ ቀድሞውኑ የተመረተውን በሽታ መከላከል ወይም አንቲቦዲ በመስጠት ሰውነታችን  ለጊዜው ከበሽታው እንዲጠበቅ ያደርጋል።

                           ልጅዎትን ለምን ያስከትባሉ? (Pediatric vaccination)

    ክትባት በተለይም ለሕፃናት ምን ጠቀሜታ አለው?

ሕፃናት እንደተወለዱ ለአካባቢያቸው አዲስ ስለሚሆኑ ለብዙ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን የተጋለጡ ናቸው።

በሽታ እንዳይበረታባቸውም የሰውነታቸውን በሽታ የመከላከል ዐቅም ማሳደግ ይገባል፡፡ ስለዚህ ልጅዎን ክትባት  ማስከተብ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።

የሕፃናት ክትባት አሰጣጥ ፕሮግራም በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ የራሱ የሆነ የተዘጋጀ መመሪያ አለው። 

በዚህም መሠረት በጤና ተቋማት ውስጥ የሚከተሉት የክትባት ዓይነቶች ለልጆች ይሰጣሉ።

  • ሕፃናት እንደተወለዱ ቢሲጂ (BCG) ክትባት ይሰጣል
  • በ 6 ሳምንት (45 ቀን)   ፖሊዮ፣ ፔንታቫለንት፣ ፒሲቪ እና ሮታ ( OPV,PCV,Penta,Rota) ክትባቶች ይሰጣሉ
  • በ 10 ሳምንት ፡ በ6 ሳምንት ከሚሰጠው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
  • በ14 ሳምንት ከ 6 ፡ ሳምንት ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ነገር ግን ሮታ አይሰጥም፡፡
  • በ 9 ወሩ ፡ የኩፍኝ ክትባት እና ቪታሚን ኤ ይሰጣል
  • ቪታሚን ኤ በየ 6 ወሩ እስከ አምስት ዓመታቸው ድረስ ክትባቱን ቢወስዱ ይመረጣል።

በተለያዩ ጊዜያት ወረርሽኞች ሲከሠቱ ለምሳሌ እንደ ማጅራት ገትር፣ ፖሊዮ፣ ኩፍኝ እና ትክትክ(pertussis)፤ በዓለምና በሀገር አቀፍ ደረጃ  እነዚህን በሽታዎች ለመቆጣጠር ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በጅምላ ለሕፃናት ክትባት ይሰጣል።

 

                         ክትባቱ የትኛዎቹን በሽታዎች ይከላከላል?

  • በቲቢ  የሚመጣ ማጅራት ገትር፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ የተሰራጨ ቲቢ
  • ፖሊዮ (poliomyelitis)
  • ዘጌ አናዳ (ዲፍቴሪያ ወይም ከባድ የጉሮሮ ኢንፌክሽን)
  • ትክትክ  እና ከባድ ሳል
  • መንጋጋ ቆልፍ (tetanus)
  • ሄፓታይተስ ቢ (የጉበት ቫይረስ ኢንፌክሽን)
  • ኢንፍሎዌንዛ
  • ሳንባ ምች (Pneumonia)
  • ማጅራት ገትር (meningitis)
  • ኩፍኝ (measles)
  • ተቅማጥ በሽታ

          ቫይታሚን ኤ ለምን ይጠቅማል?

  • ለሕፃናት በሽታ የመከላከል ዐቅማቸውን ይጨምራል፡፡
  • ለጥርስ፣ ለአጥንትና ለቆዳ ዕድገት ይጠቅማል፡፡
  •  ለዐይን ጥራትና ጤንነት አስፈላጊ ነው፡፡

 

                      ክትባት የጎንዮሽ ጉዳት አለው?

  • በአጠቃላይ ክትባቶቹ ጤና ላይ የሚያመጡት ከባድ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ የለም።
  • በሀገራችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት በየዓመቱ ክትባቱን ያለምንም የጎንዮሽ ጉዳት ይወስዳሉ፡፡ 

በጣም የተለመዱት የጎንዮሽ ጉዳቶች ቀላል የሚባሉ ናቸው። እነዚህም

  • ክትባት በወሰደበት ቦታ ላይ የሕመም ስሜት ወይም እብጠት፤
  •  እንደ ንፍፊት እብጠት ፤
  •  ቀለል ያለ ትኩሳት ፣ መነጫነጭ ናቸው፡፡

እነዚህም ችግሮች በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠፋሉ።

            ለጎንዮሽ ጉዳቱ ምን ማድረግ ይገባል?

  • ልጅዎን ምግብ መስጠት ይቀጥሉ ፣ ጡትም ከሆነ በደንብ ያጥቡት ፤
  • ሕመሙን ለማስታገስ ክትባቱን በወሰደበት አካባቢ ላይ ቀዝቀዝ ወይም ረጠብ ያለ ጨርቅ ማድረግ፡፡ 
  • አለመረበሽ

           የጎንዮሽ ጉዳቱ እየባሰ ከመጣስ?

  • ክትባት የተሰጠበት አካባቢ ተለቅ ያለ መግል መቋጠር ከጀመረ 
  • ትኩሳቱ እየጨመረ ከመጣ
  • ከወትሮ የተለየ ነገር ልጅዎ ላይ ካስተዋሉ ፈጥነው ወደ ጤና ተቋም መውሰድ ይኖርቦታል። 

                     ክትባት የማይሰጥባቸው ሁኔታዎች ምንድናቸው?

  •  ከዚህ በፊት በነበረው ክትባት ላይ ከፍተኛ የአለርጂ ችግር ከአጋጠመ
  •  ልጅዎ በሽታ የመከላከል ዐቅምን የሚያዳክም በሽታ ካለበት

ልብ ይበሉ :- በሽታ የመከላከል ዐቅምን የሚያዳክም በሽታ ያለባቸው ሕፃናት መከተብ የሌለባቸው ተሕዋሲያን በማዳከም (live attenuated vaccines) የተሠራ ክትባትን ብቻ ነው፡፡  

 

ከዚህ ቀደም ክትባት መውሰድ ላልጀመረ፣ የታቀደለትን የክትባት መጠን  ወይም ክትባት ተከታትሎ ላላጠናቀቀ ሕፃን ልጅስ ምን መደረግ አለበት? (catch up vaccination)

  • እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚገጥምበት ሰዓት ሕፃኑን ወደ ጤና ጣቢያ በመውሰድ ዕድሜውን መሠረት ያደረገ ሕክምና፤ የሚቻል ከሆነና የክትባቱ ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው ተብሎ ከታሰበ ክትባቱን እንዲጀምር፣ እንዲቀጥል እና እንዲጨርስ ይደረጋል።

                    ክትባትና ኦቲዝም የሚያገናኛቸው ነገር አለ?

  • እየተደረጉ ባሉ ሳይንሳዊ ጥናቶች እና ምርምሮች መሠረት በክትባትና እና በኦቲዝም መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለ ለመረዳት ተችሏል፡፡

                   አዳዲስ የተጨመሩ የክትባት ዓይነቶች እነማን ናቸው?

  • ሁለት አዳዲስ ክትባቶች በመደበኛ የክትባት ፕሮግራም ውስጥ ተካተዋል።

           1. ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ (H.P.V) 

           2. ዙር ሁለት የኩፍኝ ክትባት 

  • መርሐ ግብሩም በየዓመቱ ከ 3 ሚሊዮን በላይ ልጆችን የመከተብ ዕቅድ አካቷል።

 1. የኤች.ፒ.ቪ (H.P.V)

  • ሁሉም የኤች.ፒ.ቪ ክትባቶች የማሕፀን በር ካንሰርን ከሚያመጡ ኤች.ፒ.ቪ 16 እና 18 ቫይረስ ኢንፌክሽንን ይከላከላሉ።
  • በአጠቃላይ  የኤች.ፒ.ቪ (H.P.V) ክትባቶች የሚከተሉትን በሽታዎች ይከላከላሉ።

          - የማሕፀን በር ካንሰርን 70% 

          - የፊንጢጣ ካንሰርን   80%  

         - የሴት ብልት ካንሰርን 60% እና

         - የአፍና የጉሮሮ ካንሰርን 90%  ያህል በመከላከል ውጤታማ ናቸው።

      አሰጣጡስ እንዴት ነው?

  • በሀገራችን ከ 9 - 14 ዓመት የሆናቸው ሴት ተማሪዎች የኤች.ፒ.ቪ ክትባት በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በጤና ተቋማት ውስጥ ይሰጣቸዋል። 
  • ክትባቱ በሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛው ዙር  የመጀመሪያው ክትባት ከተሰጠ ከ 6 - 12 ወራት በኋላ ይሰጣል።   

2. የኩፍኝ ክትባት ዙር ሁለት

  • ከላይ እንደተገለፀው ሕፃናት በ 9 ወራቸው ዙር አንድ የኩፍኝ ክትባት ይወስዳሉ።
  • ከ 3 ዓመት ወዲህ ዙር ሁለት የኩፍኝ ክትባት ተጀምሯል። ሁለተኛው የኩፍኝ ክትባት የመጀመሪያው ክትባት ከተሰጠ ቢያንስ ከ 4 ሳምንት በኋላ ይሰጣል።
  • በአገራችን ክትባት ፕሮግራም መሠረት ሁለተኛው ዙር የኩፍኝ ክትባት ሕፃናት 15 ወር  ሲሞላቸው እንዲሰጣቸው ይመክራል፡፡

Comments (0)