ትኩረት የማጣት እና የመረጋጋት ችግር (Attention Deficit hyperactivity / ADHD)

Al Amin Worku
Jan 15, 2026
undefined

ትኩረት የማጣት እና የመረጋጋት ችግር (Attention Deficit hyperactivity / ADHD)

ትኩረት የማጣት እና የመረጋጋት ችግር (Attention Deficit hyperactivity / ADHD) የሚባለው ከተለመደው የህፃናት ችኩልነት እና አለመረጋጋት በላቀ መልኩ የመንቀዥቀዥ እና ችኩልነትን የሚያስከትል የአእምሮ ጤና መታወክ ነው ፡፡ 

የ ኤዲ ኤች ዲ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ትኩረታቸውን በአንድ ሥራ ላይ በማተኮር ረዘም ጊዜ ለማሳለፍ ይቸገራሉ፡፡ አንድ ነገር ጀምረው አፍታም ሳይቆዩ ሌላ ነገር ሀሳባቸውን ይሰርቀዋል። 

ይህ በሽታ አብዛኛውን ጊዜ ከ ሶስት እስከ 6 አመት ይሉ ልጆች ላይ የሚከሰት የስነ ልቦና ችግር ሲሆን እነዚህ ህፃናት ካደጉ በኃላም ምልክቶቹ በተለያዩ የቀን ተቀን ህይወታቸው ላይ ሊንፀባረቅ ይችላል። እድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ህፃናት መካከል ከ5 እስከ 10% የሚሆኑት በዚህ በሽታ የሚጠቁ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ወንዶቹ ከሴቶቹ ጋር ሲወዳደሩ በበሽታው የመጠቃት እድላቸው ከ 3 እጥፍ በላይ ይጨምራል።

ይህ በሽታ በምን ምክንያት እንደሚመጣ ባይታወቅም ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአምሮአችን ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች ማነስ በሽታውን ሊያመጥ ይችላሉ። በተጨማሪም በቤተሰብ ውስጥ በዚህ በሽታ የተጠቃ ሰው ካለ ለበሽታው የመጋለጥ እድሉ ይጨምራል።

የበሽታው ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?

ሁላችንም እንደምናውቀው ከአዋቂዎች ይልቅ ህፃናት የመሯሯጥ እና የመጫወት ተፈጥሮአዊ ፀባይ አላቸው። ማንኛውም ጤናማ ህፃን ከእድሜ እኩዮቹ ጋር ይጫወታል፤ እንደ አዋቂዎች ትኩረቱን ሰብስቦ ለረጅም ሰዐት ስራ ላይ ማሳለፍ ይቸገራል፤ ቤት ውስጥም ሆነ ትምህርት ቤት ውስጥ ሊያስቸግር ይችላል። በ ኤዲ ኤች ዲ በሽታ የተጠቁ ህፃናት ግን ከጤነኛ ህፃናት በጣም በተለይ መልኩ እነዚህ ምልክቶች ገነው ይታይባቸዋል።

  • ሃሳባቸውን በትምህርት፣ በቤት ስራ እንዲሁም በጨዋታ ላይ ሳይቀር ለመሰብሰብ ይቸገራሉ። በዚህ ምክንያት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ 20 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት በትምህርታቸው ደካማ ይሆናሉ።
  • ነገሮችን ቶሎ ይረሳሉ።
  • በቀላሉ ሃሳባቸው ይሰረቃል።
  • ዝንጉ ናቸው።
  • ለደቂቃ ተረጋግተው መቀመጥ አይችሉም።
  • ሌላ ሰው ሲያወራ በመሃል አቋርጠው ሊያወሩ እና ሊረብሹ ይችላሉ።
  • ለጨዋታም ሆነ ለማንኛውም ነገር ተራ መጠበቅ አይወዱም፤ አይችሉም። 
  • ሁሌም ንቁ ናቸው።
  • በቀላሉ ይናደዳሉ፤ ይበሳጫሉ።
  • እያደጉ ሲመጡ ደግሞ ለአደንዣዥ ሱስ የተጋለጡ ይሆናሉ። 

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች በትምህርት ቤት፣ ከጓደኞቻቸው ጋራ ሲጫወቱ እንዲሁም በቤት ውስጥ ይታያል። በዚህ ምክንያት በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ለማምጣት ይቸገራሉ። እንዲሁም ከጓደኞቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት አይኖራቸውም።

እዚህ ላይ መረዳት ያለብን ነገር እነዚህ ምልክቶች እንደ በሽታ የሚቆጠሩት የሚከተሉት ነገሮች ከተሟሉ ነው። እነዚህም

  • ምልክቶቹ ቢያንስ ላለፉት ስድስት ወራት መታየት አለባቸው 
  • ምልክቶቹ ሲጀምሩ የህፃኑ እድሜ ከ ሰባት አመት በታች መሆን
  • ምልክቶቹ ቢያንስ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆነ ቦታ መታየት ይጠበቅበታል። ለምሳሌ ህፃኑ ቤት ውስጥ ብቻ ከሆነ ምልክቶቹን የሚያሳየው ኤዲ ኤች ዲ ለማለት ያዳግታል። በተጨማሪም ምልክቶቹ በትምህርቱ ላይ እና በማህበራዊ ህይወቱ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር አለበት።
  • ህፃኑ እነዚህ ምልክቶች ሊያሳይ የሚችል ሌላ የስነ ልቦና በሽታ እንደሌለበት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

በበሽታው ከተጠቁ ህፃናት ውስጥ 60% የሚሆኑት ካደጉ በኃላም ምልክቶቹን ሊያሳዩ ይችላሉ። ትምህርታቸው እና ስራቸው ላይ ሃሳባቸውን መሰብሰብ ስለማይችሉ ውጤታማ ለመሆን ይቸገራሉ። በተጨማሪም ሰዐታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ይቸገራሉ፤ ነገሮችን በቀላሉ ይረሳሉ እንዲሁም ትዕግስት የላቸውም። ነገር ግን እንደአጠቃላይ እድሜ በጨማረ ቁጥር የበሽታው ክብደት እየቀነሰ የመሄድ አዝማሚያ አሳይቷል። 

የ ኤዲ ኤች ዲ በሽታ አይነቶች 

ሶስት አይነት የ ኤዲ ኤች ዲ አይነቶች አሉ። 

  1. በዋነኝነት ትኩረት ለመሰብሰብ የሚቸገሩ
  2. በዋነኝነት ለመረጋጋት የሚቸገሩ
  3. ትኩረት ለመሰብሰብም ሆነ ነገሮችን ተረጋግተው ለመስራት የሚቸገሩ ናቸው።

ምንም እንኳን አብዛኞቹ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ትኩረት ለመሰብሰብም ሆነ ነገሮችን ተረጋግተው ለመስራት የሚቸገሩ ቢሆንም በሴቶች ላይ በስፋት የሚታየው በዋነኝነት ትኩረት ለመሰብሰብ መቸገር ነው። እነዚህ ህፃናት ክፍል ውስጥ ስለማይበጠብጡ በሽታቸው ሳይታወቅላቸው ብዙ አመት ሊኖሩ ይችላሉ።

ህክምናውስ ምንድን ነው?

በ ኤዲ ኤች ዲ የተጠቁ ሰዎች ትክክለኛውን የህክምና ክትትል ማግኘታቸው በመጠኑም ቢሆን ምልክቶቻቸውን ለመቀነስ ይረዳቸዋል። ከወላጆቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው እንዲሁም ከአስተማሪዎቻቸው ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲመሰርቱ እና በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ይረዳቸዋል።

በዋነኝነት የበሽታው ህክምና አነቃቂ መድኃኒቶች ሲሆኑ የምክር አገልግሎት እና የተለያዩ የሳይኮቴራፒ አይነቶች እንደአስፈላጊነታቸው ሊጨመሩ ይችላሉ። 

ከአነቃቂ መድኃኒቶች ውስጥ በምዕራቡ አለም ሰፊው የሚታወቀው ሜታይልፌኒዴት (Methylphenidate) የሚባለው መድኃኒት ሲሆን በሃገራችን ውስጥ በስፋት አይገኝም። ስለዚህም በምክር አገልግሎች እና ሀገራችን ላይ ባሉ ሌሎች ንዴትን ለመቀነስ የሚረዱ መድኃኒቶችን በመስጠት ምልክቶቹን ለመቆጣጠር ሙከራ ይደረጋል። ለምሳሌ

  • የቀን ውሎ እቅድ በማውጣት መምራት
  • ሃሳብ ሊከፋፍሉ የሚችሉ ነገሮችን መቀነስ
  • ሃሳብን ሊይዙ የሚችሉ የጥናት መንገዶችን መጠቀም
  • በስራ ወይም ጥናት መካከል የእረፍት ሰዐት ማዘጋጀት
  • ህፃኑ የሚወደውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለይቶ ማወቅ እና እንዲሳተፉ መፍቀድ

Comments (2)

Girma Berihun
Jan 25, 2026

እኔ አሁን 35 አመቴ ነው ግን ከላይ የጠቀስካቸው ችግሮች አብዛኛዎቹ ይታዩብኛል።ትምህርቴን በእልህ ጨረስኩት ግን የስራ አለም ላይ በጣም እየተቸገርኩ ነዉ።አንድ ቦታ ላይ ብዙ ሰአት አልቆይም ;በቀላሉ ትኩረቴ ይሰረቃል:በቀላሉ ይከፋኛል:ውስጥ ትግስት ማጣት ይታይብኛል:ቶሎ መበሳጨት:ይደብረኛል

Girma undefined
Jan 25, 2026

መፍትሔ ካለው መላ በሉኝ እባካችሁ

Seyfura -_
Jan 23, 2026

i want to take you ,Please .