አስጊ የአለርጂ ችግር (Anaphylaxis)

Biruh Tesfaye
Jan 16, 2026
undefined

አስጊ የአለርጂ ችግር ወይም አናፊላክሲስ ምንድነው? 

ሰዎች አለርጂ ለሆኑባቸው ነገሮች (ለምሳሌ ምግብ፣ መድኃኒት ወይም በንብ መነደፍ) ሲጋለጡ የሚከሰት ከባድ፣ ለሕይወት አስጊ የሆኑ ምልክቶችን የያዘ የአለርጂ ችግር ነው። የተለመዱ የአለርጂ ምልክቶች ቀላል እና ለጤና የማያሰጉ ቢሆኑም አንዳንድ ጊዜ ግን እነዚህ ምልክቶች በፍጥነት በመከሰት፣ ትንፋሽን እና የልብ ምትን በማገድ፣ እስከ ሞት ሊያደርሱ ይችላሉ። 

አስጊ የአለርጂ ችግር እንዴት ይከሰታል?

አብዛኛውን ጊዜ አስጊ አለርጂ ችግር የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓት ለሰውነታችን እንግዳ ለሆኑ ነገሮች ከተገቢው በላይ ምላሽ በሚሰጥበት ጊዜ ይፈጠራል። ለአንድ ነገር አለርጂክ ሲሆኑ፣ የሰውነትዎ በሽታ የመከላከል ሥርዓት እንደ ሂስታሚን (Histamine) ያሉ ኬሚካሎችን በከፍተኛ ሁኔታ በመልቀቅ ከመጠን በላይ የሆነ ምላሽ ይሰጣል። ይህ የአለርጂ ድግግሞሽ በጨመረ ቁጥር ምልክቶቹ እየከበዱ የመሔድ ዕድላቸው የሰፋ ነው።

አንዳንድ ሰዎች ለዚህ ችግር የመጋለጥ ዕድላቸው የበለጠ ከፍተኛ ነው። አለርጂ፣ አስም ወይም ስር የሰደደ የሳንባ በሽታ

ካለብዎ እና በቤተሰብዎ ውስጥ የአስጊ የአለርጂ ችግር ካለ፣ የእርስዎም የመጋለጥ ዕድል ከፍተኛ ይሆናል። ቀደም ሲል አናፊላክሲስ አጋጥሞዎት የሚያውቅ ከሆነ፣ በድጋሚ ሌላ የአናፊላክሲስ ችግር የመከሰት ዕድሉም ይጨምራል። በተጨማሪም ሌሎች የልብ በሽታ እና ነጭ የደም ሕዋስ መዛባት የሚያስከትሉ ህመሞች የአለርጂ ችግርን ሊያስከትሉ ይችላሉ። 

የተለመዱ የአለርጂ ችግር የሚያመጡ ነገሮች ምንድናቸው?

  • የምግብ አለርጂ፤ ምግብ ልጆች ላይ የተለመደ የአለርጂ መንስኤ ሲሆን ለውዝ ወይም የለውዝ ቅቤ፣ ዓሳ፣ የላም ወተት፣ ስንዴ እና አኩሪ አተር እንደምሳሌ መጠቀስ ይችላሉ። 
  • መድኃኒቶች፤ ለምሳሌ የኢንፌክሽን መከላከያዎች (Penicillin, cephalosporin) እና የህመም ማስታገሻዎች(Aspirin, ibuprofen)
  • በነፍሳት መነደፍ፤ ለምሳሌ ንብ ፣ ተርብ እና ጉንዳን
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፤ አንዳንድ ሰዎች ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የአለርጂ ችግርን ሊቀሰቅስ ይችላል።
  • ምንም እንኳን ያልተለመደ ቢሆንም የአየር ብክለት፣ ለቀዝቃዛ ዉኃ እና አየር መጋለጥ የአለርጂ ችግር ሊቀሰቅስ ይችላል።  

ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? 

አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ምልክቶች ሰዎች አለርጂ ለሆነባቸው ነገሮች ከተጋለጡ በኋላ በሰከንዶች ወይም በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ይከሰታሉ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በግማሽ ሰዓት ወይም ከዚያም በላይ ቆይተው ሊከሰቱ ይችላል። እነዚህም

  • ቆዳ ላይ ሽፍታ መውጣት፣ መቆጣት፣ መቅላት እና ማሳከክ   
  • ድካም፣ የማዞር ስሜት፣የልብ ምት መጨመር፤ ማላብ፣ የደም ግፊት መቀነስ 
  • የአየር ቱቦዎች መጥበብ፣ ምላስ እና ጉሮሮ አካባቢ ማበጥ- ይህም ለመተንፈስ መቸገር፣ ሳል እና የመታነቅ ስሜትን ያስከትላል።
  • የትንፋሽ ድምፅ መቀየር ( ሲር ሲር የሚል ድምፅ ሊሰማ ይችላል) 
  • የመዋጥ ችግር
  • የሆድ ህመም፣ ማቅለሽለሽ ፣ ማስታወክ ወይም ተቅማጥ እና
  • መጨነቅ፣ ንቃተ ህሊና መቀነስ ወይም ራስን መሳት ናቸው።

ምርመራው ምንድን ነው?

የጤና ባለሙያው ስለክስተቱ በመጠየቅ እና አካላዊ ምርመራ በማድረግ ስለችግሩ መረዳት ይችላል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም አለርጂ የሆኑብን ነገሮች ከነበሩ ለምሳሌ ምግብ፣ መድኃኒት፣ የነፍሳት ንክሻ፣ ለጤና ባለሙያ መንገር ያስፈልጋል። 

በተጨማሪም የደም እና የቆዳ ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ። የቆዳ ምርመራ በጣም ጥቂት የሆነ የአለርጂ መንስኤን በቆዳዎ ላይ በማድረግ ምላሽ መኖሩን ማረጋገጥን ያካትታል። የደም ምርመራ ደግሞ የጤና ባለሙያ በእጅዎ ላይ ካለ የደም ስር ናሙና በመውሰድ አለርጂን የሚያስከትሉ ንጥረ ነገሮችን በቤተ ሙከራ ይለያል።

ሕክምናውስ ምንድነው?

አስጊ የአለርጂክ ምልክቶች በሚገጥሙበት ጊዜ ለእርዳታ መጣራት እና በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሔድ የጤና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል። ምክንያቱም እነዚህ ምልክቶች ትንፋሽ እና የደም ዝውውርን በማገድ ለሞት ሊያደርሱ ስለሚችሉ ነው።  

በጤና ተቋም ውስጥ ድንገተኛ የጤና እርዳታ ይደረጋል። እነዚህም የኦክስጅን ድጋፍ መስጠት እና የአለርጂውን ምልክቶች የሚቀንሱ መድኃኒቶች(Epinephrine, antihistamines) በደም ሥር መስጥዕትን ያካትታሉ። በተጨማሪም በአፍ የሚነፉ መተንፈስን የሚያቀሉ መድኃኒቶች(beta-agonists) ሊሰጡ ይችላሉ።  

ወደፊት ተመሳሳይ ችግር እዳይከሰት ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው የአለርጂ መንስኤዎችን ማስወገድ ነው። አንዳንድ ጊዜ በአደጉ አገራት ላይ የአለርጂ ችግር የአሉባቸው ሰዎች አለርጂ ምልክቶች ሲከሰቱ ራሳቸውን የሚክሙባቸው መድኃኒቶች (Auto-injector epinephrine) እዲኖሯቸው ይደረጋል።

መከላከያ መንገዶች ምንድናቸው? 

  • ዘላቂ የመከላከያ መፍትሔ የሚሆነው አለርጂ የሆኑብን ነገሮችን ለይቶ ማወቅ እና ማስወገድ ነው
  • ከዚህ ቀደም የታወቀ የመድኃኒት አለርጂ ካለብዎ የሕክምና ክትትል ለሚያደርግልዎ የጤና ባለሙያ ማሳወቅ ይገባል
  • አለርጂ የሆንብዎትን ምግብ መጠንቀቅ፤ በተለይም ከቤት ውጭ በሚመገቡበት ወቅት የምግቡን ይዘት ማጣራት ያስፈልጋል።
  • የምግብ አለርጂ ካለብዎ የሚገዟቸውንና የሚመገቧቸውን ምግቦች ይዘት ሁልጊዜ ያንብቡ።
  • የነፍሳት ንክሻን መከላከል፣ ረዘም ያሉ ሙሉ ልብሶችን መልበስ፣ ነፍሳትን አለመተናኮል 
  • የአለርጂ ችግር ካለብዎት ስለምልክቶቹ በደንብ ማወቅ አፋጣኝ የጤና እርዳታ ለማግኘት ጠቃሚ ያደርገዋል።
  • ከተቻለ አለርጂ የሆኑብንን መድኃኒቶች ወይም ንጥረ ነገሮችን የሚያመለክት አምባር ወይም የአንገት ሐብል ማድረግ። 
  • ከጤና ባለሙያ ጋር ምክክር በማድረግ የአደጋ ጊዜ መድኃኒቶችን የያዘ ቋት ማዘጋጀት ጠቃሚ ይሆናል። 

Comments (0)