የጥርስ ማንቀርጨጭ (Bruxism)
ይህ ሁኔታ ካለብዎ በንቃተ ህሊና ጥርስዎትን በተደጋጋሚ መንከስ (awake bruxism) ወይም በእንቅልፍ ወቅት ጥርስዎትን ማፏጨት እና መንከስ (sleep bruxism) ይኖርዎታል። ይህ እክል በማንኛውም የእድሜ ክልል ሲከሰት ከ15 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት እና ከ 8 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑ አዋቂዎች ላይ ይታያል።
መለስተኛ የጥርስ ማንቀርጨጭ ህክምና አያስፈልገው ይሆናል፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ሰዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰት እና ከባድ ከሆነ ወደ መንጋጋ ጡንቻ ህመም ፣ ራስ ምታት ፣ የጥርስ መቸርቸፍ እና ሌሎች የጤና እክሎች ሊያስከትል ስለሚችል የጤና ባለሙያ ማማከር ተገቢ ነው፡፡
ውስብስብ ችግሮች እስኪከሰቱ ድረስ የጥርስ ማንቀርጨጭ እንዳለብዎት ላያውቁ ስለሚችሉ ምልክቶቹን በአግባቡ መረዳት እና መደበኛ የጥርስ ህክምና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
የጥርስ ማንቀርጨጭ ምልክቶች
- የጥርስ ማፏጨት፤ ይህም አብሮት የሚተኛውን ሰው እስከመቀስቀስ ሊደርስ ይችላል
- የጥርስ መቸርቸፍ፣ መሰንጠቅ ወይም መነቃነቅ
- የጥርስ የላይኛው ልባስ (enamel) መገለጥ
- የጥርስ ህመም
- የደከሙ ወይም የጠበቁ የመንጋጋ ጡንቻዎች (ሙሉ በሙሉ የማይከፈት ወይም የማይዘጋ የተቆለፈ መንጋጋ ሊኖር ይችላል)
- የአንገት ወይም የፊት ጡንቻዎች ህመም
- የጆሮ ህመም
- ራስ ምታት
- በጉንጭዎ ውስጠኛው ክፍል ላይ በተደጋጋሚ በማኘክ ምክንያት የሚመጣ ጉዳት
- በቂ እንቅልፍ አለማግኘት
መች ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለብኝ?
ከላይ ከተዘረዘሩት ምልክቶች መካከል አንዱ ካለብዎት በተጨማሪም ስለ ጥርስዎ ወይም መንጋጋዎ ሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮች ካሉዎት ሀኪም ያማክሩ፡፡
የጥርስ ማንቀርጨጭ በምን ምክንያት ይመጣል?
የጥርስ ማንቀርጨጭ በምን ምክንያት እንደሚመጣ ሙሉ በሙሉ አይታወቅም ነገርግን በአካላዊ ፣ በስነልቦናዊ እና የዘረመል ተፅኖዎች ጥምረት ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡
የንቃት ጥርስ ማንቀርጨጭ እንደ ጭንቀት ፣ ፍርሃት ፣ ቁጣ ፣ ብስጭት ወይም ውጥረት ካሉ ስሜቶች ጋር ሲጣመር ፤ በጥልቅ ትኩረት ጊዜ የምናዳብረው ልማድም ሊሆን ይችላል
በእንቅልፍ ወቅት ጥርስ ማንቀርጨጭ ከእንቅልፍ ጋር የተዛመደ የእንቅስቃሴ እክል እንደሆነ ይታመናል፡፡
ለጥርስ ማንቀርጨጭ አጋላጭ ምክንያቶች
- ስነልቦናዊ ውጥረት፣ ጭንቀት፣ ቁጣ እና ብስጭት
- ዕድሜ የጥርስ ማፏጨት በልጆች ላይ የተለመደ ነው ፣ ይህም ብዙውን ጊዜ በአዋቂነት ዕድሜያቸው ይጠፋል።
- የስብዕና ዓይነት ጠበኛ ፣ ተፎካካሪ ወይም ግልፍተኛ የሆነን የባህርይ አይነት
- መድሃኒቶች እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች አንዳንድ የፀረ-ድብርት መድኃኒቶች፣ ትምባሆ ማጨስ ፣ ካፌይን ያላቸውን መጠጦች ፣ አልኮል፣ ጫት ወይም አደንዛዥ እፆችን መጠቀም
- ዘር የጥርስ ማንቀርጨጭ ያለበት የቤተሰብ አባል ካለዎ እርሶም ሊኖርብዎት ይችላል
- ሌሎች የጤና እክሎች እንደ ፓርኪንሰን በሽታ ፣ የጨጓራ አሲድ ወደላይ መመለስ(GERD) ፣ የሚጥል በሽታ (epilepsy)፣ በእንቅልፍ ልብ ትንፋሽ ማጠር(sleep apnea)፣ ትኩረት የማጣት እና የመረጋጋት ችግር (ADHD)
ለጥርስ ማንቀርጨጭ የሚደረግ ምርመራ
የጥርስ ማንቀርጨጭ እንዳለብዎት ከተገመተ
- ከሃኪም ጋር ውይይት
- የተሟላ አካላዊ ምርመራ እና
- አልፎ አልፎ የራጅ ምርመራ ያስፈልግዎታል።
የጥርስ ማንቀርጨጭ ከእንቅልፍ ጋር በተያያዙ እክሎች ወይም በአእምሮ መታወክ ምክንያት የመጣ ከሆነ የስነልቦና ሃኪም እንዲያናግሩ ይመከራል።
የጥርስ ማንቀርጨጭ ሕክምና
አብዛኛውን ጊዜ ሕክምና አስፈላጊ አይደለም። ብዙ ልጆች እያደጉ ሲመጡ ያለ ህክምና ጥርስ ማንቀርጨጫቸው እየቆመ ይመጣል ፣ አዋቂዎችም ህክምና እስከሚያስፈልግ ድረስ የባሰ የጥርስ ማንቀርጨጭ አይኖራቸውም። ሆኖም ችግሩ ከባድ ከሆነ አማራጮቹ የተወሰኑ የጥርስ ህክምናዎች፣ የምክር አገልግሎቶች እና መድሃኒቶችን የበለጠ የጥርስ መጎዳትን ለመከላከል እና የመንጋጋ ህመምን ለማስታገስ ይረዳሉ፡፡
የጥርስ ህክምናዎች
ምንም እንኳን እነዚህ ዘዴዎች የጥርስ ማንቀርጨጭን ባያስቆሙም የሚያስከትለውን የጥርስ ህመም እና መቸርቸፍ ለመከላከል ይረዳል።
- የጥርስ እና የአፍ ሽፋኖች (splints and mouth guards) እነዚህ ጥርስን በመፍጨት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለማስወገድ ጥርስን እንዲነጣጥሉ ተደርገው የተሰሩ ናቸው፡፡
- የጥርስ እርማት የጥርስ ህመም ካለ ወይም በትክክል ማኘክ በሚዳግትበት ጊዜ የጥርስዎን ንጣፎችን እንደገና መለወጥ ወይም ጉዳቱን ለመጠገን ዘውድ (crown) መጠቀም ያስፈልግ ይሆናል ፡፡
የስነ አእምሮ የምክር አገልግሎቶች
- በጭንቀት ወይም ፍርሃት ዙሪያ ከስንልቦና ባለሙያ ጋር የሚደረግ ውይይት
- የባህሪ ለውጥ
- ባዮፊድባክ (biofeedback) አግባብ ያልሆኑ የልምድ ዑደቶችን ለመስበር
መድሃኒቶች
በአጠቃላይ ፣ መድኃኒቶች ለጥርስ ማንቀርጨጭ ሕክምና የዛን ያህል ውጤታማ አይደሉም፡፡ ለጥርስ ማንቀርጨጭ ሊያገለግሉ የሚችሉ መድኃኒቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ:
- የጡንቻ ማፍታቻ (muscle relaxant) በአንዳንድ ሁኔታዎች የመንጋጋ ጡንቻዎችዎን መኮማተር ለመከላከል ከመተኛትዎ በፊት ለአጭር ጊዜ የጡንቻ ማፍታቻ መድሃኒቶች እንዲወስዱ ሊመከሩ ይችላሉ፡፡
- የቦቶክስ መርፌዎች (botox injections) ለሌሎች ሕክምናዎች ምላሽ ያልሰጠ ከባድ የጥርስ ማንቀርጨጭ ላለባቸው አንዳንድ ሰዎች ሊረዳ ይችላል ፡፡
- ፀረ-ድብርት ወይም ፀረ-ጭንቀት መድኃኒቶችን ከስነልቦና እክል ጋር ታያይዞ ለሚመጣ የጥርስ ማንቀርጨጭ እንዲጠቀሙ ሊመከር ይችላል ፡፡
ተያያዥ በሽታዎችን ማከም
- በመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ምክንያት የጥርስ ማንቀርጨጭ ካለ ሐኪምዎ መድሃኒትዎን ሊቀይር ይችላል ፡
- ከእንቅልፍ ጋር የተዛመዱ ችግሮች እንደ በእንቅልፍ ወቅት ትንፋሽ ማጠር የመሳሰሉት ካሉ ለነዚህ መፍትሄ መስጠት የጥርስ ማንቀርጨጩን ያሻሽለዋል
- የጥርስ ማንቀርጨጭን ሊያስከትሉ የሚችሉ ከላይ የተጠቀሱ የሕክምና ሁኔታዎች ተገቢውን ህክምና ማድረግ
የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች
- ጭንቀትን ይቀንሱ - የሚያስደስተዎን ነገር ማድረግ ፣ ሞቅ ባለ ወሃ ገላ መታጠብ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ዘና ለማለት እና ጭንቀት ለመቀነስ ይረዳዎታል
- ማስቲካ እና ሌሎች ነገሮችን የማኘክ ልምድ ካለ ማቆም ወይም መቀነስ
- ምሽት ላይ የሚያነቃቁ ንጥረ ነገሮችን ያስወግዱ - እራት ከተመገቡ በኋላ ካፌይን (ቡና ፣ ሻይ፣ ቸኮሌት የመሳሰሉትን) አይጠቀሙ በተጨማሪም አልኮል ከመጠጣት ይቆጠቡ
- ጤናማ የእንቅልፍ ልምዶችን ያዳብሩ
- መደበኛ የጥርስ ምርመራዎች ያደርጉ


