ሪህ (Gout)

Eyasu Yebeltal
Feb 9, 2026
undefined

            ሪህ (Gout)

ሪህ ማንኛውንም ሰው ሊያጠቃ የሚችል የተለመደና የተወሳሰበ የአጥንት በሽታ ነው፡፡ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ መገጣጠሚያዎች ላይ በድንገት የሚከሰት ከባድ ሕመም፣ እብጠት እና የቆዳ መቅላት የሚያስከትል የአጥንት በሽታ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በአውራ ጣት ላይ ይከሰታል፡፡ የሪህ ምልክቶች ተደጋጋሚ ሊሆኑ ይችላሉ ነገርግን ምልክቶችን ለመቆጣጠር እና ቀስቃሾችን ለመከላከል የተለያዩ መንገዶች አሉ።

የሪህ ምልክቶች ምንድናቸው?

የሪህ ምልክቶች ሁልጊዜ ማለት በሚቻል ሁኔታ በድንገት የሚከሰቱ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በምሽት ይስተዋላሉ። የተለመዱት የሪህ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ።

  • ከባድ የመገጣጠሚያ ህመም  ሪህ ብዙውን ጊዜ አውራ ጣት ላይ የሚታይ ቢሆንም በማንኛውም መገጣጠሚያ ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ሌሎች በብዛት በሪህ ሊጠቁ የሚችሉ መገጣጠሚያዎች ቁርጭምጭሚት፣ ጉልበት፣ ክርን፣ አንጓ እና ጣቶች ይገኙበታል፡፡ ምልክቶቹ ከጀመረ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ከ4 እስከ 12 ሰዓታት ውስጥ ህመሙ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡
  • ዘላቂ ምቾት ማጣት  ከባዱ የህመም ስሜት ከቀነሰ በኋላ አንዳንድ የመገጣጠሚያዎች ምቾት መንሳት ከጥቂት ቀናት እስከ ሳምንታት ሊቆይ ይችላል፡፡ ከዚህ በኋላም የሚከሰቱ ጥቃቶች ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ እና ብዙ መገጣጠሚያዎችን የሚነኩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
  • የቆዳ እብጠት እና መቅላት የተጎዳው መገጣጠሚያ በሚቆጣበት ሰዐት የቆዳ እብጠት እና መቅላት ያስከትላል።
  • ውስን የመገጣጠሚያ እንቅስቃሴ  የሪህ በሽታ እየገፋ ሲሄድ መገጣጠሚያዎች እንደ ተለመደው መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡

መች ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለብኝ?

በመገጣጠሚያዎ ላይ ድንገተኛ እና ከባድ ህመም ካጋጠምዎ ሐኪም ያነጋግሩ፡፡ በተገቢው ያልታከመ የሪህ በሽታ ወደ ከፋ ህመም እና ዘላቂ የመገጣጠሚያ ጉዳት ሊያመራ ይችላል፡፡ ትኩሳት እና የተጎዳው መገጣጠሚያ አካባቢ ሙቀት ካለ የኢንፌክሽን ምልክት ሊሆን ስለሚችል በአስቸኳይ የህክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል። 

የሪህ በሽታ በምን ምክንያት ይመጣል?

የሪህ በሽታ የሚከሰተው በመገጣጠሚያዎ ውስጥ የዩሬት ቁርጥራጮች(urate crystals) ሲከማቹ ሲሆን ይህም በደም ስርዐትዎ ውስጥ የዩሪክ አሲድ(uric acid) መጠን ሲጨምር የሚከሰት ሁኔታ ነው። ሰውነትዎ ዩሪክ አሲድን ፑዩሪን(purine) ከሚባሉ በተፈጥሮ ከሚገኙ ንጥረ ነገሮች ያመርታል። እነዚህ ንጥረነገሮች የተለያዩ ምግቦች ለምሳሌ ቀይ ስጋ፣ የጉበት ስጋ፣ ቱና እና የአልኮል እና ለስላሳ መጠጦች ውስጥ ይገኛሉ። 

በመደበኛነት በደምዎ ውስጥ ዩሪክ አሲድ በኩላሊትዎ ተጣርቶ በሽንት መልኩ ይወገዳል። ሆንም አንዳንድ ጊዜ ሰውነትዎ ከመጠን ያለፈ ዩሪክ አሲድ ሲያመርት ወይም ኩላሊትዎ በተገቢው ሁኔታ የማጣራት አቅሙን ሲያጣ የዩሪክ አሲድ ክምችት ያስከትላል፤ ይህም የዩሬት ቁርጥራጮች በመገጣጠሚያዎች ውስጥ እንዲጠራቀሙ በማድረግ የሪህ በሽታ ያስከትላል።   

 

 

ለሪህ በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች

በሰውነትዎ ውስጥ ከፍተኛ የዩሪክ አሲድ መጠን እንዲኖር የሚያደርጉ ምክንያቶች የሪህ በሽታ ተጋላጭ ያደርግዎታል፤ እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ።

  • አመጋገብ ቀይ ሥጋ እና የተለያዩ የአሳ አይነቶች አዘውትሮ መመገብ፣ የአልኮል መጠጦችን በተለይ ቢራ ከመጠን በላይ መውሰድ እና የፍራፍሬ ስኳር(fructose) የሚጠቀሙ የለስላሳ መጠጦችን አብዝቶ መጠቀም በሪህ በሽታ የመያዝ እድልን ይጨምራል።   
  • ከመጠን ያለፈ ክብደት ከመጠን ያለፈ ክብደት ካለዎት ሰውነትዎ የበለጠ ዩሪክ አሲድን ያመነጫል እናም ኩላሊትዎ ዩሪክ አሲድን ለማስወገድ ይቸገራል፡፡
  • የተወሰኑ በሽታዎች ቁጥጥር ያልተደረገበት ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ እና የኩላሊት በሽታ በሪህ የመያዝ እድልን ይጨምራሉ።   
  • መድሃኒቶች አስፕሪን እና አንዳንድ የደም ግፊትን ለመቆጣጠር የሚያገለግሉ መድሃኒቶች ለሪህ በሽታ ተጋላጭ ሊያደርጉ ይችላሉ።   
  • ዘር በቤተሰብ ውስጥ የሪህ በሽታ ያለበት ሰው ካለ የእርስዎም በበሽታው የመያዝ ዕድልዎ ከፍተኛ ነው ፡፡
  • ዕድሜ እና ፆታ ሪህ ብዙውን ጊዜ በወንዶች ላይ ይከሰታል ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ሴቶች ዝቅተኛ የዩሪክ አሲድ መጠን ስላላቸው ነው፡፡ ነገርግን በማረጥ ሂደት ውስጥ ካለፉ በኋላ በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለው የዩሪክ አሲድ መጠን ልዩነት ይቀንሳል፡፡ በወንዶች ከ30 እስከ 50 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉት ላይ በብዛት ሲታይ ሴቶች ላይ የሪህ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ ከአረጡ በኋላ ይታያል።   
  • በቅርብ ጊዜ ቀዶ ጥገና ካካሄዱ ወይም አደጋ ከደረሰብዎት 

የሪህ በሽታ መዘዞች

  • ተደጋጋሚ ሪህ(recurrent gout)  አንዳንድ ሰዎች ለሪህ በሽታ ከታከሙ በኋላ እንደገና ምልክቶች ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ሌሎች ደግሞ በተደጋጋሚ የመገጣጠሚያ ህመም ሊኖራቸው ይችላል። ይህም በአግባቡ ህክምና ካልተደረገለት የከፋ የመገጣጠሚያዎች ጉዳት እና መሸርሸር ሊያስከትል ይችላል።   
  • ከባድ የሪህ በሽታ(advanced gout)  በተገቢው ህክምና ያልተደረገለት የሪህ በሽታ ከቆዳ ስር ጠጣር እብጠቶችን (tophi) ያስከትላል። እነዚህም እባጮች አብዛኛውን ጊዜ ሀመም ባይኖራቸውም የሪህ በሽታ በሚነሳበት ጊዜ ከባድ ህመም ሊያስከትሉ ይችላል። 
  • የኩላሊት ጠጠር የዩሬት ቁርጥራጮች በሽንት መተላለፌያ ትቦ ውስጥ ተጠራቅመው የኩላሊት ጠጠር ሊያስከትሉ ይችላል። የኩላሊት ጠጠር አደጋን ለመቀነስ የሚረዱ የመድሃኒት አማራጮች አሉ፡፡

ለሪህ በሽታ የሚደረግ ምርመራ

አብዛኛውን ጊዜ ሐኪምዎ በምልክቶችዎ እና በተጎዳው መገጣጠሚያ ገጽታ ላይ በመመርኮዝ የሪህ በሽታ መሆኑን ይረዳሉ፡፡  የሪህ በሽታ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚረዱ ምርመራዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡

  • የመገጣጠሚያ ፈሳሽ ምርመራ(synovial fluid test) ከተጎዳው መገጣጠሚያዎ ላይ በመርፌ ፈሳሽ በመውሰድ የዩሬት ቁርጥራጮች መኖራቸውን በአጉሊ መነጽር የሚያይ የምርመራ አይነት ነው።  
  • የደም ምርመራ  በደምዎ ውስጥ ያለውን የዩሪክ አሲድ መጠን ለመለካት ሃኪምዎ የደም ምርመራ ሊያዝልዎት ይችላል ፡፡   
  • የራጅ ምርመራ የመገጣጠሚያ መቆጣት ምክንያቶችን ለመለየት የራጅ ምርመራ ሊታዘዝ ይችላል። 
  • አልትራሳውንድ ይህ ምርመራ በመገጣጠሚያዎች ወይም በጠጣር እብጠቶች ውስጥ የሚገኙትን የዩሬት ቁርጥራጮች ለማየት ይጠቅማል፡፡
  • ሲቲ ስካን ምርመራ መገጣጠሚያዎችን በጥራት ለማየት ይረዳል 

የሪህ በሽታ ሕክምና

የሪህ መድኃኒቶች በሁለት ዓይነት የሚገኙ ሲሆን በሁለት የተለያዩ ችግሮች ላይ ያተኩራሉ፡፡ የመጀመሪያው ዓይነት ከሪህ ጥቃቶች ጋር ተያይዞ የሚመጣውን እብጠት እና ህመም ለመቀነስ ይረዳል፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ በደም ውስጥ ያለውን የዩሪክ አሲድ መጠን በመቀነስ የሪህ ችግርን ለመከላከል ነው ፡፡

የትኛው ዓይነት መድሃኒት ለእርስዎ ትክክል እንደሆነ ለመለየት በምልክቶችዎ ድግግሞሽ እና ክብደት በተጨማሪም በታወቁ የጤና እክሎችዎ ላይ በመመርኮዝ ይመረጣል። 

የሪህ ምክንያት የሚመጣውን ህመም እና እብጠት ለመቀነስ የሚረዱ መድሃኒቶች

  • ፀረ-ብግነት መድኃኒቶች (NSAIDs) እንደ ኢቡፕሮፌን (ibuprofen) እና ኢንዶሜታሲን(indomethacin) ያሉ መድሃኒቶችን ያጠቃልላል። እነዚህ መድሃኒቶች የጨጓራ ቁስለትን ሊያስከትሉ ይችላል።   
  • ኮልሲቺን(colchicine) የሪህ ህመምን ለመቆጣጠር ውጤታማ የሆነ መድሃኒት ቢሆንም ማቅለሽለስ፣ ማስመለስ እና ተቅማጥ የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት።   
  • ኮርቲኮስቴሮይድ(Corticosteroids) የሪህ እብጠት እና ህመምን መቆጣጠር ይረዳሉ፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች በኪኒን ወይም ቀጥታ መገጣጠሚያ ላይ በሚወጋ መርፌ መልክ ይገኛሉ። የኮርቲኮስቴሮይድ የጎንዮሽ ጉዳቶች የስሜት መለዋወጥ ፣ የደም ስኳር መጠን መጨመር እና ከፍተኛ የደም ግፊትን ያካትታሉ።

በደም ውስጥ ያለውን የዩሪክ አሲድ መጠን የሚቀንሱ መድሃኒቶች

ተደጋጋሚ የሪህ በሽታ የሚያጋጥምዎት ከሆነ፣ በራጅ የተረጋገጠ የመገጣጠሚያ መሸርሸር እና ጠጣር እብጠቶች ካሉዎት፣  ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ካለብዎት የሰውነትዎን የዩሪክ አሲድ መጠን ዝቅ የሚያደርጉ መድኃኒቶች እንዲወስዱ ሊመከሩ ይችላሉ ፡፡

  • የዩሪክ አሲድ ምርትን የሚያግዱ መድኃኒቶች  እንደ አልሎፕሪኖል (allopurinol)  ያሉ መድሃኒቶች  ሰውነትዎ የሚያመርተውን የዩሪክ አሲድ መጠን እንዲገድብ ይረዳሉ፡፡ የአልሎፕሪኖል የጎንዮሽ ጉዳቶች ትኩሳት ፣ የቆዳ ሽፍታ፣ የጉበት እና የኩላሊት ችግርን ያጠቃልላል፡፡
  • የዩሪክ አሲድ አወጋገድን የሚያሻሽሉ መድኃኒቶች  እንደ ፕሮቤንሲድ (probenecid) ያሉ መድኃኒቶች ኩላሊትዎ ዩሪክ አሲድን አጣርቶ  የማስወገድ ችሎታውን ለማሻሻል ይረዳዎታል ፡፡ የጎንዮሽ ጉዳቶቹ ሽፍታ ፣የሆድ ህመም እና የኩላሊት ጠጠርን ያካትታሉ ፡፡

የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች

መድሃኒቶች ብዙውን ጊዜ የሪህ ጥቃቶችን ለማከም እና ተደጋጋሚ የሕመም ምልክቶችን ለመከላከል ውጤታማ መንገድ ቢሆኑም የሚከተሉትን የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ማድረግ የሚወስዱትን የመድሃኒት መጠን እንዲቀንሱ እና አጠቃላይ የጤንነት ስሜት እንዲሰማዎ ይረዳል። 

  • ጤናማ መጠጦችን ይምረጡ የፍራፍሬ ስኳር (fructose) የሚጠቀሙ የለስላሳ መጠጦች እና የአልኮል መጠጦችን አወሳሰድ ይገድቡ። በምትኩ  ውሃ  በበቂ መጠን ይጠጡ ፡፡
  • በፕዩሪን (purine) የተሞሉ ምግቦችን ያስወግዱ  እንደ ጉበት እና የቀይ ሥጋ በተጨማሪም እንደ ቱና፣ሳርዲን እና አንቾቪ የመሳሰሉ የአሳ አይነቶችን ከመጠቀም ይቆጠቡ። የፕሮቲን ምንጭ ሆነው እንዲያገለግሉ አነስተኛ ቅባት ያላቸውን የወተት ተዋጽኦዎች መጠቀም ይችላሉ ፡፡

በመደበኛነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ፤ ክብደትዎን ይቀንሱ  ጤናማ የሰውነት ክብደት ካለዎ በሪህ የመያዝ ተጋላጭነትዎ ያነሰ ነው፡፡ የሪህ በሽታ ካለብዎ በመገጣጠሚያዎችዎ ላይ ከባድ ጫና የማይፈጥሩ እንደ መራመድ ፣ ብስክሌት መንዳት እና መዋኘት ያሉ ዝቅተኛ ተጽዕኖ ያላቸውን እንቅስቃሴዎች ያድርጉ።

Comments (0)