ደም ማነስ (Anemia)

Biruh Tesfaye
Feb 9, 2026
undefined

ደም ማነስ (Anemia)

የደም ማነስ ለሰውነትዎ ሕብረ ሕዋሶች  በቂ ኦክስጅንን ማቅረብ የሚያስችል ጤናማ ቀይ የደም ህዋስ መጠን ሳይኖር ሲቀር የሚፈጠር  በሽታ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መሠረት በአጠቃላይ የደም ማነስ በሽታ የሚባለው ዝቅተኛ የሂሞግሎቢን (hemoglobin) ክምችት ማለትም ለወንዶች ከ13g/dl በታች ፣ እርጉዝ ላልሆኑ ሴቶች 12g/dl እና ለእርጉዝ ሴቶች ከ 11g/dl በታች ሆኖ ሲገኝ ነው። ነገርግን መደበኛ የደም ሂሞግሎቢን መጠን እንደ ፆታ ፣ ዘር ፣ ዕድሜ ፣ የአመጋገብ ልምዶች እና መኖሪያ አካባቢ ላይ ተመስርቶ ሊለያይ ይችላል ፡፡

የደም ማነስ በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ 2 ቢሊየን የሚሆኑ ሰዎችን የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን እ.ኢ.አ በ2016 በኢትዮጲያ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው 56 በመቶ የሆኑ ከ5 አመት በታች ያሉ ህፃናት፣ 23 በመቶ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ15-49 የሆኑ ሴቶች እና 18 በመቶ የሚሆኑ አዋቂ ወንዶች የደም ማነስ በሽታ አለባቸው። ይህም በሽታ የበለጠ በገጠራማው የሃገሪቱ ክፍል ባሉ አርብቶ አደሮች ላይ ይታያል።

የደም ማነስ ምልክቶች

የደም ማነስ ምልክቶች እንደ መንስኤው ይለያያሉ። አንዳንዴ ምንም ምልክቶች ላይኖርዎት ይችላል ሆኖም  ምልክቶች ከተከሰቱ የሚከተሉትን ያካትታሉ

  • ድካም ወይም የሰውነት መዛል
  • የነጣ ወይም ቢጫ ቆዳ
  • ልብዎ ሲመታ መታወቅ
  • የትንፋሽ ማጠር
  • ማዞር ወይም ጆሮ ላይ መጮህ
  • የደረት ህመም
  • ቀዝቃዛ እጆች እና እግሮች
  • ራስ ምታት
  • የምግብ ፍላጎት መቀነስ
  • የአፍ መቁሰል እና የምግብ ጠዐም መቀየር

የደም ማነስ በሽታ ከፍተኛ የሆነ ደም መፍሰስ ካላጋጠመዎ በስተቀር ቀስበቀስ እየተባባሰ የሚመጣ  በሽታ ስለሆነ ምልክቶቹን በጊዜ ላያዩ ይችላሉ።

ለደም ማነስ አጋላጭ  ምክንያቶች

  • የአመጋገብ ስርዐት የተወሰኑ ቫይታሚኖች እና ማዕድናትን ያላካተተ አመጋገብ። በአይረን፣ በቫይታሚን ቢ -12 እና በፎሌት ዝቅተኛ የሆነ የአመጋገብ ስርዐት ለደም ማነስ የመጋለጥ እድልን ይጨምራል ፡፡
  • የአንጀት ችግሮች የተመገቡትን ንጥረ ነገሮችን ወደ ሰውነትዎ መርጦ ማሰራጨት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር የአንጀት ችግር ካለብዎ ለምሳሌ እንደ ክሮንስ በሽታ(crohn's disease) እና ሴሊያክ በሽታ(celiac disease) የደም ማነስ ሊያጋጥምዎት ይችላል፡፡
  • የወር አበባ በአጠቃላይ የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች ከወንዶች እና ማረጥ ከጀመሩ ሴቶች የበለጠ በአይረን  እጥረት እና ደም መፍሰስ ምክንያት ለሚመጣ የደም ማነስ ተጋላጭ ናቸው፡፡
  • እርግዝና  ነፍሰ ጡር ከሆኑ እና ፎሊክ አሲድ እና አይረን የማይወስዱ ከሆነ የደም ማነስ ተጋላጭነትዎ ከፍተኛ ነው፡፡
  • ሥር የሰደዱ በሽታዎች  ካንሰር፣ የኩላሊት በሽታ ፣የጉበት በሽታ፣ የስኳር በሽታ ወይም ሌላ ሥር የሰደደ በሽታ ካለብዎ  እነዚህ ሁኔታዎች ቀይ የደም ህዋሶች እጥረት ሊያስከትሉ ይችላሉ ፡፡
  • የሆድ እቃ እክሎች የጨጓራ ወይም የአንጀት ቁስለት፣ በአንጀት ወስጥ የሚገኙ ትላትሎች፣ የኪንታሮት በሽታ ወይም በካንሰር  ምክንያት የሰውነትዎ የአይረን ክምችት ሲቀንስ እና ቀስበቀስ ከሆድ እቃ ደም ሲፈስ የደም ማነስ በሽታ ይከታላል።   
  • ዘር የቤተሰብ ወስጥ የደም ማነስ ያለበት ሰው ካለ እንደ ሲክል ሴል (sickle cell anemia) የመሳሰሉ በዘር የሚተላለፉ የደም ማነስ መንሰኤዎች አሉ።
  • ዕድሜ  ህፃናት እና ዕድሜያቸው ከ 65 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ለደም ማነስ  በሽታ ተጋላጭ ናቸው፡፡
  • ሌሎች አጋላጭ ሁኔታዎች አንዳንድ ኢንፌክሽኖች ፣ የደም በሽታዎች፣ የሰውነትዎ በሽታ የመከላከል ሰርዐት የራስዎን ሰውነት የማጥቃት በሽታዎች፣አልኮል አብዝቶ መጠቀም እና አንዳንድ መድሃኒቶች በቀይ የደም ህዋስ አመራረት ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩ የደም ማነስ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

የደም ማነስ የሚያመጡ በሽታዎች ምን ምንድን ናቸው?

ከላይ እንዳየነው የደም ማነስ ማለት የቀይ የደም ህዋስ በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ የሚመጣ በሽታ ነው። 

ይህ የቀይ የደም ህዋስ በበቂ ሁኔታ እንዳይኖር የሚያረጉ ነገሮችን በሶስት ከፍለን ማየት እንችላለን።

  1. ሰውነታችን በቂ የቀይ የደም ህዋስ ባለማምረቱ ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ
  2. በደም መፍሰስ ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ 
  3. በቀይ የደም ህዋሳት መጥፋት (መሰባበር) ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ

የደም ማነስን ስለሚያመጡ በሽታዎች በደንብ መረዳት ይቻል ዘንድ ስለእያንዳንዱ ክፍሎች በሰፊው ተገልጿል።

1. ሰውነታችን በቂ የቀይ የደም ህዋስ ባለማምረቱ ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ

ሰውነታችን በተለያየ ምክንያት ቀይ የደም ህዋስ ካላመረት ወይም ትክክለኛ ያልሆነ የቀይ የደም ህዋስ ካመረተ የደም ማነስ ሊያጋጥም ይችላል። ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርጉ የተለያዩ በሽታዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ በሀገራችን ውስጥ በስፋት የሚከሰቱት የሚከተሉት ናቸው።

  • በአይረን እጥረት ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ
  • በ ቫይታሚን ቢ 12 እና ፎሌት እጥረት የሚመጣ የደም ማነስ
  • በመቅኔ ችግር ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ ለምሳሌ አፕላስቲክ የደም ማነስ (Aplastic anemia)፣ የደም ካንሰር እና የመሳሰሉት በሽታዎችን መጥቀስ ይችላል።
  • ስር በሰደደ በሽታ ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ
  • የሲክል ሴል ደም ማነስ (Sickle cell anemia)
  • ታላሴሚያ (Thalassemia)

በአይረን እጥረት ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ

አይረን ሄሞግሎቢን የሚባለውን ቀይ የደም ህዋስ ለመስራት የሚያገለግል ንጥረ ነገር ለመስራት አስፈላጊ ግብአት ነው። ስለዚህም ከስር የተጠቀሱት በሰውነት ውስጥ ያለውን የአይረን መጠን የሚቀንሱ ችግሮች የደም ማነስ ያመጣሉ። 

  • በቂ አይረን የያዙ ምግቦችን አለመመገብ በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ህፃናት ላይ
  • አንዳንድ መድኃኒቶች እና የምግብ አይነቶች በሰውነት ውስጥ ያለውን የአይረን መጠን ሊቀንሱ ይችላሉ።
  • እንደ ክሮንስ (Crohn’s disease) በሽታ ያሉ የአንጀት በሽታዎች አይረን ከአንጀት ወደ ሰውነት እንዳይመጠጥ ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ።
  • እርግዝና እና ጡት ማጥባት
  • ማንኛውም አነስተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ለረጅም ጊዜ ያለው ሰው የሚያጣውን ደም ለመተካት በዙ የአይረን መጠን ስለሚያስፈልገው በአይረን እጥረት ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ ሊያጋጥመው ይችላል። ለምሳሌ ቶሎ ቶሎ ደም የሚለግስ ሰው እንዲሁም በታዳጊ ሴቶች ላይ ደግሞ የወር አበባ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል።

በአይረን እጥረት ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስን ለመከላከል እንደ ቀይ ስጋ፣ ጉበት፣ አሳ እና የወተት ተዋፅዎ ያሉ በአይረን የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ አስፈላጊ ነው። ለታዳጊ ህፃናት እና ለእርጉዝ ሴቶች ደግሞ የአይረን እንክብሎች እንደ ቅድመ ምርመራ ይሰጣሉ።

በ ቫይታሚን ቢ-12 እና ፎሌት እጥረት የሚመጣ የደም ማነስ

ቫይታሚን ቢ12 እና ፎሌት የቀይ የደም ህዋስ ለመስራት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ናቸው። ቫይታሚን ቢ 12 በዋነኝነት የሚገኘው በስጋ ውስጥ ሲሆን ፎሌት ደግሞ አረንጓዴ ቅጠል ከአላቸው የአትክልት ምግቦች ማግኘት ይችላል። እነዚህን ምግቦች አላመመገብ ወይም ደግሞ የቫይታሚን ቢ የመመጠጥ ችግር ካለ የደም ማነስ ሊያስከትል ይችላል።

በመቅኔ ችግር ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ

የደም ህዋሳት የሚሰሩበት የአጥንት የውስጠኛው ቦታ መቅኔ ይባላል። በመቅኔ ውስጥ እነዚህን ህዋሳት ለመስራት የሚያገለግሉ ስቴም ሴል (stem cell) የሚባሉ አስፈላጊ ህዋሳት አሉ። የስቴም ሴል ዋና ተግባሩ እንደ ቀይ የደም ህዋስን ጨምሮ ሌሎች የደም ህዋሳትን ይሰራል። ይህ ስቴም ሴል በካንሰር ህዋስ ከተተካ ወይም ስራውን በአግባቡ ማከናወን ካልቻለ የደም ማነስ ሊያመጣ ይቻላል።

ለምሳሌ አንድ ሰው ሊድ በሚባል ንጥረ ነገር ከተመረዘ መቅኔው ስለሚጎዳ የደም ማነስ ሊያጋጥመው ይችላል። 

በተጨማሪም አፕላስቲክ የደም ማነስ (Aplastic anemia) የተባለ ምክንያቱ በትክክል ያልታወቀ የደም ማነስ የሚያመጣ በሽታ አለ። ይህም በሽታ አብዛኛውን ጊዜ ከአንዳንድ መድኃኒቶች፣ የጨረር ህክምና እና ኢንፌክሽኖች በኃላ ይከሰታል። ይህ በሽታ በዋናኝነት መቅኔ ውስጥ ያሉትን ስቴም ሴሎች ስለሚያጥፋ እና የደም ህዋስ ስለማይሰራ የደም ማንስ ያመጣል።

ስር በሰደደ በሽታ ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ (Anemia of chronic illness)

ማንኛውም ስር የቆየ እና የሰደደ በሽታ የደም ማነስ ሊያመጣ ይችላል። ለምሳሌ ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ፣ የታይሮይድ ሆርሞን የማነስ ችግር፣ ካንሰር፣ ስኳር እና ኤች አይ ቪ በሽታ የደም ማነስ ሊያስከትል ይችላል። እንደ በሽታው አይነት ቢለያይም ስር ለሰደደ የደም ማነስ በሽታ እንደ ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ስር የሰደደ በሽታ ሰውነታችን አይረንን የማሰራጨት መጠን ስለሚቀንስ ነው።

2. በደም መፍሰስ ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ ምንድን ነው?

የደም መፍሰስ በብዙ መንገድ ሊፈጠር ይችላል። በብዛት የሚያቱ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው።

  • ከሆድ እቃ በሽታዎች ጋር ተያይዞ የሚመጣ የደም ማጣት ለምሳሌ የጨጓራ ቁስለት፣ ኪንታሮት፣ የሆድ እና የአንጀት ካንሰር
  • በሴቶች ላይ ደግሞ ከወር አበባ፣ ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚኖር የደም መፍሰስ የደም ማነስ የማምጣት እድሉ ከፍተኛ ነው።
  • ከዚህ በተጨማሪ ከአደጋ ጋር በተያያዘ አንድ ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ በዙ ደም ሊያጣ ይችላል።
  • ከቀዶ ጥገና በኃላም የደም ማነስ ሊያጋጥም ይችላል።

አጠቃለን ስናየው አንድ ሰው በሁለት መልኩ የደም መፍሰስ ሊያጋጥመው ይችላል። 

  1. በረጅም ጊዜ የሚመጣ አነስተኛ የደም መፍሰስ እና
  2. በአጭር ጊዜ የሚከሰት ከፍተኛ የደም መፍሰስ

አነስተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ለረጅም ጊዜ ያለው ሰው ሳይታወቅ በደም ማነስ ሊሰቃይ ይችላል። ነገር ግን ምልክቶቹም ሆነ በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በአጭር ጊዜ ከሚከሰተው ከፍተኛ የደም መፍሰስ ጋር ሲወዳደር አናሳ ነው። ሆኖም ግን ምልክቶቹን ተለይተው አስፈላጊውን ምርመራ እና ሕክምና ማግኘት አስፈላጊ ነው።

3. በቀይ የደም ህዋሳት መጥፋት (መሰባበር) ምክንያት የሚመጣ የደም ማነስ

በአማካኝ የአንድ የቀይ የደም ህዋስ እድሜ 90 ቀን ነው። ነገር ግን አንዳንድ ሁኔታዎች ህዋሳቱ ቶሎ እንዲጠፉ (እንዲሞቱ) የሚያረጉ በዙ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ

  • በዘር የሚተላለፉ እንደ ሲክል ሴል እና ታላሴሚያ (Thalassemia) ያሉ በሽታዎች 

የሲክል ሴል በሽታ በዘር የሚመጣ በሽታ ሲሆን የቀይ የደም ህዋስ ቅርፅ ከክብ ወደ ሞላላ እንዲቀየር ያረገዋል። ይህም የቀይ የደም ህዋስ አጭር እድሜ ከመኖሩም በላይ በቅርጹ ምክንያት በደም ቧንቧዎች ላይ ለማለፍ ስለሚቸገር በቀላሉ የመሰባበር አዝማሚያ ይኖረዋል። በዚህ ምክንያት ይህ በሽታ የደም ማነስ ሊያመጣ ይችላል።

  • እንደ ሉፐስ ያሉ አንዳንድ በሽታዎች የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ስርዐት በራሱ የቀይ የደም ህዋስን እንዲያጠቃ ሊያረጉ ይችላል።
  • አንዳንድ በሽታዎች በተለያየ ምክንያት ጣፊያ እንዲያድግ ሊያረጉ ይችላሉ። ትልቅ ጣፊያ ደግሞ የቀይ የደም ህዋሳትን ሊሰባብር ይችላል።
  • ገና የተወለዱ አራስ ህፃናት ላይ የቀይ የደም ህዋሳትን ሊሰባብሩ የሚችሉ በዙ በሽታዎች አሉ። ከነዚህ በሽታዎች ውስጥ ዋነኞቹ ሾተላይን ጨምሮ የህፃኑ እና የእናትየው ደም ባለመስማማት ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች ናቸው።

የደም ማነስ የሚያስከትለው መዘዞች 

  • ከመጠን ያለፈ ከስራ የሚያስተጓጉል ድካም
  • የሰውነታችን የበሽታ መከላከል ስርዐት መዳከም
  • የልብ ድካም እና ሌሎች የልብ እክሎች 
  • በእግዝና ወቅት ከተከሰተ የጽንስ እድገት መዘግየት፣ ያለጊዜ ምጥ እና ወሊድ፣ ድህረ ወሊድ ድባቴ

ከባድ በጊዜው ያልታከመ የደም ማነስ እስከ ሞት ደረጃ ያደርሳል።

Comments (0)