የአዋቂዎች የሆድ ድርቀት
የሆድ ድርቀት የአንጀት እንቅስቃሴ ለውጥን ሲያመለክት የተለያዩ ትርጉሞች አሉት ፡፡ የሰገራ ደረቅ መሆንን፣ በመጠን መቀነስን፣ ለማለፍ አስቸጋሪ መሆንን ወይም መምጣት ከሚገባው ድግግሞሽ ማለትም በሳምንት ከሶስት ጊዜ በታች መሆንን ያካትታል። በተጨማሪም የሆድ ድርቀት ያጋጠማቸው ሰዎች ደግሞ የሆድ መነፋት፣ ማስመለስ፣ በተደጋጋሚ ማስማጥ እና ሙሉበሙሉ ተፀዳድቶ ያለመጨረስ ስሜት ሊኖራቸው ይችላል፡፡
የሆድ ድርቀት በጣም የተለመደ ችግር ነው ፡፡ ብዙ ምክንያቶች ለሆድ ድርቀት መከሰት አስተዋፅዖ ሊያደርጉ ወይም በቀጥታ ሊያስከትሉ ይችላሉ፤ ቢሆንም በአብዛኛዎቹ ሰዎች ላይ አንድ ብቸኛ መንሰኤ ተለይቶ አይታወቅም ፡፡ በአጠቃላይ እድሜ እየገፋ ሲመጣ የሆድ ድርቀት የበለጠ ይከሰታል ፡፡
የሆድ ድርቀት መነሻዎች
የሆድ ድርቀት በአብዛኛው ጊዜ የሚከሰተው ዓይነ ምድራቸን በምግብ መፍጨት ስርዓት ውስጥ ሲያልፍ በሚዘገይበት ጊዜ ነው። ይህም እንዲሆን የሚከተሉት ሁኔታዎች ያጋልጡናል
- በቂ ውሃ አለመጠጣት
- በምግብዎ ውስጥ በቂ የልሆነ ፋይበር አለመኖር
- መደበኛ የምግብ ሠዓት ማስተጓጎል
- ከፍተኛ መጠን ያለው የወተት ተዋጽዎ መመገብ
- በቂ የሆነ እንቅስቃሴ አለማድረግ
- ጭንቀት
- ከመጠን በላይ የዓይነ ምድር ማለስለሻ መድሃኒቶች መጠቀም
- በአንጀት እና ፊንጢጣ አካባቢ ያሉ ነርቮች በሸታ
- ፓርኪንሰንስ በሽታ
- የህብረ ሰረሰር ጉዳት
- ስትሮክ
- የሰውነታችንን ሆርሞኖችን የሚያዛቡ ሁኔታዎች- የስኳር በሽታ፡ እርግዝና፡ የታይሮይድ ሆርሞን ችግር
- የአንጀት እና ፊንጢጣ ካንሰር
ለሆድ ድርቀት የሚደረግ ምርመራ
የሆድ ድርቀት አብዛኛውን ጊዜ በምልክትዎ እና በአካላዊ ምርመራ ላይ ተመርኩዞ ሊታወቅ ይችላል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ መድሃኒቶች የሆድ ድርቀት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ በመደበኛነት የሚወስዷቸው ማናቸውም መድኃኒቶች ካሉ መጥቀስ አለብዎት፡፡
የአካላዊ ምርመራ አካል ሆኖ የፊንጢጣ ምርመራ ያስፈልግዎት ይሆናል ፡፡ የፊንጢጣ ምርመራ ማንኛውንም እብጠቶች ወይም ጤናማ ያልሆኑ እክሎችን ለመለየት እና ሰገራ ውስጥ ደም መኖሩን ለማረጋገጥ ያስችላል ፡፡
በአንዳንድ ሁኔታዎች ለምሳሌ የአንጀት እንቅስቃሴ ለውጡ ያጋጠመው በቅርብ ጊዜ ከሆነ ፣ ደም የተቀላቀለው ሰገራ ካለ ፣ ክብደት መቀነስ ወይም በቤተሰብ የአንጀት ካንሰር የተገኘበት ሰው ካለ ተጨማሪ ምርመራዎች ያስፈልግዎታል። የደም ምርመራዎችን ፣ የሆድ ራጅ ፣ ሲግሞይዶስኮፒ sigmoidoscopy ፣ ኮሎንኦስኮፒ colonoscopy፣ የባሪየም ጥናት barium studies የመሳሰሉትን ሊያካትት ይችላል ፡፡
ምን አይነት ምልክቶችን ሳይ ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለብኝ?
አብዛኛው ጊዜ የሆድ ድርቀትን በቤት ውስጥ ማከም ይችላሉ ፡፡ ሆኖም የሚከተሉትን ምልክቶች ካስተዋሉ ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ ይመከራሉ
- ይህ አይነት የአንጀት እንቅስቃሴ ለውጥ ለእርሶ አዲስ ውይም ያልተለመደ ከሆነ
- ከሶስት ሳምንታት በላይ ከቆየ
- ከባድ ምልክቶችን የሚያሳይ ከሆነ
- እንደ ደም የቀላቀለ ሰገራ ፣ ክብደት መቀነስ ፣ ትኩሳት ወይም ድካም ያሉ ምልክቶች ካስተዋሉ
የሆድ ድርቀት ሕክምና
ለሆድ ድርቀት የሚደረግ ሕክምና አንዳንድ ባህሪያትን መለወጥ ፣ ከፍተኛ ፋይበር ያላቸውን ምግቦች መመገብ እና አስፈላጊ ከሆነም ሰገራ ማለስለሻ መጠቀምን ወይም የሆድ እጥበትን ያጠቃልላል ፡፡
የባህሪ ለውጦች - አንጀት ምግብ ከተመገቡ በኋላ ባሉት የተወሰኑ ሰዐቶች ጠንካራ እና ንቁ እንቅስቃሴ ያደርጋል ፣ እናም ይህ ሰገራ በፍጥነት እና በቀላሉ የሚያልፍበት ጊዜ ነው። ይህንን ሰዐት ካሳለፉ ሰገራን ለማሳለፍ እየከበደ ሊመጣ ይችላል ስለዚህ ለአንጀትዎ እንቅስቃሴ ትኩረት በመስጠት የሆድ ደርቀትን ሊከላከሉ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ጠዋት ላይ ካፊን ያላቸው መጠጦችን ወይም ለብ ያለ ውሃ መጠጣት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ፡፡
የሚወስዱትን የፋይበር መጠን መጨመር - በአመጋገብዎ ውስጥ ፋይበርን መጨመር የሆድ ድርቀትን ሊቀንስ ወይም ሊያስወግድ ይችላል። የሚመከረው የአመጋገብ ስርዐት በቀን ከ 20 እስከ 35 ግራም ፋይበር ያለው ነው ፡፡ አብዛኞቹ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች የሆድ ድርቀትን ለመከላከል ይረዳሉ፡፡
| የምግብ አይነት | ብዛት | የያዘው የፋይበር መጠን በግራም |
| ፍራፍሬዎች | ||
| አፕል(ከነቆዳው) | 1 | 4.4 |
| ሙዝ | 1 | 3.1 |
| ብርቱካን | 1 | 3.1 |
ቴምር
| 1 ኩባያ | 12.4 |
| የጁስ አይነቶች | ||
| አፕል ጁስ | 1 የውህ ብርጭቆ | 0.5 |
| የወይን ጁስ | 1 የውህ ብርጭቆ | 0.2 |
| የብርቱካን ጁስ | 1 የውህ ብርጭቆ | 0.7 |
| አትክልቶች | ||
| ፎሶሊያ | 1 ኩባያ | 4 |
| ካሮት(የተከተፈ) | ግማሽ ኩባያ | 2.3 |
| ድንች(የተቀቀለ) | 1 | 3.8 |
| የባሮ ሽንኩርት | 1 | 1.5 |
| ሰላጣ(የተከተፈ) | 1 ኩባያ | 0.5 |
| ቲማቲም | 1 | 1.5 |
| የእህል አይነቶች | ||
| ሽንብራ | 1 ኩባያ | 8.8 |
| ባቄላ(የተቀቀለ) | 1 ኩባያ | 13.9 |
| የስንዴ ዳቦ | 1 | 1.9 |
| አጃ | 1 ኩባያ | 4 |
| ማኮረኒ | 1 ኩባያ | 2.5 |
| ነጭ ሩዝ | 1 ኩባያ | 0.6 |
| ቡኒ ሩዝ | 1 ኩባያ | 3.5 |
| ፓስታ | 1 ኩባያ | 2.5 |
| ኦቾሎኒ | 1 ኩባያ | 12.4 |
የፋይበር የጎንዮሽ ጉዳቶች - ከፍተኛ መጠን ያለው ፋይበርን መመገብ ሆድ ውስጥ የጋዝ መከማቸት እና የሆድ መነፋት ሊያስከትል ይችላል። ይህን ለመቀነስ በትንሽ መጠን በመጀመር ቀስ በቀስ የፋይበር ምግብ አወሳሰዳችንን መጨመር ይመከራል ፡፡
የሰገራ ማለስለሻ መድሃኒቶች የባህሪ ለውጥ እና ፋይበርን መጨመር የሆድ ድርቀትን ካላስታገሰ እነዚህን መድሃኒቶች መውሰድ ሊመከሩ ይችላሉ። የሆድ ድርቀትን ለማከም የተለያዩ ማለስለሻዎች ይገኛሉ፤ የትኛው ለርሶ እንደሚመረጥ በመድሃኒቱ የአሰራር ሂደት ፣ ሕክምናው ምን ያህል አስተማማኝ እንደሆነ እና የጤና ባለሙያው ምርጫ ላይ የተመረኮዘ ነው ፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ መድሃኒቶች በሚከተሉት ቡድኖች ይመደባሉ-
Bulk forming የሰገራ ማለስለሻዎች
- ሳይሊየም (Psyllium)
- ሜታይልሴሉሎስ (Methylcellulose )
- ካልሲየም ፖሊካርቦፊል (Calcium polycarbophil)
- ዊት ዴክስትሪን (Wheat dextrin )
የሆድ መነፋትን ለመከላከል እነዚህን መድሃኒቶች በዝግታ መጨመር አለብዎት ፣ ተጨማሪ ፈሳሽ አብዝቶ መውሰድ አይዘንጉ።
Hyperosmolar የሰገራ ማለስለሻዎች
- ፖሊታይሊን ግላይኮል (polyethylene glycol)
- ላክቱሎስ(lactulose)
- ሶርቢቶል(sorbitol)
ፖሊታይሊን ግላይኮል የሆድ መነፋትን ስለማያመጣ ተመራጭ ነው።
Saline የሰገራ ማለስለሻዎች
- ማግኒዥየም ሃይድሮክሳይድ (magnesium hydroxide (Milk of Magnesia®) )
- ማግኒዥየም ሲትሬት (magnesium citrate)
Stimulant የሰገራ ማለስለሻዎች -
- ሴና (senna)
- ቢሳኮዲል (bisacodyl)
እነዚህን መድሃኒቶች በመደበኛነት መውሰድ በደም ውስጥ የሚገኘውን የፖታስየም መጠንን በመቀነስ ከባድ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያስተትል ይችላል፡፡ ስለሆነም እነዚህን መድሃኒቶች ከሁለት ሳምንት በላይ የሚወስዱ ከሆነ የጤና ባለሙያ ማማከር ይኖርብዎታል ፡፡
የሆድ እጥበት ከላይ ለተጠቀሱት የህክምና አማራጮች ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ የሆድ እጥበት እንዲያካሂዱ ሊመከሩ ይችላሉ።
ለሆድ ድርቀት ሕክምና ተብለው የሚቀርቡ ማስወገድ ያለብዎ ምርቶች
- ሰገራን ለማለስለስ ተብሎ የሚሸጡ ሚኒራል ዘይቶች - ሌሎች የሕክምና አማራጮች ከነዚህ ዘይቶች ያነሰ የጎንዮሽ ጉዳቶች እና እኩል ጥቅም አላቸው ፡፡
- ተፈጥሯዊ ምርቶች - የተለያዩ የተፈጥሮ ምርቶች ለሆድ ድርቀት ህክምና ተብለው ይተዋወቃሉ፡፡ ከእነዚህም አንዳንዶቹ ለንግድ የተፈቀዱ ንጥረ ነገሮችን ይዘዋል ነገርግን መጠን እና ንፅህና ላይ በጥንቃቄ ቁጥጥር ስላማይደረግባቸው በአጠቃላይ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አይመከሩም ፡፡
- እንደ ሃይድሮጂን ፐርኦክሳይድ እና ሳሙናዎች ያሉ በቤት ውስጥ የሚሰሩ ሰገራ ማለስለሻዎች ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ በአንጀት ሽፋን ላይ መቆጣት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ በመጠቀም አይመከርም፡፡
የሆድ ደርቀትን ለመከላከል
- የተመጣጠኑ በተለይም ፋይበር በብዛት ያላቸውን ምግቦችን ይመገቡ
- በቀን እስከ ሁለት ሊትር ውሃ እና ሌሎች ፈሳሾችን መጠጣት (በሌሎች የህክምና ችግር እስካልተከለከልን ድረስ)
- ካፌን የያዙ መጠጦች ለጊዜው የአንጀት እንቅስቃሴን ቢጨምሩም የሰውነት ፈሳሽን የማድረቅ ባህሪ ስላላቸው አጠቃቀሞን መቀነስ አለብዎ
- አንዳንድ ሰዎች ወተት ሲጠጡ ስለሚያባብስባቸው ቢቀንሱ ይመረጣል
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ያድርጉ
ባዮፊድባክ (biofeedback) ይህ ለረጅም ጊዜ የሆድ ደርቀት ላለባቸው ሰዎች የሚመከር የባህሪ ልምምድ ሲሆን፤ በሚፀዳዱበት ወቅት የአንጀት ጡንቻ መኮማተርን አስወግደው ጡንቻን ዘና እና ለቀቅ ማድረግን እንዲለምዱ ይረዳል።




