አልማዝ ባለጭራ ህመም ያለው ቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ ሲሆን ቫሪሴላ-ዞስተር (Varicella zoster) በሚባል ቫይረስ አማካኝነት ይከሰታል።
ጥናቶች እደሚያሳዩት ከሆነ 20 በመቶ የሚሆነው የአለማችን ህዝብ በዚህ በሽታ ይጠቃል፡፡ ይህ ህመም የሚከሰተው አስቀድሞ ጉድፍ (Chickenpox) በተያዙ ሰዎች ላይ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ሰዎች በጉድፍ ተይዘው እደነበረ ላያውቁ ወይም ላያስታውሱ ይችላሉ።
★ አልማዝ ባለጭራ እንዴት ይከሰታል?
ቫሪሴላ-ዞስተር ሰዎች በጉድፍ እዲታመሙ የሚያደርግ ቫይረስ ሲሆን ህመሙ ካለፈ በኋላ ይህ ቫይረስ በአከርካሪ እና በአንጎል አቅራቢያ በሚገኙ ነርቮች ውስጥ ይቀመጣል። አመቺ ሁኔታን ሲያገኝ ይህ ቫይረስ በነርቮች ውስጥ በመጓዝ በቆዳችን ላይ አልማዝ ባለጭራ በሽታ እዲከሰት ያደርጋል።
★ ለበሽታው መከሰት አመቺ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
በሽታ የመከላከል ዓቅም የሚቀንሱ ሁኔታዎች።
➔ ኤች. አይ. ቪ. ኤድስ ህመም
➔ የካንሰር በሽታ ወይም የኬሞቴራፒ ሕክምና
➔ አንዳንድ መድኃኒቶች(Steroids)
➔ ከፍተኛ ውጥረት ወይም ጭንቀት
➔ ዕድሜ በተለይም ከ 50ዓመት በላይ
★ የአልማዝ ባለጭራ ምልክቶች
➔ አልማዝ ባለጭራ ማንኛውንም የሰውነት ክፍል ሊያጠቃ ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ግን በአንድ ጎን በኩል በደረት፣ በሆድ ወይም በጀርባ ላይ ሲወጣ ይስተዋላል።
➔ ይህ ህመም ቆዳ ላይ ሽፍታ ከማሳየቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ የመደንዘዝ፣ የማቃጠል እና የማሳከክ ስሜት ይኖረዋል። ይህ ከታየ 1-2 ቀናት በኋላ በአንድ የሰውነት ጎን ብቻ የቆዳ መቆጣት እና የቀበቶ ቅርፅ የመሰለ ዉሃ የቋጠረ፣ ህመም ያለው ሽፍታ መታየት ይጀምራል። ብዙ ጊዜ ሽፍታው ከጥቂት ቀናት በኋላ መድረቅ እና መክሰም ይጀምር እና በ1 ወይም 2 ሳምንት ውስጥ ይጠፋል።
➔ በተጨማሪ ትኩሳት ፣ ድካም፣ ራስ ምታት እና ህመሙ በተከሰተበት አካባቢ ንፍፊት (Lymphadenopathy) መውጣት ሊኖር ይችላል።
★ አልማዝ ባለጭራ ተላላፊ ነውን?
ታማሚዎች በቀጥታ አልማዝ ባለጭራን ማስተላለፍ አይችሉም። ነገር ግን የጉድፍ ክትባት ያልወሰደ ወይም ጉድፍ ታሞ የማያውቅ ሰው በታማሚው አካባቢ በሚሆንበት ጊዜ በጉድፍ በሽታ ሊጠቃ ይችላል።
ቫይረሱ ከታማሚው ሰው ጋር በሚደረግ ቀጥታ የቆዳ ንክኪ ወይም በትንፋሽ አማካኝነት ይተላለፋል። ስለዚህ የጉድፍ ክትባት ያልወሰደ ወይም ጭራሽ ታሞ የማያውቅ ሰው ከታማሚው ጋር የቅርብ ንክኪ ባያደርግ ይመረጣል።
★ አልማዝ ባለጭራ ምን አይነት ከባድ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል?
አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ችግሮች የሚከሰቱት ዕድሜያቸው በገፋ ሰዎች ወይም በሽታ የመከላከል አቅማቸው በቀነሰ (Immunocompromised) ሰዎች ላይ ነው።
እነዚህም የሚከተሉት ናቸው።
➔ ከአልማዝ ባለጭራ በኋላ የሚከሰት የነርቭ ህመም (Postherpetic neuralgia)
● ይህ ሽፍታው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በተመሳሳይ የሰውነት ክፍል ላይ ቢያንስ ለ 3 ወራት የሚቆይ ህመም እና ማቃጠል ሲኖር ነው። ህመሙ ከቀላል እስከ ኑሮን ሊያውክ የሚችል ከባድ ማቃጠል እና ውጋት ሊደርስ ይችላል።
● አብዛኛውን ጊዜ ህመሙ ከጊዜ በኋላ እየቀነሰ ቢሔድም አንዳንድ ጊዜ ግን እየተመላለሰ ለወራት ወይም ለአመታት ሊዘልቅ ይችላል። ስለዚህ ህመሙን ለማስታገስ የጤና ባለሙያዎች የተለያዩ መድኃኒቶችን ሊያዙ ይችላሉ።
➔ የዓይን ችግር
● ይህ የአልማዝ ባለጭራ ሽፍታ ዓይን፣ ግንባር እና አፍንጫ አካባቢ ሲከሰት ሊያጋጥም የሚችል ከባድ የዓይን ችግር ነው።
● ይህ ህመም በአግባቡ ካልታከመ ዕይታን ሊያሳጣ ስለሚችል በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ሽፍታ ሲከሰት በፍጥነት የጤና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል።
➔ የቆዳ ኢንፌክሽን
● አንዳንድ ጊዜ ሽፍታው ሊቆስል እና ቆዳችን በሽታ አምጪ በሆኑ ተዋሕስያን ሊበከል ይችላል። ይህም ቆዳችን ላይ ጠባሳ ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህ ከፍተኛ ትኩሳት ወይም መግል በሚኖርበት ጊዜ ወደ ጤና ተቋም መሔድ ያስፈልጋል።
➔ የጆሮ ብግነት ወይም መቆጣት
● በተጎዳው ጆሮ በኩል የፊት ጡንቻ መስነፍ (የፊት መጣመም)፣ የጆሮ ህመም እና በጆሮ ውስጥ ሽፍታ መውጣት ምልክቶቹ ናቸው። ብዙውን ጊዜ በፀረ-ቫይረስ መድኃኒት እና ብግነትን በሚቀንሱ መድኃኒቶች(Steroids) ይታከማል።
ያልተለመደ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ አልማዝ ባለጭራ በሳንባ ፣ በአንጎል እና በጉበት ላይ ለሞት የሚዳርግ ውስብስብ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል።
★ የአልማዝ ባለጭራ ምርመራዎች ምንድን ናቸው?
የጤና ባለሙያዎች ሽፍታውን በማየት እና ስለምልክቶቹ በመጠየቅ ስለበሽታው መረዳት ይችላሉ። እንዲሁም ከሽፍታው ላይ ናሙና በመውሰድ ምርመራ ሊደረግ ይችላል።
★ የአልማዝ ባለጭራ ሕክምና
➔ በቤት ውስጥ የሚደረግ ሕክምና
● ሽፍታው ያለበትን አካባቢ ንፅህና መጠበቅ፣ በተጨማሪም እርጥበት እዳይኖር በጥንቃቄ ማድረቅ
● ቆዳን የበለጠ ሊጎዱት ስለሚችል እርጥበት ያላቸውን ቅባቶች እና ክሬሞችን ማስወገድ
● የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ በቂ እረፍት ማድረግ
● ሰፋ ያሉ እና ምቾትን የሚሰጡ ልብሶችን መልበስ
● የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ማድረግ፣ ውጥረትን መቀነስ
➔ በሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚደረጉ ሕክምናዎች
● የፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች ፣ እነዚህ መድኃኒቶች የቫይረሱን መራባት ለማገድ፣ የህመሙን ክብደት እና ቆይታ ለመቀነስ እና ሽፍታው በፍጥነት እንዲድን ለማድረግ ያግዛሉ። በተለይም ሽፍታው በተከሰተ በ72 ሰአታት ውስጥ መወሰድ ከተጀመሩ ውጤታቸው ጥሩ ይሆናል።
● የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች፣ አንዳንድ ጊዜ ህመሙ ከባድ ሊሆን እና የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ።
● የ ፀረ ተዋህስያን መድኃኒቶች ፣ ቆዳ በበሽታ አምጪ ተዋህስያን ከተበከለ እና ኢንፌክሽን ከተፈጠረ አንቲባዮቲክስ መድኃኒቶች ይታዘዛሉ።
★ አልማዝ ባለጭራ መከላከያ መንገዶች
● ሕፃናት የጉድፍ መከላከያ ክትባትን እዲወስዱ ማድረግ
● ባደጉት አገራት ዕድሜያቸው ከ 50 በላይ ለሆኑ ሰዎች የአልማዝ ባለጭራ መከላከያ ክትባትን እዲወስዱ ይደረጋል።
● የአልማዝ ባለጭራ ታማሚ እስኪያገግሙ ድረስ ርቀትን መጠበቅ ያስፈልጋል። በተለይም የጉድፍ ክትባትን ካልወሰዱ ወይም በጉድፍ ተይዘው የማያውቁ ከሆነ ይህን ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል።




