በጥልቅ ደም ሥር ሚከሰት ደም መርጋት (Deep Vein Thrombosis)

Asteraye Belay
Feb 16, 2026
undefined

● ይህ ደም ሥሮች በረጋ ደም ምክንያት ሲዘጉ የሚከሰት ህመም ሲሆን በአለማችን ላይ በየዓመቱ ከ1000 ሰዎች መካከል 1 ሰው በዚህ በሽታ ይጠቃል። 

● የደም መርጋት ችግር በየትኛውም የሰውነት ደም ሥሮች ላይ ሊከሰት ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ግን በእግር እና በዳሌ አካባቢ በሚገኙ የደም መላሽ (Vein) ሥሮች ላይ ይከሰታል። ይህም በደም ሥር በኩል የሚደረገውን የደም ፍሰት በመገደብ በአካባቢው እብጠትን እና ህመምን ያስከትላል።

●  አንዳንድ ጊዜ ይህ የረጋ ደም ሙሉ ለሙሉ ወይም የተወሰነው ክፍል በደም ውስጥ በመጓዝ ሌሎች የደም ሥሮች ውስጥ ሊወተፍ (Embolus) ይችላል። በተለይም ይህ የረጋ ደም ውትፍ የሳንባ ደም ሥሮች ውስጥ የሚከሰት ከሆነ (Pulmonary embolism) የመተንፈሻ ስርዐትን በማወክ ለሕይወት አስጊ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይችላል። 

 

   በደም ሥር ውስጥ ለሚከሰት የደም መርጋት የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

 

● በዘር የሚተላለፍ የደም መርጋት ህመም ወይም በቤተሰብ የደም መርጋት ህመም መኖር 

● የእግር እንቅስቃሴን ሚገድቡ ሁኔታዎች ለምሳሌ ከ 4 ቀናት በላይ የአልጋ ቁራኛ መሆን(Bedridden) ፣ እግር ላይ የታሰረ ጄሶ (ለአጥንት ስብራት የሚደረግ ሕክምና)

● ካንሰር ወይም የካንሰር ሕክምና (Chemotherapy and radiation)

● ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ህመም መኖር 

● ዕድሜ በተለይም ከ 65 ዓመት በላይ

● ከመጠን ያለፈ ውፍረት

● እርግዝና

● የተወሰኑ መድኃኒቶች (ለምሳሌ ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒኖች ፣ የሆርሞን ሕክምና )

● ሲጋራ ማጨስ

● የልብ ድካም፣ የኩላሊት ህመም 

● የቀዶ ጥገና ሕክምና በተለይም ቀዶ ጥገናው ዳሌ፣ እግር እና ጉልበት አካባቢ ከሆነ ደም መርጋት የመከሰት ዕድሉን ይጨምረዋል። 

● ሆስፒታል መተኛት፣ ይህም በህመም ወይም በሆስፒታል አልጋ ቁራኛነት ምክንያት ሊከሰት ይችላል።

● ደም እዲረጋ የሚያረጉ ንጥረ ነገሮች መዛባት የሚያመጡ ህመሞች (eg. Thrombophilia) 

 

ምልክቶቹ ምንድናቸው?

 

በጣም የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።

● አብዛኛውን ጊዜ በአንደኛው (የታመመው) እግር ላይ እብጠት፣ ህመም፣ መቅላት እና በመንካት ጊዜ ማተኮስ እና ህመም መሰማት ናቸው። 

● የሳንባ ደም ሥሮች ውስጥ ከተከሰተ ትንፋሽ ማጠር፣ የደረት ውጋት፣ ደም የቀላቀ አክታ፣ ሳል እና የልብ ምት መጨመር ሊኖር ይችላል።

● ስለዚህ እነዚህ ምልክቶች በሚኖሩበት ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም በመሔድ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።

 

ምርመራ

● የጤና ባለሙያዎች ስለህመሙ ምልክቶች በመጠየቅ እና አካላዊ ምርመራዎችን በማድረግ ስለ በሽታው ፍንጭ ለማግኘት ይሞክራሉ። በተጨማሪም ይህን ለማረጋገጥ የተለያዩ የደም እና የምስል ምርመራዎችን ያደርጋሉ።

የምስል ምርመራ

● የእግር አልትራሳውንድ፣ ሲቲ ስካን (CT scan)፣ ኤም አር አይ(M.R.I)

●  የደም መርጋት ህመሙን ያመጣው መንስኤ ካልታወቀ መንስኤውን ለማወቅ የተለያዩ የደም ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ። 

 

    በጥልቅ ደም ሥር ሚከሰት የደም መርጋት ሕክምናው ምንድነው?

● የዚህ ሕክምና ዋና አላማ የረጋው ደም በመጠን እዳይጨምር፣ እዳይስፋፋ እና ወደ ሳንባ ደም ስሮች እዳይሰራጭ መከላከል ነው። 

 

የደም ማቅጠኛ መድኃኒቶች (Anticoagulation)

● እነዚህ በተለምዶ የደም ማቅጠኛ ተብለው የሚጠሩ መድኃኒቶች ሲሆኑ አዲስ የደም መርጋት ችግር እዳይፈጠር የሚከላከሉ ናቸው። ነገር ግን ቀድሞውኑ የነበረውን የረጋ ደም ማስወገድ አይችሉም። 

● በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የደም ማቅጠኛ መድኃኒቶች የሚገኙ ሲሆን የጤና ባለሙያው በታማሚው ጤንነት ሁኔታ፣ መድኃኒት የመግዛት አቅም እና ምርጫ ግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊ የደም ማቅጠኛ መድኃኒቶችን ማዘዝ ይችላል።

● እነዚህ መድኃኒቶች በአፍ የሚወሰዱ፣ በደም ሥር ወይም በቆዳ ሥር የሚሰጡ ሊሆኑ ይችላሉ።

መድኃኒቶቹ የሚወሰዱት ለምን ያህል ጊዜ ነው?

● ይህ የደም መርጋት በሽታ ባመጣው መንስኤ ላይ የሚወሰን ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ግን መድኃኒቶቹ ቢያንስ ለ 3 ወራት ያህል መወሰድ ይኖርባቸዋል። 

የጎንዮሽ ጉዳታቸው ምንድነው?

● አብዛኛውን ጊዜ በአገራችን የሚገኙት መድኃኒቶች ሔፓሪን(UFH) እና ዋርፋሪን(Warfarin) የደም መፍሰስ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተጨማሪም የመድኃኒቶቹን መጠን ለማስተካከል ተደጋጋሚ የደም ምርመራ ማድረግን ይሻሉ።

●  እነዚህን መድኃኒቶች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መቀየር ለከፋ ችግር ሊያጋልጥ ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

● በተጨማሪም እርግዝና ከመከሰቱ በፊት ስለ መድኃኒቶቹ ደኅንነት ሐኪምን ማነጋገር አስፈላጊ ነው።

 

የረጋውን ደም የሚያስወግዱ መድኃኒቶች(Thrombolytics)

●  እነዚህ በደም ሥር የሚሰጡ መድኃኒቶች ሲሆኑ በደም መርጋት ምክንያት ለሕይወት አስጊ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የሚሰጡ ናቸው። በአፋጣኝ ከተወሰዱ ጥሩ ውጤት የሚኖራቸው ሲሆን ለደም መፍሰስ ተጋላጭ ለሆኑ ታማሚዎች ግን አይሰጡም።

 

የዐብይ ደም መላሽ ማጣሪያ(Inferior vena cava filter) 

● ይህ መሳሪያ በዐብይ ደም መላሽ ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን በደም ዝውውር ውስጥ የሚገኝ የረጋ ደምን ያጣራል።

 

የደም መርጋትን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ማድረግ

● የሰውነትን ክብደት ጤናማ ማድረግ

● የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር

● ሲጋራ አለማጨስ

● የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ እና ሌሎች የታወቁ ህመሞች ካሉ በአግባቡ መታከም

 

በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች በከባድ ህመም ምክንያት ሆስፒታል ተኝተው ለሚታከሙ፣ የእግር እና የዳሌ ቀዶ ጥገና ለሚያደርጉ እና የካንሰር ሕክምናን ለሚወስዱ የደም መርጋትን የሚከላከል የደም ማቅጠኛ መድኃኒት ሊያዙ ይችላሉ። 

Comments (0)