የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች መጾም ይችላሉ?

Elsabet Azezew
Mar 7, 2026
undefined

                                    የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች መጾም ይችላሉ?

ጾም በክርስትና ፣ በእስልምና እንዲሁም የአይሁድ እምነትን ጨምሮ  አለማችን ውስጥ ባሉ የተለያዩ ሃይማኖቶች የሚተገበር አንዱ የሃይማኖት መገለጫ ነው። 

እንደሚታወቀውም በሃገራችን ውስጥ እጅግ የሚታወቁት የረመዳን እና የዓብይ ጾም አጿማት የተለያየ የጊዜ እርዝማኔ፣ የአጿጿም ዘዬ እና አመጋገብ ኖሯቸው በአማኞች ይጾማሉ። 

ይሁን እንጂ እንደ ስኳር ህመም ያሉ በሽታዎች ካለብዎት ሃይማኖታዊ አጿማትን መጾም መቻልዎ ጥያቄ ፈጥሮቦት ይሆናል። ከዚህ በመነሳት በዚህ ፅሁፍ በጾም ዙሪያ የስኳር በሽታን አስመልክቶ የሚነሱ ጥያቄዎችን እንመለከታለን።

                       የስኳር በሽታ ያለበት ሰው መፆም ይችላል ?

አዎ ፤ በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች መጾም ይችላሉ ነገር ግን ውሳኔው ሙሉ በሙሉ ባሉበት የጤና ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ነው። መጾም አለመጾም የግል ምርጫ ሆኖ ሳለ ለመጾም ከመረጡ ግን  በጾም ወቅት መውሰድ ስላለብዎት ጥንቃቄዎች እንዲሁም አማራጭዎች ከሐኪምዎ ጋር መማከር ይኖርብዎታል። 

                        ጾም እንዲጾሙ የማይመከሩ የስኳር በሽታ ታማሚዎች እነማን ናቸው ?

በፆሙ ምክንያት ጤንነቱን ከባድ አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ሰው መጾም የለበትም። እነዚህም

  • የስኳር በሽታ ያለባቸው ህጻናት 
  • በእርግዝና ጊዜ የስኳር ህመም ያለባቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች 
  • የአዕምሮ እክል ያለባቸው ታካሚዎች
  • ዓይነት 1 የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ፤ በተለይ የደም የስኳር መጠን ቁጥጥራቸው ጥሩ ካልሆነ
  • አቅማቸው ደካማ የሆኑ (frail) የስኳር በሽታ ያለባቸው አረጋውያን
  • ባለፉት 3 ወራት ውስጥ በጣም ዝቅተኛ የደም የስኳር መጠን ያጋጠማቸው ታማሚዎች ማለትም ከ  54 mg/dl በታች
  • በተደጋጋሚ የደም የስኳር መጠናቸው ዝቅ የሚልባቸው ወይም የደም ስኳራቸው ሲያንስ የማይታወቃቸው ታማሚዎች (hypoglycemia unawareness)
  • ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የስኳር በሽታ ማለትም የ3 ወር የስኳር ቁጥጥሮ (HbA1c) 9% እና ከዚያ በላይ ከሆነ 
  • ባለፉት 3 ወራት ዳያቤቲክ ኬቶአሲዶሲስ (DKA) ወይም በጣም ከፍተኛ የስኳር መጨመር (HHS) ካጋጠምዎ
  • እንደ ጉንፋንን ያሉ ኢንፌክሽኖችን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት የህመም ስሜት ከተሰማዎት 
  • ከበሽታዎ ጋር ተያይዞ አይን፣ ኩላሊት፣ ነርቭ ፣ እጅ ወይንም እግር ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ
  • ከዚህ በፊት ሲጾሙ እንደ የደም የስኳር መጠን መቀነስ ወይም ከመጠን በላይ መጨመር ያሉ አሉታዊ ክስተቶች የገጠማቸው ታካሚዎች በሃይማኖታዊ አጿማት  እንዳይሳተፉ ይመከራል። 

            የስኳር በሽታ ታማሚዎች ላይ ከጾም ጋር ተያይዘው ሊደርሱባቸው የሚችሉ የጤና እክሎች ምንድን ናቸው ?

የስኳር በሽታ ሰውነትዎ ምግብን እና ፈሳሽን የሚጠቀምበት መንገድ ላይ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር መጾምዎ ለሌሎች የጤና እክሎች የመጋለጥ እድሎን ሊጨምር ይችላል።

የስኳር በሽታ ካለብዎት እና ለመጾም ከወሰኑ የሚከተሉትን የጤና እክሎች ልብ ይበሉ ፦

  • የደም የስኳር መጠን በጣም ዝቅ ማለት (Hypoglycemia)

    በጾም ጊዜም ሆነ ከፆም በኋላ በደምዎ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በጣም ሊቀንስ ይችላል። በጾም ወቅት የደም የስኳር መጠንዎ በጣም ዝቅ ካለ ወዲያውኑ ጾምዎን በማቋረጥ እንደ ወትሮው ተገቢውን እርምጃ እና ሕክምና ማድረግ ይኖርቦታል።

  • የደም የስኳር መጠን በጣም መጨመር (Hyperglycemia)

    እየጾሙ የደም የስኳር መጠንዎ ከፍ ካለ የሰውነት ፈሳሽ እጥረት (Dehydration) እና ዳያቤቲክ ኬቶአሲዶሲስ (DKA) እንዳይከሰት ለመከላከል ጾምዎን በቂ ውሃ በመጠጣት ማቋረጥ እና ቀደም ሲል ለከፍተኛ የስኳር መጠን የሚያደርጉትን ሕክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው። 

  • የሰውነት ፈሳሽ እጥረት (Dehydration)

    ረዘም ላለ ጊዜ ፈሳሽ አለመጠጣት ለሰውነት ፈሳሽ እጥረት ሊዳርግ ይችላል ፤ በተለይ የደም የስኳር መጠንዎ ከፍተኛ በሚሆበት ጊዜ ችግሩ ይባባሳል። ስለዚህ በማይጾሙባቸው ሰዓታት በቂ ፈስሽ ለመጠጣት ይሞክሩ።   

  • ዳያቤቲክ ኬቶአሲዶሲስ (DKA)

    የዓይነት 1 የስኳር በሽታ (Type 1 diabetes) ያለባቸው ሰዎች በኢንሱሊን እጥረት ምክንያት ለሚመጣውና ለሕይወት አስጊ ለሆነው "ዳያቤቲክ ኬቶአሲዶሲስ" (DKA) ሊጋለጡ ይችላሉ። ስለዚህ እንደ ማስታወክ ፣ የአተነፋፈስ መጨመር እና የሆድ ህመም ያሉ ምልክቶች ካጋጠምዎ በአስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ያግኙ።

        በጾም ወቅት ምን አይነት አመጋገብ ይመከራል?

የስኳር በሽታ ታማሚ ከሆኑ በጾም ወቅት  ከሁሉም የምግብ ቡድኖች የተወጣጡ ምግቦችን ሚዛናዊ በሆነ አግባብ እና መጠን ለመመገብ መሞከር ይኖርብዎታል። በተጨማሪም እንደ ሁልጊዜው ስኳር ወይም ካርቦሃይድሬት የያዙ ምግቦችን ሲጠቀሙ የሚወስዱትን መጠን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለብዎት አይዘንጉ። ጾምዎንም በሚፈቱበት ጊዜ አነስተኛ የስኳር እና የቅባት መጠን ያላቸውን ምግቦች መጠቀም ያለብዎት ሲሆን በተቻልዎት መጠንም በአነስተኛ ዘይት የበሰሉ ምግቦችን ይመገቡ።  

ከዚህ በተጨማሪ በጾም ወቅት ሊያጋጥምዎ የሚችለውን የሰውነት ፈሳሽ ድርቀት ወይም ዲሃይድሬሽን ለማስወገድ የለስላሳ መጠጦችን፣ ቡናን እና ሌሎች ስኳር እና ካፌይን የያዙ መጠጦችን ከመውሰድ ይቆጠቡ።

          በጾም ጊዜ ደህንነትዎን እንዴት ይጠብቃሉ?  

አንዴ ለመጾም ከወሰኑ ደህንነትዎን ለማረጋገጥ የሚከተሉትን እርምጃዎች ይከተሉ

  • የስኳር መጠንዎን በተደጋጋሚ ይለኩ

    የደም የስኳር መጠንዎን ከጾም በፊት፣ በጾም ወቅት፣ ከጾም በኋላ፣ እንዲሁም ጾምዎን ከፈቱ ከሁለት ሰዓት በኋላ መለካት ይኖርቦታል።

  • እየጾሙ ባሉበት ወቅት ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን አያድርጉ 

    ከባድ እንቅስቃሴ የደም የስኳር መጠንዎ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ የትኞቹን እንቅስቃሴዎች ማድረግ እንደሚችሉ ሐኪምዎን ያማክሩ።

  • ከጾም በኋላ በሚመገቡበት ጊዜ የሚወስዱት ምግብ ላይ ጥንቃቄ ያድርጉ

    ከጾም በኋላ ሲመገቡ ከመጠን በላይ ካርቦሃይድሬት (ስኳር እና ስታርች) ያላቸውን ምግቦች አይመገቡ።

  • ሐኪሞን ሳያማክሩ የስኳር በሽታ መድኃኒቶችዎን አያቁሙ ወይም አይቀይሩ

    ሁልጊዜም የሃይማኖት አጿማትን መጾም ከመጀመርዎ በፊት ስለሚወስዷቸው የስኳር በሽታ መድሃኒቶች መጠን እና መቼ መውሰድ እንዳለባቸው ክትትል ከሚያደርግሎት የህክምና ባለሙያ ጋር በሰፊው መወያየት ያስፈልጋል።

Comments (0)