የዲሜንሺያ የመርሳት ችግር እና ጨዋታዎች
የዲሜንሺያ በሽታ የማስታወስ፣ የማገናዘብ እና የእለት ተእለት ኑሮ ተግባርን የሚነካ ህመም ሲሆን ትርጉም ያላቸው ተግባራት የህይወትን ጥራት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ። ይህን ለማድረግ በጣም ቀላል ግን ውጤታማ የሆነው ዘዴ የዲሜንሺያ ታማሚዎች የተለያዩ የጌም ጨዋታዎችን እንዲጫወቱ ማድረግ ነው። የነዚህ ጨዋታዎች ሂደት አንጎልን በማነቃቃት፣ ማህበራዊ መስተጋብርን በማበረታታት እና ስሜታዊ ደህንነትን በመደገፍ የአእምሮ ህመም ላለባቸው ሰዎች ጥቅም ይሰጣል። ይህ ጽሁፍ የጌም ጨዋታዎች ለዲሜንሺያ እንዴት እንደሚረዱ እና የትኞቹ የጨዋታ ዓይነቶች በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰሩ ለቤተሰቦች እና ተንከባካቢዎች ጠቃሚ ምክሮችን ያብራራል።
የመርሳት በሽታን መረዳት
የዲሜንሺያ በሽታ የማስታወስ፣ የማገናዘብ እና የማመዛዘን ችሎታ እየቀነሰ እንዲሄድ የሚያደርጉና የዕለት ተዕለት ኑሮን የሚያደናቅፉ ሁኔታዎችን የሚያመለክት ጃንጥላ መጠርያ ነው። በጣም የተለመደው አይነት የአልዛይመር በሽታ ሲሆን ነገር ግን የመርሳት በሽታ በሌሎች የአእምሮ ችግሮች ምክንያትም ሊከሰት ይችላል።
የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ:-
- የማስታወስ ችሎታን ማጣት
- የቋንቋ ወይም የመግባባት ችግር
- የትኩረት እና የምክንያታዊነት ችግሮች
- የስሜት ወይም የባህሪ ለውጦች
- የተለመዱ ተግባራትን ለማከናወን መቸገር
የመርሳት በሽታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ህመም ቢሆንም የአእምሮ ማነቃቂያ እና ማህበራዊ ተሳትፎ የግንዛቤ ማሽቆልቆልን ለመከላከል እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን ለማሻሻል ይረዳል።
ጨዋታዎች ለምን የአእምሮ ህመም ላለባቸው ሰዎች ጠቃሚ ናቸው?
የጌም ጨዋታዎች የተዋቀረ እና አስደሳች መንገድን አእምሮን ንቁ ለማድረግ በቀላሉ ይሰጣሉ። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የግንዛቤ(ኮግኒቲቭ) ማነቃቂያ የአእምሮ ህመም እየገፋ ቢሄድ እንኳን የአንጎልን ተግባር ሊደግፍ ይችላል።
1. የአንጎል እንቅስቃሴን ያበረታታሉ
ጨዋታዎች ማሰብን፣ ችግር መፍታትን እና ማስታወስን ስለሚያበረታቱ ቅርፆችን እንደማዛመድ ወይም እንቆቅልሽን እንደማጠናቀቅ ያሉ ቀላል ስራዎች የተለያዩ የአንጎል ክፍሎችን ሊያነቃቁ ይችላሉ።
2. ትኩረትን እና ትውስታን ይደግፋል
ተደጋጋሚ ጨዋታ ለማስታወስ እና ለማተኮር የሚያገለግሉ የነርቭ መስመሮችን ያጠናክራል።
3. ማህበራዊ መስተጋብርን ያበረታታል
የጌም ጨዋታዎችን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ስለሚጫወቱ የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች በብዛት የሚገጥማቸውን ብቸኝነት እና መገለልን ለመቀነስ ይረዳል ።
4. ስሜትን ያሻሽላል
አስደሳች የጌም እንቅስቃሴዎችን በሚያከናውኑበት ጊዜ ጭንቀትን እና ድብርትን ይቀንሳሉ።
5. የዕለት ተዕለት ተግባርን ያስቀጥላሉ
አንዳንድ ጨዋታዎች እንደ የእጅና ዓይን መተባበርን፣ ቅደም ተከተል መጠበቅን እና የውሳኔ አሰጣጥ ያሉ ተግባራዊ ክህሎቶችን ያጠናክራሉ።
ጠቃሚ የጨዋታ ዓይነቶች
ሁሉም ጨዋታዎች ለእያንዳንዱ የመርሳት የአይምሮ በሽታ ተስማሚ ባይሆኑም ምርጦቹ ጨዋታዎች ቀላል፣ አሳታፊ እና የሚለመዱ ናቸው።
1. የፐዝል ጨዋታዎች
የፐዝል ጨዋታ ምሳሌዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:-
- የቃል ፍለጋ ጨዋታዎች
- የማዛመድ ጨዋታዎች
እነዚህም ጨዋታዎች ንድፍ መረዳት እና ችግር የመፍታት ክህሎትን ያበረታታሉ።
2. የካርድ እና የቦርድ ጨዋታዎች
የካርድ እና የቦርድ ጨዋታዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:-
- የቢንጎ ጨዋታ
- የዶሚኖ ጨዋታ
- የኡኖ ጨዋታ
እነዚህ ጨዋታዎች ትኩረትን እና ማህበራዊ ተሳትፎን ለማሻሻል ይረዳሉ።
3. የማስታወስ ጨዋታዎች
እነዚህ ጨዋታዎች የማስታወስ መንገዶችን የሚያነቃቁ ስዕሎችን፣ ቃላትን ወይም ሌሎች ነገሮችን በመጠቀም ማስታወስን ማሻሻል ላይ ያተኩራሉ።
4. አካላዊ ጨዋታዎች
እንደ ኳስ መወርወር ወይም ቀለበት መወርወር ያሉ ቀላል አካላዊ እንቅስቃሴዎች ቅንጅትን እና አካላዊ ጤናን ለመጠበቅ ይረዳሉ።
5. ዲጂታል የአንጎል ጨዋታዎች
አንዳንድ የስልክ መተግበሪያዎች እና የኮምፒውተር ጨዋታዎች የግንዛቤ ክህሎቶችን ለማሰልጠን የተነደፉ ሲሆን ለመጫወት ቀላል እና ምቹ መሆን አለባቸው።
ትክክለኛውን ጨዋታ መምረጥ
የመርሳት የአይምሮ በሽታ ላለበት ሰው ጨዋታዎችን በሚመርጡበት ጊዜ የሚከተሉትን ከግንዛቤ ያስገቡ፡-
1. ቀላልነት
ቀላል ደንብ እና ግልጽ መመሪያ ያላቸው ጨዋታዎችን ይምረጡ።
2. የሚታወቅ
አንድ ሰው ቀደም ባለው ህይወቱ የሚወዳቸው እና የሚደሰትባቸው ጨዋታዎች ብዙውን ጊዜ ቀላል እና የበለጠ አስደሳች ናቸው።
3. አጭር ቆይታ
ከ10-20 ደቂቃዎች የሚቆዩ እንቅስቃሴዎች በተሻለ ሁኔታ ሊሰሩ ይችላሉ።
4. ተስማሚነት
እንደ ታማሚው አቅም የጨዋታ ክብደት ደረጃዎችን እና ህጎችን ያስተካክሉ።
ለእንክብካቤ ሰጪዎች እና ቤተሰቦች ጠቃሚ ምክሮች
የሚወዱትን ሰው በአእምሮ ህመም ጊዜ መደገፍ ትዕግስት እና ተለዋዋጭነትን ይጠይቃል።
- ዘና ያለ አካባቢን ይፍጠሩ
እንደ ከፍተኛ ድምጽ ወይም መጨናነቅ ያሉ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን ያስወግዱ።
- በአሸናፊነት ሳይሆን በመደሰት ላይ ያተኩሩ
ግቡ ተሳትፎ እንጂ ውድድር ማሸነፍ አይደለም።
- ለስላሳ መመሪያዎችን ይስጡ
ስህተቶችን ከማረም ይልቅ ፍንጮችን ይስጡ።
- ትናንሽ ስኬቶችን ያድንቁ
ማበረታቻ በራስ መተማመንን እና ተነሳሽነትን ይጨምራል።
- ድካምን ያስወግዱ
ታማሚው ከደከመ ወይም ከተበሳጨ እረፍትን እንዲወስዱ ያድርጉ።
የመርሳት በሽታ እየገፋ ሲሄድ ውስብስብ ጨዋታዎች ከባድ እና ተስፋ አስቆራጭ ሊሆኑ ይችላሉ። በከባድ የመርሳት በሽታ ደረጃዎች እንደሚከተሉት አይነት ቀላል ጨዋታዎችን ይሞክሩ።
- ዕቃዎችን መደርደር
- የፎቶ አልበሞችን በመመልከት
- ሙዚቃ ማዳመጥ እና
- የስሜት ህዋሳት እንቅስቃሴዎች
የጌም ጨዋታዎች ከመዝናኛ በላይም በመሆን የአዕምሮ ህመም ላለባቸው ሰዎች ጠቃሚ የሕክምና መሣሪያ ሊሆኑ ይችላሉ። በአእምሮ ማነቃቂያ፣ ማህበራዊ መስተጋብር እና ስሜታዊ ተሳትፎ ጨዋታዎች ክብርን፣ ነፃነትን እና የህይወት ጥራትን ለመጠበቅ ይረዳሉ።
ያስታውሱ፡- ምርጡ ጨዋታ ፈገግታን፣ ምቾትን እና ግንኙነትን የሚያመጣ ነው።




