ለምን የ "ኮሌስትሮል መድሃኒት" ታዘዘልኝ?

Melat Geatchew
Mar 11, 2026
undefined

ለምን የ "ኮሌስትሮል መድሃኒት" ታዘዘልኝ?

ኮሌስትሮል ምንድን ነው ?

ኮሌስትሮልን በቀላሉ ለመረዳት በደም / በደም ስሮች ውስጥ የሚገኝ ቅባት ነው ልንል እንችላለን። ይህም ከደም ስር እና ልብ ጤና ጋር ከፍተኛ ተያያዥነት አለው። የደም ቅባት መጠን መዛባት (Dyslipidemia) የሚባለው ህመም የደም ውስጥ የኮሌስትሮል ወይም ስብ መጠን ከተለመደው ውጭ ሲዛባ የሚከሰት ነው። ይህ ሁኔታ የልብና የደም ሥር በሽታዎች ተጋላጭነትን ይጨምራል። ተላላፊ ያልሆነ ይህ ህመም፣ ቅባቶች በደም ስር ቧንቧዎች ውስጥ በመከማቸት እንዲዝጉና እንዲደፈኑ በማድረግ ወደ ልብ፣ አንጎል እንዲሁም ወደ ሁሉም የሰውነት ክፍላችን የሚሄድ የደም ፍሰትን ይገድባል።

የኮሌስትሮል ህመም ክብደት፣ የአመጋገብ ዘይቤ፣ ማህበራዊ ሁኔታ፣ የሃብት መጠን፣ ሃይማኖት፣ ዘር፣ እድሜና ጾታ ሳይለይ በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል።

 

የደም ቅባት መዛባት (Dyslipidemia) ዋና ዋና አይነቶች

የደም ቅባት መጠን መዛባት በሶስት ዋና ዋና የህመም አይነቶች ይከፈላል። 

እነዚህም፡-

  • የኮሌስትሮል መብዛት (High Cholesterol): በተለይ “ጎጂ ኮሌስትሮል” (LDL) ሲበዛ
  • የደም የስብ መጠን መብዛት (High Triglycerides)
  • የጥሩ ኮሌስትሮል መጠን ማነስ (Low HDL)

“ጥሩ” እና “ጎጂ” ኮሌስትሮል ምንድን ናቸው?

ኮሌስትሮል በሁለት አይነት ሁኔታ በሰውነታችን ውስጥ ሊገኝ ይችላል፤ ይህም ጥሩ ኮሌስትሮል (Good cholesterol) እና መጥፎ ኮሌስትሮል (Bad cholesterol) በመባል የሚገለጽ ነው።

 

HDL (ጥሩ ኮሌስትሮል): የ HDL ዋና ስራ ኮሌስትሮልን በሰውነት ውስጥ ከሚገኙ ሕብረ ሕዋሳት ወደ ጉበት ማዛወር ነው። ይህ በሰውነት ውስጥ ስብን ለማከፋፈል ይረዳል እና የልብ ችግርን አደጋን ይቀንሳል።

 

VLDL/LDL (ጎጂ ኮሌስትሮል): VLDL ኮሌስትሮል በጉበት ተዘጋጅቶ ወደ ደም ውስጥ ይለቀቃል። የVLDL ቅንጣቶች በዋነኛነት ትራይግሊሰርይድ የተባለውን የስብ አይነት ወደ ሰውነታችን (ቲሹ) ያጓጉዛሉ። VLDL ከ LDL ኮሌስትሮል ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ LDL በዋነኝነት ኮሌስትሮልን ወደ ቲሹዎች ያጓጉዛል (ይህም ለደም ስር መዘጋት አስተዋጽኦ ያደርጋል)።

 

ምርመራ እና መደበኛ መጠን

የሊፒድ ፕሮፋይል (Lipid Profile) የተባለው የደም ምርመራ ስለ አንድ ሰው የልብና የደም ሥር ጤንነት ጠቃሚ መረጃ ይሰጣል።

 

የተለመደው (Normal) የኮሌስትሮል መጠን

ከ 20-39 ዕድሜ፡

  • አጠቃላይ ኮሌስትሮል < 200 mg/dL
  • LDL ኮሌስትሮል < 100 mg/dL
  • HDL ኮሌስትሮል > 40 mg/dL
  • Triglycerides < 150 mg/dL

ከ 40-59 ዕድሜ፡

  • ጠቅላላ ኮሌስትሮል < 200 mg/dL
  • LDL ኮሌስትሮል < 70 mg/dL (የልብ ህመም ወይም የስኳር ህመም ካለ)
  • HDL ኮሌስትሮል > 40 mg/dL
  • Triglycerides < 150 mg/dL

ከ 60 በላይ ዕድሜ፡

  • ጠቅላላ ኮሌስትሮል < 200 mg/dL
  • LDL ኮሌስትሮል < 70 mg/dL (የልብ ህመም ወይም የስኳር ህመም ካለ)
  • HDL ኮሌስትሮል > 40 mg/dL
  • Triglycerides < 150 mg/dL

ማሳሰቢያ: እነዚህ አጠቃላይ መመሪያዎች ብቻ መሆናቸውን ልብ ሊባል ይገባል። ለልብ በሽታ በሚያጋልጡ ሌሎች ሁኔታዎች ላይ በመመስረት የእርስዎ የግል ኮሌስትሮል ኢላማዎች ሊለያዩ ይችላሉ።

የኮሌስትሮል መብዛት ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ከፍተኛ ኮሌስትሮል መጠን ለብዙ ሰዎች ምንም ዓይነት ምልክት አያሳይም (ምልክት አልባ ነው)። ከፍተኛ ኮሌስትሮል በሰውነትዎ ውስጥ ሌሎች ችግሮችን እስኪያመጣ ድረስ ምንም ዓይነት ምልክቶች ላያዩ ይችላሉ።

ከፍተኛ ኮሌስትሮል እንዳለ ለማወቅ ብቸኛው መንገድ የደም ምርመራ በማድረግ ነው!

ኮሌስትሮልን እንዴት ዝቅ ማድረግ ይቻላል?

የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች መደበኛ የኮሌስትሮል መጠንን ወደነበሩበት ለመመለስ ይረዳሉ።

 

  • የአካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማዘውተር
  • ልከኛ የሰውነት ክብደት እና የሰውነት ስብ መጠን መያዝ
  • እንዲሁም የአልኮል መጠጥ እና ሲጋራን ማስወገድ  ይህን የጤና እክል ለመከላከልም ሆነ ለመቆጣጠር ይረዳል።
  • የእግር ጉዞ ማድረግ
  • ከሁሉም በላይ ደግሞ የኮሌስትሮል መጠንን የሚቀንሱ ምግቦችን መመገብ። (ለምሳሌ፡- አጃ፣ አቮካዶ፣ እና ኦሜጋ 3 የያዙ እንደ አሳ ያሉ ምግቦች)

ኮሌስትሮልን የማከም ዋነኛ ጥቅሞች

ኮሌስትሮል በመድሃኒትም ሆነ ያለመድሃኒት (በአኗኗር ለውጥ) እንዲቀንስ የሚመከረው ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ከባድ የጤና እክሎች ለመከላከል ነው።

 

1. ድንገተኛ የልብ ድካም (Heart Attack) መከላከል

ይህ የደም ስር መጥበብ ልብ ላይ ሲከሰት የደረት ህመም ያመጣል። በተለይም እንቅስቃሴ በምናደርግበት ጊዜ ልባችን ደም ማዳረስ ስለሚያቅተው ሰቅዞ የሚይዝ የደረት ህመም ያስከትላል። ይህ ህመም ወደ ክንድ፣ አንገት፣ ሆድ ወይም ጀርባ ሊሰራጭ ይችላል። የልብ ጡንቻ የደም ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ ሲገደብ ድንገተኛ የልብ ድካም (Heart attack) የሚባል ገዳይ አደጋ ይደርሳል።

 

2. ስትሮክን (Stroke) መከላከል

ወደ አንጎላችን የሚሄደው የደም ስር ሲጎዳ ደግሞ ድንገተኛ የአንጎል መታወክ (ስትሮክ) ይባላል። ለአንጎል የሚሄደው የደም አቅርቦት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ሲስተጓጎል የሚከሰት ነው። ይህም እንደ ደረጃው ሙሉ ሰውነትን ፓራላይዝ ከማድረግ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።

 

3. ፔሪፌራል አርተሪያል ዲዚዝ እና ጋንግሪን (Gangrene) መከላከል

ወደ እግር የሚሄደው የደም ፍሰት ሲቋረጥ (Peripheral Arterial Disease) ደግሞ ጋንግሪን (Gangrene) ያመጣል። በደቂቃዎች ውስጥ የተዘጋው ደም በህክምና ወይም በኦፕሬሽን እንዲስተካከል ካልተደረገ፣ ይህ ሁኔታ እስከ እግር ወይም እጅ መቆረጥ ሊያደርስ ይችላል።

የስኳር ታካሚ ነኝ, ቅባት አልበላም፣ ለምን የ "ኮሌስትሮል መድሃኒት" ታዘዘልኝ?

የስኳር ህመም ልዩ የሆነ የደም ቅባት መዛባት ያመጣል! ይህም ከአመጋገብዎ ጋር በቀጥታ አይገናኝም!

ይህ የደም ቅባት መዛባት (Diabetic Dyslipidemia) ከተለመደው "የኮሌስትሮል መጨመር" የተለየ ነው።

ስኳር ታማሚዎች ላይ (ከሌላው በተለየ)፦

  • የመጥፎው ኮሌስትሮል (LDL-Cholesterol) መጠን ኖርማል የሆነ ወይም ብዙም ሳይጨምር 
  • የመጥፎው ኮሌስትሮል ቅንጣቶች (LDL particles) ትናንሽና ጥቅጥቅ የሆኑ ናቸው!

ይህ የባህሪ ለውጥ ኮሌስትሮል በቀላሉ ወደ ደም ስር ግድግዳዎች ገብቶ ጉዳት እንዲያስከትል ያደርጋል።

 

ይህ ምን ማለት ነው?

  • በስኳር በሽታ ውስጥ መታሰብ ያለበት የኮሌስትሮል መጠን ብቻ ሳይሆን የኮሌስትሮል ባህሪ ነው።
  • መጥፎው ኮሌስትሮል ልኬት ብዙም ሳይጨምር የልብና የደም ስር አደጋን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል። 
  • ለዚህም ነው የኮሌስትሮል መድሃኒቶች ለብዙ የስኳር ህመምተኞች እንዲወስዱ የሚመከሩት።

ኮሌስትሮልን ለመቀነስ እንዴት እንመገብ?

ኮሌስትሮል በአብዛኛው በሰውነታችን ውስጥ በተለይ በጉበት ውስጥ የሚመረት ሲሆን አነስተኛ መጠን ደግሞ ከምንመገበው ምግብ (በተለይ ከእንስሣት ተዋጽዖዎች) ጋር ተያይዞ በሰውነታችን ውስጥ ይገኛል ፤ ይህም ቢሆን ግን አመጋገባችንን በመቆጣጠር በሰውነታችን ውስጥ ሊገኝ የሚችል አላስፈላጊ ኮሌስትሮልን ልንቆጣጠረው እንችላለን።

በሕክምና ወቅት ኮሌስትሮልን ለመቀነስ ስናስብ እንድንቀንስ የሚፈለገው መጥፎውን ኮሌስትሮል (LDL) ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ጥሩ የሚባለውን የኮሌስትሮል አይነት (HDL) መጨመር እንፈልጋለን። 

 

አመጋገባችንን ውስጥ ምን ብናካትት መጥፎ የሚባለውን የኮሌስትሮል አይነት መቀነስ እንችላለን?

እንደ አጠቃላይ አመጋገባችን አትክልት እና ፍራፍሬ ተዋጽዖዎች እና ጤናማ ቅባቶች ላይ ዋነኛ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል። ስለዚህ እለት እለት በእያንዳንዱ ምግባችን ውስጥ በቂ አትክልት ማካተት እና በቀን ውስጥ በቂ ፍራፍሬ መመገባችንን እርግጠኛ መሆን ይኖርብናል። 

በተጨማሪም በልዩ ትኩረት እነዚህን የምግብ አይነቶች ብንዘወትር ይጠቅማል።

1.  ያልተፈተጉ እህሎች በተለይ አጃ

2.  ጥራጥሬዎች (ድፍን ምስር፣ ባቄላ፣ አተር፣ ቦሎቄ ወዘተ)

3.  አትክልቶች በተለይ ደበርጃን (Egg plant) እና ባሚያ (Okra)

4.  የቅባት እህሎች (ተልባ፣ ለውዝ እና የለውዝ ዝርያዎች

5.  ፍራፍሬዎች (ፖም፣ እንጆሪ፣ ወይን፣ አቮካዶ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ እና ተመሳሳይ ዝርያዎች)

6.  የወይራ ዘይት

በተቃራኒው ማስወገድ ያለብን የምግብ አይነቶች ደግሞ

1.  በጥልቅ ዘይት / ቅባት የተጠበሱ ምግቦች

2.  ከፍተኛ የስብ መጠን / ጮማ

3.  ከፍተኛ የጨው መጠን 

4.  በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና የታሸጉ ምግቦች

5.  ስኳር እና ልዩ ልዪ ተፈጠሮአዊ ያልሆኑ ማጣፈጫዎች ናቸው።

Comments (0)