የማህደረ ቆለጥ እብጠት

Eyasu Yebeltal
Jul 24, 2025
undefined

 የማህደረ ቆለጥ እብጠት

የማህደረ ቆለጥ እብጠት የወንድ የዘር ፍሬን የያዘው ከረጢት ከተፈጥሮአዊ መጠኑ እየተለቀ ሲሄድ የሚፈጠር ሁኔታ ሲሆን ከትንሽ እስከ ከባድ ድረስ ብዙ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ። ሰለማህደረ ቆለጥ እብጠት ማወቅ ያለቦትን በዚህ ጽሁፍ እነሆ። እብጠቱ ህመም የሌለው ወይም ያለው፣ ድንገተኛ ወይም ቀስ በቀስ የሚከሰት እንዲሁም አንዱን ወይም ሁለቱንም ሊጎዳ ሲችል አንዳንድ ጊዜ ለስላሳ፣ አንዳንድ ጊዜ ጠንከር ያለ እና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከመቅላት ወይም ከሙቀት ጋር አብሮ ይመጣል።

መንስኤዎች

የሚከተሉትን ጨምሮ፣ በርካታ ሁኔታዎች የማህደረ ቆለጥ እብጠትን ሊያስከትሉ ይችላሉ:-

1.ሃይድሮሴሌ

 

  • ሃይድሮሴሌ በወንድ የዘር ፍሬ ዙሪያ ፈሳሽ ማከማቸት ነው።
  • ህመም የሌው እብጠት እና ለስላሳ ማህደረ ቆለጥ ዋነኛ ምልክቶቹ ናቸው።
  • በማንኛውም ዕድሜ ሊከሰት ሲችል አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ላይ በብዛት ይታያል።

2.ቫሪኮሴሌ

  • በእግር ላይ ከሚከሰተው የደም መላሽ ቧዋንቧዎች እብጠት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን የማህደረ ቆለጥ ደም መላሽ ቧዋንቧዎች እብጠት ሲኖራቸው ይከሰታል።
  • ህመም፣ የማህደረ ቆለጥ ክብደት ስሜት እና ሲታይ ወይም ሲነካ ብዛት ያላቸው ትሎች  ስብስብ መምሰል ዋነኛ ምልክቶች ናቸው።
  • ታዳጊዎች እና ወጣቶችላይ በብዛት ይከሰታል።

3.ኢንጓይናል ሄርኒያ

  • አንጀት በደካማ የሆድ ክፍል ጡንቻዎች በኩል ወደ ብሽሽት ወይም ማህደረ ቆለጥ ሲገፋ ይከሰታል።
  • በሚቆሙበት ወይም ሰውነቶ በሚወጠርበት ጊዜ የእብጠቱ መጠን ይጨምራል። 
  • ከባድ የሆነ ህመም በድንገት ከጀመረ የአንጀት መታነቅ እና የደም ዝውውር መቋረጥ ምልክት ሊሁን ስለሚችል ድንገተኛ ቀዶ ጥገና ሊያስፈልግ ይችላል።

4.ኢንፌክሽን

  • የኢፒዲዲሚስ ወይም የወንድ የዘር ፍሬ ኢንፌክሽን ወይም እብጠት ሌላኛው መንስኤ ነው።
  • ህመም ያለው እብጠት፣ መቅላት፣ ትኩሳት እና በሽንት ጊዜ ህመም ተጠቃሽ ምልክቶች ናቸው።
  • ብዙውን ጊዜ በባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች ወይም በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ምክንያት ይከሰታል።

5.የወንድ የዘር ፍሬ መዞር

  • በወንድ የዘር ፍሬ መዞር ምክንያት የዘር ፍሬ የደም አቅርቦትን ሲቋረጥ ይከሰታል።
  • ድንገተኛ ከባድ ህመም፣ እብጠት፣ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ምልክቶች ናቸው።
  • የወንድ የዘር ፍሬን ለማዳን አፋጣኝ ሕክምና ያስፈልጋል።

6.ካንሰር

  • በወንድ የዘር ፍሬ የካንሰር እድገት ምክንያት ይከሰታል።
  • በወንድ የዘር ፍሬ ላይ ህመም የሌለው እብጠት እና በማህደረ ቆለጥ ውስጥ የክብደት ስሜት ተጥዕቃሽ ምልክቶች ናቸው።
  • ይህን ህመም ቀደም ብሎ ሳይስፋፋ ማግኘት ቁልፍ ሲሆን በአፋጣኝ ህክምና መዳን ይችላል።

ህክምና ቦታ መቼ መሄድ ያስፈልጋል?

እነዚህን ምልክቶች ካስተዋሉ በአፋጣኝ የህክምና እርዳታን ይፈልጉ፡-

  • ድንገተኛ ወይም ከባድ የማህደረ ቆለጥ ህመም ወይም እብጠት
  • የማይጠፋ እብጠት
  • መቅላት ወይም ትኩሳት
  • በሚሸኑበት ጊዜ ህመም ወይም ያልተለመደ ፈሳሽ
  • አደጋ ከደረሰ በኋላ የሚፈጠር የማህደረ ቆለጥ እብጠት

ምርመራ 

የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎ መንሳኤውን ለመለየት የሚከተሉትን ሊጠቀም ይችላል፡-

  • የአካል ምርመራ
  • የአልትራሳውንድ ምስል
  • የሽንት ምርመራዎች ወይም የደም ምርመራዎች

ሕክምና

የማህደረ ቆለጥ እብጠት ሕክምና እንደ መንስኤው ይወሰናል።

  • ሃይድሮሴሌ፡- ብዙውን ጊዜ በራሱ ሲፈታ አንዳንዴ ትንሽ ቀዶ ጥገና ሊያስፈልገው    ይችላል።
  • ኢንፌክሽኖች፡- በጸረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶች ይታከማሉ።
  • ቫሪኮሴሌ፡- ህመም ወይም መሃንነትን የሚያስከትል ከሆነ ቀዶ ጥገና ሊያስፈልግ ይችላል።
  • ኢንጓይናል ሄርኒያ፡- ብዙውን ጊዜ በቀዶ ጥገና ይታከማል።
  • የወንድ የዘር ፍሬ መዞር፡- የአደጋ ጊዜ ቀዶ ጥገና ያስፈልጋል።
  • ካንሰር፡- ልዩ የካንሰር ህክምና ያስፈልገዋል።

የዘር ፍሬ ጤናዎን እንዴት መጠበቅ ይችላሉ?

  • እብጠት ወይም ለውጦችን ለመለየት መደበኛ የራስ ምርመራ ያድርጉ።
  • ኢንፌክሽንን ለመከላከል ደህንነቱ የተጠበቀ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ያድርጉ።
  • ጊዜያዊ እንክብካቤ ወደ ተሻለ ውጤት ስለሚመራ ህመምን ወይም እብጠትን ችላ አይበሉ።

አብዛኛዎቹ የዘር ፍሬ እብጠት መንስኤዎች በህክምና ቢድኑም፣ አንዳንዶቹ በጣም ከባድ ሊሆኑ ስለሚችሉ ችላ ሊባል የሚገባው ነገር አይደለም። ስለ እብጠቶ እርግጠኛ ካልሆኑ ሁልጊዜ የጤና እንክብካቤ አቅራቢዎን ማነጋገር የተሻለ ነው።

Comments (0)