የከፍተኛ የኮርቲሶል (Cortisol) መጠን ምልክቶች እና መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
ኮርቲሶል (Cortisol) ምንድን ነው?
ኮርቲሶል ብዙውን ጊዜ 'የጭንቀት ሆርሞን' ተብሎ የሚጠራ ፤ ኩላሊቶች ላይ በሚገኙ 'አድሬናል' በተባሉ እጢዎች(adrenal glands) የሚመነጭ ስቴሮይድ ሆርሞን ነው። ይህ ሆርሞን ሰውነት ለጭንቀት ምላሽ እንዲሰጥ የሚረዳ ሲሆን የሰውነትን ጤና በመጠበቅ ረገድም ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ኮርቲሶል ሰውነታችን ስኳርን (ግሉኮስን) ለኃይል እንዴት መጠቀም እንዳለበት የሚቆጣጠር፣ ብግነትን የሚቀንስ፣ የደም ግፊትን የሚያስተካክል እና የእንቅልፍ ዑደትን የሚቆጣጠር ጠቃሚ ሆርሞን ነው።
ሰውነታችን የኮርቲሶል መጠን ተመጣጣኝ ሆኖ እንዲቀጥል በጥንቃቄ ይቆጣጠራል። ይህ ሳይሆን ሲቀር እና የኮርቲሶል መጠን በጣም ከፍተኛ ወይም በጣም ዝቅተኛ ሲሆን ግን በጤናችን ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
ከፍተኛ የኮርቲሶል መጠን (High Cortisol Levels)
ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ ከፍተኛ የኮርቲሶል መጠን ያጋጥመዋል። ይህ መጠን በቀን ውስጥ በተፈጥሮ የሚለዋወጥ ሲሆን ሰውነት ለጭንቀት ወይም ሊያጋጥም ለሚችል አደጋ የሚሰጠው መደበኛ ምላሽ አካል ነው።
ይሁን እንጂ ሰውነት ለረጅም ጊዜ ከመጠን በላይ ኮርቲሶል ካመረተ ከጤና ጋር የተያያዘ ችግር መኖሩን ሊያመለክት ይችላል።
በዚህ ፅሁፍ ከፍተኛ የኮርቲሶል መጠን ሲያጋጥም ስለሚኖሩ ምልክቶች ፣ ስለ መንስኤዎቹ እና መቼ ሐኪም ማማከር እንደሚያስፈልግ እናያለን።
የከፍተኛ ኮርቲሶል መጠን ምልክቶች
ከፍተኛ የኮርቲሶል መጠን የተለያዩ ምልክቶችን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን ምልክቶቹም በምን ያህል የኮርቲሶል መጠኑ ከፍ እንዳለ እንዲሁም መጠኑ እንዲጨምር ባደረጉት መንስኤዎች ሊለያዩ ይችላሉ። ከእነዚህም ምልክቶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
- ክብደት መጨመር ፤ ይህም አብዛኛውን ጊዜ በፊት እና በሆድ ላይ ይታያል
- ብጉር (Acne)
- የቆዳ መሳሳት
- የቆዳ በቀላሉ መበለዝ
- የፊት መቅላት
- ቁስል ቶሎ አለመዳን
- የጡንቻ መዛል
- ከፍተኛ የድካም ስሜት
- መነጫነጭ
- ትኩረት የማድረግ ችግር
- ከፍተኛ የደም ግፊት
- ራስ ምታት
የከፍተኛ ኮርቲሶል መጠን መንስኤዎች
ኮርቲሶል ሰውነት ለውጥረት ምላሽ እንዲሰጥ የሚረዳ እና በአድሬናል እጢዎች የሚመነጭ ሆርሞን ነው። የዚህ ሆርሞን መመረት ከአንጎል በሚመጡ ምልክቶች ቁጥጥር ይደረግበታል። የኮርቲሶል መጠን ሲቀንስ፣ አንጎል አድሬናል እጢዎች ተጨማሪ ኮርቲሶል እንዲያመርቱ ምልክት የሚሰጡ ሆርሞኖችን ይለቃል። ሆኖም ግን የተወሰኑ የጤና ሁኔታዎች ሰውነት ከመጠን በላይ ኮርቲሶል እንዲያመርት ሊያደርጉ ይችላሉ። እነዚህም
- ረጅም ጊዜ የቆየ ወይም ሥር የሰደደ ውጥረት(Chronic Stress)
ውጥረት የሰውነትን "የመወጋት ወይም የመሸሽ" (fight-or-flight) ምላሽን በመቀስቀስ የአድሬናል እጢዎች ኮርቲሶል እና አድሬናሊን የተባሉ ሆርሞኖች እንዲለቁ ያደርጋል። ይህ ምላሽ የልብ ምትን እና ኃይልን በመጨመር ሰውነት ለሚያጋጥመው አደጋ ዝግጁ እንዲሆን ይረዳል።
በመደበኛ ሁኔታ ውጥረቱ ሲወገድ የኮርቲሶል መጠን ወደ ነበረበት ይመለሳል። ነገር ግን ለረጅም ጊዜ የቆየ ውጥረት ሲኖር የኮርቲሶል መጠን ከፍ ብሎ እንዲቆይ ያደርጋል ። ይህም እንደ የልብ ሕመም እና ስትሮክ ላሉ የጤና ችግሮች የመጋለጥ እድልን ሊጨምር ይችላል።
- የፒቱታሪ እጢ (Pituitary Gland) እክሎች
ፒቱታሪ እጢ በሰውነት ውስጥ የብዙ ሆርሞኖችን ሥራ የሚቆጣጠር በአንጎል ስር የሚገኝ እጢ ነው። በዚህ እጢ ላይ የሚፈጠሩ ዕጢዎች (Tumors) ወይም ሌሎች ችግሮች ከመጠን በላይ አድሬኖኮርቲኮትሮፒክ (ACTH) የተባለ ሆርሞን እንዲያመርት ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህ ሆርሞን ደግሞ አድሬናል እጢዎች ተጨማሪ ኮርቲሶል እንዲለቁ ምልክት ይሰጣል።
- አድሬናል እጢ ላይ የሚፈጠሩ ዕጢዎች (Adrenal gland tumors)
አድሬናል እጢ ላይ የሚፈጠሩ ዕጢዎችም ከመጠን በላይ ኮርቲሶል እንዲመነጭ ሊያደርጉ ይችላሉ። አብዛኛዎቹ የአድሬናል እጢ ላይ የሚፈጠሩ ዕጢዎች ገራም ወይም ካንሰር ያልሆኑ (benign) ዕጢዎች ቢሆኑም ከፍተኛ መጠን ያለው የኮርቲሶል ሆርሞን ሊለቁ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ዕጢዎቹ ትላልቅ ከሆኑ ሆድ አካባቢ ምቾት ማጣት ወይም የሆድ መነፋት ስሜት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
- አንዳንድ መድኃኒቶች
እንደ ኮርቲኮስቴሮይድ(corticosteroids) ያሉ አንዳንድ መድኃኒቶች በከፍተኛ መጠን ወይም ለረጅም ጊዜ ሲወሰዱ የኮርቲሶል መጠንን ሊጨምሩ ይችላሉ። ስለዚህ እነዚህን መድኃኒቶች ሁልጊዜም በትክክል በታዘዙት መሠረት መወሰድ የሚያስፈልግ ሲሆን ያለ ሐኪም መመሪያም በድንገት መቆም የለባቸውም።
መቼ ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል?
ከፍተኛ የኮርቲሶል መጠን እንዳለብዎ ከጠረጠሩ ሐኪምዎን ቢያማክሩ የተሻለ ነው። የከፍተኛ ኮርቲሶል መጠን ምልክቶች ግልጽ ላይሆኑ እና በሌሎች የጤና እክሎች ምክንያትም ሊከሰቱ ይችላሉ። ስለዚህ ምልክቶቹን ካስተዋሉ ትክክለኛውን ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው።ሐኪምዎም ሊያዝልዎት ከሚችላቸው ምርመራዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
- የደም ወይም የሽንት ምርመራ
እነዚህ በሰውነትዎ ውስጥ ያለውን የኮርቲሶል መጠን ይለካሉ። የሽንት ምርመራው አብዛኛውን ጊዜ ለ24 ሰዓታት ሽንትዎን በመሰብሰብ ይሰራል።
- የምራቅ ምርመራ
በሌሊት የሚወሰድ የምራቅ ናሙና የኮርቲሶል መጠንዎ ከመደበኛው በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ይረዳል። በመደበኛ ሁኔታ የኮርቲሶል መጠን በሌሊት ይቀንሳል።
- የምስል ምርመራዎች (Imaging tests)
እንደ ኤም.አር.አይ (MRI) ያሉ ምርመራዎች በፒቱታሪ እና በአድሬናል እጢዎች ላይ እብጠት(ዕጢ) ወይም ሌሎች ችግሮች መኖራቸውን ለማየት ሊረዱ ይችላሉ።
ከጊዜ በኋላ ከፍተኛ የሆነ የኮርቲሶል መጠን እንደ የልብ ሕመም፣ የአጥንት መሳሳት (osteoporosis) እና የስኳር በሽታ ላሉ የጤና ችግሮች የመጋለጥ እድልን ይጨምራል። ስለዚህ የምርመራ ውጤትዎ ከፍተኛ የኮርቲሶል መጠንን ካሳየ ሐኪምዎ መንስኤውን በመለየት ተገቢውን ሕክምና ያደርግሎታል።
የኮርቲሶል መጠኔን እንዴት መቀነስ እችላለሁ?
የኮርቲሶል መጠንን ለመቀነስ እና አጠቃላይ ጤናን ለመደገፍ የሚረዱ በርካታ ቀላል የዕለት ተዕለት ልማዶች አሉ።እነዚህም
- ጥሩ ጥራት ያለው እንቅልፍ ማግኘት
እንደ እንቅልፍ ማጣት (insomnia) ያሉ የእንቅልፍ ችግሮች ወይም የሌሊት ፈረቃ ስራ መሥራት የኮርቲሶል መጠንን ሊጨምሩ ይችላሉ።
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ
አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጭንቀትን ለመቀነስ እና እንቅልፍን ለማሻሻል ይረዳል።
- በጥልቀት መተንፈስ
ቀስ ብሎ ቁጥጥር ባለው መንገድ መተንፈስ የሰውነትን "የዕረፍት እና የምግብ መፈጨት" ሥርዓት (parasympathetic nervous system) ያነቃቃል። ይህም ኮርቲሶልን ለመቀነስ ይረዳል።
- ለመዝናናት እና ለመሳቅ ጊዜ መመደብ
መሳቅ እና የሚወዷቸውን ተግባራት ማከናወን ጥሩ ስሜት እንዲሰማዎት የሚያደርግ ሲሆን የጭንቀት ሆርሞኖችንም ለመቀነስ ይረዳል።
- ጤናማ ግንኙነቶችን መመስረት
እርስ በርስ የሚደጋገፉባቸውን ግንኙነቶች መመስረት ጭንቀትን ለመቀነስ የሚረዱ ሲሆኑ ግጭት ወይም ውጥረት ያለባቸው ግንኙነቶች ደግሞ የኮርቲሶል መጠንን ሊጨምሩ ይችላል።
ስለዚህ በዕለት ተዕለት ልምዶ ላይ ትናንሽ እና ቀጣይነት ያላቸው ለውጦችን በማድረግ በጊዜ ሂደት ጤናማ የኮርቲሶል መጠን እንዲኖርዎት ያድርጉ።




