ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ (Hidradenitis suppurativa)

Biruh Tesfaye
Mar 12, 2026
undefined

ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ (Hidradenitis suppurativa) ወይም አክኒ ኢንቨርሳ (acne inversa) ተብሎ የሚጠራው፣ ከቆዳ በታች ትናንሽና አሳማሚ እብጠቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርግ የጤና እክል ነው። እነዚህ እብጠቶች ብዙውን ጊዜ የሚወጡትየላብ እጢዎች ባሉባቸው የፀጉር ቀዳዳዎች እና ቆዳና ቆዳ በሚተካሹባቸው የሰውነት ክፍሎች ላይ ነው፤ ለምሳሌ እንደ ብብት፣ ብሽሽት፣ መቀመጫ እና ጡት ስር ባሉ ቦታዎች። እብጠቶቹ ለመዳን ረጅም ጊዜ የሚወስዱ፣ ተደጋጋሚ የሆኑ፣ እንዲሁም ከቆዳ በታች እንደ መተላለፊያ ቦይ ወይም መግል የያዘ ቁስል ሊፈጥሩና ጠባሳ ሊተዉ የሚችሉ ናቸው። ቁስሎቹ እንደ ብጉር ወይም ምች (herpes) ያሉ ሌሎች የቆዳ በሽታዎችን ሊመስል ይችላል።

ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ አብዛኛውን ጊዜ የሚጀምረው ከጉርምስና በኋላ ሲሆን፣ በተለይም ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ ይከሰታል። ይህ ሁኔታ ከ 100 ሰዎች ውስጥ በአንዱ ላይ ሊከሰት እንደሚችል ይገመታል። በሽታው ለብዙ ዓመታት ሊቆይ እና በጊዜ ሂደት እየባሰ ሊሄድ ይችላል። ይህም በእለት ተእለት ኑሮዎ እና በስሜታዊ ጤንነትዎ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። የመድኃኒት እና የቀዶ ጥገና ሕክምናዎችን በማጣመር የሚሰጥ ህክምና በሽታውን ለመቆጣጠር እና ተያያዥ ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል።

ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ የሚከሰተው የፀጉር ቀዳዳዎች ሲደፈኑ ነው፤ ነገር ግን ይህ መደፈን ለምን እንደሚከሰት በትክክል አይታወቅም። ባለሙያዎች እንደሚገምቱት ከሆነ ግን ይህ ሁኔታ ከሆርሞን፣ ከዘር ተያያዥነት፣ ከሲጋራ ማጨስ ወይም ከክብደት መጨመር ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል። ኢንፌክሽን ወይም በቂ ንጽህና አለመጠበቅ ለሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ መንስኤ አይደሉም፤ እንዲሁም በሽታው ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው አይተላለፍም።

ለሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች 

ለሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ የመጋለጥ እድልን የሚጨምሩ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፦

  • ዕድሜ፦ በሽታው የመከሰት ዕድሉ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል እና በ20ዎቹ ውስጥ ባሉ ወጣቶች ላይ ከፍተኛ ነው።
  • ጾታ፦ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
  • ዘር/ብሔር፦ ዘር ወይም ብሔር በአደጋው መጠን ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። ይህ የጤና እክል በብዛት የሚታየው በጥቁር ሕዝቦች ላይ ሲሆን፣ ይህም ምናልባት ከዘር (genetic) ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። በጥናቶች መሠረት፣ በጥቁር ማህበረሰብ ውስጥ በሽታው የመከሰት ዕድሉ ከሌሎች ዘሮች ጋር ሲነፃፀር እስከ 3 እጥፍ ሊበልጥ ይችላል።
  • የቤተሰብ ታሪክ፦ ለበሽታው የመጋለጥ ዝንባሌ ከቤተሰብ ሊወረስ ይችላል። ከሶስት ታካሚዎች መካከል አንዱ (አንድ-ሶስተኛው) የመጀመሪያ ደረጃ የቅርብ ዘመድ (ለምሳሌ ወላጅ፣ ወንድም ወይም እህት) በዚህ በሽታ እንደተጠቃ ይናገራሉ።
  • ተያያዥ የጤና ሁኔታዎች፦ ከመጠን በላይ ውፍረት ባላቸው ሰዎች ላይ በሽታው በብዛት የሚታይ ሲሆን የሕመሙ መጠንም ከባድ ይሆናል። በተጨማሪም ከከባድ ብጉር፣ የመገጣጠሚያ ብግነት፣ ከስኳር በሽታ፣ ከሜታቦሊክ ችግሮች እና ከአንጀት ቁስለት (IBD) ጋር ግንኙነት አለው።
  • ማጨስ፦ ማጨስ ከሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ መከሰት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ተደርሶበታል። በኒኮቲን እና በሌሎች ንጥረ ነገሮች ምክንያት የቁስል የመዳን ሂደትን ሊያዘገይ እና የፀጉር ቀዳዳዎች መደፈንን ሊያስከትል ይችላል።
  • ከመጠን በላይ የሆነ የፀጉር እድገት (ሂርሱቲዝም/Hirsutism)።

የሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ ምልክቶች

ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ በአንድ ወይም በብዙ የሰውነት ክፍሎች ላይ ሊከሰት ይችላል። አንዳንድ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች መጠነኛ ምልክቶች ብቻ ሊታዩባቸው ይችላሉ። የበሽታው አካሄድ ከሰው ሰው በእጅጉ ይለያያል። ከመጠን በላይ ውፍረት እና ሲጋራ ማጨስ ከከባድ ምልክቶች ጋር የተያያዙ ቢሆንም፣ ክብደታቸው አነስተኛ የሆኑና ሲጋራ የማይጠጡ ሰዎችም ቢሆኑ ከባድ ሕመም ሊያጋጥማቸው ይችላል።

የበሽታው ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • ጥቁር ነጥቦች (Blackheads)፦ በቆዳ ላይ በትናንሽ ጉድጓድ መሰል ቦታዎች ላይ የሚታዩ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ በጥንድ በጥንድ ሆነው ይወጣሉ።
  • ህመም ያላቸው የባቄላ ፍሬ የሚያክሉ እብጠቶች፦ በሽታው ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው ከቆዳ በታች በሚወጣና ለሳምንታት ወይም ለወራት በሚቆይ አንድ ህመም ያላው እብጠት ነው። በኋላ ላይ ተጨማሪ እብጠቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤ በተለይም የላብ እጢዎች በሚበዙባቸው ወይም ቆዳና ቆዳ በሚተካሹባቸው ቦታዎች ላይ (ብብት፣ ብሽሽት፣ መቀመጫ እና ጡት ስር) ይወጣሉ። እብጠቶቹ በአንገት ጀርባ (nape of the neck)፣ በወገብ ዙሪያ (waistband) እና በውስጠኛው የጭን ክፍል ላይም ሊወጡ ይችላሉ። እነዚህ እብጠቶች በመድኃኒት ካልተገቱ፣ መጠናቸው እየጨመረ ሊሄድና ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጩ ይችላሉ።
  • ፈሳሽ የሚያወጡ እብጠቶች ወይም ቁስሎች፦ አንዳንድ እብጠቶች ወይም ቁስሎች እያበጡ ይሄዱና ተሰንጥቀው መጥፎ ሽታ ያለው መግል ያወጣሉ።
  • የቆዳ ስር መተላለፊያ ቦዮች (Tunnels)፦ በጊዜ ሂደት እብጠቶቹን እርስ በእርስ የሚያገናኙ የቆዳ ስር ቦዮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። እነዚህ ቁስሎች በጣም በዝግታ ይድናሉ (አንዳንዴም ጨርሶ አይድኑም)፤ እንዲሁም ደም እና መግል ያወጣሉ።

አንዳንድ እብጠቶች በባክቴሪያ ሊበከሉ ይችላሉ፤ ይህም ተጨማሪ ኢንፌክሽን እንዲፈጠር ስለሚያደርግ በፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶች መታከም ያስፈልገዋል።

የሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ ምርመራ 

ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ በቀላሉ ከወትሮው ብጉር ወይም ሽፍታ ጋር ሊመሰል ይችላል። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ትክክለኛውን የምርመራ ውጤት ለማግኘት ዓመታት ሊፈጅባቸው ይችላል።

የጤና ባለሙያዎ ምርመራውን የሚያካሂደው በሚታዩ ምልክቶች፣ በቆዳዎ ገጽታ እና በሕክምና ታሪክዎ ላይ በመመስረት ነው። ወደ ቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪም ሊመሩዎት ይችላሉ። ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫን በትክክል ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል ልዩ ክትትልና እንክብካቤ ያስፈልገዋል።

በሽታውን ለማረጋገጥ የሚረዳ የተለየ የላብራቶሪ ምርመራ የለም። ነገር ግን እብጠቱ መግል ወይም ፈሳሽ የሚያወጣ ከሆነ፣ የጤና ባለሙያዎ ለምርመራ ናሙና ሊወስድ ይችላል። ይህ ናሙና ለምርመራው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ይህ የጤና እክል ብዙውን ጊዜ የተለመዱ የቆዳ ኢንፌክሽኖችን ከሚያስከትሉ ባክቴሪያዎች ጋር ግንኙነት የለውም።

የሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ ሕክምና 

ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ (Hidradenitis suppurativa) ዕድሜ ልክ ሊቆይ የሚችልና ተደጋጋሚ የሆነ፣ እንዲሁም ለመቆጣጠር አስቸጋሪ የሆነ የጤና እክል ነው፤ ሆኖም ግን በሕክምና አማካኝነት ምልክቶቹን ማሻሻል ወይም በጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ ማድረግ ይቻላል።

በመድኃኒት፣ በቀዶ ጥገና ወይም በሁለቱም የታገዘ ሕክምና ምልክቶችን ለመቆጣጠር እና ተያያዥ ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል። የትኛው የሕክምና አማራጭ ለእርስዎ እንደሚስማማ፣ ስላላቸው ጥቅም እና ሊያስከትሉ ስለሚችሉት የጎንዮሽ ጉዳት የጤና ባለሙያዎ ይወስናሉ።

ከቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪምዎ ጋር መደበኛ ክትትል ማድረግ ይኖርብዎታል። አንዳንድ ታካሚዎች ከተለያዩ የሕክምና ዘርፎች የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ጥምር ክትትል ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

1.መድኃኒቶች (Medications)

የጤና ባለሙያዎ ከሚከተሉት የመድኃኒት ዓይነቶች አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ሊያዙልዎ ይችላሉ፦

  • የፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶች (Antibiotics)፦ በጣም የሚያምሙ፣ የቆሰሉ እና መግል የሚያወጡ እብጠቶች ካሉብዎ እና የምርመራ ውጤትዎ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን እንዳለብዎ ካሳየ፣ ከ1 እስከ 2 ሳምንታት የሚቆይ የፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒት ሊታዘዝልዎ ይችላል። የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ባይኖርም እንኳ፣ የቆዳ መቆጣትን እና መብገንን ለመከላከል ሲባል አነስተኛ መጠን ያላቸው የፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ። መለስተኛ ምልክቶች ከሆኑ በፈሳሽ ወይም በጄል መልክ ቆዳ ላይ የሚቀቡ መድኃኒቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ሕመሙ በስፋት የሚታይ ከሆነ እንደ ዶክሲሳይክሊን (Doxycycline)፣ ክሊንዳማይሲን (Clindamycin) ወይም ሪፋምፒን (Rifampin) ያሉ በክኒን መልክ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ። ከባድ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ለወራት ያህል መድኃኒት መውሰድ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
  • የስቴሮይድ መርፌዎች (Steroid injections)፦ ትራያምሲኖሎን አሴቶናይድ (Triamcinolone) የተባለ መድኃኒት ወደ ቁስሉ በመርፌ በመስጠት እብጠትን መቀነስ ይቻላል።
  • የሆርሞን ሕክምና (Hormonal therapy)፦ እንደ ኢስትሮጅን ያሉ ሆርሞኖችን የያዙ የወሊድ መከላከያ ክኒኖች ለመለስተኛ ሕመም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ስፓይሮኖላክቶን (Spironolactone) እና ለብጉር ሕክምና የሚውለው አይሶትሬቲኖይን (Isotretinoin) አንዳንድ ጊዜ የፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶችን ፍላጎት ለመቀነስ ይታዘዛሉ። በተጨማሪም ሲፕሮቴሮን አሴቴት (cyproterone acetate)፣ ሜትፎርሚን (metformin) እና ፊናስተራይድ (finasteride) የሚባሉ መድሃኒቶችም ሊታዘዝልዎት ይችላልሉ።
  • ባዮሎጂክስ (Biologics)፦ እነዚህ በመርፌ የሚሰጡ መድኃኒቶች የበሽታ መከላከል ሥርዓትን በማስተካከል የበሽታውን ዑደት ያቋርጣሉ። እንደ አዳሊሙማብ (Adalimumab) እና ኢንፍሊክሲማብ (Infliximab) ያሉ መድኃኒቶች ለመካከለኛ እና ለከባድ ደረጃ ሕክምና በፈቃድ ላይ ያሉ ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ መድሃኒቶች የበሽታ መከላከል ሥርዓትን ስለሚያዳክሙ የራሳቸው የሆን አደጋዎች አሏቸው፤ ስለሆነም እነዚህ መድኃኒቶች አብዛኛውን ጊዜ በቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪም የሚታዘዙት ሌሎች ሕክምናዎች ውጤታማ ካልሆኑ ብቻ ነው።
  • ሬቲኖይድስ (Retinoids)፦ በክኒን መልክ የሚወሰዱ ሬቲኖይዶች እንደ ብጉር ለሚታዩ ምልክቶች አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ መድኃኒቶች ለነፍሰ ጡር፣ ለሚያጠቡ ወይም ለማርገዝ ለሚያስቡ ሴቶች አይመከሩም።
  • የህመም ማስታገሻዎች፦ ያለ ማዘዣ የሚሸጡ የህመም ማስታገሻዎች ካልረዱዎት፣ ሐኪምዎ ጠንከር ያሉ መድኃኒቶችን ሊያዝልዎ ይችላል።
  • የጸረ ባክተሪያ ይዘት ያላቸው ፈሳሾች (Antiseptics)፦ እንደ 4% ክሎርሃክሲዲን (Chlorhexidine) ያሉ የጸረ ባክተሪያ ይዘት ያላቸው ፈሳሾች የተጎዱ የቆዳ ክፍሎችን በየቀኑ ለመታጠብ የሚያገለግሉ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ሕክምናዎች ጋር ተጣምረው ይታዘዛሉ።

2. ቀዶ ጥገና እና ሌሎች ሂደቶች

የቆዳ ስር ቦዮች ወይም መግል የያዙ እባጮች ካሉ ቀዶ ጥገና አስፈላጊ ይሆናል።

  • የቦዮች መክፈቻ (Unroofing)፦ በቆዳ ስር ያሉትን ቦዮች ገልጦ ለማውጣት ህዋሶችን የማስወገድ ሂደት ነው። ይህ አብዛኛውን ጊዜ ድጋሚ መደረግ የማያስፈልገው ውጤታማ ሕክምና ነው።
  • ፐንች ዴብሪድመንት (Punch debridement)፦ አንድን ያበጠ እብጠት ብቻ ለይቶ የማስወገድ ሂደት ነው።
  • የሌዘር ሕክምና (Laser therapy)፦ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ሌዘርን በመጠቀም ቁስሎችን ማስወገድ ይቻላል። ቀደም ባሉ ደረጃዎች ደግሞ የሌዘር ፀጉር ማስወገጃ ሕክምና ሊረዳ ይችላል።
  • ቀዶ ጥገና አድርጎ ማስወገድ (Surgical removal)፦ ምልክቶቹ በጣም ከባድ ለሆኑ ሰዎች የተጎዳውን ቆዳ በሙሉ የማስወገድ አማራጭ ነው። ቁስሉን ለመዝጋት የቆዳ ንቅለ ተከላ (Skin graft) ሊያስፈልግ ይችላል።
  • መቅደድ እና መግል ማውጣት (Incision and drainage)፦ ይህ ዘዴ አሁን ላይ ለሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ እንደ ዘላቂ ሕክምና አይቆጠርም፤ ምክንያቱም ቁስሉ ብዙ ሳይቆይ ድጋሚ ሊያገረሽ ይችላል። ለአጭር ጊዜ የህመም ማስታገሻነት ግን ሊያገለግል ይችላል።

የአኗኗር ዘይቤ ምክሮች

በሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ የተጠቁ ከሆኑ የሚከተሉትን ነጥቦች መተግበር ሕመሙን ለመቆጣጠር ይረዳል፦

  • ክብደት መቀነስ፦ ከመጠን በላይ ውፍረት ካለብዎ ክብደትዎን ለመቀነስ ይሞክሩ።
  • ማጨስ ማቆም፦ ሲጋራ የሚያጥኑ ከሆነ ለማቆም ይሞክሩ፤ ይህም ምልክቶቹ እንዳይባባሱ ይረዳል።
  • የጸረ ባክተሪያ ይዘት ያለው ሳሙና መጠቀም፦ ቆዳን የሚያጸዱ የጸረ ባክተሪያ ይዘት ያላቸው ፈሳሾችን ወይም ሳሙናዎችን ይጠቀሙ 
  • በሙቅ ውሃ የራሰ ጨርቅ መጠቀም፦ እብጠቶቹ መግል አውጥተው እንዲፈስሱ ለማድረግ፣ እብጠትን ለመቀነስ እና ሕመምን ለማስታገስ በሙቅ ውሃ የራሰ ንጹህ ጨርቅ እብጠቶቹ ላይ ለጥቂት ጊዜ ይያዙ።
  • ላላ ያሉ ልብሶችን መልበስ፦ የቆዳ መቆጣትንና መነካካትን ለመቀነስ ጥብቅ ያልሆኑ ልብሶችን ይምረጡ።
  • መላጨትን ማስወገድ፦ በሽታው ባለባቸው የቆዳ ክፍሎች ላይ ፀጉር ከመላጨት ይቆጠቡ።
  • ውጭ አየሩ በጣም ሞቃታማ በሚሆንበት ጊዜ ቤት ውስጥ በመቆየት ላብን ይቀንሱ።
  • መዓዛ ያላቸው ዶድራንቶችን ወይም ሽቶዎችን አይጠቀሙ።
  • የአመጋገብ ዘይቤዎን ለመቀየር ያስቡ፦ የወተት ተዋጽኦዎችን፣ ቀይ ስጋን እና የስኳር መጠንን በፍጥነት የሚጨምሩ ምግቦች ማዘውተር የሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ ምልክቶችን ሊያባብስ ይችላል።

ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ የሚያስከትላቸው ውስብስብ ችግሮች

ዘላቂ እና ከባድ የሆነ ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ የሚከተሉትን ችግሮች ሊያስከትል ይችላል፦

  • ኢንፌክሽን፦ በሽታው ባለባቸው ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ኢንፌክሽን ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን መግል መኖሩ በሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ የታወቀ ምልክት ስለሆነ ሁልጊዜ ኢንፌክሽን አለ ማለት እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
  • ጠባሳ እና የቆዳ ለውጦች፦ ቁስሎቹ ቢድኑም እንኳ እንደ ገመድ የተሳሰሩ ጠባሳዎችን ወይም የተቦረቦረ የቆዳ ገጽታን ሊተዉ ይችላሉ።
  • የእንቅስቃሴ መገደብ፦ ቁስሎች እና ጠባሳዎች እንቅስቃሴን ሊገድቡ ወይም ህመም ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ በተለይም በሽታው ብብት ወይም ጭን አካባቢ ሲሆን እንቅስቃሴን ይበልጥ ያውካሉ።
  • የቆዳ ካንሰር፦ ለረጅም ጊዜ በቆየ ሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ በተለይም በፊንጢጣ ዙሪያ (perianal area) ቁስል ባለባቸው ሰዎች ላይ የስኩዋመስ ሴል ካርሲኖማ (Squamous cell carcinoma) የተባለ የቆዳ ካንሰር ታይቷል።
  • የእጅ፣ የእግር ወይም የብልት እብጠት፦ የሂድራዴኒቲስ ሱፑራቲቫ ቁስሎች የሚወጡባቸው ቦታዎች በርካታ የሊምፍ እጢዎች/ፍርንትት (lymph nodes) የሚገኙባቸው ናቸው። ጠባሳዎች የሊምፍ ፈሳሽ ዝውውርን በማስተጓጎል የእጅ፣ የእግር ወይም የብልት አካባቢ እንዲያብጥ ሊያደርጉ ይችላሉ።
  • ሥነ-ልቦናዊ ተፅእኖ እና ራስን ማግለል፦ የቁስሎቹ መገኛ ቦታ፣ የሚወጣው ፈሳሽ እና መጥፎ ሽታ ከሰዎች ለመራቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህም ለጭንቀት ወይም ለድብርት ይዳርጋል።
  • የዕድሜ ልክ ሕመም፦ ከባድ ያለ እና ዘላቂ ህመም ሊኖን ይችላል።

Comments (0)