አንጃይና

Eyasu Yebeltal
Jul 24, 2025
undefined

                     አንጃይና  ማለት  ምን  ማለት  ነው?

        አንጃይና (Angina) ማለት የደረት ሕመም ወይም ምቾት ማጣት ማለት ነው ። የልብ ጡንቻ የደም ስር በሽታ ወይም (Coronary artery disease) በሚባል ሁኔታ ምክንያት የሚከሰት ሲሆን ይህ ችግር ብዙውን ጊዜ "የልብ ሕመም" ተብሎ ይጠራል ። ይህ በሽታ ባለባቸው ሰዎች ደም ወደ ልብ የሚያቀርቡት የደም ቧንቧዎች በስብ ክምችቶች ይዘጋሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ  ቧንቧዎቹ  ስለሚጠቡ የልብ ጡንቻው በቂ ደም አያገኝም። ይህም በተለይ በአካል እንቅስቃሴ ወቅት  የደረት ሕመም ወይም ምቾት ማጣት ሊያስከትል ይችላል ። የልብ ደም ቧንቧ በሽታ አንድ ሰው ለልብ ድካም እና ለሌሎች የልብ ሕመም የመጋለጥ እድልን ይጨምራል። የልብ ድካም የሚከሰተው የደም ቧንቧ በአብዛኛው ወይም ሙሉ በሙሉ ሲዘጋ እና የልብ ክፍል ሲጎዳ ነው ።

                የአንጃይና  አይነቶች

- ሁለት ዋና ዋና የአንጃይና አይነቶች አሉ።

  •   የተረጋጋ ( Stable )

   በዚህ ጊዜ የደረት ሕመም ወይም ምቾት ማጣት ተመሳሳይ ባህሪ ያለዉ ንድፍ ወይም ስርዓት ይከተላል ። ለምሳሌ፣ ስፖርት ሲሰሩ፣ ሲጨነቁ ወይም በዛ ያለ ምግብ ሲበሉ ሊያስተውሉት ይችላሉ። እነዚህ ሁሉ ጊዜያት ልብዎ ብዙ ደም የሚፈልግበት ሁኔታዎች ናቸው።

  •    ያልተረጋጋ ( Unstable )

በዚህ ጊዜ የደረት ህመም ወይም ምቾት ማጣት ተመሳሳይ ባህሪ ያለዉ ንድፍ ወይም ስርዓት አይከተልም። እረፍት ላይ የሚገኙበትን ሰዓት ጨምሮ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ይችላል.።ያልተረጋጋ  አንጃይና ለህይወት አስጊ እና አጣዳፊ ነው ምክንያቱም የልብ ድካም ምልክት ሊሆን ይችላል ።

          የአንጃይና  ምልክቶች  ምንድን  ናቸው?

   ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከህመም ይልቅ የደረት ምቾት ማጣትወይም ግፊት ስሜትን ይገልጻሉ ።  እንደ የታችኛው መንገጭላ፣ ትከሻዎች፣ ክንዶች፣ አንገት፣ ወይም የላይኛው ሆድ ያሉ የሰውነት ክፍሎች ጋር ሊደርስም ይችላል። ምልክቱም ከቃር ማቃጠል ጋር ሊመሳሰል ሲችል ብዙውን ጊዜ በዝግታ ጀምሮ በዝግታ ይሄዳል ። በተረጋጋ አንጃይና ፣ ያነሳሳውን እንቅስቃሴ ካቆሙ በኋላ ምልክቱ ብዙውን ጊዜ ይሻሻላል ።አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከ አንጃይና ጋር ሌሎች ምልክቶችን ሊያዩ ይችላሉ ። እነዚህም  :-

  •  ማቅለሽለሽ ወይም የምግብ አለመፈጨት
  • ማስገሳት
  • ማላብ
  • ከባድ የድካም ስሜት

           መቼ  ወደ  ህክምና  ቦታ  መሄድ  ያስፈልጋል?

  • የደረትዎ ህመም አዲስ ወይም ከባድ ሲሆን, ወይም እየባሰ ሲሄድ ።
  • የደረት ህመም እና የትንፋሽ ማጠር ሲኖር።
  • የደረት ህመም በእረፍት የማይሻል ከሆነ ።
  •  የአንጃይናን መድሃኒት ከወሰዱ በኋላ የደረት ህመምዎ የማይሻል ከሆነ።
  •  የማዞር ስሜት የሚሰማዎት ከሆነ።
  • ምልክቶቹ የሚያስፈራዎት ወይም የሚያስጨንቁዎ ከሆነ።

        ለአንጃይና  የሚደረጉ  ምርመራዎች  ምንድን  ናቸው?

ወደ ህክምና ቦታ ሲሄዱ የህክምና ባለሙያዎች  ስለ ምልክቶችዎ ይጠይቁ እና የአንጃይና እና የልብ ድካምን ጨምሮ ሌሎች የደረት ሕመም መንስኤዎችን ለማጣራት ምርመራዎችን ያደርጋሉ ።

ምርመራዎቹ የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ ፦

  •  ኤሌክትሮካርዲዮግራም ("ECG") - ይህ ምርመራ በልብዎ ውስጥ ያለውን የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ ይለካል
  • የጭንቀት ፈተና - በጭንቀት ፈተና ወቅት በኤሌክትሮካርዲዮግራም በመታገዝ እንዲሮጡ ወይም የመሮጫ ማሽን ወይንም  በትሬድሚል ላይ እንዲራመዱ  ሊጠየቁ ይችላሉ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የልብ የደም ፍላጎትን ስለሚጨምር ይህ ምርመራ ልብ በቂ ደም እያገኘ መሆኑን ለማየት ይረዳል ። መራመድ ወይም መሮጥ ካልቻሉ፣ የልብ ምት እንዲጨምር እና ደም በፍጥነት እንዲፈስ የሚያደርግ መድሃኒት ሊሰጥዎት ይችላል።
  • የደም ምርመራዎች - የደም ምርመራዎች የልብ ጉዳት ባለባቸው ሰዎች ላይ የልብ ህመም መኖሩን የሚያሳዩ እና የጨመሩ ኬሚካሎችን በማየት  ማረጋገጥ ይችላሉ
  • የልብ ካቴተራይዜሽን - በዚህ ምርመራ ወቅት ሐኪሙ ቀጭን ቱቦ በእግርዎ ወይም በክንድዎ በኩል ወደ ደም ቧንቧ በማስገባት ቱቦውን ወደ ልብዎ ያንቀሳቅሱታል ። በመቀጠል ዶክተሩ በኤክስሬይ ላይ የሚታየውን ቀለም ወደ ቱቦው ውስጥ በማስገባት በልብዎ ውስጥ ያሉት ማንኛቸውም የደም ቧንቧዎች መዘጋታቸውን ሊያሳይ ይችላል። ይህ የፈተናው ክፍል "coronary angiography" ይባላል።
  • ሲቲ ስካን - ይህ ልዩ የኤክስሬይ ዓይነት ነው። ዶክተርዎ ወደ ልብዎ የሚሄዱትን የደም ስሮች ለመመልከት ይህንን ሊጠቀም ይችላል።

        አንጃይና  እንዴት  ይታከማል?

የሕክምና አማራጮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • መድሃኒቶች - እንደ "ናይትሬትስ" እና "ቤታ ማገጃዎች" ያሉ የተለያዩ የመድሃኒት ዓይነቶችን ያጠቃልላል ።  አንዳንዶቹ ወደ ልብ ጡንቻ የሚሄዱትን የደም ሥሮች በማዝናናት ወይም በማስፋፋት ይሠራሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ልብ የሚሠራውን የሥራ መጠን በመቀነስ ይሠራሉ ።ሌሎች ተጨማሪ መድሃኒቶችንም መውሰድ ሊያስፈልግዎ ይችላል ።
  • ሂደቶች - እነዚህ በቂ ደም ወደሌለው የልብ ክፍል የደም ዝውውርን ያድሳሉ ። እነሱም የሚከተሉትን ያካትታሉ ፦
  •  ስቴንቲንግ - ስቴንት የተዘጋ የደም ቧንቧን ለመያዝ የሚገባ ትንሽ የብረት ቱቦ ነው።
  •  ቀዶ ጥገና - አንዳንድ ሰዎች የልብ የደም ቧንቧ የማለፊያ ቀዶ ጥገና ( coronary artery bypass grafting ) የሚባል ቀዶ ጥገና ይደረግላቸዋል. ።  ለዚህም ዶክተሩ ጤናማ የደም ቧንቧን ከሌላ የሰውነትዎ ክፍል ወስዶ  በተዘጋው ደም ወሳጅ ቧንቧ ዙሪያ ያለውን ደም እንደገና ለመምራት ይጠቀሙበታል ።

     አንጃይናን  እንዴት  መከላከል  እና  መቀነስ  እንችላለን ?

  • ሲጋራ ባለማጨስ
  • ጤናማ አመጋገብን በመከተል ፦  ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ያዘውትሩ እና  ስብ ያላቸውን ምግቦች ይቀንሱ 
  • የጨው መጠንን መቀነስ 
  • በሳምንት ቢያንስ ለ 30 ደቂቃ ከ 3 እስከ 5 ቀናት የአካል ብቃት  እንቅስቃሴዎችን መስራት ለምሳሌ ወክ ማድረግ፣ ሳይክል መንዳት ፣ ዋና ወይም አንዳንድ የኤሮቢክስ እንቅስቃሴዎችን ያድርጉ።
  • ክብደትን ይቀንሱ ፦ ከመጠን በላይ የሰውነት ክብደት ካለዎት ክብደት መቀነስ አንጃይናን ለመከላከል ይረዳል ።

Comments (0)