ስለ ዲቶክስ ምን ያህል ያዉቃሉ?

Biruh Tesfaye
Apr 7, 2026
undefined

“ዲቶክስ” (Detox) ወይም “ዲቶክሲፊኬሽን” (Detoxification) የምንለው ሰውነትን ከመርዛማ ነገሮች ወይም ከጎጂ ንጥረ ነገሮች ለማጽዳት የሚረዳ ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል መርዛማ ነገሮችን ከሰውነት ለማስወገድ በአሁኑ ጊዜ በሰፊው ተወዳጅነትን አትርፏል።

በተፈጥሮ በሰውነታችን ውስጥ የማይመረቱ አንዳንድ ጎጂ ንጥረ ነገሮች በተለያዩ መንገዶች ወደ ሰውነታችን ሊገቡ ይችላሉ፤ እነዚህም የህዋሳትን መዋቅር እና ዘረመል ሊያዛቡ ወይም የሰውነት ክፍሎችን መደበኛ ስራ ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ። እንደ አየር ብክለት፣ ውጥረት (stress)፣ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ልማድ እና ለተለያዩ ኬሚካሎች መጋለጥ ያሉ የተለያዩ ምክንያቶች በሰውነታችን ውስጥ መርዛማ ነገሮች (toxins) ተከማችተው እንዲቆዩ ሊያደርጉ ይችላሉ። እነዚህ መርዛማ ንጥረ ነገሮች ቀስ በቀስ የተለያዩ ህዋሳትንና የሰውነት ክፍሎችን በመጉዳት ለተለያዩ የጤና እክሎች ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ግን፣ ለሰውነት ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮች የሚመነጩት ከውጫዊ ሁኔታዎች ብቻ አይደለም። በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ህዋሳትን የሚጎዱ ንጥረ ነገሮች እንደ መተንፈስ ባሉ የተለያዩ የሰውነት ውስጥ የሜታቦሊዝም ሂደቶች ምክንያት ሊለቀቁ ይችላሉ።

የሰው አካል ተፈጥሯዊ የመርዝ ማጣራት ሂደትን ያከናውናል፤ ይህም እንደ ጉበት፣ ኩላሊት፣ ሳንባ እና ጨጓራ/አንጀንት ባሉ ወሳኝ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ ይከናወናል። እነዚህ የሰውነት ክፍሎች መርዛማ ነገሮችን እና ሰውነታችን የማይፈልጋቸውን ሌሎች ንጥረ ነገሮችን የመሰባበርና የማስወገድ ኃላፊነት አለባቸው። በመቀጠልም ሰውነታችን እነዚህን መርዞች በሽንት እና በሰገራ መልክ ወደ ውጭ ያስወጣቸዋል። 

ሆኖም ግን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች መርዛማ ነገሮች ሰውነታችን ሊያስወግዳቸው ከሚችለው በላይ በከፍተኛ መጠን ሊከማቹ ይችላሉ። የዲቶክስ ዋና ዓላማ የሰውነትን ተፈጥሯዊ የመርዝ ማጣራት ሂደት መደገፍና መርዛማ ነገሮች እንዲወገዱ መርዳት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ዲቶክስ እንደ ጉበት ያሉ የሰውነት ክፍሎችን የሥራ ክንውን በመደገፍ፣ ሰውነትን ከውስጥ ወደ ውጭ ለማፅዳት ያለመ ሂደት ነው።

የሚከተሉት ምልክቶች የሚታዩባችሁ ከሆነ ዲቶክስን ማሰብ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል፦

  • በቀላሉ መደከም፣ የትኩረት ማጣት እና የመነቃቃት ስሜት መጥፋት
  • ክብደት በቀላሉ መጨመር ነገር ግን ለመቀነስ በጣም መቸገር
  • የምግብ መፈጨት ችግሮች፦ ለምሳሌ የማቅለሽለሽ ስሜት፣ የሆድ መነፋት፣ የሆድ ድርቀት እና አጠቃላይ የህመም ወይም የትኩሳት ስሜት መሰማት
  • ተደጋጋሚ እና ድንገተኛ የሆነ፣ ምክንያት የሌለው የማዞር ስሜት
  • የእንቅልፍ ችግር እና ጥልቅ እንቅልፍ አለማግኘት
  • ለብጉር (Acne) ተጋላጭ መሆን
  • መደበኛ ያልሆነ የወር አበባ ዑደት መኖር
  • ከፍተኛ የሆነ የባህሪ ወይም የሥሜት መቀያየር

የዲቶክስ ጥቅም ምንድን ነው?

ምንም እንኳን የሰውነት ዲቶክስ ሁሉንም መርዛማ ነገሮች በአንድ ጊዜ በቀጥታ ባያስወግድም፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለመጀመር ጠንካራ መንገድ ሊሆን ይችላል። ዲቶክስ በባለሙያ ሐኪም ቁጥጥር ስር ሲከናወን ሰውነታችን ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን እንዲያስወግድ ሊረዳ ይችላል። ሆኖም ግን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች የዲቶክስ የአመጋገብ ዘይቤዎች ለተለያዩ የጤና እክሎች ሊዳርጉ ይችላሉ።

ዲቶክስ የሚሰጣቸው አንዳንድ ጥቅሞች የሚከተሉት ናቸው፦

1. የምግብ መፈጨትን ማሻሻል

የዲቶክስ አንዱ ጥቅም የምግብ መፈጨትን ማሻሻል መቻሉ ነው። ይህ በተለይ የምግብ መፈጨት ችግር ላለባቸው ሰዎች፣ ለምሳሌ ምግብን የመፍጨት አቅም መቀነስ (gastroparesis) እና የክሮን በሽታ (Crohn’s disease) ላለባቸው ጠቃሚ ነው። ይህ ሁኔታ የምግብ መፈጨት ሂደት በአንጀት ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስ ጠንካራ ምግቦችን በመገደብ ሊስተካከል ይችላል።

ንጥረ ነገሮችን ለማግኘት እንደ ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ አጃ (Oatmeal) ወይም ቡኒ ሩዝ (Brown rice) ያሉ ምግቦችን መውሰድ ይችላሉ።

2. ለሥር የሰደዱ በሽታዎች ያለን ተጋላጭነት መቀነስ

ሌላው የዲቶክስ ጥቅም ለሥር የሰደዱ በሽታዎች ያለብንን ተጋላጭነት መቀነስ ነው። እንደ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ ያሉ ጤናማ የአመጋገብ ዘይቤዎች እና መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደ ስኳር እና የልብ በሽታ ያሉ የጤና እክሎችን የመከላከል አቅም አላቸው።

3. የመኖር ዕድሜን ለማራዘም መርዳት

ከዲቶክስ የሚገኘው ሌላው ጥቅም የመኖር ዕድሜን ማራዘም ነው። ይህ የሚሳካው ወደ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመሸጋገር ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ጤናማ የሰውነት ክብደትን መጠበቅ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አለመጨስ እና አልኮልን መገደብ የመኖር ዕድሜን እስከ 14 ዓመታት ሊያራዝም ይችላል።

ከነዚህ ሁሉ በተጨማሪ፣ ደቶክስ የሚከተሉትን ጥቅሞችን ይሰጣል

  • እንደ ጉበት እና ኩላሊት ያሉ በተፈጥሮ መርዛማ ነገሮችን በማጣራት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ የሰውነት ክፍሎችን መደበኛ ተግባር ሊደግፍ ይችላል።
  • የበለጠ የንቃተ ስሜት እንዲሰማዎት ሊረዳ ይችላል
  • ካሎሪን መገደብ ላይ የተመሰረቱ የዲቶክስ ዘዴዎች የክብደት መቀነስ ሂደትን ሊያፋጥኑ ይችላሉ።
  • አትክልትና ፍራፍሬን መመገብላይ የሚያተኩሩ የዲቶክስ መንገዶች ሰውነት የሚያስፈልጉትን ቪታሚኖች እና ማዕድናት እንዲያገኝ ሊረዱ ይችላሉ

ሰውነትን እንዴት ዲቶክስ ማድረግ ይቻላል?

ሰውነትን ከመርዛማ ነገሮች ለማጽዳት በጣም ቀላል ከሆኑ መንገዶች ጀምሮ ጥረትና ወጪ እስከሚጠይቁ ድረስ ብዙ አማራጮች አሉ። ሊሞክሯቸው የሚችሏቸው ጥቂት የዲቶክስ ዘዴዎች የሚከተሉት ናቸው፦

1. በቂ ውሃ መጠጣት

ውሃ ጥምን ከመቁረጥ ባለፈ ለሰውነታችን እጅግ በጣም ብዙ ጥቅሞችን ይሰጣል። ከነዚህም መካከል፦

  • የሰውነት ሙቀትን ያስተካክላል
  • ለምግብ መፈጨት እና ንጥረ ነገሮችን ወደ ሰውነት እንዲወሰዱ ይረዳል
  • ቆሻሻን በማስወገድ ሰውነትን ከመርዝ ያጸዳል

የሰውነታችን ህዋሳት በተገቢው ሁኔታ እንዲሰሩ እና ለሰውነት የሚያስፈልገውን ጉልበት ከንጥረ ነገሮች ለማመንጨት ዘወትር እራሳቸውን መጠገን ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሂደቶች እንደ ዩሪያ (Urea) እና ካርቦን ዳይኦክሳይድ ያሉ ቆሻሻዎችን ያስወጣሉ። እነዚህ ቆሻሻዎች በደማችን ውስጥ ከተቀመጡ ለጤና ጠንቅ ሊሆኑ ይችላሉ። ውሃ እነዚህን የቆሻሻ ውጤቶች በማጓጓዝ በሽንት፣ በትንፋሽ ወይም በላብ አማካኝነት እንዲወገዱ ያደርጋል። ስለዚህ ሰውነትን በትክክል ለማጽዳት ሁልጊዜ በቂ ውሃ መጠጣትና የሰውነትን የፈሳሽ መጠን መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ሰውነት መርዛማ ነገሮችን ለማስወገድ ብዙ ውሃ ስለሚፈልግ፣ በዲቶክስ ወቅት በቀን ቢያንስ 2 ሊትር ውሃ መጠጣት ይመከራል።ይሁን እንጂ እንደ ጾታ፣ የሰውነት መጠን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ደረጃ የውሃ ፍላጎት ከሰው ሰው ሊለያይ ይችላል።

2. አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ

አትክልትና ፍራፍሬዎች ሰውነት በብቃት እንዲሰራ የሚረዱ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ይዘዋል። በተጨማሪም በውስጣቸው ያለው ፋይበር (Fiber) እና ጸረ ኦክሲዳንት ንጥረ ነገሮች መርዛማ ነገሮችን ለማስወገድ ይረዳል። እንደ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ለውዝ እና ጥራ ጥሬዎችን የመመገብ ልማድ አንጀትና ጉበት ቆሻሻን በቀላሉ እንዲያወጡ ይረዳል። አትክልቶችን በበቂ መጠን መመገብ ካልቻሉ፣ በጭማቂ መልክ አዘጋጅተው መጠጣት ይችላሉ።

3. መጾም

ጾም ሌላኛው የዲቶክስ ዘዴ ነው። በሚጾሙበት ወቅት ለተወሰኑ ሰዓታት ምግብና መጠጥ ስለማይወስዱ ሰውነትዎ እራሱን እንዲያርፍና እንዲያጸዳ ዕድል ይሰጠዋል። ጾም ሰውነት ተግባራቱን እንዲያስተካክል፣ የአካል ክፍሎችን እንዲያድስ እና ውጥረትን እንዲቀንስ ይረዳል።

4. ጤናማ ያልሆኑ ልምዶችን ማስወገድ

ሰውነትን በሚያጸዱበት ወቅት ለጤና ጎጂ የሆኑ ልምዶችን፣ በተለይም ማጨስን ማቆም ይገባል። ሲጋራና ጭሱ ለሰውነት መርዝ ናቸው። በተመሳሳይ፣ አልኮልን መቀነስ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም አልኮል የጉበትን መርዝ የማስወገድ አቅምን ያዳክማል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት በጉበት ላይ ስብ እንዲከማች፣ ለብግነት እና ለጉበት ጠባሳ መፈጠር ምክንያት ይሆናል።

5. በቂ እንቅልፍ ማግኘት

የሰውነትዎን ጤና እና ተፈጥሯዊ የመርዝ ማጣራት ሥርዓት ለመደገፍ በየምሽቱ በቂ እና ጥራት ያለው እንቅልፍ ማግኘት የግድ ነው። መተኛት አእምሮዎ እራሱን እንደገና እንዲያደራጅ እና እንዲያድስ ዕድል ከመስጠቱም በላይ፣ ቀኑን ሙሉ የተከማቹ መርዛማ የቆሻሻ ውጤቶችን እንዲያስወግድ ይረዳዋል።

በቂ እና ጥራት ያለው እንቅልፍ አለማግኘት ከአጭር እና ረጅም ጊዜ የጤና ችግሮች ጋር የተያያዘ ነው፤ ከነዚህም መካከል፦

  • ውጥረት
  • ጭንቀት
  • ከፍተኛ የደም ግፊት
  • የልብ በሽታ
  • ዓይነት 2 ስኳር በሽታ
  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት
  • የበሽታ መከላከል አቅም ስለሚዳከም ለበሽታ ተጋላጭነት ይጨምራል

የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (CDC) በየምሽቱ ቢያንስ ሰባት ሰዓት ጥራት ያለው እንቅልፍ እንዲያገኙ ይመክራል።

6. የስኳር ፍጆታን መቀነስ

ብዙውን ጊዜ ለዛሬው የህዝብ ጤና ቀውስ መንስኤ ናቸው ብለው ከሚጠቀሱ ምግቦች መካከል ስኳር እና የተቀነባበሩ ምግቦችን ዋነኞቹ ናቸው። ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር እና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን መመገብ ከውፍረት እና ከሌሎች እንደ የልብ በሽታ፣ ካንሰር እና የስኳር በሽታ ያሉ ሥር የሰደዱ በሽታዎች ጋር እንደሚያያዝ ጥናቶች ያሳያሉ። በተጨማሪም ከፍተኛ ስኳር መውሰድ ቆሽጥ (Pancreas) ኢንሱሊን ለማምረት እንዲጨነቅ ያደርጋል። እነዚህ በሽታዎች እንደ ጉበት እና ኩላሊት ያሉ ወሳኝ የሰውነት ክፍሎችን በመጉዳት፣ ሰውነትዎ በተፈጥሮው መርዛማ ነገሮችን የማጣራት አቅሙን ያዳክሙታል።

የስኳር ምግቦችን በመጠኑ በመመገብ የሰውነትዎን የመርዝ ማጣራት ሥርዓት ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ይችላሉ። እንዲሁም በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች ወይም የተመጣጠኑ ያልሆኑ ምግቦችን እንደ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ስንዴ፣ አጃ እና ቡኒ ሩዝ ባሉ ጤናማ አማራጮች መቀየር የስኳር ፍጆታን ለመቀነስ የሚረዳ ጤናማ መንገድ ነው።

7. በየማለዳው የሎሚ ውሃ መጠጣት

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሎሚ ለሰውነት ዲቶክስ ተመራጭ ከሆኑ ፍራፍሬዎች አንዱ ነው። በየቀኑ ማለዳ በባዶ ሆድ የሎሚ ውሃ መጠጣት ሰውነት መርዞችን እንዲያስወግድና የምግብ መፈጨት እንዲሳለጥ ይረዳል። ሆኖም ይህ ውጤት የሚታየው ልምዱን ለረጅም ጊዜ አዘውትረው ሲተገብሩት ነው።

8. መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ

መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሰውነት ክብደትዎን ለመቀነስ፣ ረጅም ዕድሜ ከመኖር እና ለተለያዩ የጤና እክሎችና በሽታዎች ያለብዎትን ተጋላጭነት ከመቀነስ ጋር የተያያዘ ነው። በተጨማሪም መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላብን ሊጨምር ይችላል፤ በዚህም አማካኝነት ሰውነትን በላብ የሚወጡ መርዛማ ነገሮችን ለማስወገድ ይረዳል።

የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (CDC) በሳምንት ቢያንስ ከ150–300 ደቂቃ የሚደርስ መካከለኛ ጥንካሬ ያለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (ለምሳሌ፦ ፈጣን እርምጃ)፣ ወይም በሳምንት ከ75–150 ደቂቃ የሚደርስ ከፍተኛ ጥንካሬ ያለው እንቅስቃሴ (ለምሳሌ፦ ሩጫ) እንዲሰሩ ይመክራል።

ለመጀመር ያህል፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎ ውስጥ ሊጨምሩት የሚችሉትን አንድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያስቡ፤ ለምሳሌ፦ ከምግብ በኋላ ለ30 ደቂቃ ያህል በእግር መጓዝ።

9. ጨው ይቀንሱ

በዲቶክስ ወቅት ሊታሰብበት የሚገባው ሌላው አስፈላጊ ነጥብ የጨው ፍጆታን መገደብ ነው። ከመጠን በላይ ጨው መመገብ ሰውነት ከመጠን በላይ ፈሳሽ እንዲይዝ በማድረግ ለሰውነት እብጠት (edema) መንስኤ ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት አንድ ሰው የመሽናት ፍላጎቱ ሊቀንስ ይችላል። ስለሆነም በዲቶክስ ወቅት የጨው ፍጆታን መገደብ እና የውሃ መጠጥን መጨመር መርዛማ ነገሮች ከሰውነት ውስጥ እንዲወገዱ ይረዳል።

የዲቶክስ የጎንዮሽ ጉዳቶች

ማንኛውንም ዓይነት የዲቶክስ (detox) ተግባር ከመጀመርዎ በፊት ሊከሰቱ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው።

የዲቶክስ የአመጋገብ ዘይቤ ሊያስከትላቸው የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦

  • በርካታ የዲቶክስ የአመጋገብ ዘይቤዎች መጾምን ወይም ከፍተኛ የካሎሪ ገደብን ይመክራሉ። ለአጭር ጊዜ መጾም እና የተገደበ የካሎሪ ፍጆታ ለከፍተኛ ድካም፣ ለብስጭት እና ለአፍ ጠረን መበላሸት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለረጅም ጊዜ መጾም ደግሞ የኃይል (energy)፣ የቪታሚን እና የማዕድን እጥረት፣ የኤሌክትሮላይት መዛባት እና ሌላው ቀርቶ ለሞት ሊዳርግ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በዲቶክስ ወቅት የሚመከሩ የትልቁ አንጀት ማጽጃ (Colon cleansing) ዘዴዎች የሰውነት ፈሳሽ ማነስን ፣ የጡንቻ ህመምንን፣ የሆድ መነፋትን፣ ማቅለሽለሽን እና ትውከትን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
  • በዲቶክስ (detox) ወቅት ከሰውነት ውስጥ ከመጠን በላይ ፈሳሽ እንዲወጣ የሚያደርጉ ተግባራት፣ የፈሳሽ እና የኤሌክትሮላይት (fluid-electrolyte) ሚዛንን ሊያዛቡ ይችላሉ።
  • አንዳንድ የዲቶክስ የአመጋገብ ዘይቤዎች ለሰፕልመንቶች፣ ለሰገራ ማለስለሻዎች (laxatives)፣ ሽንት ለሚያስወጡ መድኃኒቶች (diuretics) ከመጠን በላይ መወሰድ እና መብዛት ሊያጋልጡ ይችላሉ።

ዲቶክስ ለማን አይመከርም?

የዲቶክስ ፕሮግራሞች በአጠቃላይ የተወሰኑ ምግቦችን እንዲመገቡ የሚፈቅዱና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ደግሞ የሚገድቡ ልምዶች ናቸው። የተወሰኑ ሰዎች ማንኛውንም ዓይነት የዲቶክስ ወይም የካሎሪ ገደብ ያላቸውን የአመጋገብ ዘይቤዎች ከመጀመራቸው በፊት መጀመሪያ ሐኪም ማማከር ይኖርባቸዋል።

ይህም ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ያጠቃልላል፤ ለምሳሌ፦

  • ታዳጊዎች 
  • አረጋውያን
  • የምግብ እጥረት (Malnourished) ያለባቸው ሰዎች
  • ነፍሰ ጡር የሆኑ ወይም ጡት የሚያጠቡ እናቶች
  • የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች
  • የአመጋገብ ችግር (Eating disorder) ያለባቸው ሰዎች

አብዛኛው የዲቶክስ ፕሮግራሞች አንድ ዓይነት ምግብ መመገብ ወይም ረጅም ሰዓት በሚቆይ ጾም ላይ ያተኩራሉ። ስለሆነም፣ ማንኛውም ዲቶክስ ማድረግ የሚፈልግ ሰው የጤና ችግር ቢኖርበትም ባይኖርበትም፣ አስቀድሞ ሐኪም ጋር መማከርና አስፈላጊ የሆኑ ምርመራዎችን ማድረግ ይኖርበታል። 

Comments (0)