በከፍተኛ የደም ግፊት ምክንያት የሚከሰቱት በሽታዎች የትኞቹ ናቸው?
ከፍተኛ የደም ግፊት "ዝምተኛው ገዳይ" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ግልጽ ምልክቶች ስለሌለው በጊዜ ሂደት ሳይታወቅ ብዙ የሰውነት ክፍሎችን በጸጥታ ይጎዳል። የደም ግፊት ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ ለብዙ ሕይወት አስጊ እና ከባድ በሽታዎች የመጋለጥ እድልን በእጅጉ ይጨምራል። በዚህ ጽሑፍ የደም ግፊት በሰውነት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እና የሚያስከትላቸውን ዋና ዋና በሽታዎች እናያለን።
ከፍተኛ የደም ግፊት ለምን አደገኛ ሆነ?
የደም ግፊት ደማችን ወደ ሰውነታችን ለመሰራጨት በደም ወሳጅ ግድግዳዎችዎ ላይ የሚገፋበትን ኃይል ለመለካት የምንጠቀምበት መለኪያ ሲሆን፣ ይህ ግፊት ከመጠን በላይ ያለማቋረጥ ከፍ ባለ ጊዜ የደም ሥሮችን እና ዋና ዋና የአካል ክፍሎችን ያዳክማል። ከጊዜ በኋላ ይህ ጉዳት የደም ዝውውርን ሊቀንስ፣ የአካል ክፍሎች ሥራን ሊያስተጓጉል እና በሽታን ሊያስከትል ይችላል።
1. የልብ ሕመም
ከፍተኛ የደም ግፊት የልብ ሕመም ዋነኛ መንስኤዎች ከሆኑት ውስጥ አንዱ ነው።
ለምን ይከሰታል?
የማያቋርጥ እና ከልክ በላይ ከፍ ያለ የደም ግፊት ልባችን ከአቅሙ የበለጠ እንዲሰራ በማስገደድ በመጨረሻ ያዳክመዋል።
ሊያስከትለው የሚችለው የልብ ሕመሞች:-
- የልብ ደም ቧንቧ በሽታ፡- በግፊት የተጎዱ የልብ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ወደ ልብ የሚሄደውን የደም ፍሰት ይቀንሳሉ።
- የልብ ድካም፡- የልብ ጡንቻ በጣም ደካማ ወይም ግትር በመሆን በትክክል ደም መርጨት ይሳነዋል።
- የግራ የልብ ግድግዳ መወፈር:- ከመጠን በላይ በሚኖርበት የስራ ጫና ምክንያት ጤናማ ያልሆነ የልብ ጡንቻ ውፍረት ይፈጠራል።
2. ስትሮክ
ከፍተኛ የደም ግፊት የስትሮክ ህመምን ከሚያመጡ መንሰኤዎች ዋነኛው አደጋ ነው።
ለምን ይከሰታል?
የተጎዱ ወይም የጠበቡ የደም ቧንቧዎች እንዲደፈኑ ወይም እንዲፈነዱ ሊያደርግ ይችላል።ሁለቱንም ዋና ዋና የስትሮክ አይነቶች ሊያስከትል ሲችል፣ እነርሱም:-
- ሄሞራጂክ ስትሮክ፡- በአንጎል ውስጥ ያሉ የደም ስሮች ሲፈነዱ እና አንጎል ደም ማግኘት ሳይችል ሲቀር ይከሰታል።
- ኢስኬሚክ ስትሮክ፡- ወደ አንጎል የሚሄደው የደም ዝውውር በደም ስሮች መዘጋት ምክንያት ሲቋረጥ ይከሰታል።
3. የኩላሊት በሽታ (ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ)
ኩላሊቶቻችን ከሰውነታችን ውስጥ ቆሻሻን በአግባቡ ለማጣራት በጤናማ የደም ሥሮች ላይ ይመረኮዛሉ።
ማስጠንቀቂያ፡-የኩላሊት ጉዳት ብዙውን ጊዜ ሳይታወቅ ቀስ በቀስ በማደግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋል ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል።
የደም ግፊት ከልክ በላይ መጨመር በኩላሊት ላይ የሚያስከትለው ውጤቶች:-
- የኩላሊት የደም ቧንቧዎችን ይጎዳል
- የኩላሊት የማጣራት ችሎታን ይቀንሳል
- የኩላሊት ሙሉ በሙሉ መስራት ማቆምን ሊያስከትል ይችላል
4. የአይን ሕመም (የደም ግፊት ሬቲኖፓቲ)
ከፍተኛ የደም ግፊት በአይን ውስጥ የሚገኙትን ጥቃቅን የደም ስሮች ሊጎዳ ሲችል፣ ያልታከመ የደም ግፊት በመጨረሻ ወደ ቋሚ ዓይነ ስውርነት ሊያመራ ይችላል።
ከፍተኛ ግፊት ሊያደርሳቸው የሚችላቸው ጉዳቶች፡-
- የእይታ መደብዘዝ
- እይታን ሙሉ በሙሉ ማጣት
- በሬቲና ላይ የሚደርስ ጉዳት
5. የሩቅ ደም ቧንቧዎች ህመም
ይህ ሁኔታ የሚከሰተው በደም ወሳጅ ቧንቧዎች መጥበብ ምክንያት ወደ እጅ እና እግር የሚሄደው የደም ዝውውር ሲቀንስ ነው። ምልክቶች፡-
- በሚራመዱበት ጊዜ የእግር ህመም
- መደንዘዝ ወይም ድክመት
- የቁስሎች ቶሎ አለመዳን
የሩቅ ደም ቧንቧዎች ህመም የልብ ድካም እና ስትሮክ የመፈጠር እድልን ይጨምራል።
6. አንዩሪዝም
አንዩሪዝም በደም ቧንቧ ግድግዳ ላይ የሚፈጠር አደገኛ እብጠት ወይም መዳከም ነው። ከፍተኛ የደም ግፊት በደም ወሳጅ ግድግዳዎች ላይ ጫናን በመጨመር አንዩሪዝም ያባብሳል።
ለምን ከባድ ነው?
- በድንገት ሊፈነዳ ይችላል
- ለሕይወት አስጊ ደም መፍሰስን በሰውነታችን ውስጥ ያስከትላል
7. ሜታቦሊክ ሲንድሮም
የደም ግፊት የሚከተሉት ሁኔታዎች ስብስብ የሆነው የሜታቦሊክ ሲንድረም ቁልፍ አካል ነው።
- ከፍተኛ የደም ስኳር
- ከመጠን በላይ የሆድ ስብ
- መደበኛ ያልሆነ የኮሌስትሮል መጠን
ይህ ጥምረት የስኳር በሽታ እና የልብ ሕመም አደጋን በእጅጉ ይጨምራል።
8. የግንዛቤ መቀነስ እና የመርሳት ችግር
ከፍተኛ የደም ግፊት በጊዜ ሂደት የአንጎልን ተግባር ሊጎዳ ሲችል የደም ዝውውር መቀነስ እና መዛባት የአንጎል ጤናን ይጎዳሉ። ሊያስከትላቸው የሚችለው ተጽኖዎች፡-
- የማስታወስ ችግሮች
- የማተኮር ችግር
- በደም ቧንቧ ችግር የሚመጣውን የመርሳት ችግር አይነት አደጋ መጨመር
ማን አደጋ ላይ ነው?
ማንኛውም ሰው ከፍተኛ የደም ግፊት ሊያጋጥመው ሲችል የሚከተሉትን ነገሮች የመከሰት አደጋውን ከፍ ሊያደርጉት ይችላሉ።
- ከፍተኛ የጨው መጠን ያለው ምግብን አዘውትሮ መመገብ
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አለማድረግ
- ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት ወይም ማጨስ
- ከመጠን በላይ መወፈር
- የቤተሰብ የደም ግፊት ታሪክ
እንዴት መከላከል ይቻላል?
ጥሩው ዜና የደም ግፊትን መቆጣጠር መቻሉ ነው።
ቁልፍ እርምጃዎች፡-
- የደም ግፊትዎን በየጊዜው ይፈትሹ
- የተመጣጠነና ዝቅተኛ-ጨው ያለው አመጋገብ ይከተሉ
- የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በቋሚነት ያድርጉ
- ጤናማ የሰውነት ክብደትን ይጠብቁ
- በታዘዘው መሰረት መድሃኒቶችን በአግባቡ ይውሰዱ
- አልኮልን ይገድቡ እና ማጨስን ያስወግዱ
ከፍተኛ የደም ግፊት ልብዎን ብቻ ሳይሆን በሰውነትዎ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የአካል ክፍሎች ሊጎዳ ሲችል፣ ከደም ግፊት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎች ከስትሮክ እስከ የኩላሊት ሙሉ በሙሉ መስራት ማቆም ድረስ ከባድ ናቸው። ነገርግን አስቀድሞ በማወቅ እና በአግባቡ በመያዝ አብዛኛውን ችግሮች መከላከል ይቻላል። ዛሬ የደም ግፊትን መቆጣጠር ጤናዎን ለብዙ አመታት ሊጠብቅ ይችላል!




