የጥርስ መቦርቦር (Tooth decay) የሚፈጠረው የጥርስዎ ጠንካራና ውጫዊው ክፍል (Enamel) ሲሸረሸር ወይም ሲወድም ነው። የጥርስ መቦርቦር መንስኤው "ፕላክ" (Plaque) ነው። ፕላክ (Plaque) ተብሎ የሚጠራውና በባክቴሪያ የተሞላው የሚጣበቅ ዝልግልግ ነገር በጥርስዎ ላይ ዘወትር ይፈጠራል። ስኳር ያላቸውን ምግቦች ወይም መጠጦች በሚወስዱበት ጊዜ፣ በፕላክ ውስጥ ያሉት ባክቴሪያዎች በምግብ እና በመጠጥ ውስጥ የሚገኘውን ስኳር ወደ አሲድነት ይቀይሩታል። ይህም አሲድ በጥርስ የውጫዊው ክፍል (enamel) ላይ ጉዳት ያደርሳል። የጥርስ መቦርቦር የሚፈጠረው በዚህ ወቅት ነው። የጥርስ ሕመም የሚከሰተው መቦርቦሩ እየሰፋ ሲሄድና የጥርስ የውጫዊው ክፍልን ሰንጥቆ ወደ ጥርስዎ ውስጠኛው ክፍል ሲገባ ነው።
የጥርስ መቦርቦር በዓለም ላይ በብዛት ከሚታዩ የጤና ችግሮች አንዱ ነው። ይህ ችግር በተለይ በሕፃናት፣ በታዳጊዎች እና በአረጋውያን ላይ በብዛት ይታያል። ሆኖም ግን፣ ጨቅላ ሕፃናትን ጨምሮ ጥርስ ያለው ማንኛውም ሰው ለጥርስ መቦርቦር ሊጋለጥ ይችላል። የጥርስ መቦርቦር በሕፃናት ላይ በብዛት የሚታየው ብዙ ሕፃናት ጥርሳቸውን በትክክል ወይም በቂ በሆነ ሁኔታ ስለማይቦርሹ እና ጣፋጭ ምግቦችንና መጠጦችን የማዘውተር ዝንባሌ ስላላቸው ነው።
ለጥርስ መቦርቦር የመጋለጥ ዕድልዎ ከፍተኛ የሚሆነው የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲኖሩ ነው፦
- በአፍዎ ውስጥ ከፍተኛ የፕላክ (plaque) ክምችት ካለ
- ጥርስዎን አዘውትረው የማያጸዱ ከሆነ
- ስኳር የበዛበት ለስላሳ መጠጦችን፣ ጭማቂዎችን ወይም ጣፋጭና አሲዳማ የሆኑ ምግቦችን የሚያዘወትሩ ከሆነ
- በጥርስዎ ውስጥ በቂ የሆነ ፍሎራይድ ማዕድን ከሌለ
- በአፍዎ ውስጥ በቂ የምራቅ መጠን ከሌለ (ይህ ሁኔታ "ደረቅ አፍ" ወይም dry mouth ይባላል)
- የድድዎ ክፍል ወደ ታች በመሸሽ የጥርስዎ የታችኛው ክፍል ከተጋለጠ (receding gums)
- የሚያጨሱ ከሆነ
- አዘውትረው የጥርስ ሕክምና ክትትል ወይም ምርመራ የማያደርጉ ከሆነ
- በጣም የሚያቅርዎት ከሆነ
የጥርስ መቦርቦር ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የጥርስ መቦርቦር ምልክቶች እንደ መቦርቦሩ መጠን እና እንደ ጥርሱ ቦታ ይለያያሉ። መቦርቦሩ ገና ሲጀምር ምንም ዓይነት ምልክት ላይታይዎት ይችላል። የመቦርቦሩ መጠን እየሰፋ ሲሄድ ግን የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያስከትል ይችላል፦
- የጥርስ ሕመም
- የጥርስ መቆርቆር
- ጣፋጭ፣ ትኩስ ወይም ቀዝቃዛ ነገር ሲበሉ ወይም ሲጠጡ የሚሰማ መጠነኛ ወይም ከፍተኛ ሕመም መኖር
- በጥርስዎ ላይ የሚታዩ ቀዳዳዎች ወይም ጉድጓዶች መኖር
- በማንኛውም የጥርስ ክፍል ላይ የሚታይ ቡናማ፣ ጥቁር ወይም ነጭ ነጠብጣብ መኖር
- በተቦረቦረው ጥርስ አቅራቢያ የሚታይ የድድ መቅላት እና እብጠት
- የአፍ ጠረን መጥፎ መሆን ወይም በአፍዎ ውስጥ መጥፎ ጣዕም መሰማት
- የድድ መድማት
- የፊት እብጠት
የጥርስ መቦርቦር መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
የጥርስ መቦርቦር በጊዜ ሂደት የሚከሰት ሲሆን፣ ሂደቱም የሚከተለውን ይመስላል፦
- የጥርስ ፕላክ በጥርስዎ ይለጠፋል። ይህ የሚፈጠረው ብዙ ስኳር እና ጣፋጭነት የበዛባቸውን ምግቦች በመመገብ እና ጥርስን በሚገባ ባለማጽዳት ነው። ከጥርስ ላይ ካልተወገዱ፣ ባክቴሪያዎች በፍጥነት በእነዚህ ምግቦች ላይ መመገብ ይጀምራሉ፤ በዚህም ፕላክ ይፈጥራሉ። በጥርስዎ ላይ የሚቆይ ፕላክ ከድድ በላይ ወይም በድድ ውስጥ በመከማቸት ታርታር (tartar) ወደሚባል የበለጠ ጠንካራ የሆነ ንጣፍ ሊቀየር ይችላል። ይህ ንጣፍ ለባክቴሪያዎች እንደ መከላከያ ጋሻ ሆኖ ያገለግላል።
- ከባክቴሪያ የሚመነጩ አሲዶች በጥርስዎ ላይ ያሉ ማዕድናትን ያስወግዳሉ። ይህ መሸርሸር በመስተዋቱ ላይ ጥቃቅን ክፍተቶችን ወይም ቀዳዳዎችን ይፈጥራል፤ ይህም የመቦርቦር የመጀመሪያው ደረጃ ነው። አንዴ የውጪው ክፍል ከተሸረሸረ በኋላ፣ ባክቴሪያውና አሲዱ ዴንቲን (dentin) ተብሎ ወደሚጠራው ውስጠኛው የጥርስ ክፍል ይደርሳል። ይህ የጥርስ ክፍል ከመስተዋቱ ይልቅ ለስላሳና አሲድን የመቋቋም አቅሙ ዝቅተኛ በመሆኑ የበለጠ ህመም ይሰማዎታል።
- የጥርስ መቦርቦሩ እየቀጠለ ሲሄድ፣ ባክቴሪያውና አሲዱ ነርቮችንና የደም ስሮችን ወደያዘው የጥርስ ውስጠኛው ክፍል (pulp) ይገባሉ። ይህ ክፍል በባክቴሪያው ምክንያት ያብጣል እንዲሁም ይቆጣል። በጥርስ ውስጥ እብጠቱ የሚሰፋበት ቦታ ስለሌለ፣ ነርቮች ላይ ጫና ይፈጠራል፤ ይህም ለሕመም ይዳርጋል። አንዳንዴ ሕመሙና ጉዳቱ ከጥርስ ሥር አልፎ ወደ አጥንት ሊሰራጭ ይችላል፤ ይህም በጥርስዎ ዙሪያ ያለው አጥንት እንዲመናመን ወይም ጉዳቱ በአቅራቢያዎ ያሉ ሌሎች ጥርሶች ላይ እንዲደርስ ያደርጋል።
የጥርስ መቦርቦር እንዴት ይመረመራል?
የጥርስ ሐኪምዎ ብዙውን ጊዜ የጥርስ መቦርቦርን በሚከተሉት መንገዶች ሊለይ ይችላል፦
- ስለ ጥርስ ሕመምዎ ይጠይቆታል።
- በአፍዎ ውስጥ እና በጥርስዎ ላይ ያለውን ሁኔታ ይመለከታል
- የለሰለሱ ክፍሎች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ጥርስዎን በሕክምና መሣሪያዎች በመነካካት ይመረምራል
- የጥርስ መቦርቦር እና መሸርሸር ያለበትን ቦታ የሚያሳዩ የጥርስ ኤክስሬይ ምስሎችን ይመለከታል
የጥርስ መቦርቦር እንዴት ይታከማል?
አዘውትሮ የጥርስ ምርመራ ማድረግ፣ የጥርስ መቦርቦር እና ሌሎች ችግሮች ወደ ከፋ ደረጃ ከመሸጋገራቸው በፊት አስቀድሞ ለመለየት ይረዳል። ቶሎ ሕክምና ማግኘት የጥርስ መቦርቦር በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ለማቆም እና እንዳይባባስ ለማድረግ ያለውን ዕድል ይጨምራል። ሕመም ማስከተል ከመጀመሩ በፊት ከታከመ፣ ብዙም የሕክምና ሂደት ላያስፈልግዎት ይችላል።
የመቦርቦር ሕክምና እንደ ሁኔታው ክብደት እና እንደ ግለሰቡ ሁኔታ ይለያያል። የሕክምና አማራጮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- የፍሎራይድ ሕክምናዎች (Fluoride treatments)፦ መቦርቦሩ ገና እየጀመረ ከሆነ፣ የፍሎራይድ ሕክምና የጥርስ መስተዋቱን ለመጠገን እና መቦርቦሩን በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ለመቀልበስ ሊረዳ ይችላል። ፕሮፌሽናል የፍሎራይድ ሕክምናዎች በቧንቧ ውሃ፣ በጥርስ ሳሙና እና በአፍ ማጠቢያዎች ውስጥ ካለው የላቀ የፍሎራይድ መጠን አላቸው። እነዚህ ሕክምናዎች እንደ ፈሳሽ ወይም ጄል ሆነው በጥርስ ላይ የሚቀቡ ወይም በልዩ መያዣ በጥርስ ላይ የሚገጠሙ ሊሆኑ ይችላሉ።
- የጥርስ መሙላት (Fillings)፦ "ሬስቶሬሽን" በመባልም የሚታወቀው ይህ ዘዴ ዋናው የሕክምና አማራጭ ነው። መሙያው ከተለያዩ ነገሮች ለምሳሌ እንደ ጥርስ ቀለም ካለው ኮምፖዚት (composite resin)፣ ከሸክላ (porcelain) ወይም ከተለያዩ ማዕድናት ቅልቅል (amalgam) ሊሠራ ይችላል።
- የጥርስ ሽፋን (Crowns)፦ ከፍተኛ መቦርቦር ወይም የተዳከመ ጥርስ ካለዎት ኮፍያ ሊያስፈልግዎት ይችላል። ይህ ጥርሱ ተጠርቦ ከወጣ በኋላ ሙሉውን የተፈጥሮ ጥርስ የሚተካና እንደ ጥርሱ ቅርጽ ተለክቶ የሚዘጋጅ ሽፋን ነው። ኮፍያው ጥርሱ እንዳይሰበር ይከላከላል። ይህም ከወርቅ፣ ከጠንካራ ሸክላ (porcelain)፣ ከሬዚን ወይም ከብረትና ሸክላ ቅልቅል ሊሠራ ይችላል።
- የሥር ሕክምና (Root canals)፦ መቦርቦሩ ወደ የጥርስ ስር ላይ ከደረሰ የሥር ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል። ይህም በጣም የተጎዳን ወይም በኢንፌክሽን የተጠቃን ጥርስ ከመንቀል ይልቅ ጠግኖ ለማዳን የሚደረግ ሕክምና ነው። የታመመው የጥርስ ነርቭ ይወጣል። ኢንፌክሽኑን ለማጽዳት አንዳንዴ መድኃኒት ወደ ውስጥ ይጨመራል፤ ከዚያም ጥርሱ ተመልሶ ይሞላል።
- ጥርስን መንቀል (Tooth extractions)፦ አንዳንድ ጥርሶች በጣም ከመጎዳታቸው የተነሳ ሊጠገኑ ስለማይችሉ መወገድ (መንቀል) ይኖርባቸዋል። ጥርስ ሲነቀል የሚፈጠረው ክፍተት ሌሎች ጥርሶች ቦታቸውን እንዲስቱ ሊያደርግ ይችላል። ከተቻለ የተነቀለውን ጥርስ በድልድይ (bridge) ወይም በጥርስ ተከላ (dental implant) መተካት ይመከራል።
የጥርስ መቦርቦርን እንዴት መከላከል ይቻላል?
መደበኛ የጥርስ መቦረሽ እና ጥርስዎትን ፍሎስ ማድረግን ጨምሮ ተገቢ የሆነ የአፍ ንጽህና አጠባበቅ፣ ለጥርስ መቦርቦር መንስኤ የሆኑትን ፕላክ፣ አሲድ እና ባክቴሪያዎችን ለማስወገድ ይረዳል። ጥሩ የጥርስ እና የድድ እንክብካቤ የሚከተሉትን ያካትታል፦
- ለስላሳ ብሩሽ እና የፍሎራይድ ይዘት ያለው የጥርስ ሳሙና በመጠቀም በቀን ቢያንስ ሁለት ጊዜ (ከተቻለ ደግሞ ከእያንዳንዱ ምግብ በኋላ) ጥርስን መቦረሽ
- ስኳር እና ጣፋጭነት የበዛባቸውን ምግቦች እና መጠጦች መቀነስ።
- በጥርስዎ መካከል የተሰገሰጉ የምግብ ቅሪቶችን እና ፕላክን ለማስወገድ በየቀኑ ጥርስዎትን ፍሎስ ማድረግ
- በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ የጥርስ ሕክምና ምርመራ ማድረግ (ለጥርስ መቦርቦር፣ ለድድ በሽታ ወይም ለሌሎች የአፍ ጤና ችግሮች ተጋላጭ ከሆኑ ከዚህ በላይ የሆኑ ተከታታይ ጉብኝቶች ሊያስፈልጉዎት ይችላሉ)
- ፍሎራይድ ያለው የአፍ ማጠቢያ (mouth rinse) በመጠቀም አፍዎትን ይጉመጥመጡ
የጥርስ መቦርቦርን ለመከላከል ፍሎራይድ በጣም አስፈላጊ ነው። ፍሎራይድ ያለው የጥርስ ሳሙና ይምረጡ። ጥርስዎን ከቦረሹ በኋላ፦
- የተረፈውን የጥርስ ሳሙና ተፉት።
- አፍዎን በውሃ አይለቅልቁ።
ይህም የጥርስ ሳሙናው በጥርስዎ ላይ ቀጭን ንብርብር ሆኖ እንዲቆይ ያደርገዋል። ይህም ጥርስዎ ለረጅም ጊዜ ጥበቃ እንዲያገኝ ይረዳል።




