የጥርስ ብሬስ (Teeth Braces)
የጥርስ ብሬስ የተዛነፉ ጥርሶችን ለማቃናት እና የተለያዩ የጥርስ አሰላለፍ (ኦርቶዶንቲክ) ችግሮችን ለማስተካከል ያግዛል ከእነዚህም ውስጥ
- የተጣመሙ ጥርሶች (Crooked teeth)
- የተደራረቡ ጥርሶች (Crowded teeth)
- የተዘረዘሩ ጥርሶችን (Gapped teeth) እና
- ወደ ፊት የወጣ ጥርስን ለማስተካከል ያግዛል ።
የጥርስ ብሬስ እንዴት ጥርስን ያስተካክላል?
ጥርስ ላይ መለስተኛ እና የማያቋርጥ ግፊት (ጫና) በማድረግ ጥርስን በጊዜ ሂደት ወደ ትክክለኛው ቦታ እንዲመለስ ያደርጋል።
የጥርስ ብሬስ ዓይነቶች
የተለያዩ የጥርስ ብሬስ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን ለእርስዎ ተስማሚ የሆነው ዓይነት የሚወሰነው እንደ አለብዎት የችግር ዓይነት፣ የችግሩ ክብደት እና እንደ ግል ምርጫዎ ይሆናል።
1. የብረት ብሬስዎች (Metal braces)
እነዚህ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ አማራጮች ሲሆኑ ጥርሶችን ቀስ በቀስ ለማንቀሳቀስ የማይዝጉ ብረትዎች (stainless steel) እና ሽቦዎችን ይጠቀማሉ።
2. የሴራሚክ ብሬስዎች (Ceramic braces)
ከብረት ብሬስዎች ጋር ተመሳሳይ ቢሆኑም ከጥርስ ቀለም ጋር የሚመሳሰሉ ግብዓቶችን ስለሚጠቀሙ ከጥርስ ጋር ተመሳስለው ይታያሉ። እነዚህ ብሬስዎች ብዙም የማይታዩ ወይም ከጥርስ ጋር የሚመሳሰሉ ቢሆንም ከብረት ብሬስዎች ይልቅ ግን በቀላሉ የመሰበር ዕድል አላቸው።
3. የሊንጓል ብሬስዎች (Lingual braces)
እነዚህ ከጥርስዎ በውስጥ በኩል (ከጀርባ) የሚገጠሙ በመሆናቸው ከፊት ለፊት አይታዩም። ስለዚህ ብሬሳቸው እንዲታይ ለማይፈልጉ ሰዎች ጥሩ አማራጮች ይሆናሉ።
4. ሰልፍ-ላይጌቲንግ ብሬስዎች (Self-ligating braces)
መልካቸው እንደ ብረት ብሬስዎች ቢሆንም ሽቦውን በቦታው ለመያዝ ግን ከላስቲክ ይልቅ በራሱ ውስጥ የተገነባ አነስተኛ መቆለፊያ ይጠቀማሉ።
5. ክሊር አላይነርስ (Clear aligners)
ብዙውን ጊዜ "ኢንቪዚብል ብሬስዎች ወይም የማይታዩ ብሬስዎች" ተብለው የሚጠሩት ሲሆኑ ጥርስን በጊዜ ሂደት ለማስተካከል የሚረዱና ከጥርስ ላይ ሊወለቁ የሚችሉ የማይታዩ የላስቲክ ብሬስዎች ናቸው። እነዚህ ብሬስዎች መውለቅ የሚችሉ ቢሆኑም ውጤታማ እንዲሆኑ ግን በቀን ውስጥ ለ20-22 ሰዓታት መደረግ አለባቸው።
የጥርስ ብሬስ ለማድረግ የተመረጠው ዕድሜ ስንት ነው?
የጥርስ ብሬስ በማንኛውም እድሜ ክልል ላይ ያለ ሰው ማድረግ ይቻላል። ይሁን እንጂ ለሕክምናው ተመራጭ የሚባለው ጊዜ በአብዛኛው ከ9 እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ነው።ይህም የሆነበት ምክንያት በዚህ ወቅት መንጋጋ እና የፊት አጥንቶች ገና በማደግ ላይ ስለሆኑ ለመምራት ወይም ለማስተካከል ቀላል ናቸው።
ይህ ማለት ግን ለአዋቂዎች አይሆንም ማለት አይደለም። የአዋቂዎች የጥርስ ብሬስም ልክ እንደ ሕፃናቱ ውጤታማ ነው ፤ ነገር ግን የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል።
በጥርስ ብሬስ ጥርስን ለማስተካከል ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?
የሚወስደው ጊዜ ከሰው ወደ ሰው የሚለያይ ሲሆን በአማካይ ግን በጥርስ ብሬስ የሚፈለገውን ውጤት ለማሳየት ሁለት ዓመት ገደማ ይወስዳል ። ሆኖም ይህ የሚወሰነው የጥርስ አሰላለፍ መዛባቱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ላይ ነው።
አንዳንድ ሰዎች ሕክምናቸውን በ12 ወራት ብቻ ሲያጠናቅቁ ሌሎች ደግሞ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ጊዜ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
የጥርስ ብሬስ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
የጥርስ ብሬስ የፈገግታዎን ውበት ከማሻሻል ባለፈ ለአጠቃላይ የአፍ ውስጥ ጤና እና ለጥርስ ተግባር ትልቅ ድጋፍ ያደርጋል። የጥርስ ብሬስ ከሚሰጣቸው ዋና ዋና ጥቅሞች ሚከተሉት ይጠቀሳሉ ፦
- የተስተካከለ እና ይበልጥ ማራኪ የሆነ የጥርስ አሰላለፍ እንዲኖርዎት ያደርጋል።
- ጥርስዎን በቀላሉ እንዲያፀዱ ያግዛል ፤ ይህም የምግብ ዝቃጭ (plaque) ጥርስ ላይ እንዳይከማች ይረዳል።
- ለጥርስ መበስበስ እና ለድድ በሽታ የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል
- የመንጋጋ መገጣጠሚያ(temporomandibular joint (TMJ)) ህመሞችን ጨምሮ የመንጋጋ አቀማመጥ ችግሮችን ያስተካክላል።
- በደንብ የማኘክ እና የመናገር ችሎታን ያሻሽላል።
የጥርስ ብሬስ የጎንዮሽ ጉዳቶች ምንድን ናቸው?
የጥርስ ብሬስ በተለይም መጀመሪያ ህክምናውን ሲጀምሩ ወይም ማስተካከያ (adjustment) በሚደረግበት ጊዜ መጠነኛ እና ጊዜያዊ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል። እነዚህም ፦
- ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ምቾት ማጣት ወይም የሕመም ስሜት
- የከንፈር፣ የምላስ ወይም የጉንጭ ውስጠኛው ክፍል መቆጣት
- የመንጋጋ ሕመም
- የተወሰኑ ምግቦችን ለመመገብ መቸገር
እነዚህ ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ እንደ ፓራስታሞል እና አይቡፕሮፌን ባሉ ያለ ሐኪም ማዘዣ በሚሸጡ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች ሊታከሙ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በአፍ ውስጥ የሚከሰተውን መቆጣት ለመቀነስ የጥርስ ሰም (dental wax) በብሬስዎቹ ወይም በሽቦዎቹ ላይ መቀባት ይችላሉ።
ለጥርስ ብሬስዎ ምን አይነት እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልጋል?
የጥርስ ብሬስ በሚኖርዎት ጊዜ የአፍ ንጽህናን መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም የምግብ ዝቃጭ (plaque) በብሬሱ እና በሽቦዎቹ ዙሪያ በቀላሉ ሊከማች ስለሚችል ለጥርስ መበስበስ እና ለድድ በሽታ የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።
የጥርስ ሐኪምዎ ዝርዝር መመሪያዎችን የሚሰጡዎት ቢሆንም የሚከተሉት አጠቃላይ ምክሮችን ይከተሉ፦
- ለስላሳ ብሩሽ እና ፍሎራይድ ያለው የጥርስ ሳሙናን በመጠቀም በቀን ቢያንስ ሁለት ጊዜ ጥርስዎን ይቦርሹ
- ለጥርስ ብሬስ ታስቦ በተሰራ የጥርስ ክር ጥርስዎን በየቀኑ ያፅዱ
- አልኮል በሌለው የአፍ ማጠቢያ ወይም ማውዝ ወሽ(mouthwash) አፍዎን ይጉመጥመጡ
- ብሬስዎን ሊያበላሹ የሚችሉ ጠንካራ ወይም የሚያጣብቁ ምግቦችን አይመገቡ
- መደበኛ የጥርስ ምርመራዎችን እና የብሬስ ማስተካከያ ቀጠሮዎችን (adjustments) በአግባቡ ይከታተሉ።
ኢንቪዚብል ብሬስዎችን የሚጠቀሙ ከሆነ በየቀኑ ያፅዱዋቸው እንዲሁም በሚያወልቋቸው ጊዜ በአግባቡ እና በጥንቃቄ ያስቀምጡዋቸው።
ከጥርስ ብሬስ በኋላ ውጤቱ ዘላቂ እንዲሆንልዎት ምን ማድረግ አለብዎት ?
የጥርስ ብሬስ ያደረገ ማንኛውም ሰው ሕክምናውን ሲያጠናቅቅ 'ሪቴይነር' (Teeth Retainer) ማድረግ ይኖርበታል። ሪቴይነር ጥርሶችዎ ቀስ በቀስ ወደ ነበሩበት የተዛባ ቦታ እንዳይመለሱ ይከላከላል።
የተለያዩ የሪቴይነር ዓይነቶች ያሉ ሲሆኑ የጥርስ ሐኪምዎ ለእርስዎ ተስማሚ የሆነውን እንዲመርጡ ይረዳዎታል።
የባለሙያ እርዳታ መቼ ያስፈልጎታል?
ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረጉም አንዳንዴ በብሬስ ሕክምና ወቅት ወይም ከሕክምናው በኋላ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። የሚከተሉት ሁኔታዎች ካጋጠሙዎት የጥርስ ሐኪም ማማከር ይኖርብዎታል፦
- በመድኃኒት የማይሻሻል ከፍተኛ እና ቀጣይነት ያለው ሕመም ካለ
- የተበጠሱ ሽቦዎች ወይም የላላ ብሬስ ካለ
- በአፍዎ ወይም ፊትዎ ላይ ጉዳት ከደረሰብዎት
- እንደ ማበጥ፣ መድማት ወይም ምቾት ማጣት ያሉ የድድ ኢንፌክሽን ምልክቶችን ካስተዋሉ በጥርስ ሐኪም መታየት ይኖርቦታል።
ስለዚህ ለጥርስ ብሬስዎ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ እና የጥርስ ሐኪምዎን ምክር በመከተል ፈገግታዎን ለረጅም ዓመታት ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ያድርጉ።


